የዓድዋ ድል ልክ እንደ ጦርነቱ ሁሉ መልኩ ብዙ ነው። ከወታደራዊው ድል ባልተናነሰ ዲፕሎማሲያዊው፣ ሃይማኖታዊው፣ የነጭ የበላይነትን ዓይን ከሰበከት ማጋለጡ፤ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትነቱ፤ እላይ የነበረውን የዘረኝነት ርዕዮትን ከታች ማድረጉ ወዘተርፈ ሁሉ የዓድዋ ድል ልዩ ልዩ መልኮች ናቸውና እነሱን እንመለከታለን።
ዓለም እንደተገነዘበው፣ የታሪክ ልሂቃን ለታሪክ ምስክርነት እንዳበቁት፣ የሥነጽሑፍ ጠቢባን፣ ሰዓሊያን፣ ቀራፂያን (ከውስጥም ከውጭም) በየሥራዎቻቸው ላይ አስፍረውት እንደሚገኘው፣ የዓይን ምስክሮች እንዳረጋገጡት፣ እራሳቸው ጣሊያኖች “ቪቫ …” ሲሉ ድሉን ለዓለም እንዳስተጋቡት … የዓድዋ ድል ወሰን ዲካው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።
የጦርነቱ መነሻ
መነሻው በይዘቱ አራምባና ቆቦ የሆነው፣ እንግሊዘኛው “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ አለባት” ሲል፤ አማርኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች” የሚለው የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ነው።
ይህንን የጣሊያን መንግሥት ተራ ብልጣብልጥነት በመቃወም ይቀየር ዘንድ ተጠይቆ ባሳየው ትዕቢትና እምቢተኛነት ምክንያት የተቀሰቀሰው የዓድዋ ጦርነት፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ቀን ዓ.ም በኢትዮጵያና ኢጣሊያ መካከል የተካሄደ ውጊያ እና የአንደኛው የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት ክፍል ሲሆን፤ በአፄ ምኒሊክ አመራር ሰጪነት፣ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የጣሊያን የቅኝ ግዛትና ማስፋፋት እቅድ የተኮላሸበት ዐውደ ውጊያ ነው።
ዐውደ ውጊያውና የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት
ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት (ይህ 300ሺህ ሚሊሺያ ወደ ጦር ሜዳ በመሄድ በእብሪተኛው ዚአድባሬ ወረራም ተደግሟል)፤ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ድባቅ የመታበት (ጆርጅ በርክሌይ በፃፈውና ዳኘው ኃይለሥላሴ “የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ” በማለት በተረጐሙት መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ እንደተነበበውና ለታሪክ ምስክርነት እንደበቃው) ድል ነው።
የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ፣ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ ባበደ መንፈስ (በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ) በጀግንነት የተዋጋበት፣ ይህም በዓለም ታሪክ ላይ በደማቁ ተጽፎ ይሰፍር ዘንድ ያስገደደ ድል ነው።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው ። የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሰብዓዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትሕ ሕልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው … በዓድዋ የታላቅ ሕዝቦች ታላቅ ድል ነው ።
በጦርነቱ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጄኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር እግሬ አውጭኝ በማለት የፈረጠጡበትና የኢትዮጵያ ጦር በተጎናፀፈው ድል ዓለም ጣቱን ከንፈሩ ላይ የጫነበት ድል ነው።
ከሃምሣ ስድስቱ የኢጣሊያ መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር የተማረኩበት፤ አጠቃላይ የጠላት ምርኮኛ በአምስት መቶ አጋሰሶች ተጭኖ ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዝ የተደረገበት ድል ነው።
የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም (የድሉ ማግስት) ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የኢጣሊያ ምርኮኞች በምኒሊክ ድንኳን ፊት ሲያልፉ የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት እየፎከረ እየሸለለ ያሳለፋቸው ታሪክ የተመዘገበበት እለት ነው የአድዋ ድል።
ጄኔራል አልቤርቶኒ በምርኮኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይቶ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ ላይ “ከሚፎክሩት ጥቁር የነፃነት ተዋጊዎች መሐከል አንዱ እንደ እኛው ነጭ አውሮጳዊ [ከፈረንሣይ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ጥገና የመጣና ከጨረሰ በኋላ ተመለስ ቢሉት እምቢ ብሎ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ዓድዋ ድረስ የዘመተው ካፒቴን ኦርዲናንስን ማለቱ ነው] ነው” ሲል እንዳሰፈረው እውነት ወዳድ ነጮች ሁሉ የተሳተፉበት ነው የዓድዋ ድል።
ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ላይ ከተዋጋችባቸው የጦር መሣሪያዎች ሰማንያ ሺህ የሚሆኑት አሮጌ ጠመንጃዎች የተገዙት ከፈረንሳይ አገር በምሥጢር ነው ። ጠመንጃዎቹን ገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ መኪና ወደ ኢትዮጵያ ያስገቡት በሥጋ በደምና በትውልድ አርመናዊ በነፍስና በመንፈስ በዜግነትና በልብ ፍቅር ኢትዮጵያዊ የሆኑት የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ ሰርኪስ ቴሪዝያንም ልክ ካፒቴን ኦርዲናንስም በታሪክ የሚታወሱበት ነው የዓድዋ ድል ።
የዓድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በሰባተኛ ዓመቱ በ1895 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ1903) ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፣ ምኒሊክ አደባባይ ነው። በክብረ በዓሉ ላይ ዲፕሎማቶችና የውጪ ሀገር መንግሥታት ተወካዮች፣ አርበኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖች፣ ብዙ ሺህ ፈረሰኞችና ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንዲገኙ ምክንያት የሆነ፤ ከፈረሰኞቹ ብዛት የተነሳ ፀሐይ በአቧራ እስከመጋረድ/መሸፈን የደረሰችበት (ጳውሎስ ኞኞ በ“የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ጦርነት” መጽሐፉ እንደፃፈውና በብዙዎች እንደ ተጠቀሰው) ነው የአድዋ ድል።
የዓድዋ ድል “ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል” የሆነ፤ በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች ይመጡ ዘንድ፣ በድሉ ማግስት የእንግሊዝ ጋዜጦች የዓለም “ታሪክ ተገለበጠ”፤ ”ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ” … ብለው ይጽፉ ዘንድ ያስገደደ ነው።
የዓድዋ ድል በኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፣ “ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠረ” የተባሉት ዳግማዊ ዓፄ ምኒሊክ (አባ ዳኘው) በሌሉበት (እርሳቸው በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ) ”የአፍሪቃና የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ” ተደርገው ይመረጡ ዘንድ እድሉን የፈጠረ ነው።
የዓድዋ ድል እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ መጀመሪያ ጀርመን ሀገር በርሊን ከተማ ላይ በተደረገው የአውሮጳ ቅኝ ገዢ (ኮሎኒያሊስት) መንግሥታት ባለሥልጣናትና ልሂቃን የጦር ጄኔራሎችና ሊቃውንት ስብሰባ ላይ “ጥቁር ትልቅ ትል ነው፤ ቅንቡርስ ነው እንጂ ነፍስ ያለው ሰው አይደለም” ብለው የነበሩ ያፈሩበት፤ እውነት፣ ፍትሕና ርትዕ ለአደባባይ የበቁበት ነው።
የዓድዋ ድል ከፈረንጅ የአውሮጳ መንግሥታት ሩሲያና ፈረንሳይ የዓድዋን ድል እንዲደግፉ፤ ጀኔራል ባራቴሪ በሀገሩ በኢጣሊያ ጦር ፍርድ ቤት ቀርቦ ማዕረጉ እንዲገፈፍ፤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲኞር ክሪስፒ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲለቁና ሌሎች በርካታ ክስተቶች በዓለማችን እንዲስተናገዱ፤ የነጭ የበላይነት መንፈስ እንዲሰበር ያደረገ ነው።
የዓድዋ ድል የኢጣሊያዊው ንጉሥ አማኑኤል ኡምቤርቶ የልደት ቀን የኅዘን ቀን (የተገላቢጦሽ ማለት ነው) ሆኖ እንዲወሰን፤ ሮማን ፍሎሬንስን ሚላኖ (ሚላን)ን ቬነስን…የመሳሰሉ የኢጣሊያ ከተሞች “ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር” በሚሉ የተቆጡ አውሮጳውያን ትዕይንተ ሕዝብ አድራጊዎች እንዲጥለቀለቁ ያስገደደ ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአራት መስክ ሠለጠነች በምትባለው አውሮጳዊት ሀገር፣ ኢጣሊያ ላይ ድል እንድትቀዳጅ፤ በወታደራዊ ሳይንስ (በጦርነት እና በወታደራዊ መረጃ፣ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ) ሰገነት ላይ ከፍ ብላ እንድትታይ፤ በዚህም ስሟ በዓለም እንዲናኝ ያደረገ ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመታት በላይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት ብቸኛ አፍሪቃዊት ሀገር ትሆን ዘንድ፤ ከኢጣሊያ፣ ከፈረንሣይ፣ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከሩሲያና ከጀርመን . . . ጋር ከመቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አዳብራ እና አፅንታ እንድትቆይ መሠረቱን የጣለ ነው።
በሁዳዴ ፆም ውስጥ የተደረገው (በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት የተደረገው የመቅደላ ጦርነትም በሁዳዴ ፆም ውስጥ ነበር) የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ምርኮኞቿን ግብር አብልታ አካላቸውም፣ ምቾታቸውም ሳይጓደል ወደ ሀገራቸው መልሳ በመላክ የሰብዓዊ መብት አክባሪነቷን ለዓለም በይፋ ያሳየችበትና በዘርፉ ታሪክ ያስመዘገበችበት ነው።
የዓድዋ ድል ዋንኛው መገለጫ፣ የማንነት ልዩ መለያና የመላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ዓርማና የነፃነት ተምሳሌት ሲሆን፤ ያለ ምንም ውሽልሽል ምክንያቶች፣ ድጋፍና ርዳታዎች ድሉ በጦር ግንባር ፍልሚያና ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው።
የዓድዋ ድል በወቅቱ በዓድዋ ጦርነት ተማርኮ የተያዘው ኮሎኔል ጋሊያኖ“ የምኒሊክን ፊት ከማይ ግደሉኝ” ማለቱ የተመዘገበበት፤ የመቀሌውን ውጊያ በልዩ ጥበብና ወታደራዊ ብቃት የመሩትን፣ ጣይቱ ብጡልን ለዓለማችን፣ በተለይም ለጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ያፈራ ነው (ጀግኒቷን ቢቢሲ የሚሌኒየሙ “ምርጥ ሰብዕና” ያላቸው ብሎ የሰየማቸው፤ የአፍሪካ ኅብረት የክፍለ ዘመኑ እንስት ጀግና ሲል የመረጣቸው መሆናቸውን ልብ ይሏል)።
የዓድዋ ድል “አንዲት ሀገር በጦር ሜዳ አሸናፊ የምትሆነው በፍትሐዊ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ከሆነች ብቻ ነው።” የሚለውን የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብት፣ ተመራማሪና አጥኚዎች መደምደሚያና ፍልስፍና መሬት ያስረገጠ ነው።
የዓድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ውጤት ሲሆን፤ እነ ዳግማዊ ምኒሊክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኮንን፣ ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ እና ሌሎች ባለውለታ ጀግኖችም ስማቸው በወርቅ ቀለም የተፃፈላቸውን አርበኞች ያፈራ ነው። (ሌሎቹን ከሌሎች ምንጮች፣ ለምሳሌ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “ኢትዮጵያ ታሪክ” ማየት ይቻላል።)
የዓድዋ ድል በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የውጭ ጠላት የኢትዮጵያን የባሕር በር አልፎ መምጣቱን በአዋጅ መናገራቸውንና የክተት አዋጁን ተከትሎ በግንባር ቀደምትነት ምላሽ ከሰጡት አርበኞች መካከል ቀዳሚ የሆኑት፣ በዓድዋ ጦርነት የተሰዉት፣ አፄ ምኒሊክ “ሀገሬን አዳንኩ ገበየሁንም አጣሁ” ያሉላቸው ዳዊት ደጋሚው፣ ፆምና ፀሎት አዝወታሪው፣ የጦር አበጋዝ ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) “በጦርነት ስዋጋ በጥይት ተመትቼ ብወድቅ የተመታሁት ጀርባዬን ከሆነ ስሸሽ ነው [ስጋዬን] አሞራ ይብላው እዛው ተውኝ፤ ግንባሬን ከተመታሁ ግን ሃገሬ ቅበሩኝ” በማለት ጀግንነታቸውን ያስመሰከሩበት ነው።
የዓድዋ ድል እስከ አፍንጫው የታጠቀው የጣሊያንን ጦር መሸነፍ በሰሙ ጊዜ ጣሊያናውያን አደባባይ ወጥተው የሀገራቸውን መንግሥት በመቃወም “ቪቫ ጣይቱ፤ ቪቫ ምኒሊክ፣ ቪቫ ኢትዮጵያ” በማለት እማይደፈረውን ለደፈረና ላዋረዳቸው መንግሥታቸው የስላቅ መልዕክት ያስተላልፉ ዘንድ ምክንያት ነው። (በጣሊያንኛ “ቪቫ” ማለት “ለዘለዓለም ኑር” ማለት ሲሆን፣ ያስተላለፉት መልዕክትም “ጣይቱ ለዘልዓለም ትኑር”፣ “ምኒልክ ለዘልዓለም ይኑር”፤ “ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር” የሚል መሆኑን ልብ ይሏል።)
የዓድዋ ድል የቅዱስ ጊዮርጊስ እለት የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፤ ወጂግራ፣ ዲሞትፈርና ሰኔኔ ይዞ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ዘመናዊ የጦር መሣሪያን እስከ አፍንጫው የታጠቀውን፣ የሮማ ሊቃነ ጳጳሳት በአደባባይ ተገኝተው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስም “ይቅናችሁ፤ በድል ተመለሱ!!!” (ይህ በGlobal alliance for justice the Ethiopian Case እና በሌሎችም ይፋ የተደረገ መረጃ ነው) በመባል ተባርኮ የተላከው የፋሺስት ጦር ድል የተመታበት ነው። (ለተጨማሪ በዲ/ን ኅሊና በለጠ የተጠቀሰውን የፕሮፌሰር ሬይሞንድ ጆናስ ‹‹THE BATTLE OF ADWA:-African victory in the age of Empire›› ይመለከቷል።)
የዓድዋ ድል በመቶ ሺህ የሚሠላ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የአውሮጳ ቅኝ ገዢ ወራሪዎችን ድባቅ ከመታና ረግጦ ካስወጣ በኋላ ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም (የካቲት 23 ቀን) እንዳማርያም ላይ ተሰባስቦ በአንድ እግሩ ቆሞ ቀኙን (ድሉን) ለሰጠው አምላክ፡-“የመጡ የአገራችንን ድንበርና ልዕልና የደፈሩ የአውሮጳ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎችን እንድናሸንፍ (ድል እንድናደርግ) ስለረዳኸን እናመሰግንሃለን …”በማለት ለአምላካቸው ምሥጋና ያቀረቡበት ነው ።
የዓድዋ ድል እኛ ኢትዮጵያውያን፣ በተራዛሚውም መላው ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ፣ አንድ ከሆንን የማንችለው ምንም ነገር እንደሌለ በተጨባጭ ያሳየ ታሪካዊ ሁነት ነው።
የዓድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን የሚያምኑትና የሚከተሉት አንድ ጠንካራ መንግሥት፣ አንድ ሀገር እንደ ነበረ ተገቢ የሆነ ማሳያ ነው። የዓድዋ ድል ወጉ፣ ባሕሉና እምነቱ እንዳይበረዝበት ከመላ ሀገሪቱ ከ100 ሺህ በላይ የሚገመት ኢትዮጵያዊ፣ የብሔር፣ እምነት፣ ቋንቋ . . . ልዩነቶች ሳያግዱት በአንድነት ስንቁን በመያዝ መዝመቱና በጽናት በመዋጋት ድል ማድረግ መቻሉ የታየበት ነው።
የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ ነው። የዓድዋ ድል የዓድዋ ጀግኖች ያደረጉት ተጋድሎና ያስገኙት ድል ኢትዮጵያውያን ሁሌም ምን ጊዜም በሀገር ጉዳይ ላይ የማይደራደሩ መሆናቸው የታየበት ነው። የዓድዋ ድል የድሉ ዋና መሠረት የኢትዮጵያውያን የሥነ ልቡና፣ መንፈሳዊ ጥበብና አስተሳሰብ ሚዛን መሆኑ በግልፅ የታየበት ነው።
የዓድዋ ድል ‹‹…በቅርብ ቀን ምኒሊክን በቀፎ ውስጥ አሥሬ ሮማ ውስጥ አመጣዋለሁ…›› ይል የነበረውን፣ ገና ከጦርነቱ አስቀድሞ በራሱ ሕዝብ ‹‹ድል አድራጊው›› በመባል ሲሞካሽ የነበረውን የኢጣሊያ የጦር መሪ የጄኔራል ባራቲዬሪ ትዕቢት ልክ የገባበትና በዓለም ፊትም ያሳፈረ ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ያደረገ፤ በጣሊያን የመንግሥት ለውጥ ይደረግ ዘንድ ያስገደደ (Adwa turned Ethiopia into a symbol of freedom for black people globally. It also led to a change of government in Italy. ተብሎ በታሪክ እንደተዘገበው) ድል ነው።
“የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ።” የሚል ዜና በድፍን አውሮፓ ይናኝ ዘንድ ምክንያት የሆነ ድል ነው የዓድዋ ድል። (ለተጨማሪ በጳውሎስ ኞኞ፣ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ የተጠቀሰውን Berkeley, George; The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik ያነቧል።)
በመጨረሻም፣ የወታደራዊው ድል የበላይነታችን እንዳለ ሆኖ፣ ዓለምአቀፍ ኅብረት ለፍትሕ የኢትዮጵያ ጉዳይ (Global alliance for justice the Ethiopian Case) የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የየካቲት 12/1929 ዘግናኝ እልቂትን ጨምሮ ጣሊያን በአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፈች (ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ከብቶችን ጨምሮ) ሲሆን ለዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቷ ለኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢ ካሳ ልትከፍልና ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባል የሚለው ያልተቋረጠ ጥያቄም ምላሽ ሊያገኝ ይገባል። ኢጣሊያ በሊቢያ ላይ ለፈፀመችውና ከ30ሺ በላይ ሊቢያውያን ላለቁበት ጭፍጨፋ የኢጣሊያ መንግሥት በቅርቡ አምስት ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ይታወሳል ። በሚለው እንሰናበታለን።
ዘላለማዊ ሕይወት ለአባት አርበኞቻችን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም