«ታሪክ ራሱን አይደግምም፤ የእገሌ ዘመን፣ የምንትሴ ዘመን ከሚለው መመሳሰል ውጪ» ይላል አሜሪካዊው ፀሐፊ ማርክ ትዌይን፤ እርግጥ ነው ፀረ ቅኝ አገዛዝ ጦርነት በብዙ ሀገሮች ተደርጓል፤ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ ለነፃነታቸው ለረጅም ዘመናት የታገሉና ድልም የተቀዳጁ አሉ፤ የአድዋው ጦርነት ግን በተደረገበት የታሪክ የዘመን ነቁጥና ሥፍራ አኳያ ሲታይ እጅግ አንፀባራቂና ቀዳሚ ቦታ ያለው ነው፤ ብዙ ተብሎለታል፤ ለዛሬው መልዕክታችን ከዚሁ የአድዋ ገድል ጋር በቅርብ የተገናኘ አንድ ሩሲያዊን ማስታወስ ፈልጌ ነው፡፡
ኒኮላይ እስቴፓኖቪች ሊዎንቴቭ ይሰኛል፤ ይህ ሰው የአድዋ ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ጊዜያት በፊት ከአፄ ምኒልክ ጋር በቅርብ የተዋወቀ ነበር፤ ሰውየው የሩሲያ የሚሊታሪ መኮንን የነበረ ሲሆን በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የተጓዘ አገር አሳሽና የጂኦግራፊ ሚሲዮን አባልም ሆኖ ሀገሩን ሩሲያን አገልግሏል።
በ1887 ዓ.ም ነው ከጥቂት ረዳቶቹና ከበጎ ፈቃድ ተጓዦች ጋር ኢትዮጵያ ገብቷል፤ አመጣጡም በኦፊሴላዊ መንገድ ሲሆን የሩሲያ መንግስትን ተልእኮ በመያዝ በጊዜው ለነበሩት ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ለማድረስ ነበር፡፡
አፄ ምኒልክ ከዚህ ሰው ጋር ጥሩ ወዳጅነትና መቀራረብ እንደፈጠሩና አንዳንድ ሀገራዊ ጠቄሜታ ያላቸውን ጉዳዮች እንደፈፀሙ በታሪክ ተፅፎ ይገኛል፤ ወቅቱ ቅኝ ገዢዎች በኢትዮጵያ ዙሪያና ባጠቃላይም አፍሪካውያንን በተገዥነትና በባርነት በመግዛትና በመቆጣጠር የያዙበት ጊዜ ነበር።
ዛሬ የኢትዮጵያ ጎረቤት የነበሩት ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን ሀገራት በቅኝ ገዥዎች የተያዙበት ነበር። በአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት እሽቅድድም ወደኋላ የዘገየችው ኢጣሊያም ኢትዮጵያን ለመያዝ ዝግጅቷን ሁሉ ጨርሳ ትንኮሳዎችን እምታደርግበት ሰዓት ነበር፡፡
ሊዎንቴቭ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ ሃገሩ ሲመለስ ምኒልክ 30‚000 ጠመንጃ፣ ከ5 ሚሊዮን በላይ አረርና ጥይት፣ 42 ያህል የተራራ ላይ መድፎች እንዲያመጣላቸው ከአደራ ጋር ልከውታል፤ ይህን የችግር ቀን ወዳጃቸውን አፄ ምኒልክ ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላ የማዕረግ ሽልማትም እንደሰጡት በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።
የሩሲያ የኢትዮጵያ እርዳታ ለቀጠለው ለኢትዮ -ሩስያ ግንኙነት መነሻ ነበር፣ ሩሲያ የቀይ መስቀል ተልዕኮ አደራጅታ ልካ ነበር፣ ይህ ተልዕኮ የወታደራዊ እንደምታም ነበረው፤ ለዐድዋ ዘመቻ ለተንቀሳቀሰው ጦር የሕክምና ዕርዳታም ማድረግን ዓላማ ይዞ ነበር የመጣው፤ ይሁንና ይህ ቡድን አዲስ አበባ የደረሰው የአድዋ ውጊያ ከተፈፀመ ከሦስት ወራት በኋላ ነበር፡፡
እርግጥ ነው ዐድዋ የመላው አፍሪቃ (ፓን- አፍሪካዊነት) ምልክት ሆኗል፤ የአይበገሬነትና የአንድነት ትግል ተምሳሌት በመሆንም ይቀጥላል፤ በተጨማሪም ከአድዋ የኢትዮጵያ ድል ማድረግን ተከትሎ አገራችን የታፈረችና የተከበረች ሆና እንድትቆይ ምክንያት ሆኗል፤ ይህንን ጦርነት በማሸነፏም የተነሳ ዙሪያዋን ከከበቧት ኢምፔሪያሊስቶችና ቅኝ ገዢዎች ተከላክላ ድንበሯንም አስከብራለች፡፡ በበርሊኑ ኮንፈረንስ አፍሪቃን ለመቀራመት ያሴሩት መንግስታት እንኳን ከአድዋ ጦርነት በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡
የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን የሚጠቅስና መልከ ብዙ ቢሆንም በሊዎንቴቭ የተጀመረው ወዳጅነት ግን ዘመን ተሻጋሪ ሆኗል፤ የኋላ ኋላ ተጠናክሮ በርከት ላሉ የሁለቱ ሀገራት በተግባር ለተተረጎሙ ክንዋኔዎች ምክንያት ሆኗል፤ከጊዜ በኋላ ተጠናክሮ ለተከፈተው የደጃች ባልቻ ሆስፒታል እርሾ ሆኖ አገልግሏል።
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 16 ቀን 1950 ዓ.ም የደጃች ባልቻ ሆስፒታል ምሥረታ 10ኛ ዓመት በዓል ላይ ሲናገሩ ፤የሩሲያ መንግስት ለዜጎቻቸው ጤንነትና ደህንነት የሚየግዙ ተግባራትን በመፈፀሙ እጅጉን መደሰታቸውን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ከዚያም በኋላ የሩሲያና የኢትዮጵያ ግንኙነት እጅግ መልካም በሆነ መንገድ ቀጥሏል፤ ሩሲያም በየዓለም አቀፉ መድረክ ለኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች፤ የታሪክ ምፀት ሆነና ኢትዮጵያ ድል ቀንቷት ራሷን ስታስከብር እንደቀደመው ዘመን ፊት የነሷት አገሮች ግንኙነት ለመቀጠል ሲሽቀዳደሙ ደግሞ ታዝበናል፡፡
ይህ በኒሎላይ እስቴፓኖቪች ሊዎንቴቭ የተጀመረው ምንም ዓይነት ቅኝ ግዛታዊና ኢምፔሪያሊስታዊ ፍላጎትና ዓላማ ያልነበረው የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በሌሎችም መስኮች በተደረጉ ትብብሮች ተደግመዋል፤ ሩሲያኖች (ሞስኮቦች) በባሕርዳር የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተወረረችበት ጊዜ በወታደራዊ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር መቆም፤ በኦጋዴንም በምሥራቅና ምዕራብ ጋሻሞ፣ በካሉብና ጎዴ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋና ቁፋሮ ሥራዎች፤ በባሕልና በትምህርት መስክ በተደረጉ ስምምነቶች ብዙ ኢትዮጵያዊያኖች ወደ ሩሲያ ተልከው ተምረው መመለሳቸው ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው።
በመሠረቱ እነዚህ በሩሲያ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ተርፈዋል፡፡ ይህ በንጉሳዊው ሥርዓትም ሆነ በሪፑብሊካዊው አስተዳደር ዘመን የቀጠለ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ ለመሆኑ እምብዛም ማስረጃ የሚጠይቅ አይደለም፡፡በታላቅ ሀገርና በትንሽ ሀገር፣ በሀብታምና በድሃ መካከል የሚታይ ሳይሆን ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ በእኩልነትና በፍትህ አደባባይ በእኩልነት ይታያሉ በሚለው መርህ መሠረት መሆኑ ነው፡፡
ዛሬ ስለ አድዋና ሊዎንቴቭን ስናስታውስ ኢትዮጵያውያን አንድ እውነት እንዳለን መናገር እንሻለን፤ ጠላት የፈለገውን ያህል መሣሪያ ታጥቆና ተደራጅቶ ቢመጣም ያ የአድዋ ጦርነት ለሀገራችን የሞራል የበላይነት እንደነበረውና ብዙዎችም ምስክርነት እንደሰጡ ማስታወስ እንፈልጋለን፤ ኮሎኒያሊዝምን ያሸነፍነው በዚህ የበላይነት ነው፡፡ ነበልባሉን የአድዋ እሳት ወደ ከሰመ ፍም ላለመቀየር በአዲስ የፓንአፍሪካዊነት መንፈስ ችቦ ይዘን በመነሳት እናስቀጥል፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም