የጽንሰ ሃሳብ መነሻ፤
ዋናው ርዕሳችን የተወሰደው “agree to disagree” ከሚለው የባዕድ ሀረግ ተተርጉሞ ነው። በተቃርኖ ሃሳብ የተዋቀረ የሚመስለው ይህ ሀረግ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው እ.ኤ.አ ጁን 29 ቀን 1750 ዓ.ም ጆርጅ ዋይትፊልድ በተባሉ በእንግሊዛዊ የቤተክርስቲያን አገልጋይ አማካይነት ነበር። እኚህ ካህን ይህንን ሀረግ የተጠቀሙት ጆን ዌሲሊ ከተባሉትና አብረው ከሚያገለግሉት የቅርብ ጓደኛቸውና ወዳጃቸው ጋር በተፈጠረ የእምነት ቀኖና ዶግማ ልዩነት ምክንያት በመካከላቸው ጠላትነት ተፈጥሮ እርስ በእርስ እንዳይጎዳዱ በጻፉላቸው የማሳሰቢያ ማስታወሻ ውስጥ ነበር።
ደብዳቤው የደረሳቸው ካህኑ ዌስሊ ያንን የቀድሞ ወዳጃቸውን ጦማር በክብር ካስቀመጡ ከሃያ ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ1770 ዓ.ም ከሰንዱቃቸው ውስጥ አውጥተው ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት ወዳጃቸው ጆርጅ ዋይትፊልድ አርፈው በቀብር ሽኝታቸው መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነበር። የንግግራቸው ይዘት የሚከተለውን ይመስላል፤
“ወዳጆች ሆይ!…” አሉ ጆን ዌስሊ ለሀዘንተኞቹ ቀብርተኞች ንግግራቸውን ሲጀምሩ፤ “…በእኔና በወዳጄ ጆርጅ ዋይትፊልድ መካከል የተፈጠረው የዶግማ አስተምህሮ ልዩነት በፍጹም ስሜታችንን አሻክሮ ጓደኝነታችን ላይ ጥላ አላጠላም። በልዩነታችን ተከባብረን አብረን ለመኖር የቻልነው ልበ ብርሃኑ ወዳጄ “ባለመስማማት መስማማት` – ‹agree to disagree› የሚለውን መርህ በልበ ሰፊነት አክብረንና ተከባብረን ልዩነታችን እንደተጠበቀ በራሳችን መረዳት ልክ በነፃነት እንድናገለግል የቃል ኪዳን ያህል ስለተስማማን ነው።
ስለዚህም በአስተሳሰብና በአስተምህሮ ብንለያይም በወዳጅነታችንና በጓደኝነታችን መካከል ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ በፍጹም ነፋስ ሊገባ አልቻለም። ወዳጄ አርፈዋል፤ እኔም ተራዬን እየጠበቅሁ ነው። የሁለታችንም በድን ከአፈር ጋር መቀላቀሉ ግድ ነው። ሁለታችንም ከአገልግሎታችን ፍሬ የተነሳ ህያው ሆነን ስንጠቀስ እንኖራለን ብለን ብናስብ አንኳን፤ ስማችንን ‹እነ እከሌ› እያሉ የሚያስታውሱን ወዳጆቻችንና በዘመናችን የታተሙት የጽሑፍ ውጤቶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ።”
“ስለዚህም ወዳጄ ዋይትፊልድ ሆይ! ‹ባለመስማማት መስማማት› በማለት የገለጹት የአስተምህሯችንን ልዩነት ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ከሚቀረው ከየራሳችን ማንነትም ጋር ሳይቀር የልዩነት ሃሳብ እንደምናስተናግድ ጭምር እንድናስታውስ ረድቶናል። ሰው ነና! ከልዩነታችን ይልቅ በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም አብረን እንደምንኖር በሚገባ ስለተረዳን ‹ባለመስማማት ተስማምተን› በፍቅርና በመከባበር ኖረን ዛሬ እርስዎን እንሸኛለን፤ ነግ ተነገወዲያ ደግሞ እኔ እከተልዎትና በልዩነታችን ከማንከራከርበት የአምላካችን ዙፋን ሥር ነፍሶቻችን እየሰገዱ በየፊናችን በዘመናችን ያገለገልነውን ልዑል አምላክ በማመስገን ለዘለዓለም አብረን እንኖራለን። ወዳጄ ሆይ ነፍስዎት በሰላም ትረፍ! አክባሪዎ።”
“ባለመግባባት መግባባት” የሚለው የዚህ ዘመን ዘለል ሀረግ ዕድሜ ወደ ሦስት መቶ ክፍለ ዘመን እየተጠጋ ቢሆንም አገልግሎቱ ገንኖ በዓለም ዙሪያ በሁሉም አንደበትና ጽሑፍ ውስጥ የዕለት ተዕለት መግባቢያና የልዩነት ማቻቻዬ መርህ ተደርጎ ሲተገበር አይስተዋልም። ቢሆን ኖሮማ ዓለማችን በሰላም አሸብርቃ በተረጋጋች ነበር። ጉዳዩን ወደ ራሳችን በመመለስ የአገራችንን ገመና ብንፈትሽበት ይበልጥ ትርጉም ስለሚሰጠን “ሙታንን ከማመስገን፤ ሕያዋንን ማስተንተን” እንዲሉ ትኩረታችንን ሰብስበን “ኢትዮጵያ ሆይ!…” እያልን እንቃትታለን።
“አታምጣው አታምጣው ስለው ከቤቴ በላይ ቆልሎት ሄደ”፤
ሰውየው ማንምና ምንም ሊሆኑ ይችላሉ። የፈለጉትን አመለካከትና ፍልስፍናም ማራመድ መብታቸው ነው። በአገራችን ባገለገሉበት ዘመንም ቢሆን ባበረከቱትም ሆነ ባጎደሉት ውጤቶች የሚያውቋቸው ወገኖች ስለ ሰውዬው የፖለቲካ አቋምና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስላላቸው አቋም የወደዱትንና የመሰላቸውን አስተያየት ሊሰጡ እንደሚችሉ አይጠፋኝም። የሚያመሰግኗቸው የመኖራቸውን ያህል የሚኮንኗቸው እንዳሉም ይገባኛል። ይህ ጸሐፊ በማንም አመለካከት ላይ ጫና ለማድረግ አይሞክርም። ምክንያቱስ? ከተባለ መርሁ የጆርጅ ዋይትፊልድ “ባለመስማማት መስማማት” የሚለው ፍልስፍና ስለሆነ ነው።
እናፍታታው፡- ሰውዬው በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ሚ/ር ቲቦር ናጊ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያገለገሉትም እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2002 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ነው። እኝህ አንጋፋ ዲፕሎማት ከጥቂት ቀናት በፊት በቲዩተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ሰፋፊ እውነቶችን የያዘ የግል አስተያየታቸው የአገሬን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ የገለጸ ስለሆነ እንደሚከተለው በተዛማጅ ትርጉም ወደ ቋንቋችን መልሼዋለሁ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ቀረ የሚባል አጨቃጫቂ ተጨማሪ ርእሰ ጉዳይ ይኖር ይሆን?…” በማለት ቲቦር ናጊ ከጠየቁ በኋላ በእኛው በራሳችን የአገሪቱ ልጆችና በዓለም ፊት መሳቂያና መሳለቂያ ያደረጉንን ትዝብታቸውን እንዲህ በማለት ይዘረዝራሉ። “…በዘረኝነት፣ በሃይማኖት፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ የታሪካቸው አንድ አካል በሆነው በአድዋ የጦርነት የድል ታሪክ እንኳን መስማማት አልቻሉም። በአስደማሚ ታሪኮች የተዋበችው ኢትዮጵያ ራሷን ለመከፋፈል የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን ተግታ የምትፈልግ መስላ ትታየኛለች። አንድነታቸው እንዲጠበቅ እግዚአብሔር ይርዳቸው።”
ኢትዮጵያን በሚገባ የሚያውቋት እኚህ ጉምቱ አሜሪካዊ ዲፕሎማት በትዝብታቸው ከጠቀሷቸው እውነቶች መካከል አንድም ስህተት የለበትም። ፖለቲካው ሲግተን የኖረው የዘረኝነት መርዝ ውሰጣዊ ሰላማችንን እያናጋ ሞት፣ መፈናቀል፣ የንብረት መውደምና እጅግ በርካታ ተያያዥ ችግሮች የታሪካችን አካል ሆነው ከተዋሃዱን ሰነባብቷል። ዘመኑን በተግባራዊ ማሳያ እናመላክት ካልን ይህ ክፉ የእንክርዳድ ዘር እውቅና ተሰጥቶት ከተዘራና እንድንመራበት ከተደረገ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከሦስት አሥርት ዓመት በላይ ተቆጥሯል።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንድ ልጅ ተወልዶ፣ አድጎ፣ ተምሮ፣ ትዳር በመያዝ ልጆች ወልዶ የሚስምበት ጊዜ ነው። ዕድሜያቸው በዚህ ዘመን ውስጥ የሚወድቀው ዜጎች ቁጥር ምን ያህል ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል ትክክለኛውን አሀዝ ለመጥቀስ ያስቸግር ይሆናል። ነገር ግን “ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት” የሚለውን ማሞካሻ እውነትነት የምንቀበል ከሆነ ከአገሪቱ ዜጎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚታቀፉ የዘርፉ ምሁራን ግምት ያረጋግጥልናል።
ስለምንድን ነው ብሔራችንን በአግባቡ በማክበርና የሌሎችንም እንዲሁ በአክብሮት እየተቀባበልን በጋራ ከማደግ ይልቅ የዘረኝነት ደዌ ሰልጥኖብን ታማሚ ልንሆን የቻልነው? ስለምንስ ነው በአንድ ካቆራኘን የኢትዮጵያዊነት ክብር ይልቅ በራስ ጎጥ ውስጥ መወሸቅን እንደ ፀጋ ቆጥረን የምንገፋፋው? የጥያቄው መልስ ተወሳስቦብናል ወይንም ኅብረ ብሔራዊነታች ደምቆ እንዲኖር አልተፈቀደለትም። የትኛውም ዘር ከየትኛውም የበለጠ ወይንም ያነሰ ያለመሆኑ እየታወቀ ስለምን ለመቋሰል በየጓዳችን እንበረታታለን። የተመረጠም ይሁን የተወገዘ ብሔር በኢትዮጵያ ምድር ይኖራል ብሎ ለመገመት ከኅሊና የመጣላት ያህል የከበደ ነው።
ሁሉም ብሔር የራሱ ውብ መገለጫዎች አሉት። በራሱ ባህል፣ ቋንቋና ወግ ይኮራል፣ መኩራትም ክብሩ ነው። እኔነት የሚደምቀው ከሌሎች ጋር አብሮና ተከባብሮ በመኖር እንጂ የራስን አካባቢ ብቻ እንደ ኤደን ገነት አቆንጅቶ “ነፍሴ ሆይ! እረፊ፣ ደስም ይበልሽ” እያሉ የስንፍና ዜማ በማንጎራጎር አይደለም። የራስን መገኛና ማንነትን ተራራ ላይ ሰቅሎ የሌላውን ብሔር ህልውና ከተራራው እግር በታች አሳንሶ ሸለቆ ውስጥ መክተት የአስተሳሰብ ድኩምነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ስያሜ የሚሰጠው አይሆንም።
እርግጥ ነው ከአገራዊ የታሪኮቻችን መሰዊያ ላይ ፍሙን ከመጫር ይልቅ፤ አመዱን እየዛቅን በእርስ በራሳችን የማስተዋል ዕይታ ላይ እንድንበትን “የፖለቲካው ግብዣ የቀረበልን” ገና ከጠዋቱ መሆኑ አይጠፋንም። ባህር ማዶኞቹ “from the alter of history take the fire not the ash” የሚለውንና ባለፉት ጽሑፎቼ ውስጥ ደጋግሜ ያነሳሁትን ሃሳብ ለማብራራት መሞከሬ እንደሆነ ልብ ይሏል።
የብሔራችንን መንፈስ አጀግነን “የፍልሚያ ሸማ የተጣጣልንባቸው” ያለፉት ዓመታት ምን ትርፍ አስገኙልን? በመቆራቆዝ ያጣነው ነፍስና የወደመው ንብረት የሀዘን ከል እንድንለብስ ምክንያት ከመሆን ውጭስ ምን ፈየደልን? አገራዊ ችግሮቻችንን “ባለመስማማት በመስማማት” እየተከባበርን ከመኖር ይልቅ በዱላና በጎመድ ካልተፋለምን እያልን ማቅራራቱ ምንና ማንን ጠቀመ? ቲቦር ናጊ ታዝበውን ገመናችንን አደባባይ ያሰጡት እኛን እንደቸገረን እሳቸውንም ቢቸግራቸው እንደሆነ የትዝብታቸው ይዘት ምስክር ነው።
ድንበሬን አትለፍ፣ ክልሌን አቋርጥ፣ በመንገዴ ላይ አትራመድ፣ የሚለው የጅሎች ፍልስፍና ውሎ አድሮ “አየሬን አትተንፍስ፣ የወንዜን ውሃ አትጠጣ፣ በማሳዬ ላይ የበቀለውን እህል እንዳትቀምስ ወዘተ.” ወደሚል እብደት እንዳንገባ ከፍ ያለ ሥጋት አድሮብናል፤ ምልክቶቹም የሚጠቁሙት መርዘኛ አካሄድ ነው። ይህ በሽታ በአጭሩ ካልተቀጨና መፍትሔ ካልተፈለገለት በስተቀር በወንዝ ከሚመሰለው የትውልዶች ጅረት ውስጥ እንደ ፈረሰኛ ውሃ እየጋለበ ሲበክል እንደሚኖር ለመገመት አይከብድም።
የፖለቲካ ህመማችንን በተመለከተ ምክርም፣ ምክክርም፣ ጸሎት/ዱዓም፣ ጾምም ሆነ ወደ ፈጣሪ የምንጮኸው ጩኸት ለጊዜው ሰሚ ያገኘ አይመስልም። በተማጽኗችንም ሆነ በኪራላይሷችን ላይ ስለምን ጀንበሯ እንደከፋችብን አልገባንም፤ ከውስብስብነቱ መጦዝ የተነሳም መፍትሔው ዳምኖብናል። መፍትሔ የጠፋለት ይህ የዘመናችን አገራዊ ስራይ በምን መድኃኒት ተፈውሶ እንደምናይ በእጅጉ ጓጉተናል። ሙሾ አሙሺዋ የአገሬ አስለቃሽ፡-
“ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፤ ከቤትሽ አልወጣ፣
የገደለው ባልሽ፤ የሞተው ወንድምሽ”
በማለት አልቅሳ እንዳላቀሰችው፤ ሟቹም ገዳዩም፣ ዒላማውም ተኳሹም፣ ቀብረተኛውም ተቀባሪውም ከዚህቺው አገር ይሏት ጉድ ማህጸን የተገኙ ልጆቿ ናቸው።
በሁሉም የሕይወታችን ውሎ አምሽቶ ውስጥ ጆርጅ ዋይትፊልድ ፈጠሩት የሚባለው፡- “ባለመስማማት መስማማት” መርህ ባህላችን ሆኖ ልንገዛለት ቀርቶ እንግዳ አድርገንም እንኳን አልፎ አልፎ በየመድረኮቻችን ላይ ስሙን ያለማንሳታችን የእንቆቅልሻችንን ግዝፈት፣ የልባችንን ድንዳኔና ጽናት በሚገባ ያመለክታል። ወደ ጋራ መተማመን ደረጃ ባንደርስ እንኳን ስለምን መቀባበልና መከባበር ተሳነን? የዚህን አዚማችንን ሥርወ መነሻ የሚያስረዳን ብናገኝ ለጊዜውም ቢሆን መንፈሳችን ይረጋ ነበር።
“በቡሐ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ ዘረኝነቱና የፖለቲካ ነውጡ ያነሰን ይመስል ስለ ሰላምና ስለ ዘላለማዊነት በሚሰብኩ ቤተ እምነቶቻችን ውስጥ ሳይቀር ተጋቦሹ ተዛምቶ እንደ አገር ህመማችንን አባብሶታል። ክርስቶስን እንደሰቀሉት አይሁዶች ወይንም ነብዩ መሐመድን ከመካ ወደ መዲና እንዲሰደዱ ምክንያት እንደሆኑት “የክፉ ዘመን ክፉዎች” ዛሬም ስመ ፈጣሪ በሚጠራባቸው ቤተ እምነቶች ውስጥ “የአምልኮ መልክ አንጂ የግብር ፍሬ” በማያፈሩ ጉዶች ተጥለቅልቋል። “ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይውጡ” እንዲሉ ለነፍስና ለመንፈስ ፈውስ እንደሚሰጡ የሚታመንባቸው ቤተ እምነቶች ራሳቸው እንደ ባሕር ወጀብ ሲነዋወጡ ማስተዋል ለወሬም ለፍርድም አይመችም።
በታሪኮቻችን ላይ የምንሰናዘረው የእንካ ሰላንትያ ፍልሚያዎች ከእኛም አልፈው ወደ ቀጣዩ የትውልድ ዘመን ሲሸጋገሩ ምን ውጤት እንደሚያስከትሉ ለመተንበይ “የአራት ዐይናማነት ፀጋ” ለመታደል ግድ አይልም። “ባለመግባባት ተቻችሎ መግባባት” እየተቻለና የሚያግባቡንን ታሪኮቻችንን እያደመቅን፣ በአብሮነታችን ከመዝለቅ ይልቅ የሚለያዩንን የጠገጉ ቁስሎች እየደነቋቆልን ሕመማችን እንዲያገረሽ መትጋት ለማንምና ለምንም የሚጠቅም አይደለም። አምባሳደር ቲቦር የታዘቡት አንዱ አገራዊ ችግራችን ይህንኑ ከታሪክ ጋር ፍልሚያ የገጠምንበትን አገራዊ እብደት በሚገባ የሚያሳይ ነው።
ለማጠቃለያነት የሚያግዘን አንድ ጥቅስ ከቅዱስ መጽሐፍ በመዋስ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ እንደምድምበት፡- “ከተምች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣ የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያ የቀረውን ኩብኩባ በላው።” የእኛስ ሁኔታ ከዚህ እውነታ በምን ይለያል? መፍትሔው የመነሻ ሃሳባችን ነው፡- “ባለመስማማትም ቢሆን መስማማትና” አብሮና ከብሮ በጋራ ድምቀት መኖር። ይኼው ነው። ሰላም ለሕዝባችን፤ በጎ ፈቃድም ለዜጎች።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም