የቦረና አርብቶ አደር ለእለት ጉሩሱና ልብሱ፣ ለሰርግ ጥሎሹ የሚያውለው፤ የሁሉ ነገሩ መገለጫውና መመኪያው የሆነውን ከብቱ አይኑ እያየ እየሞተበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ሀብት ስሟ ተጠቃሽ እንዲሆን አስተዋጽኦ ካበረከቱት አካባቢዎች አንዱም ይኸው የቦረና አካባቢ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ቦረናና አካባቢው በወሳኝ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ካጣ ሶስት አመታት አለፈ፡፡ ድርቁ ተባብሶ የአካባቢውን ማህበረሰብ ከብቱን ሸጦና ለውጦ ኑሮውን የሚመራውን የቦረና ህዝብ ለእርዳታ ጠባቂነት ዳርጎታል፡፡በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ከ807ሺ ያላነሰ ህዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገውና ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 167ሺ የሚሆኑት አስቸኳይና ተከታታይ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው በድርቁ የተነሳ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ከብቶች ማለቃቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ በአሁኑ ወቅት የሰው ሕይወት የማትረፍ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ መንግሥት፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ማህበራት፣ አርቲስቶች፣ ተቋማትና በተለያየ ሙያ ውስጥ የሚገኙ ለቦረና ማህበረሰብ ለመድረስ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ ርብርቡ ጥሩ ነው፤ ከዚህም በላቀ መልኩ መፈጸም ይኖርበታል፤ ይህ ግን ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፡፡ አርብቶ አደሩ ለእንስሳቱ መኖ፣ ከፊል አርብቶ አደሩም የእርሻ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለው ዘላቂ መፍትሄ ያስፈልጋል፡፡
አሁን የበልግ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ዝናብ ከሚጠበቅባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ቦረና አንዱ ነው፡፡ ጠብ የምትለውን ዝናብ ይዞ ለሚፈለገው ልማት በማዋል እንስሳቱንና ሰውን ለመታደግ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቃል፡፡
በበልግና ቀጣይ የክረምት ወቅቶች ላይ የሚጠበቀውን ዝናብ በመያዝ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመታደግ እየተከናወነ ስላለው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እንዲሁም ስለወቅታዊው የዝናብ ሁኔታ መረጃ የኦሮሚያ ክልል የመስኖና ቆላማ አርብቶ አደሮች ቢሮ ኃላፊ ኢኒጅነር ግርማ ረጋሣ እንደሚናገሩት፤ ቢሮው በዋናነት የውሃ አቅርቦት ላይ ይሰራል፡፡ እንደ አንድ መፍትሄ የተያዘውም በመደበኛነት የሚጥለውን ዝናብ ጨምሮ በጎርፍና በተለያየ መንገድ አልፎ የሚሄደውን ውሃ መያዝ ነው። ለዚህም የግድብ ሥራ በፕሮጀክቶች ተቀርጸው እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዝናብ እጥረቱ ምክንያት የደረቁ አነስተኛ ወንዞችም ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ተጨማሪ ሥራ ተሰርቷል፡፡
በዚህ መልኩ በተለይም ዝናብ አጠር በሆኑ እንደ ቦረና ባሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎች በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረዋል፡፡ በዚህ መንገድ የተጠራቀመው ውሃ አርብቶ አደሩ ለከብቶቹ የሚውል መኖ እንዲያለማ፣ ከፊል አርብቶ አደሩም የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውንና ለመጠጥ አገልግሎትም እንዲጠቀም ያስችላል፡፡
እንደ ኢንጂነር ግርማ ማብራሪያ፤ የፕሮጀክት ሥራው ከአምና ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን፣እስካሁን በተሰራው ሥራም ውሃ መያዝ የሚችሉ 12 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በአጣዳፊ ሁኔታ ሥራ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ደግሞ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እስካሁን የተከናወኑት ሥራዎች ለእንስሳት መኖ እና ለግብርና ሥራ እንዲሁም ለመጠጥ የሚውል ውሃ ለማግኘት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስችለዋል፡፡
በተለያየ አቅጣጫ የሚገኘውን ውሃ ለመያዝ እንዲያስችሉ ተብለው የተሰሩት ግድቦች 16 ሜትር ከፍታና ሰፋ ያለ ርዝመት ያላቸውና በሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ የሚገመት ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ናቸው። እነዚህ የቅድመ ዝግጅት የግድብ ፕሮጀክት ሥራዎች ቦረና ላይ ትኩረት ያደረጉ ቢሆኑም፣ ስራው በተለይ በቆላማውና አርብቶ አደር የሚበዛባቸውን አካባቢዎች (ምሥራቅና ምእራብ ባሌ፣ ሐረርጌ) አካቶ ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡
የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራን በተመለከተ ኢንጅነር ግርማ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የጉድጓድ ውሃ ስራው ችግሩ የከፋባቸው በአካባቢያቸው በጉድጓድ ውሃ እንዲጠቀሙ የተከናወነ መጠነኛ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ስራውን በሁሉም አካባቢዎች በስፋት ለማከናወን ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በዘላቂነት የአካባቢውን የውሃ ችግር በመፍታት መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ግን በፌዴራል መንግሥት የሚመራውና ‹‹ቦረና ኔት ወርክ›› በሚል በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እየተከናወነ የሚገኘው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ግዙፍ እንደሆነና ሥራውም ከተጀመረ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
የግድብ ሥራ ቅድመ ዝግጅቱ በበልግና በመደበኛ የሚጠበቀውን የዝናብ ውሃ ለመያዝ በመሆኑ የአየር ትንበያ መረጃን መከታተልና መረጃው ከሚሰጠው አካል ጋር የተናበበ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ እየተደረገ ስላለው ጥረትም ኢንጅነር ግርማ እንደሚገልጹት፤ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ያለው የእለት ተእለት ግንኙነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ‹‹ኢመርጀንሲ ሪስፖንስ›› በሚል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳታዎች (መረጃዎች) ተሰብስበው ለፌዴራል መንግስት ጭምር የሚላክበት አሰራር በቢሮው በኩል ተዘርግቷል ብለዋል፡፡ ባለው ተሞክሮ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ቦረና ላይ ዝናብ ይጥላል፤አሁንም እንደሚጥል ትንበያዎች ያሳያሉ፤እየተጠበቀ ነው ይላሉ፡፡
ያለፈውን ክስተትና ወደፊት የሚጠበቀውን የዝናብ ሁኔታ በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚቲዮሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አሳምነው ተሾመ እንዳብራሩት፤ ከነበረው የደመና ሽፋንና ክምችት በመነሳት አብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መጠነኛ ዝናብ አግኝተዋል፡፡ በጥቂት የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል፡፡ ለአብነትም ያለፈው ቅዳሜ ሳምንት በድሬዳዋ 33፣ በሊሙ ገነት 32፣ በጅንካ 30 በጅማ 27 ሚሊ ሊትር የዝናብ መጠን በ24 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተመዝግቧል፡፡ በተለይም በምሥራቅ አማራ፣ በመካከለኛውና የምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል፡፡
ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነው የሀገሪቱ አካባቢዎች በምሥራቅ አማራ፣ በመካከለኛውና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለፉት ቀናት በተለያየ መጠን የጣለው ዝናብ የበልግ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ነው የጠቆሙት፡፡ በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍል ከመጋቢት አጋማሽ በኋላ ጥሩ የሆነ የተጠናከረ የደመና ሽፋንና በተለያየ መጠን ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩም ነው የጠቆሙት፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚሰጠውን መረጃ መሠረት በማድረግ የሚኖረውን የአየር እርጥበትና ዝናብ ወደ ጥሩ አጋጣሚ በመቀየር በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በደቡብ ኦሮሚያ በቦረናና በሌሎችም አካባቢዎች በልግ ዋና የዝናብ ወቅታቸው በጋ ደግሞ ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር አሳምነው፤ በአካባቢዎቹ ላይ የተከሰተው ድርቅ በ2013 እና በ2014 የበጋና የበልግ እንዲሁም በ2015 የበጋ ወቅቶች የነበረው ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ ስርጭት ያመጣው ተጽእኖ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከ2013 የበጋ ወቅት ጀምሮ በአካባቢዎቹ ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር በወቅቱ የትንበያ መረጃ በኢንስቲትዩቱ እንዲደርስ መደረጉንም ዶክተር አሳምነው አስታውሰዋል፡፡ ችግሩን የሚያስከትለው ወቅያኖስ ላይ ያለ የአየር ክስተት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የባህር ወለል መቀዝቀዝና መሞቅ በኢትዮጵያ በበጋ፣ በበልግና በክረምት አሉታዊና አዎንታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደቻለም ጠቁመዋል፡፡ በየጊዜው የሚተነተነው መረጃ የሚያሳየው በአጠቃላይ ከአየር መዋዠቅ ጋር በተያያዘ በበልግ የሚጠበቅ ዝናብ እየተዳከመና እየቀነሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ዶክተር አሳምነው ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የዝናብ ወቅቶች ክረምት፣ በልግና በጋ ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው አራት ወራት ጊዜያቶች አሏቸው፡፡ በተለይ አመታዊ የዝናብ መጠኑ እስከ 85 በመቶ የሚደርሰው ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው የክረምት ወቅት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የክረምት ዝናብ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ የደቡብ አጋማሽ አካባቢዎች ደግሞ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎችም በደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ አካባቢ የሚገኙት ጉጂና ቦረና፤ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኙት ጋሞ ዞን፣ ኮንሶ፣ ጅንካ አካባቢዎች እንዲሁም ሶማሌ ክልል ይጠቀሳሉ፡፡
ሁለተኛው የበጋ ወቅት ከጥቅምት እስከ ጥር ያሉት ወራቶች ናቸው፣ በነዚህ ወቅቶችም አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ደረቅና ነፋሻ የአየር ሁኔታ የሚስተዋልበት ነው፡፡ የመኸር ሰብልን ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ወቅት ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በደቡብ አጋማሽ ለሚገኙ የሀገሪቱ ክፍሎች ለደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ፣ ቦረና ቆላማ አካባቢዎች፣ ለሲዳማ እና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል፣ ለሶማሌ ክልሎች እንደ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ሲሆን፤ እነዚህ አካባቢዎች ከአመታዊ የዝናብ መጠን እስከ 30 በመቶ ዝናብ የሚደርሳቸው በነዚህ ወቅቶች ነው፡፡
ሶስተኛው የበልግ ወቅት ከየካቲት እስከ ግንቦት ጊዜ ያሉትን ወራት ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ ወራት ለደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ፣ ቦረና ቆላማ አካባቢዎች፣ ለሲዳማ እና ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ለሶማሌ ክልሎች ዋና የዝናብ ወቅቶቻቸው ናቸው፡፡ ከአመታዊ የዝናብ መጠንም እስከ 55 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ያገኛሉ፡፡ ምሥራቅ አማራ፣ ሐረርና ድሬዳዋን ጨምሮ ለመካከለኛ የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩትም እነዚህን ወቅቶች መሠረት ያደረገ ሥራ እንዲሰራ ቀድሞ መረጃ ይሰጣል፡፡ የግንዛቤ ሥራም ይሰራል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በ2015 በጀት አመት ስለሚጠበቀው የአየር አዝማሚያ የትንበያ ሁኔታ ጥር 2015 ዓ.ም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ መድረክ አካሂዷል፡፡
እንደ ዶክተር አሳምነው ማብራሪያ፤ ኢንስቲትዩቱ ወቅታዊውን በተለይም የበልግ ወቅትን ትንበያ በሚያዘጋጅበት ጊዜ የምሥራቅና መካከለኛው የፓስፊክ ውቅያኖስ ከመደበኛ በታች መቀዝቀዝ ወይንም ደግሞ ላሊና በሚባለው የአየር ሁኔታ ክስተት ውስጥ ነበር፡፡ በሂደት ግን ከመጋቢት ወር አጋማሽ በኋላ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የአየር ጠባይ ሊኖር እንደሚችል በትንበያው ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሁለተኛው ምዕራባዊ የህንድ ውቅያኖስ ክፍል ደግሞ ከመደበኛ በታች የሆነ መቀዝቀዝ መታየቱና በሂደት ለውጥ እንደሚመጣ ተለይቷል፡፡
እነዚህንና ሌሎችንም የአየር ሁኔታ ገጽታዎች ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የወቅቱ ትንበያ በኢንስቲትዩቱ በኩል ይፋ ተደርጓል፡፡ በትንበያው መሠረት የአየር ሁኔታ ክስተቶቹ ወደ መደበኛ እስኪመለሱ ድረስ በወቅቱ የዝናብ አጀማመር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው ወይንም መጠነኛ የሆነ መዘግየት ሊፈጠር እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ መረጃ ሰጥቷል፡፡
የትንበያ መረጃውን መሠረት ያደረገው በደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደሆነና በአንጻሩ ግን አካባቢዎቹ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ሚያዚያና ግንቦት ወራት ላይ ጥሩ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት ሊያገኙ እንደሚችሉ ትንበያው ያመለክታል ያሉት ዶክተር አሳምነው፣ በተለይም በልግ ዋነኛ ወቅታቸው የሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ማለትም በደቡብ ኢትዮጵያ አጋማሽ ሶማሌ፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ ሲዳማ፣ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል 15 በመቶ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
50 በመቶ የሚሆነውን የዝናብ መጠን የሚያገኙት የደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ እንዲሁም 35 በመቶ ደግሞ ከመደበኛ በታች የሆነ የዝናብ መጠን ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበያው መለየቱን አስረድተዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የሀገሪቱ ሰሜን አጋማሽ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ እንዲሁም የምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎችም ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም