የደም ማነስ በሽታ የሚከሰተው በሰውነታችን ውስጥ የሚገኙ ቀይ የደም ህዋሳት ቁጥር ሲያንስ ወይም በውስጣቸው የሚገኘው ሄሞግሎቢን የሚባለው ሞለኪውል መጠን ሲያንስ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቀይ የደም ህዋሳት በደማችን ውስጥ ከሚገኙ ብዙ አይነት ሌሎች ህዋሳት አንደኛው ሲሆኑ ዋነኛ ስራው በደም ስራችን ውስጥ ኦክስጅንን ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ነው። ሁሉም የሰውነት ክፍሎቻችን ይህንን ኦክስጅን ከምግብ የምናገኘውን ንጥረ ነገሮች ወደ ኃይል (ጉልበት) ለመቀየር ይጠቀሙበታል። በመሆኑም የደም ማነስ በሚኖርበት ጊዜ የሰውነታችን ህዋሳት በሙሉ በቂ ኃይል ስለማያገኙ ድካም፣ አቅም ማጣት እና የመሳሰሉ ምልክቶች ይስትዋላሉ።
የደም ማነስ ህመም ብዙ ሰዎችን ያጠቃል። ይሄ ችግር በተለይ እንደኛ ባሉ ታዳጊ አገራትና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ላይ በብዛት ያታያል። በተለይም በህጻናት፣ እርጉዝ ሴቶች እና በእድሜ የገፉ አረጋውያን ላይ የችግሩ ተጋላጭነት ይበልጥ የጨመረ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች 25 በመቶ የሚደርሱት ወይም ከአራት ሰው አንዱ የደም ማነስ በሽታ ይገኝበታል፤ ይህም ወደ 1 ነጥብ 62 ቢልየን ሕዝብ በዓለም ላይ የደም ማነስ ችግር ውስጥ መሆኑን ያመላክታል ።
50 በመቶ ያህሉ ለትምህርት ያልደረሱ ህፃናት የደም ማነስ ህመም አለባቸው፣ የሚለው ይኸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከእርጉዝ ሴቶች መሃል 40 በመቶ የሚደርሱት ለደም ማነስ ህመም የተጋለጡ ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ በእርግዝና እና ወሊድ ጊዜ ለተለያዩ ህመሞች ከማጋለጡም በላይ ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን ይጠቀሳል።
የደም ማነስ በምን ምክንያት ይፈጠራል ?
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው የደም ማነስ በቀይ የደም ሴሎች (ህዋሳት) ቁጥር ማነስ ወይም በውስጣቸው የሚገኘው ሄሞግሎቢን መጠን መቀነስ የሚመጣ ችግር ነው። ይህ ደግሞ በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ይከሰታል ተብሎ በዓለም ጤና ድርጅት ተቀምጧል።
1. ሰውነታችን በቂ የሆነ ቀይ የደም ሴል (ህዋሳት) ሳያመርት ሲቀር፦ መቅኒ (bone marrow) ቀይ የደም ሴሎች (ህዋሳት) የሚመረቱበት ቦታ ነው። ለግንባታው የሚያስፈልጉት ንጥረ ነገሮች አይረን (Iron፣ ቪታሚን ቢ 12 /Vitamin B 12፣ ፎሊክ አሲድ Folic acid በ በቂ ሁኔታ ካላገኘን የምርት መጠናቸው ስለሚቀንስ የደም ማነስ ይከሰታል።
2 ቀይ የደም ህዋሳት በተለያዩ ምክንያቶች ቶሎ ቶሎ የሚሞቱ ከሆነ፦ ቀይ የደም ሴሎች በአማካይ 120 ቀን ወይም 3 ወር ያህል ይኖራሉ። ከዛ መቅንያችን በሚያመርተው በአዲስ ሴሎች (ህዋሳት) ይተካሉ። ለዚህም ነው አንድ ጤነኛ ሰው ሌላ ችግር እስከሌለበት ድረስ በየሶስት ወሩ ደም ቢሰጥ ችግር የለውም የሚባለው። የተለያዩ አይነት በሽታዎች ለምሳሌ ወባ፣ ቀይ የደም ህዋሳት ከላይ ከተገለጸው ጊዜ ቀድመው ቶሎ እንዲሞቱ በማድረግ የደም ማነስ በሽታ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
3 የደም መፍሰስ፦ ከአደጋ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ከፍተኛ የደም መፍሰስ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሴቶች ከወር አበባ ጋር ተያይዞ ብዙ ደም የሚፈሳቸው ከሆነ ወይም በወሊድ ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ለአጣዳፊ እና ዘላቂ የደም ማነስ ሊያጋልጥ ይችላል።
አደገኛ የደም ማነስ ምክንያት የቫይታሚን ቢ 12 እጥረት ነው። ስለዚህ፣ ምንም እንኳን በአመጋገብ በኩል በቂ ውሃ በማይጠጣበት ጊዜ ሊታይ የሚችል እውነት ቢሆንም፣ ይህ ምክንያት በውስጡ የበለፀጉ ምግቦችን በማስተዋወቅ በቀላሉ የሚስተካከል ነው:: ነገር ግን የቫይታሚን ቢ 12 ጉድለት መንስኤ የጄኔቲክ ችግር ወይም የአንጀት ሁኔታ በሚሆንበት ጊዜ ለአደገኛ የደም ማነስ ችግር የመጋለጡም መጣን በዛው ልክ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
ስለዚህ አንጀት ቫይታሚን ቢ 12 ን በበቂ ሁኔታ መምጠጥ በማይችልበት ጊዜ ይህ አደገኛ የደም ማነስ ይታያል። ይህ በአጠቃላይ በቂ ሞለኪውሎች (ውስጣዊ ምክንያቶች በመባል የሚታወቁት) በመኖራቸው ምክንያት በመደበኛ ሁኔታዎች ውስጥ እነዚህ ቫይታሚኖች በምግብ ውስጥ በመግባት በአንጀት ይመረታሉ።
አሁን፣ አንጀቶች ለምን በቂ ውስጣዊ ነገር አያደርጉም? ቢባል ምክንያቱ የአንጀት መታወክ እና በጄኔቲክ ስህተቶች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በጨጓራ ህመም ምክንያት የሆድ ውስጠኛው ሽፋን ሲዳከም ነው። እናም ይህ አንጀቶች ከዚያ በኋላ ቫይታሚን ቢ 12 እንዲወስዱ ይገደዳል። ቫይታሚን ቢ 12 በዚህ መንገድ መወሰዱ ደግሞ ለደም ማነስ ችግር ያጋልጣል፡፡
አደገኛ የደም ማነስ መንስኤዎች መከላከልን አስቸጋሪ ነው፤ እንደ እድል ሆኖ፣ በፍጥነት ከተያዙ፣ በህክምናው ብዙ ውጤቶችን ማምጣት ይቻላል።
የደም ማነስ ካለብን ምን ምልክቶች እናያለን?
የደም ማነስ በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጣ ስለሆነ ምልክቶቹ እንደ ምክንያቶቹ ሊለያዩ ይችላሉ። በዋነኝነት ግን የድካም ስሜት፣አቅም ማጣት፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የከለር መገርጣት ወይም ነጭ መሆን፣ አንዳንዴ ደግሞ እንደ በሽታው አይነት የአይን እና ቆዳ ከለር ቢጫ መሆን፣ የማዞር ስሜት፣ ራስ ምታት፣ የትኩረት ማጣት በተለይ ህጻናት ላይ ትምህርት የመማር አቅማቸውን እና የማስታወስ ችሎታቸው እንዲቀንስ ማድረግ ይጠቀሳል።
አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ምልክቶች ላይታዩና የግድ የላብራቶሪ ምርመራ ሊያስፈልግ የሚችልበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል።
በላብራቶሪ የደም ምርምራ የደም ማነስ አለ ምንለው መቼ ነው ?
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት አገላለጽ በላብራቶሪ የደም ምርመራ የደም ማነስ አለ የምንለው ለወንዶች የሄሞግሎቢን መጠን ከ 13 mg/dl በታች ሲሆን ለሴቶች ደግሞ ከ 12 mg/dl በታች ሲሆን ነው። ይህ ቁጥር እንደ እድሜያችን፣ የእንቅስቃሴያችን አይነት እና የምንኖርበት ቦታ ሊለያይ ይችላል:: ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ከፍታማና ተራራማ ቦታዎች በሚበዙበት አካባቢ ለምንኖር ሰዎች የሄሞግሎቢን መጠን ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።
በምርመራ ወቅት ከሄሞግሎቢን በተጨማሪ የደም ማነስን ሊያመጡ የሚችሉ ምክንያቶችን በተመለከተ የህክምና ባለሙያዎች ምርመራ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለምሳሌ የቫይታሚን ቢ12፣ የፎሊክ አሲድ መጠን እና የአይረን (የብረት ንጥረ ነገር) አብሮ ሊመረመር ይችላል።
የደም ማነስ እንዴት ይታከማል ?
የደም ማነስ በግዜ ካልታከመ ዘላቂ ችግር ሊያመጣ ይችላል። ህክምናውም እንደ ምክንያቱ ይለያያል። ለምሳሌ ህፃናት ከአይረን (የብረት ንጥረ ) ጋር በተያያዘ ለሚከሰት የደም ማነስ በጣም ተጋላጭ ናቸው። ይሄ ደግሞ አካላዊ እና አእምሮኣዊ እድገታቸውን ይጎዳዋል። በተለይ በትምህርት ዕድሜ ላይ ያሉ ህፃናት ትምህርት የመቅሰም ችሎታቸውን ይቀንሰዋል። ስለዚህ ተገቢ የሆነ መደበኛ ምርመራ ህፃናት ማግኘት ይኖርባቸዋል።
የአይረን እጥረት ያለባቸው ከምግብ ጋር ወይም በእንክብል መልክ ንጥረ ነገሩን እንዲያገኙ በማድረግ ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የአይረን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች ማለትም ቀይ ስጋ፣ አሳ፣ ባቄላ፣ ጥቁር ጎመንና አተር የመሳሰሉት አዘውትሮ መመገብ የደም ማነስን ለማከም ይጠቅማል።
በዚህ መስተካከል ያልቻለን የደም ማነስ ችግር ግን እንደሁኔታው ሀኪሞች የአይረን እንክብሎችን በማዘዝ እንዲስተካከል ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም እንደ ብርቱካን፣ እንጆሪ፣ ቃሪያና ቲማቲም ያሉ ከፍተኛ ቫይታሚን ሲ ያለባቸው ምግቦች መመገብ በራሱ ከምግብ የምናገኘውን አይረን ወደ ሰውነታችን ተብላልቶ እንዲገባ ያግዛል።
እንደኛ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ የአንጀት ውስጥ ጥገኛ ተዋሲያን ሌላው የደም ማነስ ምክንያቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ በተለይም ህፃናት ላይ ለዚህ የሚሆን ተገቢ ምርመራና ህክምና ማግኘት አለባቸው። እርጉዝና የሚያጠቡ እናቶች ደግሞ ለደም ማነስ በጣም ከፍተኛ ተጋላጭ ስለሆኑ እነሱም ተገቢውን ክትትልና ህክምና ማግኘት አለባቸው፡፡ በእርግዝና ወቅት የአይረን እጥረትና የፎሊክ አሲድ እጥረት ለደም ማነስ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ዋንኞቹ ሆነው በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ውስጥ የተካተቱ በመሆኑ እጥረቱ እዳይከሰት ነፍሰ ጡር እናቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል፡፡
ቫይታሚን ቢ 12 ከአስራ ሦስቱ አስፈላጊ ቪታሚኖች አንዱ ነው እና “የተመረቱ” ቀይ የደም ሴሎችን በማምረት ውስጥ የተካተቱትን ሁሉንም የፊዚዮሎጂ ሂደቶች የሚያነቃቃ ስለሆነ ከአመጋገብ ጎን ለጎን በጣም አስፈላጊ ነው። አጥንት በቂ የቫይታሚን ቢ 12 ደረጃዎች ከሌሉ ሰውነት አስፈላጊውን የኦክስጂን ትራንስፖርት ለማረጋገጥ በቂ ቀይ የደም ሴሎችን ማምረት አይችልምና።
ሕክምና
ሰዎች የደም ማነስ በተለይም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የደም ማነስ ከታየባቸው ሐኪሞች በተቻለ ፍጥነት ሕክምናውን ይጀምራሉ ፣ በመሆኑም ሰዎች ከላይ የገለጽናቸው ምልክቶቸን እንዳዩ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም መምጣት ቢችሉ ውጤታማ ይሆናሉ ነገር ግን የሕመም ምልክቶች ከታዩ በኋላ ብዙ ወራት ከወሰደ፣ የሚያስከትለው የነርቭ ጉዳቱ ዘላቂና የማይቀለበስ ሊሆን ይችላል።
በሌላ በኩልም ከተለመደው ወይም ቀላል ከሆነው የደም ማነስ ችግር ከፍ ብሎ አደገኛ የሚባለው ደረጃ ላይ ከደረሰ ብዙውን ጊዜ በየወሩ የቫይታሚን ቢ 12 መርፌን መጠቀም ሊጠይቅ ይችላል። በዚህ መንገድ፣ በሽተኛው በቂ የደም ደረጃዎች ላይ በመድረስ፣ ቀይ የደም ሴሎችን ማምረት እንዲነቃቃ እና ሰውዬው መደበኛ ደረጃዎች እንዲኖሩት በማድረግ የሰውነት ትክክለኛ ኦክስጅኔሽን እንዲኖር ያስችላል። ለከባድ የደም ማነስ በወር ከአንድ በላይ መርፌ ሊያስፈልግ ይችላል፣ ግን ይህ በጣም የተለመደ አይደለም።
በእርግዝና ወቅት አይረን እና ፎሊክ አሲድ የያዙ እንክብሎች በመደበኛነት እንዲሰጡ ይደረጋል። በእርግዝና ወቅት ተገቢውን ክትትል ማድረግ እና መድሃኒቶችን ሰዓት ጠብቆ መውሰድ የእናትንም የልጅንም ጤና ይጠብቃል።
የደም ማነስ በሌሎችም ተጓዳኝ ህመሞች ምክንያት የሚከሰት መሆኑም ሊታወቅ ይገባል፤ ለምሳሌ የኩላሊት ህመም የተለያዩ የካንሰር ህመሞች የደም ማነስ ችግርን ሊያመጡብን ስለሚችሉ ሃኪም ጋ በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል።
የደም ማነስ በድንገት በደረሰ አደጋ ወይም በልጅ መውለድ ወቅት በሚፈስ ከፍተኛ የደም መጠን ከተከሰተ ለሕይወት አስጊ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ወቅት ደምን የመተካት ሕክምና ይደረጋል። ብዙዎች በተለይ እናቶች የደም መተካት ሕክምና ባለማግኘት ለሞት ይዳረጋሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም