« ቆሞ ቀር ሰው ለቀብር አያስቸግርም፣
የቋንቋችን ገለጻ ስፋትና ጥልቀት በእጅጉ ያስደንቃል።አንዱ ማሳያ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ጥንታዊ አገርኛ ብሂል ነው።ምሳሌያዊ አነጋገሩ የተሸከመው መልዕክት በአንድ ትርጉም ብቻ የሚበየን ሳይሆን በርከት ባሉ የአንድምታ ፍቺዎች የሚብራራ ነው።«ቆሞ ቀር» ማለት አንድም በጋብቻ የ«ውሃ አጣጭ» አቻ ያጣ/ች ማለት ነው።አንድም፡- አስተሳሰቡ የሻገተ ማለት ሲሆን፤ አንድም፡- የአቅሙን ያህል ተንቀሳቅሶ ሕይወትን ከማሸነፍ ይልቅ ቆሞ በማላዘን ዕድሜውን የሚፈጅ መንፈሰ ልል ሰብዕና የተላበሰ ማለት ነው።አንድም፡- የዛሬና የነገን ተስፋ ገድሎ የትናንትን ጀንበር ካልሞቅሁ ብሎ ከራሱ ጋር ጠብ የተጋባ ማለት ነው።
«ቆሞ ቀር ሰው» ለቀብር ያለማስቸገሩም «ዕድሜውን» ያለ ፍሬና ያለ ውጤት ገብሮ ስለሚኖር አንድ ቦታ ተገትሮ «የቆመበት» መሬት ሠርጉዶ ስለሚጎደጉድ ለመቃብር ቆፋሪዎች ሥራ ያቀላል ማለት ነው።ከበርካታ የአንድምታ ትርጉሞች መካከል መጥነን ይህንን ያህል ቆነጠርን እንጂ የብሂሉን ይዘት ፈታ አድርገን እናብራራ ካልን አድማሱ ይለጠጣል።ይህ ጽንሰ ሃሳብ የውሎ አምሸቶ ሕይወታችንንና ኑሯችንን እየፈተሽንበት ወደ ኋላ ግድም ዘርዘር ተደርጎ በአግባቡ ይብራራል።
የጠበበችው ዓለማችን፤
ኸርበርት ማርሻል ሚክልሃን (ከ1911 – 1980) ዓለም አቀፍ እውቅናን ያተረፉ ካናዳዊ የኮሚዩኒኬሽን የዕውቀት ዘርፍ ተመራማሪ ሳይንቲስት ነበሩ።እ.ኤ.አ በ1962 እና በ1964 ዓ.ም በጻፏቸው ሁለት መጻሕፍት ውስጥ “Global Village” የሚል የዕውቀት መገለጥ ለዓለማችን አስተዋውቀዋል።የፍልስፍናው ዋና ይዘት «ይህ ልኩ» ተብሎ ስፋትና ወርዱን ለመግለጽ የማይደፈረውን የአጽናፈ ዓለማችንን ዕድሜ ጠገብ አመለካከት በመሻር «ዓለማችን እንደ አንድ መንደር መጥበቧን» ያመላከተ የምርምር ውጤት ነበር።
የዚህ ፍልስፍናቸው እውነታነት ፍንትው ብሎ መረጋገጥ የጀመረው ዘመነ ግሎባላይዜሽን ሰፊዋን ዓለማችንን እንደ አንድ ጠባብ መንደር ማቀራረቡ እየተገለጠ መሄድ ሲጀምር ነው።መቀራረቡ በአካል ሳይሆን በአስተሳሰብ ቁርኝት ነው።ሰበበ ምክንያቱ ደግሞ ያለንበት የዲጂታል ዘመን የወለደውና በአግባቡ ለማስተዳደርና ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆነው የነባሩ ሚዲያና የአዲስ መጤው የሶሻል ሚዲያ በረከተ መርገም ትሩፋትና ጦስ ነው።
የዓለማችን መጠነ ዙሪያ እንደ ትንሽ መንደር ከመጥበቡና የሕዝቦች የአስተሳሰብ ቁርኝት እጅግ ከመቀራረቡና ከመሳሳቡ የተነሳ «ኢንተርኔትና የማኅበራዊ ሚዲያ ባይኖር ኖሮ ሕይወት በተለመደው ዑደት እንደምን ሊቀጥል ይችል ነበር?» በማለት በርካቶች ያለ ቴክኖሎጂ የተኖረባቸውን የቀድሞዎቹን የሌጣ ሕይወታችንን የአኗኗር ዘይቤዎች በመዘንጋት ጥርጥር ላይ እስከ መውደቅ ደርሰዋል።
ይህ ዘመነ ግሎባላይዜሽን ዓለምን በተራቀቁ የተክኖሎጂ መረቦች አቆላልፎ ወደ አንድ አስተሳሰብ ቋት ውስጥ ለመክተት ተግቶ እየተሠራበት ስለመሆኑ እጅግም ማብራራት ላያስፈልግ ይችላል።የጥልፍልፉ መርቀቅ ፈጣሪውን የሰውን ልጅ ሳይቀር የዕውቀት አቅም እየተፈታተነ ለቁጥጥር እስከ ማዳገት ደረጃ ደርሶ ከእጁና ከአቅሙ በላይ አፈንግጦ መውጣቱንም በብዙ ማስረጃዎች ማሳያት ይቻላል።
ጥቂት እናፍታታው፡- በተራቀቁ የዓለማችን የኮሚዩኒከሽን መረቦች አማካይነት በየሰከንዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መረጃዎችና ዕውቀቶች፣ አስጨናቂ ክፋቶችና እርኩሰቶች፣ የሃሰት ወሬዎችና ተዓማኒ ዜናዎች፣ የግለሰብ የድምጽና የምስል ገመናዎች፣ የቡድን ምሥጢሮችና የአገራት ጓዳ ጎድጓዳዎች ወዘተ. ሲሰራጩ፣ ሲብጠለጠሉ፣ ሲተነተኑና ሲነገዋለሉ የሚውሉት «ሃይ ባይ» እረኛ በሌላቸውና በጣታችን ጥቆማ ብቻ በሚተገበሩ የማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ነው።
«የግሌ» እየተባለ በራስ አመለካከት ብቻ ማሰብ እስከሚያዳግት ድረስ ነገሮች ሁሉ አደባባይ ሲሰጡ ስናስተውል የነገው ሕይወታችን ምን ሊመስል እንደሚችል ማሰቡ ያናውዛል:: እንደ ቀዳሚ ዘመናት በኤሮግራምና በፖስታ መልዕክት መላላክና «ቀጭኑን ሽቦ» እያወደሱ «በስልክ አነጋግረኝ/አነጋግሪኝ» እየተባባሉ ናፍቆትን መገላለጽና መልዕክት መለዋወጥ ቀን መሽቶባቸው ወደ ዳር እየተንገዋለሉ በመሄድ ላይ ናቸው።በደቂቃዎች ውስጥ መቀመጫን «እንቶኔ» አገር አድርጎ «እከሌ» ወደሚባሉ አገራት በመስፈንጠር ከመረጃ ቋታቸው መረጃን መበርበር፣ ኢንፎርሜሽን መመንተፍና መልሶ ማሰራጨት «የውሃ መንገድ» ከሆነ ሰነባብቷል።
«ምሥጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም» የሚለው ነባሩ ብሂል ትርጉሙም ፋይዳውም ዋጋ እስከ ማጣት እየደረሰ ነው።ምክንያቱም ዓለማችን እየከነፈች ያለችው የማራቶን ሯጮችን ጫማ ተጫምታ ወይንም የንሥር ክንፍ ተውሳ ሳይሆን እየተመነጠቀች ያለችው በብርሃን ፍጥነት ስለሆነ ነው።
ይህ ረቂቅ የቴክኖሎጂ ዘመን ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን፣ አገራትንና አህጉራትን በውድም ይሁን በግዴታ አቆራኝቶ አስተሳስሯቸዋል።ደስታና ኀዘን፣ ምሬትና ብሶት፣ ክፉም ይሁኑ ደግ የዓለም አቀፍ ሺህ ምንተ ሺህ ክስተቶች እንደ እብቅ በመላው ዓለም እየተዘሩ ውለው የሚያድሩት በአውሎ ነፋስ ፍጥነት ቴክኖሎጂውን እየጋለቡ ነው።
የዘመንን ዱካ የናቀ፤ በራሱ ሃሳብ የታነቀ፤
ማንኛውም ዘመን ይወቀስም ይወደስ የአውራሽነቱ ባህርይ ግን በፍጹም አይለወጥም።ዘመን ይታመንም ይጠርጠር የነበረውን አስተላልፎ፣ ያከማቸውን ዘርግፎ ለቀጣዩ ትወልድ ማድረሱ የግድ ነው።ነፍሰ ሄሩ ደራሲያችን ከበደ ሚካኤል «አዝማሪና የውሃ ሙላት» በሚለው ግጥማቸው ውስጥ «ብልህነት የጎደለው» አንድ አዝማሪ የተገለጠበት ግጥማዊ ትረካ ለዘመናችን ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
አዝማሪው መሰንቆውን እየገዘገዘና ድምጡን እያሳመረ ወንዙ ዳር ቆሞ ያንጎራጉር የነበረው ምናልባት ወንዙ ልቡ ራርቶ እንዲያሻግረው በመመኘት ነበር።እንዲህ በማለት፡-
«አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት፣
እያሞጋገስኩኝ በግጥም ብዛት፣
አባብለዋለሁ እስቲ ምናልባት።
የአዝማሪውን «ቅን ልብ» ያስተዋለ ሌላ መንገደኛ ለዚያ ምስኪንና የዋህ ዜመኛ የመለሰለት መልስ በቂልነቱ እየተሳለቀ በማፌዝ ሳይሆን ትህትና በሚስተዋለበት ብልህ የመምህርነት ችሎታ ነበር።እንዲህ በማለት፡-
ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማሞገስ፣
ግን እንደዚህ ፈሶ በችኮላ ሲፈስ፤
እስቲ ተመልከተው ይህ አውራረድ፣
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፤
ድምጡን እያውካካ መገስገሱን ትቶ፣
ማን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ።
እነዚህ ጥቂት ስንኞች ብዙ ቁምነገሮች አጭቀው ይዘዋል።መጪና ሂያጁ በማይለይበትና ነገሮች ሁሉ በቴክኖሎጂው ጎርፍ እየተጥለቀለቁ እያስተዋልን በወጀቡ መካከል ቆምን «የእኔን ሃሳብ ብቻ ካልካደማችሁ» ብለን ብንሞግት ወይንም ብንሟገት ብልጠት ሳይሆን ጅልነት ነው።
የሰው ልጅ ቅርርብ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ እየገሰገሰ ባለበት በዚህ ፈጣን ዘመን ነገሮችን መመርመር የሚቻለው በተረጋጋ መንፈስና ቀልብ በመግራት፣ የሌሎችስ ሃሳብ ምን ይመስላል? እኔ ከሌሎች ምን ልማር እችላለሁ? ሌሎችስ ከእኔ ምን ይማራሉ? ወዘተ. በማለት ልበ ክፍት ሆነን ነገሮችን በጥበብ እስካልመራን ድረስ «የእኔ» ብቻ ትርፉ፤ «ከእኛነት» እውነታ ጋር ተጋጭቶ ተሸናፊና ቆዛሚ መሆናችን አይቀርም።«እኔነት» «በእኛነት» እስካልተመዘነ ድረስ ስኬትም ሆነ ውጤት እጅግም ላይረባን ይችላል።
«ቱባ ባህሌ፣ አይደፈረው ወጌና ቋንቋዬ፣ ለእኔ ብቻ ተለይቶ የተሰጠኝ ታሪኬና ማንነቴ ወይንም የተፈጥሮ ሀብቴ ወዘተ.» የሚባሉት «መኩሪያና መመኪያዎቻችን» እንደነበሩ ውለው፣ እንደነበሩ ማደር የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆናቸውን በነጋ በጠባ እያስተዋልን ነው:: የእኛ ብቻ የምንላቸው ብዙ ጉዳዮቻችን ልንቋቋማቸው በማንችላቸው ተግዳሮቶች ሲፈተኑ ስናይ በቸልታ ልናልፋቸው አይገባም። የሚሻለው የራስን ውበት ማድነቅ ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም መዓዛ ለማሽተት «ቸር» መሆን ነው።
«አትድረስብኝ አልደርስብህም»፣ «አንተም በክልልህ እኔም በገደቤ» እየተባባልን የምንገፋፋባቸው «የግሌ/ የግላችን» የሚሰኙ «መፎከሪያዎቻችን» እንደምንመኘውና እንደምንጓጓው ከእኛነታችን ጋር «በቱባ» ባህርያቸው ቢሰነብቱ ባልጠላን፤ ነገር ግን ዘመኑ ሊፈቅድልን ስላልቻለ የሚሻለው የ«አንተ ትብስ እኔ እብስ» ፍልስፍናን በመተግበርና በመደጋገፍ መገስገስ ብቻ ነው።እንደ ምስኪኑ አዝማሪ «ይህንን ጋላቢ ፈረሰኛ ዘመን» እየሸኘን የምንቀበለው በአንድ አስተሳሰብ ላይ ተቸክለን ቆመን ብቻ ከሆነ ትዝብቱ የሚተርፈን ከሌሎች ብቻ ሳይሆን ከኅሊናችንም ጭምር ነው።
ቅዱስ መጽሐፍ «ዘመኑን ዋጁ እንጂ ሞኞች አትሁኑ» (ኤፌሶን 5፡17-18) ብሎ የመከረን ከዘመናት በፊት ነው።ዓለም ከመቼውም ዘመናት ይልቅ እጅግ እየጠበበች ስትሄድ የሰዎች አስተሳሰብም የዚያኑ ያህል እየሰፋና እየላቀ መሄዱ እሙን ነው።ከዘመኑ ፍጥነት ጋር በእኩል ደረጃ «ዘመኑን እየመረመርን» ጎን ለጎን እየተጋፋን መሄድ ባንችል እንኳን በአቅማችን ልክ ሱክ ሱክ ለማለት መሞከር በራሱ ብልህነት ነው።
መራር አገራዊ እውነቶቻችን፤
የዘመኑ ሩጫና ፍጥነት፣ የቴክኖሎጂው ምጥቀትና ርቅቀት ምሥጢር የገባቸው አገራትና ሕዝቦች ወደ አንድ እየተሰባሰቡ፣ ሪሶርስ እየተከፋፈሉ፣ «እኔ ዘንድ ይህ አለ፤ አንተ ዘንድ ምን አለ?» እየተባባሉ ለመኖር በሚገደዱበት በዚህ ወቅት በእኔዋ «ሀገር» ጓዳ ውስጥ ግን ግለኝነት ሰፍኖ፣ የእኔነት ፈርጥሞ፣ በአትድረሱብኝ አልደርስባችሁ ፍልስፍና «ራስ ሲመለክ፤ የራስ ብቻ ሲወደስ» መመልከት ምንኛ አያሳዝን።
በራስ ጎጥ ውስጥ «ዋሻ» ገንብቶና ራስን ብቻ እየካቡ በመኖር «ለራስ ብቁ መሆንን ለማሳመን መሞከር» ብልህነት ተብሎ የሚታሰብ ዘዴ ሳይሆን ከራስ ጋር ጠብ ፈጥሮ የመኳረፍ ያህል የከፋ ነው።«ቋንቋን» ማክበርና ማድነቅ ተገቢ ነው።«ባህሌ» እያሉ በራስ ነገር ማጊያጌጥና መኩራራት ምንም ክፋት ባይኖርበትም የሌላውንም ውበት ማድነቅና ማዳመቅ ግን የአስተዋይ ሰው ባህርይ ነው።
«የእኔ ዙሪያ ገብ በበረከት ተትረፍርፏል፣ የአንተ እና የእናንተ ግን…» ብሎ የተቃርኖ አዋጅ ማወጅና ማሳወጅ ግን የአስተሳሰብ ጉድለት ጭምር ነው።«በእኔነት ትምክህት» ተለብጦ ሌሎችን ዝቅ ማድረግ፣ ራስን ተራራ ላይ ሰቅሎ ሌሎችን ወደ ሸለቆ ማመልከት ተገቢ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን «የዝቅተኝነት» ስሜት ተጠቂ የመሆን ምልክትም ስለሆነ ቆም ብሎ ማሰቡ በእጅጉ ይጠቅማል።
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ በብዙኃን ባህሎች ውበት የደመቀች፣ የበርካታ ቋንቋዎች ባለቤትና ገና ያልተነኩ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ሀብቶች ባለጸጋ መሆኗ በሚገባ ይታወቃል።ይህ ሁሉ መደነቂያዋ ሊደምቅና ሊፈካ፣ ለበረከትና ለአብሮነት ጥቅም ሊውል የሚችለው ዜጎቿ እርስ በእርስ ተፋቅረው፣ እርስ በእርስ ያላቸውን እየተከፋፈሉ ሲኖሩ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋርም ቢሆን “Win-Win እንዲሉ” በፍቅርና በመደጋፍ በጋራ መኖር ሲቻል ብቻ ነው።
«እኔ ለራሴ ብቁ ነኝ፣ የማንም ድጋፍ አያስፈልገኝም፣ በራሴ ዛቢያ ላይ እየተሽከረከርኩ መኖር አያቅተኝም ወዘተ.» የሚሉ የግለኝነት መገለጫ እብሪቶች፣ የማንአለበኝነት መኮፈሽያ ትምክህቶች ይመስናል እንጂ ሩቅ ሊያስኬዱን አይችሉም።ዓለም ወደ አንድ መንደር እየጠበበች በምትገሰግስበበት በዚህ ዘመን፣ አመለካከትን «በእኔነት» ሼል ውስጥ ለመሸሸግ መሞከር ትርፉ «ዜሮ»፣ ውጤትም «ምንም» መሆኑ በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባል።ዕለት በዕለት እየጠበበች በምትሄደው ዓለማችን ውስጥ ስንኖር አስተሳሰባችን እንዲሰፋ ጥረት ካላደረግን በስተቀር ተቸክለን የቆምንበት መሬት ሊከዳን ስለሚችል ደጋግሞ ማሰቡ አይከፋም።ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም