ባህር አቋርጦ ከመጣው የጣሊያን ወራሪ ሰራዊት ጋር ኢትዮጵያዊያን ተፋልመው ድል ያደረጉበት የዓድዋ ጦርነት በዓለም ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጉልህ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው። የአድዋ ጦርነት ድል አህጉራትን አቋርጦ በዓለም ዙሪያ ጉልህ ተጽዕኖን አስከትሏል። ይህ ድል የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲተከል ከማድረጉ ባሻገር ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከልነት እርሾ የሆነ ነው፡፡ አዲስ አበባ ከኒዮርክ እና ጄኔቭ ቀጥሎ በዓለም ሦስተኛው የዲፕሎማሲ ሚሽኖች ማዕከል እንድትሆን የአድዋ ድል ሚናው የላቀ ነው፡፡
ከዓድዋ ድል ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ እንድትሆን አንዱ ምክንያት የዓድዋ ድል ነው፡፡ ነጮች ብቻም ሳይሆኑ ጥቁሮች ራሳቸው ጭምር ከነጮች እኩል ነን ብለው ለማሰብ በሚቸገሩበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን የተቀዳጁት የአድዋ ድል ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የሃያልነት ትርክት ከመሰረቱ ቀይሯል። ይህ ለብዙዎች ጥቁሮች የነጻነት ትግል እንዲጀምሩ ጥሩ መሰረት የሆነ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የነጻነት ቀንዲል ተደርጋ የምትታየው። ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የነጻነት ቀንድል መሆኗ ለአፍሪከ ህብረት ለመቀመጫነት እንድትመረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
በእርግጥ በፖለቲካዊ አንድነት ያለው የአፍሪካ ሀገራት ፌዴሬሽን በአስቸኳይ መፈጠር አለበት ሲል በነበረው የካዛብላንካ ቡድን እና ቀስ በቀስ በኢኮኖሚ ትብብር ላይ የተመሰረተ የላላ ትብብር ይኑር ሲል በነበረው የሞኖሮቪያ ቡድን መካከል የነበረውን የሀሳብ መከፋፈል በማስታረቅ ረገድ የኢትዮጵያ መሪዎች የተጫወቱት ሚና ኢትዮጵያ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፤ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንድትሆን ዋና ሚና ቢጨወትም ኢትዮጵያ የዓድዋ ድል የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር ዓለም አቀፍ ተቋማትም መቀመጫ ነች፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ በርካታ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትም መቀመጫቸውን እዚሁ አዲስ አበባ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ ዩኔስኮ በአዲስ አበባ መቀመጫ አላቸው፡፡
አዲስ አበባ ላለፉት 60 ዓመታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኘላት ሲሆን፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ወሳኝ በሆኑ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች የአህጉሪቱ ሀገራት በተሻለ መልኩ ድምጽ እንድትሆን እድል ፈጥሮላታል፡፡ ከተማዋ የአህጉሪቱ መሪዎች መሰባሰቢያ መሆኗ በራሱ የሚሰጣት ክብርም አለ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከተማዋ ዳጎስ ያለ ገቢ ከምታገኝባቸው ትላልቅ ኩነቶች መካከል የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ የዓድዋ ድል አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን ከማስቻሉም ባሻገር በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን ወክለው ለሚሰሩ ዲፕሎማቶቻችንም ትልቅ አቅም ሆኗቸዋል፡፡ አድዋ ኢትዮጵያ በየአገሮች የምትታወቅበት፣ የምትከበርበትና በተለያዩ የዓለም ሀገሮች ለተወከሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፣ ለኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች እስከ ዛሬም ድረስ የኩራት አክሊል ነው። ለሚመጣው ትውልድ ጭምር የኩራት አክሊል ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ይህ ለዲፕሎማሲያችን ትልቅ አቅም የሚሆን ነው፡፡
ድሉ ኢትዮጵያ ከየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት ቀድማ በወቅቱ ሀያላን ከነበሩ የአውሮፓ ሀገራት ጋር በጋራ ጥቅም እና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንድትጀምርም ረድቷ ታል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ነገስታት ከአድዋ ድል በፊትም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር ግንኙነቶች ያደርጉ ነበር። ከአንዳንዶቹ ጋር ጤናማ ግንኙነት ሲኖራቸው፤ ከአንዳንዶች ጋር ደግሞ ጤናማ ያልሆኑ ግንኙነት እንደነበራት የታሪክ ድርሳናት የሚያወሱን ቢሆንም፤ ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ትኩረት መሳብ በመቻሏ ከኢትዮጵያ ጋር ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር የሚፈልጉ ሀገራት ቁጥር ከፍ እንዲል ትልቅ ሚና የተጫወተ ድል ነበር፡፡
ድሉ ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የሃያልነት ትርክት ከመሰረቱ በመቀየሩ ምክንያት የነጮችን የበላይነት ሲያቀነቅኑ የነበሩ አውሮፓዊያን ጭምር የጥቁሮች ሀገር ከሆነቺው ኢትዮጵያ ጋር ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለማቋቋም እና ከንጉሰ ነገስቱ መንግስት ጋር በተለያዩ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነቶችን ለመፈራረም መሯሯጥ የጀመሩት በድሉ ማግስት ነው፡፡ በዓድዋ ድል ማግስት ሀገራት በአዲስ አበባ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን መክፈት የጀመሩ ሲሆን አዲስ አበባ የበርካታ ሀገራት ኤምባሲዎች ከሚገኙባቸው ከተሞች በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡
ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ቋምጣ የመጣችው ጣሊያን ምኞቷ ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ የዓድዋ ጦርነት ምክንያት የነበረውን የውጫሌ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርገውና የኢትዮጵያን ነጻ ሀገርነት የተቀበለችበትን የአዲስ አበባ ስምምነትን እንድትፈርም ተገዳለች፡፡ በተለይም የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጉሙ ለየቅል የሆኑ አንቀጾች የተካተቱበት እና ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ የጋረጠው የውጫሌ ስምምነት በአዲስ አበባ ስምምነት መሻሩ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ዝና በመላው ዓለም ከፍ ማለቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ተዓማኒነቷ ከፍ ብሏል፡፡ ተዓማኒነቷ ከፍ ማለቱን ተከትሎ ከጀርባ ሆነው ጣሊያንን በርቺ ሲሏት የነበሩት የወቅቱ የአውሮፓ ሀያላን ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነቶችን ለመፈራረም እንዲመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ ባሉት አስራ ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ አዋሳኝ አካባቢዎችን ይገዙ የነበሩ የፈረንሳይ እና የብሪታኒያ መንግስታት ከኢትዮጵያ ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ በርካታ ሀገራት ወደ ንጉሰ ነገስቱ መልዕክተኞችን ለመላክ እና ከኢትዮጵያ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀምሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
የዓድዋ ድል ለአውሮፓዊያን ጭምር ከሀይል ይልቅ ዲፕሎማሲ እንደሚጠቅማቸው ትምህርት ሰጥቶ አልፏል፡፡ ከአድዋ ድል በፊት አውሮፓዊያን በወታደራዊ ሀይል እነሱን የሚገዳደራቸው ሀይል አለ ብለው አያምኑም ነበር፡፡ ዓድዋ አፍሪካ ውስጥ አውሮፓዊያንን የሚገዳደር ወታደራዊ ኃይል እንዳለ አሳይቷል። ለዚያውም የአውሮፓዊያንን ያህል ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቅ የአውሮፓ ወታደሮችን ማሸነፍ የሚችል ሀይል እንዳለ ጥሩ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ አቅም ሳይሆን ጥቅማቸውን በዲፕሎማሲ ማሳካት እንዳለባቸው ጥሩ ትምህርት ሆኗቸዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በትብብር መንፈስ ላይ የተቃኘ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አዕማድ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ስትከተል የነበረው ፖሊሲ የዚህ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ የወንዙ ባለቤት ሆና ሳለች ወንዙን ብቻዬን ልጠቀም ሳይሆን በጋራ እንጠቀም ስትል ኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር በመከባበር ላይ የተመሰረተ፣ የጋራ ጥቅምን ባስጠበቀ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ባስከበረ እና ለዜጎቿ ቅድሚያ በሚሰጥ የዲፕሎማሲ ፖሊሲ በመከተል የአድዋ ድልን ተከትሎ የመጡ የዲፕሎማሲ ትሩፋቶች ለማስቀጠል ዛሬም በትኩረት ልትሰራ ይገባል፡፡
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም