ኢትዮጵያ ባካሄደችው ብሔራዊ የስንዴ ልማት መርሀ ግብር በመኸር፣ በበልግና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ መሆን ችላለች:: የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተለያዩ የዓለም አገራትን ድጋፍ ስትሻ የነበረችው ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አገራዊ የስንዴ ፍላጎቷን ሸፍና፣ ስንዴ ከውጭ ማስገባቷን አቁማለች፤ በቅርቡ ደግሞ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ በይፋ ጀምራለች::
የስንዴ ምርት እና የምግብ ፍጆታ ሚዛን ታይቶ ከአገሪቱ ፍጆታ የሚተርፍ 32 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ እንደሚኖር ተረጋግጦ ስንዴን ለውጭ ገበያ የመላክ ሥራው መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህ ስንዴን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ጅማሮ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ::
የምጣኔ ባለሀብት ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ የስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረብ ለወጪ ንግዱ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል:: የወጪ ንግድን መጠን ከፍ በማድረግ የአገርን ኢኮኖሚ በጠንካራ መሠረት ላይ መገንባት፣ የሕዝቡን ኑሮ ማሻሻል ይቻላል:: ተመጣጣኝ የወጪና ገቢ ንግድን ለመፍጠር ወጪ ንግዱን ከገቢ ንግዱ ማስበለጥ አልያም ማመጣጠን ያስፈልጋል::
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየርአይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሞላ አለማየሁ እንደሚሉት፤ አንድ አገር የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲኖራት፣ ለዜጎቿም የሚጠበቀውን ማቅረብ እንድትችል አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል ተመጣጣኝ የንግድ ሚዛን መኖር ወሳኙ ነው:: ይህ እንዲሆን የወጪ ንግዱ ከገቢ ንግዱ መብለጥ አለበት::
የወጪ ንግዱን የተሻለ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት:: አንደኛ አምራቹ ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ በዓለም ገበያ ምርቱን እንዲቃኝና የዓለም ገበያ ምን እንደሚፈልግ መለየት እንዲችል፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሳለጥ ያደርጋል:: እነዚህን መሠረት በማድረግ የወጪ ንግዱ ዕድገት ሲያስመዘግብ የመጨረሻ ውጤት የሆነው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ይጨምራል:: ለአምራቾችም የገበያ ፍላጎታቸው እንዲጨምር በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና በተሻለ ዋጋ መሸጥ እንዲችሉም ይጠቅማል::
ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እውን መሆን የወጪ ንግዱንና የገቢ ንግዱን ማመጣጠን ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ አገራት ለውጭ ንግድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ::
ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ደንቃራ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በየጊዜው የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ለዚህም አንዱና ዋነኛው የወጪ ንግዱን ማጠናከር መሆኑን ይገልጻሉ:: የስንዴ የወጪ ንግዱ ለእዚህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ዶክተር ሞላ ይጠቁማሉ::
የዋጋ ግሽበት በተደጋጋሚ በሚያጠቃው ኢኮኖሚ ላይ የሚመረተው ስንዴ ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ቢቀርብ ምናልባትም ግሽበቱን ሊያረጋጋውና ሊቀንስ አልያም ባለበት ሊያቆመው ይችል ይሆናል ሲሉም ዶክተር ሞላ ይናገራሉ:: መታሰብ ያለበት ግን የረጅም ጊዜ መፍትሔን ነው ባይ ናቸው:: አሁን ስንዴውን ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ማቅረብ የአጭር ጊዜ መፍትሔ እንጂ የረጅም ጊዜ ችግርን አይፈታም ሲሉ ያስገነዝባሉ::
በአገር ውስጥ ያለው የዋጋ ግሽበት እንዳለ ሆኖ ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ዘለቄታዊ መፍትሔን የሚሰጥና በርካታ እጥረቶችን መቅረፍ እንደሚያስችል ይገልጻሉ:: የወጪ ንግድ ጠቀሜታ በአጭር ጊዜ የሚታይ እንዳልሆነም ጠቁመው፣ በረጅም ጊዜ የአገር ኢኮኖሚ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያሳድግ፣ የዜጎችን ኑሮም እንደሚያሻሻል ያመለክታሉ:: ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ተገቢነት ያለውና የአገሪቷን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሠረት ላይ መጣል የሚያስችል ጅማሮ ነው ይላሉ::
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ኦርጂ እንደሚሉት፤ የወጪ ንግድ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል:: ስንዴን በስፋት ማምረት መቻሉ እጅግ እንደሚበረታታና አገሪቷን በሁለት መንገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ስንዴን ለውጭ ገበያ በማቅረቧ ከምታገኘው ገቢ በተጨማሪ ስንዴን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪም መቀነስ እንደሚያስችላት ይገልጻሉ::
እሳቸው እንዳሉት፤ የስንዴ የወጪ ንግዱ አገሪቷ ያለባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ መንግሥት የወሰደው ትክክለኛ መንገድ ነው:: ነገር ግን በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ፍጆታ ግምት ውስጥ በማስገባት የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት እንዲሁም በአገር ውስጥ ያለውን የስንዴ ምርት ፍላጎት ማመጣጠንና ገበያውን ማረጋጋት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ምርትና ምርታማነት ላይ መሥራት ያስፈልጋል::
የስንዴ ምርቱ የሕዝቡን ተጠቃሚነት አረጋግጦ የተረፈው ኤክስፖርት ተደርጎ ከሆነ መልካም ነው፤ ያ ካልሆነ ግን ሕዝብ ምርቱን ማግኘት ካልቻለ በአገሪቱ ከፍተኛ እጥረት ይፈጥራል:: ስለዚህ ጉዳዩ በልኩ ቢታይ ጥሩ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ::
የሕዝቡን የምግብ ፍጆታ ታሳቢ በማድረግ በተመጣጠነ መንገድ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ተገቢና አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰው፣ የወጪ ገበያው በአገር ውስጥ ፍላጎት ላይ ጫና እንዳያሳድር ምርትና ምርታማነት ላይ አሁን በተጀመረው አግባብ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት እየለማ ነው:: ይህም በእጅጉ የሚበረታታና የስንዴ እጥረት እንዳይከሰት የሚያደርግ ነው:: በተለይም ከዚህ ቀደም ስንዴ አልምተው የማያውቁ አካባቢዎች ጭምር ስንዴን እያለሙ መሆኑ ጅማሬው ሊበረታታ ይገባል::
በሲዳማ ክልል ለሙከራ ሰባትና ስምንት ቦታዎች ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን መመልከታቸውን ፕሮፌሰሩ በአብነት ጠቅሰው፣ በዚህ ልክ በየአካባቢው ከተሠራ የአገር ውስጥና የውጭ ገበያውን መሸፈን እንደሚቻልና በአገር ውስጥ የሚታየው የስንዴ እጥረት በቀጣይ እንደማይከሰትም ያመለክታሉ::
በበጋ መስኖ እየለማ ካለው ስንዴ በተጨማሪ የተለያዩ የግብርና ልማቶችን በሲዳማ ክልል አይቻለሁ የሚሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ አርሶ አደሩን በማንቃት፣ በመደገፍና በማበረታታት የወጪ ንግዱን ማሳደግ ይቻላል ይላሉ:: አርሶ አደሩም ከምርቱ ተጠቃሚ ሲሆን በራስ ተነሳሽነት ስንዴም ይሁን ሌሎች ምርቶችን በስፋት ያመርታል:: ይህም የምግብ እጥረትን ከመቀነስ ባለፈ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ያስችላል ሲሉ ያብራራሉ::
ይህን የእሳቸውን ሃሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ የሰጡት ዶክተር ሞላ በበኩላቸው የኤክስፖርት ንግዱን ለማጠናከር ከስንዴ በተጨማሪ ሌሎች ምርቶችንም ወደ ኤክስፖርት ማስገባት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ:: ይህም ኢኮኖሚው አስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲመሠረት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረው፣ ሌሎች አገራትም ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እንደቻሉ ነው ያስረዱት::
ዶክተር ሞላ እንዳሉት፤ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ የዋጋ ግሽብት ያጋጠማቸው አገራት ለአብነትም ጀርመን እንዲሁም ጃፓን ችግሩን መፍታት የቻሉት ኤክስፖርት መር የሆነውን ኢኮኖሚ መገንባት በመቻላቸው ነው:: ይህን ተከትሎም እነዚህ አገራት ጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ በመድረስ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል:: አገራቱ ወደ እዚህ ደረጃ የደረሱት በአጭር ጊዜ መፍትሔ ወይም እሳት በማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምደው አይደለም፤ በዚያ መንገድ ተጉዘው ቢሆን አሁን የደረሱበት የዕድገት ደረጃ ላይ አይደርሱም ነበር::
የእንግሊዞች ታሪክም የሚያሳየን ይህንኑ ነው የሚሉት ዶክተር ሞላ፤ እንግሊዞች ‹‹ሁላችንም ለአንድ ዓመት እንራብ፤ ከዚያ በኋላ ግን ረሃብ አይነካንም›› በሚል ስትራቴጂ ተነስተው ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ይጠቅሳሉ:: በኢትዮጵያም በአገር ውስጥ አጋጥሟል የተባለውን የስንዴ እጥረት ታግሶ በማለፍ እንደ እንግሊዞቹ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ላይ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ:: ይህን መሰል ስትራቴጂ መከተል ካልተቻለ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት እንደማይቻል ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያም ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንዲህ ዓይነት ልምድ ማዳበር ይኖርባታል ብለዋል::
‹‹የስንዴ የወጪ ንግዱ ጠንካራ የምጣኔ ሀብት እንዲገነባ መሠረት ይጥላል ›› ያሉት ዶክተር ሞላ፤ ይህን መሠረት ማጽናትና በቀላሉ እንዳይናጋ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ:: ለችግሮች ጊዜያዊ መፍትሔ እየሰጡ መጓዙ መሠረቱ የጸና ኢኮኖሚ መገንባት እንዳላስቻለም አስታውቀው፣ በኢኮኖሚው ጠንካራ መሠረት ለመጣል የወጪ ንግድን ተወዳዳሪ ማድረግ፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ መሆኑን ያመለክታሉ:: ይህም ኢኮኖሚውን በአስተማማኝ መሠረት ላይ መጣል ከማስቻሉም ባለፈ በየጊዜው የሚፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚያስችል አስረድተዋል::
ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንደተናገሩት፤ በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ፍጆታ በማረጋገጥ ትርፍ ምርት ሲኖር ኤክስፖርት በማድረግ የአገርን ኢኮኖሚን መገንባት ይገባል:: ለዚህም ተግባር አገሪቷ ሰላም መሆን ይኖርባታል:: አገሪቷ ሰላም አግኝታ ከሠራች ለምና በተፈጥሮ የታደለች በመሆኗ ትለወጣለች፤ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል:: ሰላሟን በማስጠበቅ በአገሪቷ ተጠናክሮ የቀጠለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው በማስቻል ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይቻላል::
ዶክተር ሞላም በሰላም ፋይዳ ላይ የፕሮፌሰር ብርሃኑን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀሳብ ጠቅሰዋል:: ኤክስፖርቱ ዘላቂ እንዲሆን መሥራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀው፣ ስንዴን ለውጭ ገበያ የማቅረቡን ሥራ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ሰላም ወሳኝ እንደሆነ በማመን ጠንክሮ መሥራት የግድ ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ:: ለዚህም መንግሥት፣ ባለሀብቱና አምራቹ የየድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ባይ ናቸው::
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻ፤ ስንዴ አምራች አካባቢዎችን እየለዩ በዚያ ላይ እየጨመሩ መሄድና መረጃዎችን በማጥናት የዓለም ገበያ ምን ዓይነት ጥራትና ምርት ይፈልጋል፤ የማምረት ዘዴው በምን መልኩ ይሁን፣ ወዘተ. የሚለውን በመለየት ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲሁም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የስንዴ ልማቱንና የወጪ ንግዱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይቻላል::
በስንዴ ኤክስፖርት ንግዱ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ባሉ አካላት ላይ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ አስፈላጊነትንም ዶክተር ሞላ ይጠቅሳሉ:: አርሶ አደሩ ባቀረበው ምርት ነጋዴዎች የበለጠውን ድርሻ የሚወስዱና ተጠቃሚ የሚሆኑ ከሆነ ገበያው ቀጣይነት ሊኖረው እንደማችልም ነው ያመለከቱት::
ዶክተር ሞላ በኤክስፖርት ንግዱ የሚገኘው ገቢ ፍትሐዊ ስርጭት ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁመው፣ ይህም ቀጣይነቱ ላይ ጉልህ አዎንታዊ ድርሻ እንዳለው ይናገራሉ:: አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ሲሆን በቀጣይ ያለማንም ገፊ በራሱ ተነሳሽነት እንደሚያመርት በመግለጽ በተለይ የሚመለከታቸው አካላት ለቀጣይነቱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል::
ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ገበያ የመላክ የማስጀመሪያ መርኃ ግብር በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መጀመሩ ይታወሳል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባሌ ላይ የተጀመረው የስንዴ ኤክስፖርት ለኢትዮጵያ መደረግ ከሚገባው ትንሹ ስኬት እንደሆነ ገልጸው፤ ‹‹የምናደርገውንና የምናቅደውን በተግባር በአረንጓዴ አሻራና በህዳሴ ግድብ እያሳየን መጥተናል፤ አሁን ደግሞ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ከማቆም ባለፈ ስንዴን ወደ ውጭ በመላክ ያሰብነውን በተግባር ፈፅመን ለኢትዮጵያውያንና ለዓለም አሳይተናል›› ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የኤክስፖርት ኮሚቴው አስተባባሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ የማቅረቡ ሂደት በተጀመረበት ወቅት እንዳሉት፤ የስንዴ ምርት እና የምግብ ፍጆታ ሚዛን ታይቶ በዘንድሮው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል::
እስከ ቅርብ ጊዜ ባለው መረጃ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ከስድስት ገዥዎች ጋር ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ የ3 ሚሊዮን ኩንታል ውል መፈረሙን መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃ አመልክቷል። የረድኤትና ሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን በአገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት እየተፈረመ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል። የስንዴ የወጪ ንግዱ የሎጂስቲክስና የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱ ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ ታምኖበታል::
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በእርዳታ የምትቀበለውን ስንዴ ጨምሮ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ታስገባ ነበር:: ከውጭ ለሚገዛ ስንዴም በየዓመቱ እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ስታደርግ ቆይታለች::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም