ለግብርና ዘርፍ እድገት እምርታ ዘላቂነት

ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ የሚያስችላትን የአስር ዓመት እቅድ ነድፋ እየተገበረች ትገኛለች፡፡ በተለይ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ተብለው በተለዩት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በቱረዝምና በማእድን ዘርፎች ላይ ሰፋፊ እቅዶች ወጥተው እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ በእቅዶቹ በየአመቱ ውጤቶች እየታዩ ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ ደግሞ የላቁ ውጤቶች እየተመዘገቡም ናቸው፡፡

በተለይ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥና ከተረጂነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ለምታደርገው ጥረት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ምርታማነት የሚያጎለብቱ በርካታ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻለች ሲሆን፣ ክፍለ ኢኮኖሚው ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት የመሪነት ሚና መጫወት እንዳስቻለው ነው የሚገለፀው፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ባለፈው ዓመት ዓመታዊ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ከታቀደው በላይ 8 ነጥብ 1 በመቶ ተመዝግቦበታል። ለዚህም እድገት መመዝገብ የግብርናው ዘርፍ የመሪነት ሚና የተጫወተ ሲሆን፤ ዘርፉ በበጀት ዓመቱ 6ነጥብ1 በመቶ እድገት ተመዝግቦበታል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ዘርፉን ወደ ተሻለ ምርታማነት ለማሸጋገርና ግብርናውን ለማዘመን ሲባል በሁሉም መስኮች ሰፋፊ ስራዎች በመከናወናቸው ነው፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የግብርና ዘርፉን የሩብ ዓመት አፈፃፀም አስመልክተው ባለፈው አርብ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩትም፤ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል፡፡ በዚህም አበረታች የሚባሉ ውጤቶች ከመገኘታቸውም ባሻገር ዘርፉ ለአጠቃላይ ሀገራዊ እድገቱ ዘርፉ ወሳኝ ሚና እንዲጫወት አስችሎታል፡፡

ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት የተገኙትን ውጤቶችን መሰረት በማድረግ በ2016/17 የምርት ዘመን የተሻለ ክንውን እንዲመዘገብና ግብርናው ለሀገር እድገት ያለውን አበርክቶ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመትም በሰብልና ሆርቲካልቸር፣ በቡና ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ በሌማት ቱሩፋት፣ በግብአት አቅርቦት እንዲሁም በግብርና ወጭ ንግድ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውንም ዶክተር ግርማ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በዘርፉ የመጡ ውጤቶች ለቀጣይ ሥራ ትልቅ ስንቅ ይሆናሉ፤ የበለጠ ለመስራት መሰረት የሚጥሉ ናቸው፡፡ የበልግ፣ የመኸርና መስኖ ወቅቶችን መሰረት በማድረግም የሰብልና ሆርቱካልቸር ምርትና ምርታማትን የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ሲሆን፣ በምርት ዘመኑ መኸር እርሻ በእቅድ ከተያዘው 20 ሚሊዮን 560 ሺ ሄክታር መሬት በማልማት 608 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

እስከአሁን 20 ነጥብ 4ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን የተቻለ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ በክላስተር የለማ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በአሁኑ ወቅት በአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለ የደረሰ ሰብል ተሰብስቦ ከ5ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በላይ መገኘቱንም አስገንዝበዋል። በተጨማሪም ሰሊጥ፣ ለውዝ ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎችም ቀድሞ ከነበራቸው የምርት ሁኔታ በእጅጉ እንደሚጨምርም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ባለፉት ሦስት ወራት ከኤክስፖርት ምርቶች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅደን፤ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር አግኝተናል፤ ይህም ትልቅ ስኬት ነው›› በማለት በዘርፉ የተገኘውን ውጤታማነት አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የግብርናው ዘርፍ በዚህ ዓመትም 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ የታቀደ ቢሆንም፣ ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ አኳያ ከእቅዱ በላይ መፈፀም እንደሚቻል ነበራዊ ሁኔታዎች ያመላክታሉ፡፡ በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ 30 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝም ይጠበቃል፡፡ ባለፈው ዓመት ከቡና ምርት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡንም ጠቅሰው፣ በተያዘው ዓመት ከቡና ምርት 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታስቧል ይላሉ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም በ2017 ምርት ዘመን የመስኖ ስንዴ በሁሉም ክልሎች 4ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ ‹‹እስከ ጥቅምት ወር አጋማሽ ድረስም በባህላዊና በትራክተር በድምሩ 850ሺ 094 ሄክታር መሬት ታርሶ 505ሺ113 ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል›› ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ክረምት እና በጋ በስንዴ ከተሸፈነው 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 300 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀው፣ ‹‹በአጠቃላይ በእርሻና ሆልቲካልቸር በ2016/17 ምርት ዘመን 30ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ኩንታል ለማምረት በዕቅድ ተይዟል›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በዚህም ምርታማነትን በማጎልበት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ርብርብ እንደሚደረግ ያስገነዝባሉ፡፡

ሚኒስትሩ የግብዓት አቅርቦትን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ በምርት ዘመኑ አንድ ነጥብ 65 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ተሰራጭቷል፤ ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 512ሺ 216 ነጥብ 9 ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት ተችሏል፡፡

ለቀጣዩ የምርት ዘመን ለመስኖ፣ ለበልግ እና ለመኸር የሚውል 2 ሚሊዮን 404ሺ 729 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት መታቀዱንም አያይዘው ጠቅሰው፣ ለዚህም በአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ተፈቅዷል ብለዋል። በቀጣዩ የምርት ዘመን ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡

ዶክተር ግርማ እንዳስታወቁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በሌማት ትሩፋት ምርቶች የ5 ነጥብ 4 በመቶ እድገት የሚመዘገብ ሲሆን፣ ለአብነትም በወተት ብቻ በዓመቱ 12 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት ይጠበቃል፡፡ በዓመቱ 8 ቢሊዮን የዶሮ እንቁላል እንዲሁም 218 ሺ ቶን ስጋ እና 297 ሺህ ቶን ማር ምርት ለማምረት የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል። የዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በዓሣ ግብርና አንድ ነጥብ34 ሚሊዮን የዓሣ ጫጩት ለመጨመር ታቅዶ እየተተገበረ ይገኛል። በጀት ዓመቱ 2ሚሊዮን 134ሺ 275 ዘመናዊ የንብ ቀፎ ለተጠቃሚዎች ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፣ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 259 ሺ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎች ተሰራጭተዋል፡፡

ከእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሥራ ጋር በተያያዘም ‹‹የፈሳሽ ናይትሮጂን ምርትን በተመለከተ በክልሎችና በኢንስቲትዩት ውስጥ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 170ሺ ሊትር ፈሳሽ ናይትሮጂን ለማምረት ታቅዶ 500 ሺ ሊትር በማምረት ከእቅድ በላይ ማሳካት ችለናል›› ሲሉ ገልጸዋል። በተመሳሳይ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 250 ሺ ጥጆች እንደሚወለዱ ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው፣ 227ሺ 501 ጥጆች መወለዳቸውንም አመልክተዋል። የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 776 ሺ ቶን ሥጋ ለማምረት ታቅዶ 888 ሺ ቶን የሥጋ ምርት መገኘቱን ይገልፃሉ።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በምርት ዘመኑ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀምን ለማሳደግ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በ2016/17 ምርት ዘመን 6ነጥብ5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 7ነጥብ 52 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 618 ሚሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል። በ2017 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

በአጠቃላይ በአረንጓዴ ዓሻራ፣ በደን ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በጥምር ግብርና በሁሉም መስክ ከፍተኛ የሆነ እምርታ መመዝገቡን ዶክተር ግርማ ጠቅሰው፣ ‹‹በአጠቃላይ ከግብርና የወጪ ምርቶች 628 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ 665ነጥብ97 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ተችሏል ብለዋል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 33 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ የምርት ዘመን በሁሉም ክልሎች ምርታማነትን በተሻለ መልኩ ለማሳደግ ርብርብ የሚደረግ መሆኑን፤ በተለይም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አሁን ከሚገኘው ምርት በላቀ ሁኔታ ለማግኘት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለሀገር እድገት እያደረገ ያለውን አበርክቶ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል ተብሎ መታመኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው፤ ግብርና ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ መነቃቃት እንዳመጣ ጠቅሰው፤ ‹‹በዚህ ዓመት 6ነጥብ1 በመቶ እድገት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፤ ይህም ሲባል አምና በነበረው መሠረት ቢሆን ይሄ ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል›› በማለት በዘርፉ የላቀ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል አመላክተዋል። ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ ሰብል፣ ጥጥ፣ ሆርቲካልቸር ተደምሮ ክረምት ከበጋ 30 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን እሳቸውም አስታውቀዋል፡፡

ይህም ትልቅ ዜናና የሚያኮራ ተግባር እንደሆነ አስታውቀው፣ ‹‹ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በታች ነበር የምናርሰው፤ አሁን ግን በመሬት ስፋት ብቻ ሳይሆን የበጋ ወቅትን በስፋት የመጠቀም በመስኖ የመጠቀም በኩታ ገጠም የመጠቀም ልምምዳችን በማደጉ በሰብል ምርት 6ነጥብ6 በመቶ እድገት ይጠበቃል›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በቡና ባለፈው ዓመት የአንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት እድገት ተገኝቷል፤ በካቻምናና በአምና መካከል የቡና ምርት እድገት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ዘንድሮ ከብራዚልና ከቬትናም በስተቀር በቡና ምርታማነት ኢትዮጵያን በዓለም የሚበልጣት ሀገር አይኖርም፡፡ በርካታ ሀገራትን በምርት መብለጥ የተቻለ ሲሆን፣ ብራዚልና ቬትናም ላይ ለመድረስም የሚሰራ ይሆናል። ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የተጀመረውን የቡና ተክል ጉንደላና ችግኝ ተከላ አጠናክሮ በመቀጠል ከብራዚል በስተቀር በቡና ምርት ኢትዮጵያን የሚበልጣት ሀገር እንዳይኖር ታቅዶ እየተሠራ ነው።

‹‹ከቬትናም ጋር ያለንን ልዩነት እናውቀዋለን በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት በምንሰራቸው ሥራዎች ከዚያ ያላነሰ ምርት ልናመርት እንደምንችል ይጠበቃል፤ ዘንድሮ ግን ከብራዚልና ከቬትናም ቀጥሎ ሶስተኛዋ ትልቅ ቡና አምራች ሀገር ኢትዮጵያ ናት›› ሲሉም አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ከቡና የወጪ ንግድ መገኘቱን ጠቅሰው፣ በዚህ ዓመት ከቡና የወጪ ንግድ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ይህ እድገት በቡና ብቻ ሳይሆን በሻይም ምልክት መታየት መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፤ ‹‹ሻይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በስፋት ተተክሏል፤ በጣም አስደናቂም ውጤት እያገኘንበት ነው። ሻይ ግን በባህሪው እንደ ቡና ለቅመን የምንሸጠው አይደለም። ሻይ ቅጠል ከተሰበሰበ በኋላ ፕሮሰስ መደረግ ይኖርበታል›› በማለት ያስረዳሉ።

አሁን ከተተከለው የሻይ ምርት ሶስት እጥፍ ለማግኘት የመሬት እና የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸው፤ አሁን የተተከለው ሲታሰብ በጣም በርካታ ፋብሪካዎች ማቋቋምና ፕሮሰስ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው፣ ይህን ማድረግ ካልተቻለ አርሶ አደሩ ገበያ ሊያጣ የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር ያመለክታሉ።

በመሆኑም ከግል ባለሀብቶች ጋር በመነጋገር እና በአንዳንድ ሀገራት ጉብኝት በማድረግና ልምድ የመቅሰም ስራ በመስራት በቅርቡ ከግሉ ሴክተር ጋር ቢያንስ 20 የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ለመትከል ከስምምነት ላይ መደረሱን ይጠቁማሉ። ‹‹ይሁንና በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተከልን ስለሆነ ሃያ ማቀነባበሪያም በቂ ስለማይሆን አሁንም በጣም በርካታ ፋብሪካዎች ያስፈልጋሉ›› ሲሉ ያስገነዝባሉ።

በግብርና ዘርፍ የመጡ ውጤቶች የተገኙ ድሎችን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ዶክተር ዐቢይ ተናግረው፤ ድካማ ጎኖችን በማረምና በማረቅ ልማቱን እያሰፉ መሄድ ከተቻለ እድገቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ከታቀደው የልማት ግብ አኳያ በርካታ የቤት ስራዎች ማከናወን ይጠበቃል፡፡ በተለይም በጥራትና በብዛት ማምረት፤ ለዚህ ደግሞ ዘርፉን የበለጠ ማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲመራ ማድረግ ይጠበቃል፤ የግብዓት አቅርቦቱን ለአርሶአደሩና ለአርብቶአደሩ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ማድረግና ክትትልና ድጋፉንም ማጠናከር ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለም ዘርፉ ትልቅ እምርታ የመጣበትና ወደፊትም የሚመጣበት ስለመሆኑ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችና የተገኙ ውጤቶች ያመለክታሉ፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You