ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በአፍሪካ በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ መሆኗ ይታመናል። እ.ኤ.አ በ1921 የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በወቅቱ ልዑል ተፈሪ መኮንን የሚመራ የብሪታኒያ ንጉሣዊ አየር ኃይልን የመጎብኘት ዕድል አጋጠመው።ይህም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በኢትዮጵያ የማስተዋወቅን ሐሳብ ተፈጠረ። ተፈሪ እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት «ፖቴዝ-25»የተባለ የመጀመሪያው አውሮፕላን ከጅቡቲ ተነስቶ ከአምስት ሰዓት በኋላ ነሐሴ 1929 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ«ገፈርሳ» ተብሎ በሚጠራው ቦታ አረፈ። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂን መጀመሩን ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በዘመናት ውስጥ አልፏል። ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ያለው አንጋፋ ተቋም ሲሆን፤ በአዋጅና መመሪያዎች መሠረት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚካሄዱ በረራዎች በዋናነት ኃላፊነቱን ይወስዳል። በዛሬው ተጠየቅ አምዳችን ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ጋር ቆይታ እናደርጋለን።
ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ ረጅም ልምድ ያካበቱ ናቸው። የተወለዱት ጎንደር አዘዞ የሚባል ከተማ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከቤልጂየም አግኝተዋል።በሥራ ዓለም የአማራ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። በትራንስፖርት ሚኒስቴር 10 ዓመታትን ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል።በመንግሥት ልማት ድርጅትም ለሁለት ዓመታት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሠርተዋል። በካናዳ በሚገኘው በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው ለአራት ዓመታት ሠርተዋል።በዛሬው ቆይታችን ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ሥራ እንቅስቃሴ እና ተያያዥ ተግባራት እንቃኛለን-መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አቪዬሽንን ታሪክና የመጣበትን ሂደት እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ጌታቸው፡– የመጣንበት መንገድ በጣም ጥሩ ነው።እኔ ለብዙ ዓመታት በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ስለቆየሁ ሁኔታዎችን ለመረዳት አግዞኛል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ ሆኜ በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሎም የሲቪል አቪዬሽንን የመምራት ዕድል ነበረኝ። የቦርድ አባልም ነበርኩ። በዚህ ውስጥ የተረዳሁት ግን ዘርፉ ገና አልተነካም።በአየር ትራንስፖርት ያሳካውን ትልቅ ዕድገት በሌሎች አቪዬሽን መስኮች ማሳካት እንደምንችል ተረድቻለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያሉን ኤርፖርቶች በአቪዬሽን ባለስልጣን እይታ ምን ይመስላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አራት ዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጣቸውን ጨምሮ 22 መደበኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ኤርፖርቶች አሉን።በቁጥርም ይሁን ከሚሰጡት የአገልግሎት አድማስና ቅልጥፍና አኳያ ሲታዩ በበቂ መጠንና ሁኔታ ላይ ሆነው አይገኙም። ከእነዚህ በተጨማሪ በጣት የሚቆጠሩ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች (Airstrips) ለሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ማዕድን ለማውጣት፣ ለግብርና፣ ለመዝናኛ፣ ለአምቡላንስ ወይም ለሕክምና አገልግሎትና ሰብዓዊ አገልግሎቶችና ሌሎች ተግባራትንም በመስጠት ላይ ናቸው።
የአውሮፕላን ማረፊያ ስፍራዎች ማስፋፋት፤ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ማሳደግ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን እና በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶችን በአስተማማኝና በጥራት ለማመላለስ የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ ነው። የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስኮች መስፋፋትና መመንደግ የሚኖራቸው አበርክቶ እጅግ በጣም ትልቅ ነው። የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ ወሳኝ ነው። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ያሉን ኤርፖርቶች አገልግሎት በሚጠበቀው ደረጃ ያደገ ባይሆንም በርካታ ተስፋ ሰጪ ነገሮች አሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብቻው የተመለከትን እንደሆነ ደግሞ በጣም ጥልቅ ደረጃ የሚሰጠውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን አቪዬሽን ታሪክ ሲታይ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያውያን በነፃነት በራሳቸው ባለሙያና አቅም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን እየመሩና እያስተዳደሩ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በጣም ወደኋላ የቀረንባቸው ዘርፎች ስለመኖራቸው ይነገራል።እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ ጌታቸው፡- ወደኋላ ቀርን የሚለው እንዳይምታታ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል። በአየር ትራንስፖርት መስክ ከፍተኛ ለውጥ አለ። በአቪዬሽን አካዳሚ እና በሬጉላቶሪ ትልቅ እምርታ አለ።ግን እነዚህን በሚደግፉ ላይ የሚቀረን ነገር አለ። በጥገና ብንሄድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱን አውሮፕላኖች የሚጠግንባቸው መዳረሻዎች በጣም በርካቶች ናቸው። ችግር እየተፈጠረ ያለው ለጀነራል አቪዬሽን የሚሆን የጥገና አገልግሎት ነው። በዚህ ዘርፍ በሀገር ውስጥ አቅም አልተፈጠረም። በአንድ በኩል ጀነራል አቪዬሽን በደንብ አልተጠናከረም፤ ትንሽ ናቸው። ወደ ጥገና ኢንዱስትሪ ለመግባት ደግሞ የአውሮፕላን ብዛት ወሳኝ ነው፡፡
ሌላው ወደዚህ ሥራ ለመግባት፤ ይህን የሚያስተናግድ በቂ የአሠራር ሥርዓት አልነበረም። አሁን ብዙ ኦፕሬተሮች እንዲገቡ እያደረግን ነው። በዚያው ልክ ለኦፕሬተሮቹ የሚሆኑ አገልግሎቶች የሚሰጥበት ዕድል መፍጠር የግድ ነው። አሁን የጥገና አገልግሎት ላይ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንዲገቡበት እያደረግን ነው። ባለሃብቶችም ‹‹ሃንጋርድ›› ሠርተው የሚገቡበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው።እነዚህ ጉዳዮች ተሸፍነው የቆዩ ናቸው። ለምን ከተባለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ ስለሚንቀሳቀስ ሌሎች መስኮች ላይ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ለኦፕሬተሮች ጥሪ አቅርባችኋል።ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ለነበሩ ኦፕሬተሮች ለምን ቀና መልስ አልተሰጠም?
አቶ ጌታቸው፡- በኤርፖርት ልማት ላይ ገፍቶ የመጣ ጥያቄ የለም። አሁን እኛ እየጠየቅን ነው። በመሠረቱ ይህ ሥራ የሚገመተው የመንግሥት ተብሎ ነበር።ነገር ግን ሥራው አሁን የግል ባለሃብቶች ከተማ አስተዳደሮች፤ የክልል መስተዳድሮች እና የፌደራል መንግሥት በጋራ የሚሠሩት ነው። ከዚህ በፊት ነበረው በጀነራል አቪየሽን ላይ የነበረ ሲሆን አዲስ ጥሪ አያስፈልግም። አሁን እየተመቻቸ የመጣ ምሕዳር ስላለ መጠቀም ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ባለሃብቶችን ‹‹ኤርፖርት አልሙ›› ብሎ በዚህ ወቅት ጥሪ ማቅረብ የታሰበውን ለማሳካት ያስችላል?
አቶ ጌታቸው፡- ሁሉም የኢንቨስትመንት ቅድመ ሁኔታዎች ቀዳሚ ሰላማዊ ሁኔታዎች ናቸው። ከዚህ አኳያ እዚህም እዚያም የሚታዩት የሰላም ችግሮች ተፈትተው እና ተረጋግተው የሚቀጥሉ ይሆናል፤ ይህ ውጪውን ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያግዛል ብለን እናምናለን። ኤርፖርትን መገንባትን በተመለከተ ይህ ትልቅ መሰናክል አይሆንም። ግንባታቸው በብዛት ከተማ አካባቢ የሚገነቡ በመሆናቸውም የሰላም ሁኔታው ያን ያክል አሳሳቢ የሚሆን አይደለም። ነገር ግን ማንኛውም ኢንቨስትመንት መነሻ እና መዳረሻው ሰላምና መረጋጋት መሆኑን በማሰብ ሰፊ ሥራ መጠየቁ አይቀርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቱሪዝምን ዕድገት ከማገዝ አኳያስ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- የአየር ትራንስፖርት በመሠረቱ ብዙ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮችን ይነካካል። ንግድ፤ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ላይ ጉልህ ድርሻ አለው። ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች መጓጓዣቸው በአውሮፕላን ነው።ይህ ከሌለ እና በሰፊው ካላደገ ቱሪስት አይኖርም። ኢትዮጵያ ደግሞ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ትልቅ ውጥን አላት። ይህን ለማሳደግ አየር ትራንስፖርት መዘመንና ማደግ አለበት።ለዚህ ደግሞ መዳረሻ ቦታዎችን ማስፋት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት 128 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉን።በዚህ ዓመት ደግሞ ከስምንት ሀገራት ጋር የአየር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት አድርገናል። በቀጣይም እያሰፋን እንሄዳለን። የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች 22 ናቸው፤ ግን በቂ አይደሉም። በመሆኑም ይህን ለማሳደግ ባለሃብት በሰፊ መሳተፍ አለበት።በዚህ መስክ የሚሳተፍ ካሉ ለማገዝ ዝግጁ ነን። እነዚህ እያደጉ ሲሄዱ ቱሪዝም ያድጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ለባለሃብቶች የሚቀርበው ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝና በርካታ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪው ሲገቡ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ድርሻ አይሻሙም?
አቶ ጌታቸው፡- ዋናው እንደ ሀገር እና መንግሥት የሚፈልገው ኢኮኖሚው የሚደግፍ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ማስቻል ነው።አገልግሎቱ በማን በኩል ይሰጥ የሚለው ሁለተኛው ጥያቄ ነው። ለዚህ ስትራቴጂክ የሆነ ብሔራዊ የበረራ ‹ኬረር› ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ ማጠናከር በጣም ስትራቴጂክ ጉዳይ ነው።ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ በተለይም በአፍሪካ በጣም ያልተነካ ዘርፍ ነው።ገበያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በላይ ነው።አፍሪካ በዓለም አጠቃላይ በረራ ያላት ድርሻ ሦስት ከመቶ በታች ነው።በመሆኑም እነዚህ ወደ ገበያ ሲመጡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለፉክክር ሳይሆን በትብብር የሚሠሩና እጥረቱን የሚያሻሽሉ ይሆናሉ። በእርግጥ ፉክክር ቢኖርም ለአገልግሎቱ መፋጠንና ጥራት መጨመር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል::
በአፍሪካ ያልተነካ ገበያ አለ።ባለሃብቶች በተለይም በሀገር ውስጥ በረራ መሳተፍ ስለዚህ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ወደ ፉክክር የሚያስገባ ሳይሆን ሥምና ዝናውን ለማስጠበቀም ያግዛል፤ እንደ ሀገርም ተጠቃሚ ያደርጋል። በመሆኑም የኢትዮጵያን አየር መንገድ ፍላጎት የሚነካ ብዙ ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዘርፉ ለሚሳተፉ ባለሃብቶች የመንግሥት ድጋፍ እስከ ምን ድረስ ነው?
አቶ ጌታቸው፡-የኤርፖርቶች ማደግ ኢኮኖሚውን ትርጉም ባለው ደረጃ ይደግፋል።ለዚህም ባለሃብቶችን ለመደገፍና ለማሳተፍ እንሠራለን፤ እየሠራንም ነው። የአየር ትራንስፖርት ተደራሽ ነው ሲባል በተወሰነ ርቀት ኤርፖርት መኖር እና ትራንስፖርት ማግኘት ነው።እኛ ያሉን 22 ኤርፖርቶች ናቸው።ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡
ያሉን ኤርፖርቶች ካለን ሕዝብ ብዛትና መልክዓ ምድር ስፋትም አኳያ በቂ አይደሉም።በመሆኑም ባለሃብቶች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የክልል መንግሥታት በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ ጥረት እያደረግን ነው። እኛ ወደዚህ ልማት የሚገቡትን ባለሃብቶች ካሉ የቴክኒክ ድጋፍ እናደርጋለን። እስካሁን ስምንት ባለሃብቶች በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ ባለሙያዎች ልከን አስፈላጊነቱን ከማየት ጀምሮ ድጋፍ አድርገናል።በቀጣይም ሌሎች ሲመጡ ድጋፍ ማድረጋችን እንቀጥላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከሚቀርቡ በርካታ ጥያቄዎች ኤርፖርት እንዲገነባ ፍላጎት ያላቸው በርካቶች ናቸው።በአሁኑ ወቅት ደግሞ አብረን እንሥራ የሚል ጥሪ እየቀረበ ነው።ከሚጠይቀው መዕዋለ ንዋይ አኳያ የአዋጭነት ጥናት ተሠርቷል?
አቶ ጌታቸው፡- የኤርፖርቶችን ግንባታ አዋጭነቱን በተመለከተ እና ብክነት እንዳይከሰት ማሰብ ተገቢ ነው።እኛ በቂ ጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲሆን ምክር እንሰጣለን። ነገር ግን አዋጭነትን ስንመለከት በፋይናንስ ዓይን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ አዋጭነት መታየት አለበት ብለን እናምናለን።ለምሳሌ በሀገራችን በቱሪዝም ዘርፍ ሰፊ ዕቅድ አለ። ቱሪስቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በአግባቡ ለማንቀሳቀስና ምቾታቸውን ለመጠበቅ እነዚህ ኤርፖርቶች ያስፈልጋሉ። ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም የሚኖራቸው ሚና ቀላል አይደለም።በመሆኑም መንግሥት ለሚገነባቸው ኤርፖርቶች በአግባቡ እንዲሆን ምክር እንሰጣለን፡፡
በግል የሚገነቡ ኤርፖርቶችን በተመለከተ ለራሳቸው ጥቅም የሚል ነው። ነገር ግን ከዚህ ተርፎ ወደ ቢዝነስ መቀየር አለባቸው። ስለዚህ እኛ ይህን እናግዛለን። አየር ትራንስፖርት ለማሳደግ አደረጃጀት ፈጥረን እየሠራን ነው።እኛ ዓለማችን በአፍሪካ ደረጃ የአየር ትራንስፖርት ማዕከል መሆን ነው።ለዚህ በሰፊው እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጀነራል አቪየሽን ላይ ከሚሳተፉት አንፃር ደረጃቸውን ያልጠበቁ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ ሰማይ እየበረሩ ስለመሆናቸው ይነገራል።ባለስልጣኑ በዚህ ላይ ምን እየሠራ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- ማረጋገጥ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የደህንነት ቁጥጥር ሥራ ከአፍሪካ አህጉር ብቻ ሳይሆን ከዓለም ሀገራት ተርታ ሲታይ ጥሩ ከሚባሉት አንዱ ነው። ለዚህ ማሳያው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በየዓመቱ የሚሰጠውን ውጤትና ኦዲት ነው። ያመጣነው 89 ከመቶ በላይ ነው። ይህ የሚያሳየው የመቆጣጠር አቅማችን ትልቅ ነው ማለት ነው። ነገር ግን ድንገት አደጋ አይከሰትም፤ እኛ ፍፁም ነን ማለት አይደለም።ስለዚሀ ደረጃቸውን ያልጠበቁ አውሮፕላኖች እና ደረጃቸውን ያልጠበቁ አብራሪዎች በኢንዱስትሪው ውስጥ አይቀጥሉም።ነገር ግን መፈተሽ ያለብን ነገር ካለ እንፈትሻለን። የአቪዬሽን ቁጥጥር በባሕሪው ዓለም አቀፋዊነት የተላበሰ እና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበት ነው። ሆኖም ችግሮች ካሉና ጥቆማ ከመጣም ለማረም ዝግጁ ነን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከጀነራል አውሮፕላኖች በተጨማሪ«ድሮን ኦፕሬት» እስከ ማድረግ ለሚችሉት ፈቃድ ለመስጠት ጥሪ ቀርቧል።ይህ ከደህንነት አኳያ ስጋት አይፈጥርም?
አቶ ጌታቸው፡- በቀጣይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መቆጣጠራቸው አይቀርም። ይህን በተመለከተ የድሮን አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ድሮኖችን እዚህ እስከ መገጣጠም መሥራት አለብን። የሚገጣጥሙት አካላት ካሉም በጣም ሊደገፉ ይገባል። ይህን በተመለከተ በባለስልጣኑ በኩል ‹‹ሬጉሌሽን›› አውጥተናል። የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በዋናነት ይቆጣጠራል።ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም ድርሻቸውን ይወጣሉ።
በድሮን ጉዳይ የደህንነት ከፍተኛ ሥጋት መኖሩ ይታወቃል። ‹‹ፕራይቬሲ›› ጉዳዩም በጣም ትልቅ ነው። በአጠቃላይ ግን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መራመድ አለብን። ለዚህ የሚጠቅም አሠራር መዘርጋት አለብን። በመሆኑም የደህንነት ሥራውንም እየሠራን የሚጠበቅብን መወጣት አለብን ብለን ተነስተናል፡፡
በአሁኑ ወቅት እኛ ከስድስት ሺህ በላይ ፓይለቶችን ፈቃድ ሰጥተን አድሰንላቸዋል። ከስምንት ሺህ በላይ ቴክኒሻኖችን ፈቃድ ሰጥተንና አረጋግጠን ወደ ሥራ ተሠማርተዋል። ስለዚህ ሌሎች ሁኔታዎችም ሲኖሩ በዚህ ልክ መዘጋጀት አለብን። በድሮን ቴክኖሎጂ ላይም መሥራት አለብን የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አቪዬሽን ከዓለም አቀፍ ደረጃ አንፃር ሲመዘን ተወዳዳሪ ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ ጌታቸው፡- በባሕሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመራ ነው። ድንበር ዘለል ስለሆነ ከአንዱ ሀገር ተነስቶ ወደ ሌላ የሚሄደውና የሚሰጠው አገልግሎት በተመሳሳይ ደረጃ ነው። እስካሁን አቪዬሽን በተመለከተ 12ሺህ ደረጃዎች ወጥተው እየተተገበሩ ነው። ከዚህ አንጻር በቅርቡ በተደረገ ኦዲት ኢትዮጵያ 89 ነጥብ 5 አግኝታ አጥጋቢ ደረጃ ላይ ነች። ከትራንስፖርት ተደራሽነት አኳያ ሲታይ ግን አንዱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ነው። አሁንም ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የምንባል ነን።የሀገር ውስጥ ግን አነስተኛ ነው።
መዳረሻችን ትንሽ ናቸው። የክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ግንኙነትም ከማዕከል ወይንም ከአዲስ አበባ ጋር ነው። በአንድ በኩል መዳረሻችን ውስን ነው፤ ግንኙነትም አነስተኛ ነው። ይህ መሻሻል አለበት፤ በዋናነት መሠራት ያለበት በግል ባለሃብቱ ነው።በመሆኑም እኛም እነዚህን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንገኛን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሀገሪቱ የተመዘገቡ የግል ኦፕሬተሮች ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት አኳያ እንኳን በጣም አነስተኛ ናቸው።ይህ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡– በአሁኑ ወቅት 13 የሚሆኑ የግል ኦፕሬተሮች ተመዝግበው እየሠሩ ነው። እነዚህ ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ነው። የሚሰጡት አገልግሎትም በጣም ውስን ነው። በአብዛኛው የሚሰጡት የቻርተር አገልግሎት ነው።መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። የግብርና ሥራ፣ የፎቶግራፊ ሥራ፣ የሰርቬይ ሥራዎች እየሠሩ አይደለም። የተወሰነ የፖሊሲ ችግር ቢኖርበትም በካርጎ በኩልም እንቅስቃሴው በጣም ጥቂት ነው። ስለዚህ የግል ኦፕሬተሮች ሚና ውስን ነው። በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀርም አነስተኛ ነው።ግን ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን ብለን እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሀገሪቱ የአየር ክልል የሚሸፍን በቂ ራዳሮች የሉም፤ ያሉትም የዘመኑ አይደለም የሚል የባለሙያዎች አስተያየት አለ።በዚህ ላይ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- የራዳር ሰርቪሊያንስ በተመለከተ አሁን ያለን ‹‹ኤር ናቭጌሽን ፋሲሊቲዎች›› ዘመናዊ የሚባሉ ናቸው። ዘመናዊ መሣሪያዎችን እየገጠምን ነው። ግን ማሻሻልና ማሳደግ አለብን። አብዛኛው የሀገሪቱን ክፍል እንሸፍናለን። ግን ምን ያክል የሀገሪቱ ክፍል ተሸፍኗል የሚለው ጥናት መደረግ አለበት። አንዳንድ የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ አሉ። እነዚህ በአዲስ መተካት አለባቸው። ይህን ለማከናወን አዳዲስ የራዳር ግዥ እየተፈጸመ ነው።
የአዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርትን ለማሻሻልም ጥረት እየተደረገ ነው።ደረጃው የበለጠ ለማሳደግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው።የኮሙኒኬሽን አቪዬሽንና ሰርቪሊያንስን በተመለከተ የሚቀሩ ሥራዎችና የበለጠ ዘመናዊ የማድረግ እንዲሁም ሽፋኑን የማሳደግ ተግባራት ቢቀሩንም በመሠረታዊነት አሁን ያለን አገልግሎት አስተማማኝ እና ጥሩ የሚባል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የባለስልጣኑን ስድስት ወር አንኳር አፈፃፀም የሚባሉትን ቢጠቅሱልን?
አቶ ጌታቸው፡- ከስምንት ሀገራት ጋር የአየር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት አቅደን ነበር፤ ይህን አሳክተናል። ጥሩ ሴፊቲ ሪከርድ አለን፤ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ባደረገው ኦዲት አፈፃፀማችን 88 ነጥብ 5 ነው። ያለንን አጠናክሮ መሄድ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበረብን ጉድለት አይተን ጉድለቱን አሟልተን ከ90 ከመቶ በላይ አድርሰናል። ኤር ናቭጌሽን ላይ አውሮፕላኖች በየሁለት ደቂቃ እንዲያርፉ አቅደን ይህን ማሳካት ችለናል። ኤር ናቭጌሽን አገልግሎታችንም ደህንነቱ የተጠበቀ፤ ወጪ ቆጣቢና የዘመነ መሆን አለበት። በእነዚህ መለኪያዎች መሠረት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በአጠቃላይ መስፈርቶች አኳያ ሲታይ አፈፃፀማችን በጣም የተሻለና በእቅዳችን መሠረት የሄደ ነው። የሚጎለን የተቋማችንን አቅም እያሳደጉ መሄድ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።ተጨማሪ ሐሳብ ካለ መጨመር ይችላሉ፡፡
አቶ ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዘመናትን የተሻገረ አንጋፋ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርባ አጥንት ሲሆን፤ ደህንነቱ የተጠበቀ ሥራ በማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ አየር መንገድ መሆኑ የተመሰከረለት ነው። ለዚህ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ትልቅ ሚና አለው።
በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዘርፍ ለውጦች እየተመዘገቡ ነው። ቀደም ሲል ለመንግሥት ብቻ የተሰጡ የሚመስሉ አገልግሎቶች አሁን ለባለሃብቱ እየተሰጡ ነው። ለአብነት ኤርፖርት ልማት ላይ የግል ባለሃብቶች፣ ከተማ አስተዳደሮችና እና ክልሎች እንዲሳተፉበት ዕድሉ ተመቻችቷል፤ ይህን መጠቀም ይገባል። የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ደግሞ የደህንነት ቁጥጥር ሥራው በጣም የተጠናከረና በአግባቡ የተጠበቀ አሠራር እንዲኖረው በኃላፊነት እየሠራ ያለ ተቋም መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም