አቶ ብርሃኑ ሞላ ከቀድሞው የአየር ኃይል አባላት አንዱ ናቸው ።የተወለዱት በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም ያደጉትም ሆነ የተማሩት በአዳማ ከተማ ነው ።ከልጅነታቸው ጀምሮ አገራቸውን በውትድርና የማገልገል ፍላጎት ስለነበራቸው በ1970ዎቹ አጋማሽ በበረራ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ሰልጥነው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተቀላቅለዋል ።በበረራ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከሰለጠኑ በኋላ በቀጥታ አየር ኃይሉን ተቀላቅለው በመላ አገሪቱ እየተዘዋወሩ አገልግለዋል ።በ1981ዓ.ም በአገሪቱ ተካሂዶ በነበረው መፈንቅለ መንግሥት ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ጀነራሎች በወታደራዊ መንግሥቱ መገደላቸውን ተከትሎ አብዛኛው አባል ኩርፊያና ማጉረምረም ውስጥ ገባ ።ጥቂት የማይባለውም የሚያበረውን አውሮፕላን ይዞ እስከመጥፋት ድረስ በመንግሥት ላይ ያለውን ተቃውሞ አሰማ። አቶ ብርሃኑም መንግሥትን ተቃውመው አውሮፕላን ይዘው የመን ከተሰደዱት አባላት መካከል አንዱ ናቸው ።ለሁለት ዓመታት በየመን በስደት ከቆዩ በኋላም የአሜሪካ መንግሥትን ጥገኝነት ጠይቀው አሜሪካ ገብተዋል ።
አሜሪካ ቨርጂኒያ ግዛት በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚኖሩት እኚሁ ሰው ከ30 ዓመታት በፊት የቀድሞ አየር ኃይል ማህበርን በማቋቋም በስደትና በአስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ ያሉ አባላት የሚደገፉበት ሁኔታ ፈጥረዋል ።በተለይም በማህበሩ የነበረውን ሥርዓት ተቃውመው ከአገር የተሰደዱ አባላትን በመቀበልና ሕጋዊ የሆነ የጥገኝነት ሰነድና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድም የዛሬው የእኚህ ሰው ሚና የላቀ ነበር ።
የለውጡን መምጣት ተከትሎ የሚወዷትን አገር ዳግም ለማየት የቻሉት የዛሬው የዓድዋ ድል በዓል ልዩ እንግዳችን በተለይም የለውጡ መንግሥት እየፈጠረ ባለው ምቹ ምህዳር በመደሰታቸው ይህ ሥርዓት ከዚህ በላይ ያብብ ዘንድ ለማገዝ ደጋግመው በመምጣት አጋርነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ።አዲስ ዘመን ጋዜጣም ለ127ኛ ጊዜ ዘንድሮ የተከበረውን የዓድዋን የድል በዓል ምክንያት በማድረግ በዚህና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከቀድሞው አየር ኃይል ማህበር መሥራችና ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ሞላ ጋር ውይይት አድርጓል ።እንደሚከተለው ቀርቧል ።
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ እስቲ እንደአንድ የሰራዊቱ አባል የዓድዋ ድል ለእርስዎ ምን እንደሆነ ይግለፁልን?
አቶ ብርሃኑ፡– ዓድዋ ለሰራዊቱ አባላት ብቻ ሳይሆን ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ጥቁር ሕዝብ ክብር ነው። ዓድዋ አሁን ላለንበት ህልውና መሠረት የጣለ ሲሆን፣ በዚያ ጦርነት ዋጋ የከፈሉ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ትልቅ ጀግንነትና ተምሳሌትነትን አስተምረው ነው ያለፉት። ዓድዋን ባሰብን ቁጥር ለነፃነት ሲባል የተከፈለውን የወገኖቻችንን የደም ዋጋ ነው የምናስታውሰው። እንደሚታወቀው እነዚያ የኢትዮጵያ ጀግኖች ለእናት አገራቸው በተዋደቁበት ሰዓት ልክ እንዳሁኑ ቴክኖሎጂ አልነበረም፤ ዘመናዊ መሣሪያና መረጃ መቀባበያ መንገድ በማይታሰብበት ወቅት በተቃራኒው ደግሞ በዘመናዊ ትጥቅ ታጥቆና ተደራጅቶ የመጣን ጠላት በጦር በጎራዴ ተዋግቶ አገርን ነፃ ያወጣበት፤ ብሎም ለአፍሪካም ሆነ ለመላው ጭቁን የዓለም ሕዝብ ከግፈኞች ቀንበር ነፃ መውጣት ጥርጊያ መንገድ ያበጃጀበት ነው ።
ዓድዋ በተለይ ለአፍሪካ ሕዝብ ትልቅ ኩራት ነው፤ በወቅቱ እንደሚታወቀው መላ አፍሪካውያን ከቀኝ ግዛት ቀንበር መላቀቅ የቻሉት ኢትዮጵያ የጣሊያንን ጦር ድባቅ ከመታችና ካሸነፈች በኋላ ነው ያ ድል የሞራል ስንቅ ሆኗቸው ለነፃነታቸው መታገል የጀመሩት ።ስለዚህ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውን ድል ብቻ አይደለም፤ የመላው ጥቁር ሕዝብ ነው ።ያ ድል ደግሞ እስካሁን የምንኮራበትና ወኔ ተላብሰን እንድንኖር ያደረገን ነው ።
እውነቱን ለመናገር በወቅቱ አፍሪካውያን ሳይቀሩ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለው አላሰቡም ነበር ።በመሠረቱ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ያለብዙ ችግር በቀጥታ ቅኝ መግዛት ስለቻሉ ኢትዮጵያ ሲመጡ በቀላሉ መውረርና መግዛት የሚችሉ መስሏቸው ነበር ።ግን የነበረው ምላሽ እንደጠበቁት ሳይሆን ቀርቶ ውርደትን ተከናንበው ነው የሄዱት ።ይህ ድል ለመላ አፍሪካ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶ ነው ያለፈው ።በውጭ ያለን ኢትዮጵያውያንም በስደት አገር በኩራት አንገታችንን ቀና አድርገን መኖር የቻልነው በዓድዋ ምክንያት ነው ።አሁንም ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊት በሚሰለፍበት የጦር ግንባር ሁሉ በጀግንነት እንዲያሸንፍ ያደረገው ዓድዋ ላይ የተፈፀመው ጀግንነትና የነበረውን ወኔ በመሰነቁ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- በሚኖሩባት አገር አሜሪካ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች አሁንም በጭቆና ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ ለመሆኑ ለእነዚህ ሕዝቦች በዓድዋ ስለተሠራው የጀግንነት ታሪክ በውል ማስተዋወቅ ተችሏል ብለው ያምናሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- በመሠረቱ ስለዓድዋ የሚገባውን ያህል አስተዋውቀናል ብዬ አላስብም፤ ያም ቢሆን ግን በዚህ ዙሪያ ብዙ የታገሉ፣ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ያጠፉ ብዙ ዲያስፖራዎች አሉ ።እንደተባለው ከዚህ ቀደም አሜሪካ ያለው ጥቁር ሕዝብ ስለዓድዋ እምብዛም አያውቅም ነበር፤ አሁን ግን የበለጠ እየታወቀና በዚያ ጊዜ የተሠራውን የጥቁር ጀግንነት ጀብዱ እንደምሳሌነት በመውሰድ ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ ።አንዳንዶቹም የመብት ታጋዮች ያንን የድል ታሪክ እየተጠቀሙበት ያለው ሌሎችን ለመቀስቀሻ እንደ አንድ ጥሩ መሣሪያ አድርገው ነው ።
ዓድዋንና የኢትዮጵያን ቅኝ አለመገዛት ለዓለም ሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በርካታ ሥራዎችን ሠርተወል ።የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት እኚሁ ሰው፣ በርካታ ፊልሞችን በመስራት ጭምር ታሪኩ ለትውልድ ተቀርፆ እንዲቀር በማድረግ ረገድ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም ።እኔ እንኳን ከዛሬ 24 ዓመት በፊት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሊንከን ቴአትር ቤት እርሳቸው የሠሩት ፊልም ጥቁሩም ሆነ ነጩ ተሰልፎ ያየው እንደነበር አስታውሳለሁ ።ያ ፊልም ትልቅ ግንዛቤ ፈጥሯል ።ከዚያ በኋላም ሌላ ፊልም በመሥራት የኢትዮጵያን የጀግንነት ታሪክ እና ታላቅነት፤ ዓድዋ ምን ማለት እንደሆነ በአግባቡ እንዲታወቅ ያደረጉ በመሆናቸው ሊመሰገኑ ይገባል ።
በሌላ በኩል ከተወሰኑ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ‹‹ኢትዮጵያን ሄሪቴጅ ሶሳይቲ›› የሚባል ድርጅት አቋቁመን ነበር ።በዚያ ድርጅት አማካኝነት ለተወሰነ አመታት ባለንት አገር ሆነንም ዓድዋን እናከብር ነበር ።እኔም የዚያ ድርጅት ኮሚቴና ከመስራቾቹም አንዱ ነበርኩ ።የዚያ ድርጅት ዋነኛ አላማ አዲሱ ትውልድ ስለዓድዋ ድል በሚገባ ማወቅ አለበት የሚል ነው ።በበዓሉ ዕለት ትልቅ ዝግጅት በማዘጋጀትና ትልልቅ እንግዶችን ጋብዘን ታሪኩን እንዲያስተምሩ እናደርጋለን ።አሁን ያ ድርጅት ያለበትን ሁኔታ በትክክል ባላውቅም ለረጅም ዓመታት በየጊዜው የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን እያዘጋጀ የበኩሉን ሚና ሲወጣ ቆይቷል ።ያም ቢሆን ዲያስፖራው በያለበት አገር የመላ ጥቁሮች ድል የሆነው ዓድዋንም ለማሳወቅ የራሱን ጥረት ያደርጋል ።ይህ ደግሞ አሁን የተጀመረ ሳይሆን ለረጀም ጊዜ ተደርጓል ።ግን ደግሞ የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለዓድዋ ድል ስኬት ዋነኛው ምስጢሮች ተብለው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል ሕዝቡ ቋንቋ፣ ነገድና ሃይማኖት ሳይለየው መዝመቱ ነው ።በእርስዎ እምነት አሁን ያለው ትውልድ ከዚህ ምን ይማራል?
አቶ ብርሃኑ፡– እውነት ለመናገር ትክክለኛ የሆነ ኢትዮጵያዊነት የነበረው በዚያ ጊዜ ነው ብዬ ነው የማምነው ።አንቺም እንዳልሽው ብሔር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሳይለየው ሁሉም የመሪውን ጥሪ ተቀብሎና በአንድነት መትመሙ እጅግ አስደናቂና አኩሪ ታሪካችን ነው ። እናም ለዚህም ነው የዓድዋ ድል የአንድ ዘር ጎሳ አይደለም የምንለው ።ከዚያ ድል ብዙ ነገር መማር መቻል አለብን ብዬ አምናለሁ ።ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ሁሉ ነገር እየሰለጠነ በመጣ ቁጥር መበታተንና መፈረካከስ ታይቶብናል ።አሁን ላይ እኮ አገርን የሚያክል ትልቅ የጋራ ጉዳያችንን ትተን ያበዛነው በጥቃቅን ነገር መቧቀሱና መቦጫጨቁን ነው ።እናም ይህንን ሳስታውስ በዚያ ዘመን የነበረው ኅብረተሰብ በኩሩ ኢትዮጵያዊነቱ አሁን ካለነው ሰዎች የበለጠ እንደነበር አስባለሁ ።
ምክንያቱም በአንድ ጥሪ ነው ያለምንም ማቅማማት ጓዜን ጨርቄን ሳይል የተመመው ።ሊያውም ደግሞ እንዲህ እንደአሁኑ መገናኛ ብዙኃን ሳይኖሩ በባህላዊ መንገድ የሰማው ላልሰማው አዳርሶ ነው በአንድ ድምፅ ከአራቱም አቅጣጫዎች ጥሪውን የተቀበለውና ዓድዋ ላይ የተገናኘው ።በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላይ ከመጣው የጎጠኝነት በሽታ ጋር ሲታይ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን የምርም ቆራጦችና ጀግኖች ለአገራቸው ዋጋ የሚከፍሉ እንደነበሩ ያረጋግጥልናል ።ይህንን ስል አሁን ላይ አገሩን የሚወድ የለም ለማለት እንዳልሆነ ግን ግልፅ ሊሆን ይገባል። ግን ደግሞ አንድ ከሚያደርገን ይልቅ የሚያለያየንን ብቻ መርጠን ለአገራችን እድገት እንቅፋት መሆናችን ከምንም በላይ ሊያስቆጨን ይገባል ባይ ነኝ ።አስቀድሜ እንዳነሳሁት እነዚያ የዓድዋ ጀግኖች በቆራጥነታቸው፤ አይበገሬነታቸው፤ እንዲሁም ከጎጥ አጥር ወጥተው በኢትዮጵያዊነት ሥነ-ልቦና በመዋጋታቸው ነው ድል ሊያመጡ የቻሉት ።በመሠረቱ ጠላቶቻችን እንዲህ እንደአሁኑ በዘር ተከፋፍለን ቢያገኙን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ባልኖረች ነበር ።አሁንም ቢሆን በማንነትና በጎሳ መከፋፈል ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን በተግባር አይተነዋል ።በአጠቃላይ በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ናት ያሸነፈችው፤ አሁንም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ከከበበን የልዩነት እና የእኔ ብቻ ይታይ ከሚለው አስተሳሰብ ልንወጣ ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ጊዜ ድሉን የአንድ አካል ወይም ሕዝብ አድርጎ የማሰብ ችግር አለ። በመሠረቱ ይህ ዓይነቱ ግንዛቤ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- ይህ የጥቂት ግለሰቦች አስተሳሰብ ከጊዜ በኋላ የመጣ ነው ።ምንም ጊዜም ቢሆን በዘረኝነት ላይ የተዋጠ አስተሳሰብ ሲመጣ ያንን ድል የማኮሰስ ነገር ሊታይ ይችላል ።ግን ፈፅሞ ሊያጠፋው አይችልም ።እኔ እንደማምነው ዓድዋ የመላ ኢትዮጵያውያን ድል ነው ።ለአንዱ ብሔር ወይም ጎሳ የምንተወው አይደለም ።አስቀድሜ እንዳልኩት የዳግማዊ ምኒልክን ጥሪ ሰምቶ በጦርነቱ ላይ ያልተሳተፈ ብሔር ወይም ጎሳ እንዲሁም የእምነት ተከታይ የለም ።ሁሉም ከየአቅጣጫው ወጥቶ አገርን ከወራሪ ነፃ አድርጓል ።ስለዚህ ድሉ የሁላችንም ነው ።እርግጥ ነው ድሉን ወደአንድ ብሔር የምናስጠጋው ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የአገርንም ሆነ የድሉን ዝና ሊያበላሸው ይችላል ።
በዚያ የጦርነት አውድማ የተፈፀመውን ትክክለኛ ታሪክ ለትውልዱ በማውረስ ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለብን አምናለሁ ።እንደሚታወቀው ታሪክን ከመጽሐፍ እና ከወላጆቻችን እናገኛለን ።ያንን ታሪክ በታሪክነቱ ተቀብለን እያሳደግነውና ለዓለም ማሳወቅ ሲገባን ከውስጡ ስንጥሮች እየመዘዝን የምንቀጥል ከሆነ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ መስማማትም ሆነ መግባባት አንችልም ።አሁን ላይ በተወሰኑ ለአካላት ላይ የሚታየው ልዩነት በጊዜ ማስታረቅና ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት ካልቻልን አሁንም የውጭ ጠላት ቢመጣ ልናሸንፍ አንችልም ።
ስለዚህ አሁንም የሚያስፈልገንና የሚጠቅመን አንድነታችን ነው ።ቀደም ሲል ጣሊያን ሲገባ በዘር ሊከፋፍለን ሞክሯል ።አንድነታችን ጠንካራ በመሆኑ ግን ሊያሸንፈን አልቻለም ።ለዚህ ደግሞ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ በጻፉት መጽሐፍ ላይ እንደምንረዳው ጣሊያን እርሳቸው የተወለዱበት አካባቢ በመሄድ አባ ዶዮ የተባሉት የእሳቸው አጎት ጣሊያን ሰብስቦ አማራና ኦሮሞን ለማፋጀት ቅስቀሳ ሲያደርግ ተመልክተው የተናገሩት ጥሩ አስተማሪ ነው ብዬ አምናለሁ ።በወቅቱ እኚህ አባ ዶዮ የተባሉ ሰው ለሕዝቡ ነጭና ጥቁር ጤፍ አምጡልኝ ካሉ በኋላ ሁለቱን ደባለቁና ‹‹ከእነዚህ መካከል ጥቁርና ነጩን ለዩ›› ብለው ሕዝቡን መልሰው ጠየቁ ሕዝቡም ከባድ እንደሆነ ሲመልስላቸው ልክ እንደዚያ ሁሉ አማራና ኦሮሞን መለያየት ከባድ እንደሆነ ነው ምላሽ የሰጧቸው ።
በሌላ በኩልም ትውልድን ለማጥፋት ሆነ ብለው ታሪክን እያጣመሙ የሚፅፉ ሰዎች አሉ ። ግን ትክክለኛው ኢትዮጵያዊነት አንዱ በአንዱ ላይ የተገመደ ፈፅሞ ሊነጣጥሉት የማይችሉ መሆኑ ነው ።በዚያ ጊዜ የነበሩ ሰዎች አገር ማዳን ላይ ነው እንጂ ትኩረታቸው ጎሰኝነትን ማስፋፋት ላይ አልነበረም ።እርግጥ ነው ሁላችንም የመጣንበት ማንነነት አለ፤ ይህንንም እንወደዋለን፤ ሆኖም ዋናችን አገር ናት ።አገር ስትኖር ነው ስለቋንቋም ሆነ ስለሌሎች ልዩነቶቻን ማውራት የምንችለው ።
አዲስ ዘመን፡- አገራዊ አንድነትና ሕዝባዊ ህብረት ኢትዮጵያን እንደአገር አፅንቶ ለማቆየት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ሁሉ ህብረታችንና አንድነታችን አገርን አፅንቶ ለማቆየት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነገር ጠቃሚ ነው ።በተለይ በአሁኑ ሰዓት በመካከላችን የመግቢያ ቀዳዳ እያነፈነፉ ያሉና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቋመጡ ኃይሎች በዙሪያችን በበዙበት ወቅት አንድ መሆን ካልቻልን አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው ።ድህነትን ለማሸነፍና አገራችን በኢኮኖሚ ለመገንባት ልክ እንደዓድዋ ጀግኖች አንድ ሆነን መሥራት ይጠበቅብናል ።አንዱ ሲሠራ ሌላው እያፈረሰ የሚኖርበት ሁኔታ ሊቆም ይገባል ።አሁን ላይ እውነተኛ እድገት ከተፈለገ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን ትተን ህብረታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል ።
በዚህ አጋጣሚ ጠላቶቻችንም የእኛን መከፋፈል ስለሚፈልጉት አይተኙልንም ።በነገራችን ላይ ጠላት ፊት ለፊት መጥቶ አይጋጨንም፤ እርስ በርስ እያባላን ነው መጠቀም የሚፈልገው ።ባለፈው ዓመት እንዳየነው እኛ እንድንፍረከረክ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሲደረግብን ነበር፤ ይህንን ተፅዕኖ ማሸነፍ የቻልነው ውጭ ያለነው ሆነ በአገር ውስጥ ያለው እንደአንድ ሰው በአንድነት በመጮህና ተባብሮ በመሥራቱ ነው ።ይህም ህብረት ድል እንደሚያመጣ ትልቅ ምሳሌ ነው ።እንደዚህ አሰፍስፈው ሊበትኑን የነበሩት ሁሉ አንገታቸውን ደፍተው ተመልሰው ተደራድረው አገራችን ሰላም መሆን ችላለች ።እናም ምንጊዜም ቢሆን ህብረት ከሌለ መፍረስ አይቀርም። ስለዚህ አንድ ሆነን ለአገራችን መቆም እንጂ እርስበርስ መባላታችንን የምቀጥል ከሆነ ጥፋቱ ቀላል አይሆንም ።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአባቶቹ የተረከበውን የአገርን ህልውና በማስጠበቅ ረገድ የተጫወተውን ሚና እንደአንድ አባል እንዴት ያዩታል?
አቶ ብርሃኑ፡– የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ በዓለም ላይ ገናና እና የደመቀ ነው ።ከአፍሪካም ቀደምት የሚባል አየር ኃይል ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአህጉሪቱም ኩራት የሆነ ነው ።አየር ኃይሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በትጥቅም ሆነ በሰው ኃይል በአግባቡ የተደራጀ ሆኖ ብዙ ውጊያዎችን ሁሉ በድል ማጠናቀቅ የቻለ ሰራዊት ነው ።በተለይ ደግሞ ከሱማሊያ ጋር በነበረን ጦርነት ብቃቱን በሚገባ ያስመሰከረ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ጎረቤት አገሮች ችግር ሲያጋጥማቸው ድጋፍ በማድረግም አለኝታነቱን አረጋግጧል ።
በተለይ በውጊያ ብቃቱ ትልቅ የነበረ ከአፍሪካ ስመጥር ከሚባሉት አንዱ የነበረ፤ አገርን ያዳነ ኃይል ነው ።ይህንን ደግሞ አስቀድሜ እንዳነሳሁት በሱማሊያ ጦርነት ተፈጥኖ ብቃቱን በሚገባ አስመስክሯል ።በዚያ ጦርነት ላይ የታጠቀው መሳሪያ አነሰተኛ እና ጊዜው የለውጥ ሰዓት በመሆኑ ከባድ ፈተና ገጥሞት ነበር ። ሆኖም በተቃራኒ ወገን ደግሞ ዘመናዊ የተባሉ አውሮፕላኖችን ነበር የያዙት።ግ ን ደግሞ የሕዝብ አንድነትና የአየር ኃይላችን በወኔና በስልጠና የማይታማ በመሆኑ ድል መቀዳጀት ችሎ ነበር ።የተቀዳጀው ድል በአየር ውጊያ በምሳሌ የሚጠቀሱ እነጄነራል ለገሰ ተፈራ ሚግ 21 የተባሉ ዘመናዊ አምስት የጠላት አውሮፕላኖች በአየር ላይ አመድ አድርገዋል። ይህ ሁኔታ የሱማሊያን ጦር ተስፋ ከማስቆረጡም ባሻገር እንዲያውም አንዳንዴ በእነሱ አየር ክልል እየተገባ ብዙ ውርደትን አሸክሟቸው ነው የተመለሰው፡፡
በነገራችን ላይ ለአንድ ተዋጊ ኃይል በሰላሙ ጊዜም ቢሆን ስልጠና እና ልምምድ በጣም ወሳኝ ነው። የእኛ አየር ኃይል በስልጠና ረገድ የሚታማ አልነበረም። በየጊዜውም ልምምድ ያደርግ ስለነበር እነኚህን ሁሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች በተወሰኑ አውሮፕላኖች ጥለው ተመልሰዋል ።በወቅቱ አየር ኃይላችን በማሸነፉ ምክንያት የእኛ አብራሪዎች ይይዙት የነበረው ኤፍ 5 አውሮፕላን በገበያ ላይ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዲኖረው አድርጓል። ያንን ያመጣው አየር ኃይል ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስልጠና እና የውጊያ ብቃት በመኖሩ ነው ።
አየር ኃይሉን ለድል ካበቁት ጉዳዮች ዋነኛው ምስጢር ስልጠናውና ልምምዱ ነው ።በሰላሙ ጊዜ በአግባቡ የሰለጠ ከሆነ ለሚመጣ ማንኛውም ጦርነት አሸናፊ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ።በዚያ ጊዜ በየአመቱ የሚቀጠረው ሰራዊት በቁጥር ከ300 ላይበልጥ ይችላል። ግን ስልጠናው ጠንካራ ነበር ።በሰላሙ ጊዜ ሳይሰለጥኑ ጦርነት መጣ ሲባል ብታሰልፊ ልምድ የሌለው ወታደር አሸናፊ ሊሆን አይችልም ።ከዚህ በተጨማሪም ወታደራዊ ዲሲፕሊኑ በጣም ጠንካራ መሆኑ ለድሉ ሌላው ምክንያት ነው ባይ ነኝ ።ምንጊዜም ቢሆን አንድ ሰራዊት ከዲሲፕሊኑ ጋር አብሮ የሚቀረፀው ከአገር ፍቅር ጋር ነው ።አገር ፍቅር የሌለው ጦር አሸናፊነቱም አጠራጣሪ ነው ።ማንኛውም የሰራዊት አባል አገሩን ሊወድ ይገባል ።
እውነት ለመናገር ለአገር ፍቅር እንጂ ለደመወዝ ብሎ ውትድርና የሚገባ የለም ።በመሠረቱ አገርን ለማገልገል እንጂ የረባ ደመወዝ የለውም ።በአጠቃላይ ስልጠናው፤ ዲሲፕሊኑ፤ በአገር ፍቅር የታነፀ መሆኑ ነው ለውጤት የሚበቃው ።እኔ በነበርኩበት ጊዜ ቅዳሜና እሁድ ሳንል ነበር የምናገለገለው፤ በትርፍ ሰዓት ስለሠራሁ ደመወዝ ይጨመርልኝ ማለት አይቻልም ።ያንን ሰራዊት ያቆየው የአገር ፍቅሩና ዲሲፕሊኑ ነው ።ምድር ጦሩ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነበር የሚታየው ።ለምሳሌ በፈንጂ የታጠረ ወረዳ ሲያጋጥም ከአገር ፍቅር የተነሳ ያንን ፈንጂ ላዩ ላይ አፈንድቶ ሌላው ጦር እንዲረማመድ ያደረጉ ብዙ ሰዎች አሉ ።ያንን ያህል አገር መውደድ ነበር ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ አሁን ያለውን ሰራዊትንም ሆነ አዲሱን ትውልድ እንዲህ ባለ የአገር ፍቅርና ዲሲፕሊን ለማነፅ መሥራት ይገባል ብለው ያምናሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- ከሁሉ በላይ በትውልዱም ሆነ በሰራዊቱ ላይ መሠራት አለበት ብዬ የማምነው ከጎጠኝነት ይልቅ የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረው ብዙ መሥራት ላይ ነው ። ምክንያቱም ደግሞ በታሪክ ባየንባቸው አገራት በሙሉ ጎጠኝነት ለማንም አላዋጣም፤ አልበጀምም ።ግን አንድ ሆነን አዲሱን ትውልድ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ካነፅነውና በጋራ ሠርተን ካሳየነው ብዙ ለውጥ ማምጣት እንችላለን ።ለዚህ ደግሞ ታሪክን በትክክል ማስተማር ወሳኝ ሚና አለው ብዬ አምናለሁ ።ምክንያቱም ደግሞ አስቀድሜ እንዳነሳሁልሽ መከፋፈሉ ጥፋት እንጂ ጥቅም አላመጣልንም ።በመሆኑም ተባብረን ከሠራን ጠላትን መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ትልቁ ጠላታችንን የሆነው ድህነትን እናስወግዳለን ።ይህንን ዓይነት ትምህርት ለወጣቱ በሚገባ ከተሰጠው አስቀድሞ የነበሩት ዓይነት አገር ወዳድ ዜጎች ይፈጠራሉ ።አለበለዚያ ግን እንዲሁ በፍሬከርስኪ የምንቦጫጨቅ ከሆነ ጠላትም ሳይመጣ እርስበርሳችን ተባልተን እናልቃለን ።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት አራት ዓመታት አየር ኃይሉ ወደቀድሞ ገናና ዝናው ለመመለስ እየተሠራ ያለውን ሥራ እንዴት ተመለከቱት? ምንስ ይቀራል?
አቶ ብርሃኑ፡– እኔ ከለውጡ በኋላ ስመጣ ለአምስተኛ ጊዜ ነው ።በመጣሁባቸው ጊዜያት ሁሉ አየር ኃይሉን የመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቼ ስለነበር ለውጡ በሚገርም ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ስለመምጣቱ ታዝቤያለሁ ።ለውጡ እንደመጣ ያየሁት አየር ኃይልና አሁን ያለው ከፍተኛ ልዩነት አለው ።ያም ሲባል ባለፉት አራት ዓመታት ብዙ እድገት አሳይቷል ።የቀደሙት ሰዎች ጥለው የሄዱት የደከመ አየር ኃይል ነው ።ከጊቢው አቅም እንኳን ቆሻሻ የበዛበት፤ የጦር ካምፕ የማይመስል ነበር ።እናም ከለውጡ በኋላ ከሕንፃ ግንባታው ጀምሮ የትምህርት ሥርዓቱን ከማሻሻልና አጠቃላይ አየር ኃይሉን ዳግሞ እስከማዋቀር ድረስ የተሰራው ሥራ ጥሩ ውጤት ያየሁበት ነው ።ይህ ማለት ግን የሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ደግሞ ለ27 ዓመታት የወደመን ተቋም በአንድ ጊዜ መተካት የማይቻል በመሆኑ ነው ።
በአራት ዓመት ውስጥ ግን ከምጠብቀው በላይ ብዙ ለውጦችን አይቻለሁ ።የጎደሉትን ነገሮች ደግሞ በሂደት ያሟላል ብዬ እገምታለሁ ።ያሉት አመራሮችም ሰራዊቱንም ሆነ የቀደሙ አባላትን የሚቀበሉበት መንገድ ትህትና የተሞላው ነው ።በቀድሞ አየር ኃይል ተጀምረው የነበሩ ዴፖዎች ዛሬ ትልቅ መጠገኛ ሆነው የውጭ አውሮፕላኖችን አምጥቶ እስከመጠገን ደርሰዋል። ድሮ ራሺያና ሌሎች ቦታዎች ተልከው ይጠገኑ የነበሩ አውሮፕላኖች አገር ውስጥ መሠራት ጀምረዋል ።በዚህ ረገድ ትልቅ ውጤት እየታየ ነው ያለው ።ጊቢውን በማሳመር ረገድ የተሰራው ሥራ በጣም አስገራሚ ነው። ቆሻሻ ተሞልቶበትና ጥሻ ሆኖ የነበረው ያ አየር ኃይል አሁን የደብረዘይትን ሕዝብ በሙሉ ሊመግብ የሚችል ትልቅ የእርሻ ቦታ ሆኗል ።በጦሩ ብቃት፣ በስልጠና እና ዲሲፕሊን ረገድም ጥሩ ጅምሮች ነው ያሉት ።ወደነበረበት ክብርና ዝና ለመመለስ ግን የሚቀሩት ነገሮች አሉ፤ ይህንንም አሁን ያለው አመራር ያሳካዋል ብዬ አምናለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራው አንድነቱን አጠናክሮ ለአገሩ ዘብ ከመቆምና ለእድገቷ በመሥራት ረገድ ምን ይቀረዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- በዚህ ረገድ ከዲያስፖራው ብዙ ሥራ ነው የሚጠበቅብን ብዬ አምናለሁ ።በእርግጥ የእኛ ማህበርም ኃላፊነት አለበት፤ ሆኖም ከእኛ በላይ በተለይም የማህበረሰብ አንቂ የሆኑ የዲያስፖራ አባላት ከፍተኛውን የማስተባበርና የመቀስቀስ ሥራ ሊሠሩ ይገባል ብዬ አምናለሁ ።በተለይ ሁሉንም ሊያሳትፍና ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ መልኩ ዲያስፖራውን በአንድ ማሰባሰብና ለአገሩ በጋራ እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል ።እንደቀድሞ ኢትዮጵያዊነት የሚሰበክ፤ የአገር አንድነት እንዲኖር ማድረግ ከተቻለ ማንኛውንም የውጭ ኃይል የማናሸንፍበት ምክንያት አይኖርም ።
ብዙ ጊዜ ዲያስፖራው የሚከፋፈለው በአገር ውስጥ ካለው ፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ነው፤ እዚህ የሆነ ችግር ሲፈጠር እዚያ ሲደርስ ይጋነኑና መከፋፈልና ልዩነት እንዲፈጠር ያደርጋል ።አገር የሚለው ትልቁ ቁምነገር ይረሳና ወደተራ ነገር ውስጥ እንገባለን ።መንግሥት ይመጣል፤ ይሄዳል፤ ጥያቄው ያ አይደለም፤ ከሁሉ በላይ አገር ናት የምትቀድመው ።ተደጋግሞ እንደሚባለው በአገር ተስፋ አይቆረጥም፤ ዞሮ መግቢያችን አገራችን ናት፤ ከአገር ልንሸሽ አንችልም ።በዚህ ጉዳይ ላይ የማህበረሰብ አንቂዎች በተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጥና ዲያስፖራውን ማንቃት አለባቸው። ይሁንና ጥቃቅን ነገሮችን እያነሳን ከአገር ጋር ካያያዝን አገር ላይ የሚያሳርፈው ጠባሳ የከፋ ነው የሚሆነው ።በመሆኑም በየአመቱ ሰልፍ እየወጣን ዓድዋን ከማክበር በዘለለ በዓድዋ ስለአገር የተከፈለውን ዋጋ በማሰብ አሁንም ቂምና ቁርሾ በመተው ስለአገር ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ።ለአዲሱ ትውልድም ከአባቶቻችን የወረስነው ጀግንነትና የአገር ፍቅር ስሜትን ማስተማር አለብን ።
አዲስ ዘመን፡- የአሁኑ ዘመን ዓድዋ ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡– ዓድዋን ለመድገም የግድ በጦርነት ብቻ መሆን የለበትም ።የጦርነት ታሪክ ከመጣም መልሰን ዓድዋን መድገም ያቅተናል ብዬ አላምንም ።ግን ደግሞ አሁን ያለብን ትልቁ ተግዳሮት ድህነት ነው፤ ከዚያ በተጨማሪ አገራዊ አንድነት መፍጠሩ ላይ ያሉብን ችግሮች ናቸው ።አስቀድሜ እንደገለፅኩት ያ ትውልድ ታጥቆ የመጣን ጠላት ማሸነፍ የቻለው አንድ ስለሆነ ነው፤ እኛም አሁን በልማቱም ሆነ በአገራዊ አንድነት አንድ ሆነን ኢትዮጵያዊነትን ሊያጎላና ሊያሳድግ በሚችል መልኩ ተባብረን መስራት አለብን ።ለዚህ ደግሞ ከምንም በላይ ልዩነታችንን አጥብበን አንድነታችንን ማስፋት መቻል አለብን ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ብርሃኑ፡– እኔም አመሰግናለሁ ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም