ተስፋ የተጣለበት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች አውደ ርዕይ

የዓለም ምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚ ያመለክተው፤ የእንስሳትሀ ባደጉት ሀገራት 40 በመቶ የሚጠጋውን፣ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት 20 በመቶውን የግብርና ምርት ይሸፍናል። በዚህም 13 ቢሊዮን የማያንሱ የዓለም ሕዝቦችን ኑሮ ይደግፋል።

የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓት ምሰሶዎች መሆናቸው ይገለጻል። መረጃዎች እንዳሰፈሩት፤ በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ማደግ፣ በተጠቃሚዎች የመግዛት አቅም መጨመር እና በከተሞች መስፋፋት ምክንያት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ይገኛል። ይህን ፍላጎት ተከትሎ አምራቾችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በእንስሳት እርባታ ሥርዓትና የእሴት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ልማት በአህጉሪቱ እድገት ላይ ጉልህ እና ዘላቂ ተጽዕኖ እንዲኖረው ለማስቻል ልማቱን በጠንካራ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ወሳኝ ነው።

ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም በዘርፉ ያላት ምርታማነትና የነፍስ ወከፍ ፍጆታ ከዓለም ዝቅትኛ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሀገሪቱ የእንስሳት ተዋፅኦ ምርት ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም፣ የሀገር ውስጥ ምርት አቅርቦት ግን በሚፈለገው መጠንና ጥራት የምርት ፍላጎቱን ማዳረስ አልቻለም።

ይህን የተረዳው መንግሥት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በሌማት ትሩፋት ዕቅዱ የአራት ዓመት መርሃ-ግብር ነድፎ እየሠራ ይገኛል። በዚህ እቅድም የወተት፣ ዕንቁላልና የዶሮ ስጋ እንዲሁም የማር ምርት ለማሳደግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በዕቅዱም የላም ወተት ምርትን አሁን ካለበት ስድስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሊትር ወደ ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ሊትር ለማሳደግ፤ የዕንቁላል ምርትን ከሶስት ነጥብ ሁለት ሁለት ቢሊዮን ወደ 91 ቢሊዮን ከፍ ለማድረግ፤ የዶሮ ስጋ ምርትን ከ 90 ሜትሪክ ቶን ወደ 296 ሺ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም የማር ምርትን ከ 147 ሺ ወደ 296 ሺ ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ዘርፉን ለማሳደግና እንደሀገር ያለውን የግብርና ኢንቨስትመንት መጠን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ይህን የልማት ሥራ ለማስተዋወቅና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በመንግሥትና በአጋር አካላት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ይጠቀሳሉ።

ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ዓለም አቀፍ የእንስሳት ዘርፍ አውደ ርዕይና ጉባዔ ማካሄድ ይጠቀሳል። አውደ ርዕዩ በተለይም በእንስሳት ሀብት ልማት የተሠማሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በመሳብና የቴክኖሎጂ ብሎም የእውቀት ሽግግር እንዲመጣ አይነተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ዓውደርዕዮች እና ጉባዔዎች ለዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ እና ስጋ፣ ንዑስ ዘርፎች ዕድገትና ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይገለጻል። እነዚህ ኹነቶች የዘርፉ ባለሙያዎችና የንግዱ ማህበረሰብ ዋና ዋና ማሰባሰቢያዎች በመሆናቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ አዳዲስ ቴከኖሎጂዎችንና የኢንቨስትመንት እድሎችን በማስተዋወቅ፣ የእውቀት ሽግግርን በማምጣት ወዘተ. ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማረጋገጥ መቻላቸውን አውደርዕዩን ያዘጋጀው የፕሬና ኢቨንትስ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ይናገራሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ዘንድሮ የሚካሄደውና ከመጪው ጥቅምት 21 እስከ 23 ቀን 2017 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚከናወነው ይኸው ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ ከ14 ሀገራት የተውጣጡ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ዘርፍ ተዋናዮችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም የንግድ ጎብኚዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። አውደርዕዩ 13ኛው የኢትዮ ፖልተሪ ኤክስፖ (ኢትዮፔከስ)፤ ዘጠነኛው የአፍሪካ እንሰሳት ዓውደርዕይና ጉባዔ (አሌከ) እንዲሁም አራተኛው የአፒካልቸር እና አኳካልቸር ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒትና ዘንድሮ የሚጀመረው የባዮ-ኢነርጂ የንግድ ትርዒት እና ጥራት ያላቸው የዘርፉ ዋነኛ አንቀሳቃሾች ይሳተፉበታል።

ሁሉን አቀፍ የእንስሳት ሀብት እሴት ሰንሰለት በመፍጠር ረገድም ንግድ ትርዒቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል። በዚህ ረገድም የኢትዮ ዶሮ ኤከስፖ፣ በኢትዮጵያ ባህላዊ የዶሮ ርባታ በስፋት የሚዘወተር ልምድ በመሆኑ ዘመናዊ የዶሮ ርባታን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊውን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚዘጋጅ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ኹነት መሆኑንም አቶ ነብዩ ጠቁመዋል።

‹‹የኢትዮጵያ የዓሳ ኤክስፖ በዓለም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የሚገኘውን ይህንን ዘርፍ በሀገራችን የሚስፋፋበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ ኋላ ቀር የሆነውን የዓሳ ዘርፍ በመቀየር ለምግብ ዋስትና እንዱ አማራጭ እንዲሆን ዘርፉ የሚተዋወቅበት ዓውደርዕይ ነው›› ሲሉም ይጠቅሳሉ። በኢትዮጵያ የማር ኤክስፖ በተጓዳኝ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፤ ‹‹ሁኑቱ ሀገሪቱ በአፍሪካ ትልቁ የማር አምራች ሀገር እንደመሆኗ ከዚህ ሀብት ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ዘርፉን ለማዘመን ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታስቦ የተጀመረ ዓለም አቀፍ መድረክ ነው›› በማለት ያብራራሉ።

አቶ ነብዩ እንዳስታወቁት፤ በዓውደ ርዕይና ጉባዔው አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለቱን የሚወከሉ መሠረታቸውን በቻይና፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢትዮጵያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ኬንያ፣ ጆርዳን ኔዘርላንድሰ፣ ስኮትላንድ፣ ቶጎ፣ ቱርክ፣ ዩጋንዳ እና አሜሪካ ያደረጉ ዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎች እና ጠንካራ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ከንግድ ጎበኚዎች ጋር ጠንካራ የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር ዝግጅት አድርገዋል። በኹነቱ ከሶስት ሺ በላይ የኢትዮጵያ፣ የምስራቅ አፍሪካና ዓለም አቀፍ ሀገራት ጎብኚዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኤክስፖ ቲም ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ኦሳማ ሙስጠፋ እንዳሉት፤ ኹነቱ በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ይገኛል፤ ዘንድሮም ከተሳታፊዎች ጥራትና ከብዝሃነት አንጻር ትልቅ ውጤት እንደሚመዘገብበት ይጠበቃል። ከዓለም አቀፍ የዘርፉ መሪዎች በተጨማሪ በሀገሪቱ ያሉ ትላልቅ የአንድ ቀን ጫጩት አቅራቢዎች፣ መኖ አምራቾች ያደርጋሉ፤ ይህም ዘርፉን አንድ ርምጃ ወደፊት እንደሚያስመነድገው ይጠበቃል። በንግድ ልውውጥ መድረኩ አስፈላጊው የመንግሥት ድጋፍ ከታከለበት የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የወጪ ንግድን ሊያሳድግ እንደሚችል ይገመታል፡፡

የዘንድሮው ጉባዔ “የእንስሳት ርባታ አሁን እና ወደፊት አሁናዊ ዕድሎች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት ተስፋ’’ በሚል መሪ ቃል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የግሉ ዘርፍ መሪዎችና ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ እንደሚካሄድም ያመለክታሉ።

ጉባዔው በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ጠቅሰው፣ በዶሮ ርባታና በእንቁላል ምርት ላይ የገጠሙ ተግዳሮቶች የወተትና የወተት ተዋፅኦ ገበያ ትስስርና የተሻሻሉ የፈጠራ ሥራዎች፤ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የመድሃኒት አቅርቦትና የመኖ ቀመሮች ማሻሻያና የአንስሳት ጤና ላይ ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል። በዘርፉ ተዋንያን በሳል ውይይት የሚደረግበት ይህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለሕግ አውጪዎች ግብዓት ሊሆን የሚችሉ ጉዳዮች የሚነሱበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የፖሊሲ አርታቂዎች በንቃት ይሳተፉበታል ብለዋል፡፡

የኔዘርላንድ ኤምባሲ የግብርና አማካሪ ሚስተር ሚዩዌስ ብሩወር በበኩላቸው፤ በዓውደ ርዕዩ ከዶሮ ርባታ ጋር የተያያዙ እንደ መኖ፣ ማምረቻ መሣሪያ፣ ክትባቶችና የማርቢያ ቴክኖሎጂ ያሉ ምርቶችንና አገልግሎቶች እንደሚቀርቡበት ጠቁመዋል። የባለድርሻ አካላትን ትስስር ለማጠናከር፣ የንግድ እድሎችን ለማሰስ፣ ከኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ደንበኞች እና አቅራቢዎች ጋር የሚገናኙበት እድል እንደሚፈጠርም አመልክተዋል። ባለሙያዎች ስለ የዶሮ ርባታ ኢንዱስትሪው የተለያዩ ገፅታዎች፣ የምርት ቴክኒኮችን ፣ በሽታን መከላከል እና የገበያ አዝማሚያዎችን ጨምሮ ግንዛቤዎችን እና እውቀትን የሚጋሩበት መድረክ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፅጌሬዳ ፍቃዱ እንደተናገሩት፤ የእንስሳት ሀብት ልማት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ሀብቱን ወደ ሥራ በመቀየር ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። ለዚህም እንዱ ማሳያ በቅርቡ ይፋ የሆነው የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ እንዲሻሻል መደረጉ ተጠቃሽ ነው። ፖሊሲው ከእስከ አሁኑ በላቀ የግል ባለሀብቱን ሊያሳትፍ በሚችልና ሁሉንም አሠራሮች ባቀፈ መልኩ ተሻሽሎ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

ሌሎችም የአሠራር ማነቆዎችም በመመሪያ እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ ፅጌሬዳ ጠቅሰው፤ በተለይ በቅርቡ የፀደቀው ኮንትራት ፋርሚንግ ባለሀብቱና አርሶአደሩ ሌሎች ወጣቶች ተቀናጅተው እንዲሠሩና የዘርፉን አሠራር ለማሻሻል እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ተጠቃሚነትን ለማሳደግም ለአራት ዓመታት የሚተገበር የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር አቅድ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ዘርፉን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ይናገራሉ። ‹‹ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት ብዙ ሠርተናል፤ በርካታ ንቅናቄዎች በሁሉም ክልሎች ተካሂደዋል። ይህም ከፍተኛ የምርት እድገት አምጥቷል›› ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ የመርሃ-ግብሩ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው። ከዚህ አኳያ በእንስሳት ሀብት ልማት ብዙ ሥራዎች ተከናውነዋል። በመርሃግብሩ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የምርት እድገት መጥቷል። ይህም የሚበረታታና በቀጣይ በትኩረት ሊሠራበት የሚያስችል፤ ብዙ ማህበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በቀጣዮቹ ዓመታትም ሰፋፊ ሥራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። እቅዱን ለማሳካት በተለይም ከዶሮ ጋር ተያይዞ የመሥራች ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ‹‹ከዚህ በፊት የዶሮ ቅድመ ወላጅ ከውጭ ነበር የሚመጣው፤ አሁን በሀገራችን ቅድመ ወላጅ ማዕከል ተቋቁሟል፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ የማሠራጨት ሥራ ይጀመራል›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህም ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚመጣውን ቅድመ ወላጅ ዶሮ በሀገር ውስጥ ለመተካት እንደሚያስችል እንዲሁም ለአርቢዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የዶሮና የዓሳ ጫጩት ማባዣ ማዕከላትን በመገንባት በስፋት ግብዓት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም ወይዘሮ ፅጌሬዳ ይጠቅሳሉ። ‹‹በንብ ማነብ ሥራም ዘመናዊ ቀፎ በስፋት እያሰራጨን ነው። ከወተት ሀብት ልማት ጋር ተያይዞ ደግሞ በተለይ ዝርያ ማሻሻል ላይ በስፋት እየሠራን ነው›› ይላሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ ጎን ለጎን በመኖ ልማት በእንስሳት ጤና አገልግሎት እንዲሁም ኤክስቴንሽኑን ለማጎልበት ጥረት ተደርጓል። ቀደም ሲል የእንስሳት ኤክስቴንሽኑ ከግብርና ጋር አብሮ የሚሰጥበት ሁኔታ ነበር፤ አሁን ራሱን ችሎ የእንስሳት ሀብት ልማት ኤክስቴንሽን አገልግሎት ተቋቁሟል፤ በዚህም የአርሶአደሩንና አርብቶአደሩን አቅም ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በመንግሥት በኩል ዘርፉን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ እንዲህ አይነትአውደ ርዕዩች ወሳኝ ሚና አላቸው። ዓለምአቀፉ የእንስሳት ዘርፍ አውደርዕይ እና ጉባዔ ለረጅም ዓመታት እየተካሄደ እንደመሆኑ ለእንስሳት ሀብት ልማቱ መጎልበትም ሆነ ዘርፉን እንደሀገር ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።

ከሌላ አካባቢ የተሻለ እውቀት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ በማድረግና ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የሚመሰገን ነው። በዘርፉ ዓለምአቀፍ ኢንቨስተሮችን ትኩረት ለመሳብ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የዘርፉ ተዋናዮች የተፈጠረውን እድል በመጠቀም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

የግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ሪጉላርቶሪ ዘርፍን ወክለው የተገኙት ዶክተር ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባለሥልጣኑ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ ወዲህ በተለይም የኢትዮጵያን የእንስሳትና እፅዋት ምርቶች ጥራትና ደህንነት በመቆጣጠር በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ለማድረግ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው።

ከዚህ ቀደም በእንስሳትና በእፅዋት ግብዓትና ውጤቶች በተለያየ ሁኔታ ቁጥጥር ሲደረግ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የሀገሪቱ ምርቶች ጥራታቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ነው። በተለይም ጥራቱ፣ ደህንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድሃኒትና ክትባት ለዘርፉ ተደራሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎችም ውጤት እየተገኘ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አውደ ርዕዩ ዘርፉን ለማሳደግ እያበረከተ ካለው አስተዋፅኦ ባሻገር ባለሥልጣኑ በመድረኩ በመሳተፍ የሚሠራቸውን ሥራዎች ለተጠቃሚዎች ለማስተዋወቅ እድል እንደሚፈጥረለትም አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በተለይም የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር መጀመርን ተከትሎ እየጎለበተ የመጣውን የእንስሳት ሀብት ልማት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You