የንባባችን መደላድል፤
ድርቅ፡- በዝናብ መጥፋት ወይንም እጥረት መንስዔነት ለተራዘሙ ጊዜያት የሚፈጠር የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ነው ። ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የድርቅን ዐውዳዊ ትርጉምን ለመበየን የመዝገበ ቃላት ድጋፍ ወይንም የሳይንሳዊ ምርምሮች ትንታኔ እጅግም አስፈላጊዎቻችን አይደሉም ። ታሪካችን ራሱ በድርቅና በርሃብ ሰነዶች የታጨቀ መሆኑን ችላ ብለን ወደ ሌሎች ምንጮች ብናንጋጥጥ ትርፉ፤ “ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ሲሸከም ያነጋል” ይሉት ብጤ ይሆንብናል ።
“ቀና ብዬ ባየው ደመናው ቀለለኝ፣
እግዜሩን ሠፈራ ወሰዱት መሰለኝ ።
ግዴለም እግዜሩስ እንዳሻው ብለናል፣
መንግሥት ምነው ከፋ ድምጡ ከእኛ ርቋል ። ”
በማለት በራሱ ጥበባዊ የግጥም ሥነ ቃል ለሚራቀቀው የሀገሬ ባለ ሀገር የባዕዳንን ቋንቋ እያደበላለቅን የሚከተለውን መሰል ፈረንጅኛ ትንታኔ ብንግተው እንደለመደው እንደ እሳት በሚፋጀው ትዝብቱ “ንቆን” ይገላምጠናል እንጂ “ጎሽ አበጃችሁ! ትምህርቱ ደግ ነው!” በማለት በእንቱፍቱፍታ አይመርቀንም ።
“ከመደበኛ ሥርጭት ያነሰ ዝናብ ሲከሰት የሚቲዮሮሎጂካል ድርቅ (A Meteorological Drought) ይባላል ። በዝናብ እጥረት ምክንያት የእርሻ መሬት የእርጥበት ችግር ሲገጥመው የግብርና (Agricultural Drought) ይሉት ዓይነት ድርቅ ይከሰታል ። ወንዞች፣ ሃይቆች፣ ኩሬዎችና ምንጮች በዝናብ መጥፋት ምክንያት ክው ብለው ሲደርቁ ደግሞ የውሃ እጥረት ድርቅ (Hydrological Drought) ይከሰታል” እያልን ለደጉና ለገራገሩ የሀገሬ አርሶ አደር የተራቀቀውንና አንዳንዴም ለባለሙያዎቹ ለራሳቸው በማይገባቸው “የተወሳሰበ የሳይንስ” ፍልስፍና ልንሸነግለው ብንሞክር ምላሹ፤ “ይብላኝ ለራሳችሁ! ለኔውስ ድርቅ የሕይወቴ አንዱ አካል ስለሆነ ምክንያቱን አውቀዋለሁ” እንደሚለን አይጠፋንም።
በኢትዮጵያ ዐውድ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ብዙ ጊዜ ከፍተኛ የአንበጣ መንጋና የተምች ወረርሽኝ ተከስቶ የተዘራውን ሰብል እምሽክ አድርጎ እየበላ ድርቅ እንደሚያስከትል የውጭ “አጥኚ” ተብዬዎቹ ስለምን እንደሚዘሉት ለጊዜው ግልጽ አይደለም ። ይልቅስ ከሀገሬ ባይተዋር አርሶ አደር የተፈጥሮ ድርቅ ተጠቂ ጋር ልንግባባ የምንችለው ነፍሰ ሄሩ ባለቅኔያችን ጸጋዬ ገ/መድኅን የዚያን ምስኪን ወገናችንን ስሜትና የልቡን ትርታ በብዕሩ የገለጸበትን ውብ ግጥም አንብበንለት “እህ” ብንለው ልብ ተቀልብ ሆኖ በማድመጥ ብሶቱን እንደሚዘረግፍልን ጥርጥር የለውም ።
“እስቲ እናንተ ተናገሩ ተርባችሁ የምታውቁ፣
ከቸነፈር አምልጣችሁ ተርፋችሁ እንደው ሳታልቁ።
ትንፋሽ ቀርቷችሁ እንደሆን ያስችላችሁ እንደሆን ጥቂት፣
ቀጠሮ ይሰጣል እልቂት?
ስንት መዓለት? ስንት ሌሊት?
ጥንብ አንሳው ሳይወርድ በፊት፤ ሳይሞዠርጣችሁ ጥፍሩ፣
በጣረ-ሞት አክናፋቱ አንዣቦ በመቅሰፍት እግሩ፣
አንደበት ተርፏችሁ እንደሁ ሳትነግሩን ከምትቀሩ፣
ካስቻላችሁ ተናገሩ ።
[የእኔ ቢጤማ ምሁሩ የት ይገባዋል የርሃብ ምሥጢሩ] ።
ከባለ ሀገሩ መጻተኛ ጋር በዚህ ቋንቋ ስንግባባ ነው መደማመጥና መግባባት የምንችለው ።
“የርሃብ ስንቅ” ያልነውን ጥቂት እናፍታታ፤
አንድን ጉዳይ ቢያሻ ለማሳጠር፤ ካስፈለገም ለማስረዘም ሲፈለግ፤ “ስንቅና ማሕሌት እንደያዢው ነው” ይባላል ። የሀገሬ ብሂለኛ እውነቱን ተናግሯል ። ስንቅ፡- ዓይነቱ ቢለያይም ለመንገድ ወይንም ለረጂም ጉዞ ተዘጋጅቶ የሚያዝ የበሰለ ምግብ ነው ። “እጃቸው ያጠረ” መንገደኞች ቆሎ፣ በሶ፣ ድርቆሽ እና መሰል ቤት ያፈራውን ቋጥረው ለጉዞ ይነሳሉ ። ኑሮውና ማጀቱ ደምቆ የተባረከለት ወገን ደግሞ በቅቤ የወረዛ ጩኮ፣ በጨው የታሸ ቋንጣ፣ ቅባት የጠገበ ጭብጦ በስንቅ መያዢያ አገልግሉ ውስጥ በወግ በወጉ ሊሰደርለት ይችላል ። “ስንቅህን በአህያ፤ አምልህን በጉያ” እንዲሉም የጉዞ ዝግጅቱ የሚጀመረው የራስን ባህርይ በራስ ቤት ቆልፎ፣ የስንቅ ኮሮጆን በአግባቡ ሸክፎ ጉዞን መያያዝን የሚያመለክት ነው ።
“ርሃብ እንዴት የስንቅ ማዕረግ ሊሰጠው ይችላል?” ብሎ ለክርክር ለሚጣደፍ ተሟጋች “ሀገራዊ ታሪክህን ፈትሽ!” ብሎ አጭር መልስ መስጠት ይቻላል ። ቀዳሚዎቹ መንግሥታዊ ሥርዓቶቻችን “ትተውልን አልፈዋል ከምንላቸው በጎ አሻራዎች (ሌጋሲዎች) ጎን ለጎን” ርሃብንም አንደ በጎ ነገር ለተከታዩ ትውልድ “ቅርስና ውርስ” አድርገው ሲያቀባብሉ የኖሩት “እንደ ስንቅ እየቆጠሩ” ጭምር ይመስላል ።
የድርቅና የርሃብ፣ የጠኔና የቸነፈር ታሪካችን በዝርዝር የተሰነደባቸው የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትንና የሌሎች መሰል የታሪክ መጻሕፍትን ገጽ በገጽ ብንፈትሻቸው በየትኞቹም ሥርዓተ መንግሥታት ውስጥ ድርቅና ርሃብ ሳይከሰት እንዳልቀረ ማስተዋል አይገድም ።
“እከሌ በሚባለው የሀገራችን ንጉሥ/መሪ ዘመን ከዚህ ዓመት እስከዚህ ዓመት ድረስ የቆየ ድርቅ፣ ርሃብና ቸነፈር ተከስቶ ይህንን ያህል የሞት እልቂት አስከተለ፣ ይህንን ያህል ከብት ፈጀ፣ በእንቶኔ የአገዛዝ ዘመንም ተፈጥሮ ፊቷን በማጥቆር ተቀይማን በዚህን ያህል መጠን ዜጎቻችን ረገፉ፤ እንስሳት አለቁ ይህንን ያህል ሰውም አካባቢውን ለቆ ተሰደደ ወዘተ.” በማለት በርካታ ታሪኮችን ማንበብ ይቻላል ።
ለምሳሌ፡- በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የርሃብ እልቂት ተከሰቶ ነበር ከሚለው የዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የስንክሳር ታሪክ ተነስተን፣ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት (1880 – 1883) ደርሶ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቦ እስከሚገኘው እጅግ ዘግናኝ የድርቅና የርሃብ ታሪክ እንተንትን በማለት የ“ጥቁሩን የርሃብና የቸነፈር መከራችንን” ገጾች ብንገልጥ ብዙ ታሪካዊ እድፋችንን ማስተዋል ይቻላል ።
የሩቅ ዘመኑን ታሪካዊ ትንተና ለጊዜው “በተከድኖ ይብሰል” ትዝብት አልፈን ዕድሜውን ያደለን ዜጎች በኖርንባቸው ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ብቻ በድርቅና በርሃብ ምክንያት ምን ያህል የተፈጥሮ ቅጣት እንደደረሰብን በቃላትና በምስል እንዘክር ብንል በተመደበልን ዐምድ ብቻ ሳይሆን የዚህን አንጋፋ ሙሉ የጋዜጣ ገጾች የሚያጣብቡ መረጃዎችን መዘርገፍ ይቻላል ።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የሰማኒያኛ ዓመታቸውን ባከበሩ ማግሥት (1965/66 ዓ.ም) በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ድርቅና ርሃብ ምክንያት በደረሰው የወገን እልቂት መንስዔነት የሀገሪቱን ሕዝብ ከዳር ዳር ያነቃነቀና መዘዙም የከፋ አመጽ በማስነሳቱ በወቅቱ የታየውን ሥር ነቀል ለውጥ ማስከተሉ አይዘነጋም ። ይኸው የድርቅና የርሃብ መዘዝ ዋና ምክንያት ስለሆነም ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋን ላይ ገፍትሮ እንዴት እንደጣላቸው የምናስታውሰው የቅርብ ዘመን ክፉ ትዝታችን ነው ።
ንጉሡን ከመንበረ ሥልጣናቸው ያስወገደው የወታደራዊ የደርግ መንግሥትም “የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓ)” መሠረትኩ ብሎ ጮቤ በረገጠበት ማግሥት (1977 ዓ.ም) በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው ድርቅና ርሃብ ምን ያህል ዜጎቻችንን ቀርጥፎ እንደበላ አንዘነጋም ።
ወያኔ/ኢህአዴግ “ከተሰነጣጠቀበት እንሽፍሽፍ” በኋላ እና “ከኤርትራ ወረራ በአሸናፊነት ተወጥቻለሁ” በማለት ባስተጋባበት ማግሥትም በሀገሪቱ ተከስቶ ለሌላ መራራ ልቅሶና ዋይታ ያበቃንንና አንገት ያስደፋንን የ1990 ዓ.ም መባቻ የድርቅና የርሃብ ክስተትም የሚዘነጋ አይደለም ።
ዛሬም “ከርሃብ የስንቅ አገልግላችን” ውስጥ አሳራችን ተዝቆና ታፍሶ ስላላለቀ እነሆ “ለመከራ የጣፈው ቢነግድ አይርፈው” ሆኖብን ስለ ልማትና እድገት እየደከምን ነው ብንልም የየዕለቱ ዜናና መርዷችን ድርቅና ርሃብ ሆኖ ዳግም አንገት አስደፍቶናል ። በቦረናና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ለጊዜው እንደሚፈራው በሰዎች ነፍስ ላይ ያለመሰልጠኑ ተገልጾልናል ። ከሕዝቡ ነፍስና ሥጋ ጋር ቁርኝታቸው የጠበቀው እንስሳቶቻቸው ግን በየመስኩ ረግፈውና ተረፍርፈው ማየት በእምባ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ በስሜት ላይ ታትሞ የሚቀር ክፉና መራር ታሪክ ነው ።
እርግጥ ነው እንኳንስ እኛን መሰል የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ተስኗቸው የዑደት ጊዜውን ሳያዛንፍ ለድርቅ ለሚጠቁት ሀገራት ቀርቶ የዓለም ኢኮኖሚና የፖለቲካው ጡንቻ የሚገኘው በእኔ ጓዳ ነው እያለች “ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ” በማለት የምትዘምረው አሜሪካም ብትሆን ከድርቅ በላ ነፃ ሆና አታውቅም ። ከ1900 – 2014 በነበሩት 115 ዓመታት ውስጥ ብቻ 13 ታላላቅ የድርቅ ክስተቶችን ይህቺው “ታላቅ ተብዬ” ሀገር ማስተናገዷ በታሪኳ ውስጥ በግላጭ ተመዝግቦ ይገኛል ።
ቀረብ እንበል ካልንም “The 1930 Dust Bowl Drought” ተብሎ በታሪካቸው የተመዘገበው ከ1928 – 1942 የቆየው እጅግ የከፋው ድርቅ፤ ከ1949 – 1957 (The 1950s drought) በሚባል የሚታወቀው ድርቅ እና ከ1998 – 2014 የተፈተኑበት (The early 21st century drought) እያሉ የሚጠቅሱት ታሪካቸው ብዙ ዋጋ አስከፍሏቸዋል”
አሜሪካንን እየተገዳደረች ባለችው በሌላዊ ልዕለ ኃያል ሀገር በቻይናም እንዲሁ ከ1936 – 37 አምስት ሚሊዮን ዜጎቿን በሞት የነጠቀና ከሃምሳ ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተፈናቃዮች የተመዘገቡበት “Sichuan famine” በመባል የሚጠቀሰውን የተፈጥሮ አደጋ ማስታወስ ይቻላል ። ከ1942 – 1943 እና ከ1959 – 1961 የቆዩት ሁለቱ የድርቅ ወቅቶች፣ የታይፉ ዐውሎ ነፋስና የተምች አደጋዎችም እንዲሁ ከ46 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ዜጎች ህልፈተ ሕይወት የተመዘገበበት ጥቁር ታሪካቸው ነው ።
የእኛን የድርቅ አደጋ ከእነርሱ የሚለየው በተቻለ መጠን የሞት መጠን እንዲቀንስና ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎችም ዳግመኛ ሌላ ድርቅ እንዳያገረሽ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ዜጎቻቸውን የመታደግ ከፍተኛ ሥራዎች ይከናወናሉ ።
መቼም “እናቱ የሞተችበት ሕጻን ልቅሶ እናቱ ወንዝ በወረደች ሕጻን ይቀማል” እንዲሉ ሆኖ “ርሃብ” የሚለው ስያሜ ለድርቅም ለሰዓታት የምግብ እጦትም እኩል ስለምንገለገልበት እንጂ እውነታው ቢፈተሽ ቃሉ እንጂ ውጤቱ በእጅጉ የተለየ ነው ። ከላይ የጠቀስነው ገጣሚያችን እንዳለው፤
“ላልቀመሰው ለእኔ ብጤማ ትርጉሙ፣
የአንድ ፊደል ድምጽ ነው
ርሃብ የሚሉት ከነስሙ ።
እንጂማ የት አውቆት ጠባዩንማ፣
ብቻ ሲነገር ይሰማል ይህንን አንድ ፊደል ቃል ።
ቃሉማ ያው በዘልማድ ይነገራል ይለፈፋል፣
ይተረካል፣ ይዘከራል፣ ይደጋገማል ይተቻል ። ”
እናስ ምን ይደረግ? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው። አንድም፡- ርሃባችን ወደ ትውልዶች “በቅርስነት” እንዳይተላለፍ መንግሥት የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። በቦረናም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች “ለሦስት ዓመታት ይህል ዝናብ ስላልዘነበ ነው” ተብሎ ምክንያት ሲሰጥ “እናስ ሦስት ዓመት ሙሉ ዝናብ አለመዝነቡ እየታወቀ የየክልል መንግሥታትም ሆኑ የፌዴራሉ መንግሥት ምን ሲሰሩ ከረሙ?” ብለን በካርዳችን መንበር የሰጠናቸውን መሪዎች ብንሞግት ተገቢ ይመስለናል ። መልሱም ከሚመለከታቸው አካላት ለጠያቂው ሕዝብ በአግባቡ ሊገለጽ ይገባል እንጂ ተድበስብሶ ሊዘለል አይገባም ።
“ርሃቡ የሰው ሕይወት አልቀጠፈም” የሚለው ገለጻም ቢታረም ይበጅ ይመስለናል ። የሰው ሕይወት ባያልፍ እንኳን ለኑሯቸው ዋስትና የሆኑት እንስሳቶቻቸው እንደቅጠል ሲረግፉ የመከራው ተሸካሚዎች “እንስሳቶቹ ካለቁ እኔስ ኖሬ ምን እፈይዳለሁ አንደኛውን ሞት በስንት ጣዕሙ” ብለው ተስፋ እንደሚቆርጡና መኖርን እንደሚጠየፉ እንዴት ሊረሳ ይችላል ።
ማሳረጊያችን እንደተለመደው ለሕዝባችን አቤቱታ ማቅረብ ነው ። ምንም ተባለ ምን ድርቁ በወገኖቻችን ላይ ከፍ ያለ የመከራ ውርጅብኝ እያዘነበባቸው ስለሆነ የተጀመረው የትድግና ጥረት በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ። መቼም እየታዘቡንም ቢሆን ከጎናችን የሚቆሙ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችም እጃቸውን ከመዘርጋት ችላ ስለማይሉ እነርሱንም የማስተባበሩ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል ይገባ ይመስለናል ።
እንደ ልማድ የተጣባንን “ይህ መቼ ጠፋን፤ ነጋሪም ሆነ መካሪ አንፈልግም” ለሚለው የሹሞቻችን የመከራከሪያ አባዜ ለጊዜው ጆሮ ባለመስጠት ዜጎች ሁሉ የአቅማቸውን እንዲያደርጉ አደራ ከማስተላለፍ ልንቦዝን አይገባም ። ቀድመው ለተጉት አርአያ ሰብ ወገኖቻችን የአክብሮት ምሥጋናችንን ማድረሱንም አንዘነጋም ። በዚያም ተባለ በዚህ ጩኸታችን “ድርቅ የትውልዶች ተወራራሽ የርሃብ ቅርስ እንደሆነ የመታሰቡ ምዕራፍ ተዘግቶ መከራችን ያብቃ” የማጠቃለያ መልእክታችን ነው ። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም