ዋሊያ አንደኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አክብሯል:: አዲስ አበባ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ከ76 ዓመታት በፊት ይህችን ምድር የተቀላቀሉት አቶ ሸዋንግዛው ጥላሁን ደግሞ ትምህርት ቤቱን መሥርተዋል:: አቶ ሸዋንግዛው ለቤተሰባቸው ሰባተኛ ልጅ ናቸው:: ወላጆቻቸው እርሳቸውን ጨምሮ አምስት ሴት እና አራት ወንድ ልጆችን ሲወልዱ፤ ታታሪ በመሆናቸው በተትረፈረፈ ሃብት ዘጠኙንም ልጆች አንደላቅቀው ለማስተማር የሚያንሱ አልነበሩም::
በቤተሰባቸው ልዩ እንክብካቤ ያደጉት ልጆች ወላጆቻቸው በሕይወት እያሉ በ1958 ዓ.ም ለእያንዳንዳቸው ካርታ ያለው 380 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸዋል:: ለየራሳቸው ቦታ ቢሰጣቸውም ቤት የሰራ ሰው አልነበረም:: የሁሉም መሬት ዛፍ ተተክሎበት ቆየ:: የአቶ ሸዋንግዛው አባት አቶ ጥላሁን በላይነህ ለልጆቻቸው ብቻ አይደለም፤ አልፈው ተርፈው በቅርብ ተከራይቶ ለሚኖር ‹‹አባቴ›› እያለ ለሚጠይቃቸው ወዳጅ ሳይቀር 200 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥተዋል:: ሙሉ መሬት እና ቤቱን ከማውረስ በተጨማሪ፤ አቶ ጥላሁን ለባለቤታቸው ማለትም ለአቶ ሸዋንግዛው እናት መርካቶ እና ሌሎችም አካባቢዎች የሚከራዩ ሱቆችን በባለቤትነት ይዘው ገንዘቡን እንዲሰበስቡ እና ለፈለጉት ሰውም እንዲሰጡ ፈቅደው ነበር::
አቶ ሸዋንግዛው እንደሌሎቹ ወንድም እና እህቶቻቸው ሁሉ በልዩ እንክብካቤ ትምህርታቸውን ተከታተሉ:: በ1962 ዓ.ም ምኒልክ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ፤ በአዋሽ ሸለቆ ባለስልጣን አሳይታ ልዩ ስሙ ዱብቲ በሚባል አካባቢ ሥራ ተመደቡ:: የልጅ ሸዋንግዛው እናት በረሃ በመሆኑ ልጃቸው እንዳይሔድ ከለከሉ::
አቶ ሸዋንግዛው የእናታቸውን ይሁንታ ባለማግኘታቸው ከአዲስ አበባ አልወጡም፤ ሥራም አልተቀጠሩም:: ከገነት ሆቴል በታች ከማሞካቻ በላይ ያሉት የሚከራዩት ሱቆች እና ቤቶች የእርሳቸው ቤተሰብ ቤት ሃብት ነበሩ:: ከፊት ለፊትም ገራዥ ነበራቸው:: መርካቶ ያሉት ሱቆች ተጨምረው ገቢያቸው ከፍተኛ በመሆኑ አልተቸገሩም:: የግድ ሥራ ለመሥራት አልተገደዱም:: ነገር ግን የሥራ ፍላጎት ስለነበራቸው፤ ትምህርት ቤት ለመክፈት አሰቡ::
በቅርብ አካባቢያቸው ቤት ተከራይተው ትምህርት ቤት ከፈቱ:: አባታቸው የታወቁ ነጋዴ እና ባለሃብት በመሆናቸው የእናታቸው ዕገዛ ታክሎበት ትምህርት ቤቱን ለመክፈት በገንዘብ እጥረት አልተቸገሩም:: ጭራሽ አስፋፍተው እስከ ሶስተኛ ክፍል የነበረውን ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ለማስተማር እንዲቻል እድርገው ገነቡት:: በኋላ ግን ትምህርት ቤቱ በደርግ ስርአት ተወርሶ ነገር ግን በኋላ እንደፈለጉት አልሆነም፤ ትምህርት ቤቱ ለሕዝብ ተሰጠ:: የህዝብ ትምህርት ቤት ተሰኘ:: እርሳቸውም በመሠረቱት ትምህርት ቤት ተቀጣሪ ሆኑ:: ነገር ግን ተቀጥረው ለመስራትም አልተመቻቸውም፤ ስለዚህ በስደት አሜሪካ ሄዱ:: እነሆ ዛሬ ደግሞ ትምህርት ቤቱ አድጎ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት አከበረ:: እርሳቸው ተጋባዥ እንግዳ ሆነው በመገኘት፤ የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ እንኳን ለ50ኛ ዓመት በዓል አደረሳችሁ አደረሰኝ ለማለት በቁ::
እንዴት ከ50 ዓመት በፊት የግል ትምህርት ቤት አቋቋሙ? እንዴት ትምህርት ቤቱ የሕዝብ ሆነ? በምን ምክንያት ትምህርት ቤቱን ለቅቀው ተሰደዱ? የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት በተመለከተ ምን ይላሉ? በሚሉ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል:: መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- በ1962 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርትዎን አጠናቀቁ፤ በ1964 ዓ.ም ትምህርት ቤት ከፍተው እንደነበር ሰምቻለሁ:: በዛ ዘመን ትምህርት ቤት የመክፈት ሃሳቡ እንዴት መጣልዎ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሥራ ባገኝም ወደ በረሃ አትሔድም ተብዬ ተከለከልኩ፤ በ1963 ዓ.ም ትምህርት ቤት ለመክፈት ፍላጎት ስለነበረኝ፤ ምን ዓይነት መንገድ ብጠቀም የተሻለ ይሆናል? ብዬ ፈቃድ አውጥቼ ሶስት ክፍል ቤት ተከራየሁ:: ህዳር 4 ቀን በ1963 ዓ.ም የምግብ ማብሰያ ኩሽናውን ቢሮ አድርጌ መምህራንን ቀጥሬ በሶስቱ ክፍል ማስተማር ጀመርኩ:: የተማሪዎቹ ቁጥር 68 ነበር፤ ክፍሎቹ በቂ አልነበሩም:: ስለዚህ ለእናቴ ትምህርት ቤቱን በቤተሰቡ መሬት ላይ አስፋፍቼ ልሥራ አልኳት:: እህት እና ወንድሞቼን አስፈቀደች:: የተቃወመ አልነበረም::
በጊቢው የነበረው ዛፍ ተቆረጠ:: በዛ ጊዜ የተቆረጠው ዛፍ ብቻ 990 ብር ተሸጠ:: ይህ ብር በጣም ብዙ ነበር:: ዛፉ ተሸጦ ገንዘብ ቢገኝም ጉቶውን መቁረጥ ፈተና ሆኖ ነበር:: ሰዎች በነፃ ነቅለው እንዲወስዱ ብፈቅድም፤ ብዙ ሰው ባለመውሰዱ የጉልበት ሰራተኛ ተቀጥሮ ጉቶ ተነቅሎ ሜዳው ተስተካከለ:: በአስቤስቶስ (በሲሚንቶ) ግድግዳቸው ያማረ 10 ክፍሎች ተሰሩ:: መጀመሪያ ለማስተማር ፈቃድ የተሰጠኝ እስከ ሶስተኛ ክፍል ብቻ ነበር:: ክፍሎቹ ተገንብተው ሲታዩ ትምህርት ቤቱ አስደሳች ሆነ፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል እንዳስተምር ፈቃድ ተሰጠኝ፤ ሥራዬን ቀጠልኩ::
አዲስ ዘመን፡- በ1964 ዓ.ም በግለሰብ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ተማሪዎች በክፍያ ይማሩ ነበር?
አቶ ሸዋንግዛው፡- አዎ! ብዙ ቦታ የግል ትምህርት ቤቶች ነበሩ:: በጊዜው መምህራንን በተለይ አስራ ሁለተኛ ክፍል አጠናቀው ሥራ ያልያዙትን መቅጠር የተለመደ ነበር:: በመጀመሪያ መምህራን የሚቀጠሩት በ40 ብር ነበር:: ተማሪዎች ደግሞ በወር የሚከፍሉት ለ1ኛ ክፍል አንድ ብር ከሃምሳ፤ ለሁለተኛ ክፍል ደግሞ ሁለት ብር ነበር:: በየደረጃው ክፍያው እንደዛው እየጨመረ ይቀጥላል:: እስከ መስከረም 18 ቀን 1968 ዓ.ም ድረስ ትምህርት የሚሰጠው በክፍያ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ትምህርት ቤቱን ሲከፍቱ ዓላማዎት ምን ነበር? ማትረፍ ነው? ወይስ ሌላ ዓላማ ነበርዎት?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ስለዕድገት እና መልካም ዜጋን ስለማፍራት በተደጋጋሚ አስባለሁ:: ይህ ሊሆን የሚችለው በትምህርት እንደሆነ ልቤ ያምናል::
ስለዚህ መምህር መሆንንም አስብ ነበር:: መምህር ትልቅ የአገር ባለውለታ ነው:: ወታደር ዳር ድንበር ጠብቆ አገር እንደሚያቆየው ሁሉ፤ መምህርም ጥሩ ዜጋን በመቅረፅ አገር የሚረከብ ትውልድን የሚያፈራ ሰው ነው:: በአገራችን ብዙ ክብር እና ቦታ ተሰጥቶት ባይኖርም፤ የሚከፍለው መስዋዕትነት ቀላል አይደለም:: የመምህር አበርክቶ በህዝብ ዕድገት ላይ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም:: ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ትምህርትን ለማስፋፋት እና ለማሳደግ አስቤ ነበር:: ገንዘብ ትርፍ ብፈልግማ ነጋዴ መሆን እችል ነበር::
ትምህርት ቤቱን የጀመርኩት ሙሉ ለሙሉ እናቴ ገንዘብ ሰጥታኝ ነው:: ከመርካቶ የሚገኘው ገንዘብ ወደ ሶስት ሺህ ብር እና ሌላም ተጨማሪ ገንዘብ ጨምራልኝ ለመምህራን ደሞዝ እና ለሌሎችም የትምህርት ቤት ወጪዎች ሳውል ነበር:: የተማሪዎቹ ክፍያ ለመምህራን ደሞዝም በቂ አልነበረም::
እናቴ ትምህርት ቤቱን እንድገነባ ከመፍቀድ አልፋ፤ በገንዘብ ስትደግፈኝ በጣም ደስተኛ ነበርኩ:: ግርማ አካሉ ከተባለው ከታላቅ እህቴ ልጅ ጋር ማስተማር ስንጀምር ጥረታችን በስነምግባር የታነፀ ብቁ ዜጋን ማፍራት ነበር:: የትልቋ እህቴ ልጅ ግርማ ግን ብዙ አልቆየም:: ለትምህርት ወደ ራሺያ ሔደ:: እኔ ግን ትምህርት ቤቱን ማጠናከር ቀጠልኩ:: የተማሪዎችም ቁጥር 258 ደረሰ። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ የደርግ መንግስት የግል ትምህርት ቤቶችን የሕዝብ እንዲሆኑ የሚደነግገውን አዋጅ አወጀ።
አዲስ ዘመን፡- አዋጁ ሲታወጅ እና ትምህርት ቤትዎ ሊወረስ መሆኑን ሲሰሙ ምን ተሰማዎ?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ሁልጊዜም መኝታዬ አጠገብ ሬዲዮ እና ትንሽ ቴፕ አስቀምጥ ነበር:: ደርግ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሚታወጁ አዋጆችን ዕቀዳ ነበር:: በየዕለቱ የሚታተሙ ጋዜጣዎችን ተከታትዬ አነባለሁ፤ አሰባስባለሁ:: አዲስ ዘመን፣ ፖሊስ እና እርምጃው እንዲሁም ሌሎች ጋዜጦችንም እየገዛሁ እያነበብኩ ጠርዤ አስቀምጥ ነበር:: አዋጆችንም በተመሳሳይ መልኩ ጠዋት፣ ምሳ ሰዓት ላይም ሆነ ማታ በማንኛውም ሰዓት ሲታወጅ ቀድቼ አስቀምጥ ነበር::
መስከረም 18 ቀን 1968 ዓ.ም ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ተኝቼ ጊዜያዊው ወታደራዊ አስተዳደር የግል ትምህርት ቤቶችን የሕዝብ የሚያደርግ አዋጅ አውጇል ሲል እንደልማዴ አዋጁን ቀዳሁት:: ለጊዜው ደነገጥኩ፤ ግን የተወረሰው የግል ትምህርት ቤት ብቻ አይደለም:: ትልልቅ የእርሻ መሬቶች ፣ ሱቅ እና ቤቶች የተወረሰባቸው ብዙ ናቸው:: የእኔ የተለየ አልነበረም:: ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ የቤተሰቦቼ የከተማ ቦታ እና ብዙ ቤት ተወርሷል::
እናቴ በጠዋት ቤተክርስቲያን ሔዳ ነበር:: ሰዎች ነግረዋት ተደናግጣ ወደ ቤት መጣች፤ አመጣጧ ካልሰማሁ ቀሥ ብላ ነግራ ልታፅናናኝ ነበር:: ነገር ግን ወደ ቤት ስትገባ ሬዲዮ እያዳመጥኩ ነበር:: ቀድሜ መስማቴን ስታውቅ ‹‹ያለ የሌለ ገንዘቤን ሰብስቤ እሰጥሃለሁ፤ ሌላ ሥራ ትጀምራለህ›› አለችኝ:: ይናደዳል ብላ ሰግታ ነበር:: በኋላ ግን እውነት ለመናገር ምንም አልመሰለኝም:: ምክንያቱም አዋጁ የታወጀው በእኔ ላይ ብቻ አይደለም::
በማግስቱ መስከረም 19 በጠዋት እንደለመድኩት ትምህርት ቤት ሔድኩ፤ ምንም አልነበረም:: ያሉ ነገሮችን አዘጋጀሁኝ:: ከትምህርት ቢሮ ተደውሎ የሚያረካክቡ ሰዎች እንደሚመጡ እና እንድዘጋጅ ተነገረኝ፤ የነበረውን የዕለት መንቀሳቀሻ ገንዘብ ፒቲ ካሽ ሳይቀር አዘጋጀሁ::
አረካካቢዎች መጡ:: በአካባቢያችን የኮንጎ ዘማች የወታደር ልጆች ይበዙ ነበር:: የኑሮ ሁኔታቸው ዝቅተኛ ስለነበር የፅህፈት መሳሪያ እና መፅሃፍት ሳይቀር እየሠጠሁ ወደ 58 ተማሪዎች በነፃ አስተምር ነበር:: አረካካቢዎች የትምህርት አመራር ኮሚቴ ይመረጣል አሉ::
የትምህርት አመራር ኮሚቴ መምህራንንም ሆነ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር መቅጠርም ማባረርም ይችላሉ ተባለ:: የአካባቢው ማህበረሰብ ተሰበሰበ፤ የትምህርት አመራር ኮሚቴ ለመሆን መስፈርት አልነበረውም:: በኮሚቴነት ከተመረጡት መካከል ሶስቱ ጉሙሩክ ውስጥ የጉልበት ሥራ የሚሠሩ ነበሩ:: በኮሚቴው ውስጥ ሌሎችም ደህና የተማሩ ሰዎችም ነበሩ:: እኔ በዛን ጊዜ ትንሽ ንብረት ያለው ሰው ‹‹አድሃሪ ›› ይባል ስለነበር፤ ለመመረጥ አልፈለግኩም::
ህዝቡ ግን በሆታ ‹‹በፍፁም ልጆቻችንን በነፃ ሳይቀር ሲያስተምር የነበረ ሰው ከትምህርት ቤቱ መለየት የለበትም…›› አለ:: የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ይሁን ተባልኩኝ:: አዋጁ ላይ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር የኮሚቴው ሊቀመንበር ይሆናል ይላል:: ስለዚህ ኮሚቴው የሚለውንም ሆነ የሚወስነውን ከመስማት አልፌ በትምህርት ቤቱ ጉዳይ ላይ ድምፅ መስጠት ቻልኩ:: ነገር ግን ሌላ ነገር ተከሰተ:: እኔ ትምህርት ቤቱን ስመራ ለራሴ የምወስደው ምንም ገንዘብ አልነበረም:: በርዕሰ መምህርነት ስቀጠር ቀድሞ ደሞዝህ ስንት ነበር የሚል ጥያቄ ቀረበ:: እኔ ደግሞ እውነቱን ተናገርኩ፤ የማገኘው ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበረም አልኩ፤ እኔም ሆንኩ የእህቴ ልጅ ስንሰራ በደሞዝ አልነበረም::
አንዳንዶቹ የኮሚቴ አባላት ሆን ብለው በቀል በሚመስል መልኩ ‹‹ለራሱ ሲከፍል የነበረውን ደሞዝ በማስረጃ ያቅርብ ያለበለዚያ ለመክፈል እንቸገራለን›› በማለታቸው ለረዥም ጊዜ ያለደሞዝ ቆየሁ:: በኋላ በአንድ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ስምንት የሚደርሱ የጊዜው አመራሮች የተወረሱ ትምህርት ቤቶችን እየዞሩ ሲጎበኙ፤ እኛ ትምህርት ቤት መጡ:: የዛን ጊዜ የተማሪዎቻችን ቁጥር ከፍ ብሏል፤ የትምህርት ቤቱም ሁኔታ ተጠናክሮ በደንብ መስመር በመያዙ እና የሚመጡ የትምህርት መመሪያዎች በደንብ እየተተገበሩ ነበር::
ሁሉን ነገር በሥነሥርዓት ይዤ ስለነበር ባዩት ሁኔታ በጣም ተደሰቱ:: ‹‹ደሞዝ ስንት ነው?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ:: ደሞዝ እየተከፈለኝ አይደለም አልኩኝ:: ‹‹ቤተሰብ የለህም እንዴ?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡ፤ ‹‹አዎ›› የሚል ምላሽ ሰጠሁ:: ‹‹ቤተሰብም ባይኖር ደሞዝ ሊከፈለው ይገባል›› ብለው የትምህርት አመራር ኮሚቴውን ጠየቁ::
የትምህርት አመራር ኮሚቴው ‹‹ደሞዙን ለመወሰን እርሱ መነሻ ደሞዝ ስለሌለው ተቸግረን ነው›› ሲል ምላሽ ሠጠ:: ‹‹እንደዛ ቢሆን ሰው እየሠራ እንዴት አይበላም? በአስቸኳይ ደሞዙን ወስናችሁ እንድታሳውቁን::›› ብለው ትዕዛዝ ሰጡ:: በአጋጣሚ እናቴ የገዛችልኝ መኪና ነበረኝ:: አንዱ የኮሚቴው አባል ‹‹እርሱ የሕዝብ ገንዘብ እየበላ ተንደላቆ መኪና እየነዳ የሚኖር ነው::›› አለ::
ሌላ የኮሚቴ አባል ደግሞ ‹‹ታዲያ መኪና ቢነዳ ምን አገባን የሠራውን ትምህርት ቤት ወርሰን እያሠራነው የግል ሕይወቱ ውስጥ መግባት የለብንም::›› አሉ:: እኔ ወጥቼ ኮሚቴው ተነጋግሮ በጊዜው እርግጠኛ ባልሆንም የቆረጡልኝ ደሞዝ ከ200 ብር አይበልጥም ነበር:: ነገር ግን ደሞዝ ባይከፈለኝም ስራዬ አልተደናቀፈም ነበር:: ከዛ ተነስተን ትምህርት ቤቱ አደገ፤ ተማሪው በሺ መቆጠር ጀመረ::
አዲስ ዘመን፡- የመሠረቱትን የለፉበትን ትምህርት ቤት ትተው የሄዱት መቼ ነው? ለምን ሔዱ? ይህንን ውሳኔ ለመወሰን ያደረስዎ ምን ነበር?
አቶ ሸዋንግዛው፡- ጊዜው 1983 ዓ.ም ነበር:: ኢህአዴግ አገሪቷን ሲቆጣጠር በየቀበሌው ሰላምና መረጋጋት፤ በየትምህርት ቤቱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተቋቋመ:: መምህራኑ ኮሜርስ አካባቢ አውሮራ ጎን ያለው የኢህአዴግ ተወካይ ጋር በትምህርት ሰዓት ስብሰባ ብለው በመሄዳቸው ተማሪዎቹ በበቂ ሁኔታ የሚማሩበት ዕድል ተመናመነ:: እኔ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በመሆኔ ብዙ አለመግባባት ተፈጠረ::
ቦታው ላይ በመሆኔ ትምህርት ቤቱን የመምራት ሙሉ ኃላፊነት ነበረብኝ፤ ስለዚህ መምህራኖቹን እባካችሁ ተው አልኩኝ:: ኃላፊ የተባለው ሰው ታጋይ ነው፤ መምህራኖቹን በአግባቡ ሥራችሁን ሥሩ በማለቴ ቢሮ ጠርቶ መሳሪያ አስቀምጦ እጅግ አዋርዶ ሰደበኝ:: ተስፋ ቆርጬ እኔ ልጆች ወልጃለሁ፤ አንተንም ብወልድህ አደርስሃለሁ፤ ለህዝብ መጥተናል እያላችሁ ይህን ያህል ሰው ማዋረድ ተገቢ አይደለም፤ ብዬ ተናገርኩት::
አስተማሪዎችን ትንቃለህ፤ ታዋርዳለህ ብሎ ለመገሰፅ ሞከረ:: እኔ በፍፁም ሰው አልንቅም፤ ሰውን ካላከበርኩ ክብር እንደማላገኝ አውቃለሁ:: እነርሱ የነገሩህን ብቻ ሳይሆን እኔንም እኩል ማዳመጥ አለብህ አልኩት:: ስንነጋገር አንድ ሌላ እንደእርሱ አይነት መሣሪያ የያዘ መጥቶ ሲያዳምጥ የነበረ ሰው ‹‹እርሳቸው ይሂዱ እኔ እፈልግሃለሁ›› አለው:: ‹‹ትምህርት ቤት ድረስ እመጣለሁ፤ እንደዚህ ህዝብ ላይ እያላገጡ መኖር አይቻልም፡ አሁን ከቢሮዬ ውጣ›› አለኝ::
ከቀናት በኋላ ወደ ትምህርት ቤት መጥቶ እርሱ ጋር ከሚመላለሱ መምህራኖች ጋር ሲያወራ ቆይቶ፤ ‹‹ ከአሁን በኋላ ወደ እኔ ሊመጡ ሲሉ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳትፈጥርባቸው›› አለኝ:: እኔም እሺ አንተ ጋር ሁለት እና ሶስት ሆነው ሲመጡ ተማሪዎቹ ስለማይማሩ ተማሪዎቹን ወደ ቤታቸው እሰዳቸዋለሁ አልኩት:: ትቶኝ ሔደ:: ወዲያው በሳምንቱ ቅዳሜ ከሰዓት የትምህርት አመራር ኮሚቴው እና መምህራኖቹ እንዲገኙ አዘዘ::
በዕለቱ ሶስት ታጣቂዎችን ይዞ ተገኙ:: ሁለቱ ታጣቂዎች ስብሰባው ውስጥ ገቡ፤ አንዱ ታጣቂ እደጅ ቆመ:: በሰዓቱ እነዛ የቅሬታ ኮሚቴ አባላት የተባሉት መምህራኖች ብዙ ነገር ተናገሩ:: ‹‹ይንቀናል፤ ትሸታላችሁ ይለናል›› አሉ:: ነገር ግን እኔን የሚለካኝ የትምህርት ቤቱ ውጤታማነት ነበር:: በዛን ጊዜ በዞኑ ጠንካራ ተብሎ የሚጠራ ትምህርት ቤት ነበር:: ለዛ ደረጃ ያደረስኩት ብዙ ለፍቼ ነው::
የትምህርት አመራር ኮሚቴዎቹ ደግሞ ቅሬታ ያቀረቡትን መምህራኖች ‹‹እስከዛሬ ምንም ሳትሉ ለምን ዛሬ እንደዚህ ትላላችሁ?›› አሏቸው:: በእርግጥ እኔ ተማሪዎች በሳምንት ሁለት ጊዜ ጥፍራቸውን እንዲቆረጡ እና አጠቃላይ ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ ፀጉራቸውን እንዲያበጥሩ እና ንፁህ እንዲሆኑ እቆጣጠር ነበር:: ተማሪዎቹም ጎበዝ ነበሩ:: ‹‹እኛ ክትትል እንደሚደረግብን፤ መምህራኖችስ ለምን ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ አትከታተሉም፤ ጫማቸው የሚሸት መምህራኖች አሉ::›› ብሎ ስሙን ሳይፅፍ በጣም የማከብረው አንድ ጎበዝ ተማሪ በሃሳብ መስጫ ሳጥን ውስጥ የተቀነባበረ አስተያየት ፅፎ አገኘሁ:: ማንነቱን ደረስኩበት፤ ሃሳቡም ትክክል ነበር:: የመምህራን ስብሰባ ላይ በተማሪዎች የተፃፈውን ተናገርኩ፤ መምህራን ንፅህናችሁን ጠብቁ በማለቴ በዕለቱ ያንን ስብሰባ አስታውሰው ወቅሰው ተናገሩ::
ቢሮው ውስጥ ሲያዋርደኝ የነበረ ሰው በድጋሚ በሰዎች ፊት አዋርዶ መናገር ጀመረ:: ስነስርዓት ያዝ አልኩት:: ከትምህርት ቤቱ አጠገብ ቀበሌ 24 አለ:: እዛ የሠፈሩ ታጣቂዎች ነበሩ:: እኔ ታጣቂዎቹን ሳይቀር ማታ ማታ አስተምር ነበር:: ነገሩ ጠንከር ሲል ሃይለኛ ራስ ምታት ጀመረኝ፤ ከዛ ወስዶ ሊያስረኝ እንደሚችል ገመትኩ፤ ስለዚህ ዶክሜንት አምጥቼ እንዳሳይ ይፈቀድልኝ አልኩ::
ሲፈቅዱልኝ ቀድሜ በሳምሶናይት ያዘጋጀሁትን የተዘጋጀ ሰነድ ከቢሮዬ ይዤ በግቢው በዋናው በር ሳይሆን፤ በሴቶች መፀዳጃ ቤት አድርጌ ወደ ሰው ጊቢ ዘለልኩ:: አቆራርጬ ቤቴ ገባሁ፤ ራሴን ሳትኩ በኃይል ነሰረኝ:: ብዙ ደም ፈሰሰኝ:: ባለቤቴም በጊቢው ውስጥ ያሉ እህት ወንድሞቼ መላው ቤተሰቤ ተደናገጠ:: ለሶስት ቀን ሆስፒታል ተኛሁ::
ከሆስፒታል ስወጣ ባለቤቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የቅሬታ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ የሆኑትን ሰው ቀጠሮ አስይዛ በጋራ አብረን አስረዳን:: ሲያዋርደኝ የነበረው ቂርቆስ አካባቢ የነበረው ሰው እና ቅሬታ አቀረቡ የተባሉ የቅሬታ ሰሚ መምህራን ስለጉዳዩ ማስረጃ ይዘው እንዲያስረዱ እኔም ማስረጃዬን እንዳቀርብ ተነገረኝ:: የቅሬታ ሠሚ ኮሚቴዎች ተብለው እኔን ሲያሰቃዩኝ የነበሩት መምህራን ብዙ ጥፋት ነበረባቸው፤ ስለዚህ ሰነዳቸውን ማደራጀት ከባድ አልነበረም:: በቀጠሮ ቀን ተገኘሁ፤ ኮሚቴዎቹ ግን ቀሩ::
ዋና ሰብሳቢው በብስጭት ማስረጃቸውን ይዘው እንዲያቀርቡ በድጋሚ አዘዛቸው:: እኔ በሙሉ አቀረብኩ:: እነርሱ ግን ማስረጃ ለማቅረብ ሁለት ወር ጠየቁ:: ‹‹አይሆንም ሁለት ወር ብዙ ነው፤ የከሰሳችሁት ውሸታችሁን ነው ማለት ነው::›› አላቸው:: ተጨማሪ ዕድል ቢሰጣቸውም በድጋሚ ማስረጃ ማቅረብ አቃታቸው፤ በመጨረሻም ከስራዬ አግደውኝ ነበር:: ወደ ሥራ እንድመለስ፤ በምትካቸው አዲስ ኮሚቴ እንዲመረጥ ለደቡብ ትምህርት ዞን ፅህፈት ቤት ደብዳቤ ተፃፈ::
መምህራን በትምህርት ሰዓት ከጊቢ መውጣትም ሆነ ስብሰባ መሔድ እንደማይችሉ በመግለፅ በመመሪያ መሠረት ሥራዬን እንድቀጥል ተነገረኝ:: ያ እንደዛ ሲያዋርደኝ የነበረ ሰው ተጠርቶ በድጋሚ ያንን ድርጊት እንዳይፈጽም ማስጠንቀቂያ ተሰጠው:: ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በሳምንቱ አሜሪካን እሄድ ነበር:: ሰኞ ግን ሥራ ገባሁ:: በሥራ ላይ ቂም በቀል የለም፤ የሚሰማችሁን አቅርባችኋል የሚዳኘን ህግ ነው፤ በሥራ ሰዓት ስብሰባ መሄድ አትችሉም ብዬ ተናግሬ ስራዬን ቀጠልኩ::
እሁድ የወላጆች ስብሰባ ነበር:: አርብ እስከ ምሽት ሶስት ሰዓት ሥሠራ ቆይቼ ማንም ሳይሰማ ቅዳሜ ጠዋት እንገናኛለን ብዬ ወደ ቤቴ ሄድኩኝ:: እኔ ግን ቅዳሜ ጠዋት ወደ አሜሪካ ለመሄድ ኤርፖርት ተገኘሁ:: መሔዴን ማንም ሰለማያውቅ ከአገር እንዳይወጡ ከተዘረዘሩ ስሞች ውስጥ የእኔ ስም አልነበረም፤ በዚህ መልኩ የመሠረትኩትን ትምህርት ቤት ትቼ ሄድኩ::
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ወደ አሜሪካ የሄዱት በሁኔታው ተማረው ነው ወይስ ቀድሞም አሜሪካ መሄድ ይፈልጉ ነበር?
አቶ ሸዋንግዛው፡- በፍፁም አሜሪካን መሔድ አልፈልግም ነበር:: በዛ በ45 ዓመት እድሜዬ አሜሪካንን እንዴት አስባለሁ? በ45 እና በ46 ዓመት ስደት እና ኑሮን ከዜሮ መጀመር በጣም ከባድ ነው:: ከዛ በፊትም ዕድሉ ነበረኝ:: ግን አልሔድኩም:: ፈጣሪ በዚያ ኑር ልጆችህንም በዛ አሳድግ ሲል በዛ ዕድሜ ከአገሬ ወጣሁ::
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ቤቱን 50ኛ ዓመት ለማክበር ተጠሩ፤ ምን ተሰማዎት?
አቶ ሸዋንግዛው፡- በጣም ተደስቻለሁ፤ በአጥር ዘልዬ እስከ መውጣት ደርሼያለሁ:: አሁን ግን ተገቢው ክብር ተሰጥቶኝ ትምህርት ቤቱም እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በማየቴ ደስ ብሎኛል:: ያስተማርኳቸውን ተማሪዎቼን አሜሪካንም በተለያዩ ቦታዎች አግኝቻቸዋለሁ:: ዋሽንግተን ሆስፒታል ውስጥ ሌሎችም ትልልቅ ቦታዎች ላይ ደርሰው ያገኘኋቸው አሉ:: በሆነው ባለውና ባለፈው በሁሉም ነገር ደስተኛ ነኝ:: ጓደኞቼ አልፈዋል:: እኔ ጤነኛ ነኝ:: 76 ዓመቴ ነው፤ ጡረታ ወጥቻለሁ:: ነገር ግን ረዥም ሰዓት ኮምፒውተር ላይ አሳልፋለሁ:: መፅሃፍ አነባለሁ፤ እዋኛለሁ፤ እስፖርት እሰራለሁ:: ምንም አይነት ችግር የለብኝም::
አዲስ ዘመን፡- ከ50 ዓመት በፊት ትምህርት ቤት ከፍተዋል:: መምህር ነበሩ፤ ውጪም ኖረዋል:: የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓትን በተመለከተ ምን ይላሉ?
አቶ ሸዋንግዛው፡– የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ነው:: ቀድሞም ቢሆን መምህራን እና ተማሪዎች ግንኙነታቸው የአባት እና የልጅ መሆን አለበት:: ከአገር ከወጣሁ በኋላ ተማሪዎች መምህራንን ይገመግሙ ነበር ሲባል ሰምቼያለሁ:: መምህራን ተከብረው በተሰጣቸው ኃላፊነት ትውልዱን የሚቀርፁ መሆን አለባቸው:: ተማሪዎች ትምህርት ቤቱን እና መምህራኖችን አክብረው ቀለም መቅሰም አለባቸው:: በቀዳማይ ኃይለስላሴ ጊዜ በቀዳማይ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ተማሪ ነበርኩ:: የትምህርት ስርዓቱ ጥሩ ነበር::
በደርግ ጊዜ ግን ሥርዓቱን ለማራመድ የሚያስችል የትምህርት ስርዓት ተቀረፀ:: ብዙ ችግር የተፈጠረው በዛ ምክንያት ነው:: ነገር ግን አሁንም በተመሳሳይ መልኩ መምህሩ ምን ማስተማር አለበት ተማሪውስ ምን መማር አለበት ለሚለው የነጠረ መመሪያ የለም:: በዚህ ምክንያት በትምህርት አመርቂ ውጤት ማግኘት አልተቻለም::
በእርግጥ የዛሬ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምጡቅ አዕምሮ ያላቸው ብዙ መሆናቸውን ተከታትዬ አይቻለሁ:: አሜሪካን ድረስ ሔደው የሚማሩ፤ በኢትዮጵያም ያሉ ብዙ ናቸው:: ነገር ግን በአግባቡ አልተያዙም:: ዋናው ችግር ግን ፖለቲካው እና ትምህርት የተለያዩ አለመሆናቸው ነው:: በተጨማሪ የችግር መነሻ መንግስት እና ፖለቲካው ነው ብንልም፤ ዋናው ግን የህብረተሰቡ በአግባቡ ኃላፊነትን አለመወጣትም ዋነኛው መንስኤ ነው:: ወላጆች አጠቃላይ ማህበረሰቡ ግፊት አያደርግም:: መስተካከል ያለበት ሥርዓተ ትምህርት እንዲስተካከል ሕዝብ መጠየቅ አለበት::
ትምህርት የሥርዓት ለውጥን ተከትሎ የሚቀያየር መሆን የለበትም:: በአፍሪካ ውስጥ የተለመደው አንድ መንግስት ሔዶ ሌላ ሲተካ የትምህርት ስርዓቱ ላይም የተሠራውን አፍርሶ እንደአዲስ መጀመር ይስተዋላል:: ይሔ ትክክል አይደለም:: ይህ እንዳይሆን ሕዝብ መታገል አለበት:: ትምህርት ከሁሉም ነገር በላይ ነው:: የትኛውም መንግስት ይምጣ የትኛውም መንግስት ይሒድ ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር መገናኘት የለበትም:: ማንኛውም መንግስት የትምህርት ሥርዓቱን እንደፈለገው የማድረግ መብት የለውም:: የትኛውም መንግስት የሚመጣው በሕዝብ ምርጫ ነው:: ግን ደግሞ መሥራት ያለበት ለህዝብ የሚበጅ ነገር ብቻ ነው:: በእርግጥ እዚህ ላይ የሕዝቡም ዳተኝነት አለ::
አዲስ ዘመን፡- አገር እንድታድግ እና እንድትለወጥ ቀጣይነት ያለው የትምህርት ስርዓት እንዲኖር ምን መሠራት አለበት?
አቶ ሸዋንግዛው፡- እንደኔ ሃሳብ ቀጣይት ያለው ሥርዓተ ትምህርትን መቅረፅ የሚችሉ ብዙ ምሁራን አሉ:: ስርዓተ ትምህርቱ ልክ እንደ ህገመንግስት ምሁራን ተቀምጠው ከሃይማኖትም ሆነ ከብሔር ተፅዕኖ ውጪ ሆነው ማዘጋጀት አለባቸው:: ይህ ሥርዓት እንደ ህገመንግስት ሁሉም ሊመራበት ይገባል:: አሁን የሚታዩት ባለምጡቅ ዓዕምሮ ልጆች ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው እንጂ ከትምህርት ቤት ባገኙት ዕውቀት ነው የሚል እምነት የለኝም::
እንደሚታየው የሥርዓተ ትምህርት በየጊዜው እየተለወጠ ነው:: መጀመሪያም ቢሆን ተማሪዎች 10ኛ ክፍል ተፈትነው ትምህርት እንዲያቆሙ መደረጉ በየትኛውም ዓለም የሌለ ነው:: በሰለጠነውም ዓለም ትምህርት እስከ 12ኛ ክፍል ነው:: አሜሪካንም ተመሳሳይ ነው:: በኢትዮጵያ ግን ትምህርት ከፖለቲካ ጋር የተቆራኘ ነው:: ነገር ግን ቋሚ እና አገሪቷን ሊወክል የሚችል የትምህርት ሥርዓት መኖር አለበት:: እዚህ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡- በውጪው ዓለም ለትምህርት እና ለምርምር ዘርፍ የሚመደበው በጀት ከፍተኛ ነው:: ከህዝብ ባሻገር መንግስትስ ለትምህርት ዘርፍ በጀት ከመመደብ ጀምሮ የሚሰጠው ትኩረት ምን ያህል መሆን አለበት?
አቶ ሸዋንግዛው፡– ለትምህርት ዘርፉ በቂ በጀት ሊያዝለት ይገባል፤ ነገር ግን እንደማውቀው ከሆነ ለትምህርት ዘርፉ የሚወሰነው በጀት በቂ አይደለም:: በቅድሚያ መንግስት በትምህርት ዘርፍ ላይ የሾማቸው ሰዎች የትምህርት ችግር ምንጩ ምንድን ነው የሚለውን ማየት አለባቸው:: አገሪቷን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የሚቻለው ተረካቢ የሚኖርበትን ሁኔታ በመፍጠር ነው:: ስርዓተ ትምህርቱ ላይ ብዙ ነገሮችን እያየን ነው:: የሚያስተውል የሚመረምር ትውልድ ካልተፈጠረ ዞሮ ዞሮ አገርን መግደል ነው:: ያልተማረ ትውልድ የአገርን እግር መተብተቡ አይቀርም::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ::
አቶ ሸዋንግዛው፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም