ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ ከተሞች የመም እና የጎዳና ላይ ውድድሮች በስፋት ተከናውነዋል። በእነዚህ ውድድሮችም ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳትፎም ሆነ በአሸናፊነት በስፋት ስማቸውን ማስጠራት ችለዋል። ከእነዚህ ውድድሮች መካከል አንዱ በሃዋሳ የተካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ነው። በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ከሚካሄዱ ዓመታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ ይህ ውድድር ሲሆን፣ በወንዶች አትሌት አበባው ደሴ 1:01:52 በሆነ ሰዓት በመግባት የበላይነቱን ሊይዝ ችሏል። ጠንካራ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር በሁለት ሰከንዶች የዘገየው አትሌት ገመቹ ጊሼ ሁለተኛ ሲሆን፤ አንድ ሰከንድ የዘገየው ሃፍታሙ አባዲ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳሊያውን አጥልቋል። በሴቶች በኩል ደግሞ አትሌት የኔነሽ ደጀኔ 1:12:45 የሆነ ሰዓት አስመዝግባ አሸናፊ ለመሆን ችላለች። በሰከንዶች ልዩነት ተከትለዋት የገቡት አትሌት ብዟገር አደራ እና አጸደ ባዪሳ ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።
በስፔን የተካሄደው የካስቴሎ ማራቶን በወንዶች ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች የበላይነቱን ለመያዝ ችለዋል። ከ5ሺ በላይ ሯጮች የተሳተፉበት ይህ ውድድር፤ ለሩጫ ተስማሚ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል አንዱ ሲሆን በዓለም አትሌቲክስ የነሃስ ደረጃ የተሰጠውም ነው። በውድድሩም 2:11:15 በሆነ ሰዓት ርቀቱን የሸፈነው ዳዲ ያሚ ሲሆን፤ ሶስት ሰከንዶችን ዘግይቶ የገባው ለሚ ዱሜቻ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አብርሃም ግርማ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ሊይዝ ችሏል።
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ባለውና በጃፓኗ ኦሳካ በተካሄደው ማራቶንም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ውጤታማ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በወንዶች በኩል አሸናፊ የሆነው አትሌት ኃይለማርያም ኪሮስ ሲሆን ሩጫውን የፈጸመበት 2:06:01 የሆነ ሰዓትም የቦታው ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። በሴቶች በኩልም ፈጣን ሰዓት የተመዘገበ ሲሆን፤ አሸናፊዋ ሄለን በቀለ 2:22:16 በሆነ ሰዓት የቦታው ባለ ክብረወሰን ለመሆን ችላለች። ሌላኛዋ አትሌት በየኑ ደገፋ ደጋሞ ሄለንን ተከትላ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
በደቡብ አፍሪካዋ ፖርልዛቤት የተካሄደው የ50 ኪሎ ሜትር ሩጫ ሲሆን፤ ኢማኔ ሰይፉ አሸናፊ ሆናለች። ርቀቱ ከማራቶን ውድድር የሚረዝመውና ‹‹አልትራ ማራቶን›› የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና የተሰጠው ነው። በዚህ ውድድር በርካታ ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉ ቢሆንም በተለያዩ ኪሎ ሜትሮች አቋርጠው ወጥተዋል። የውድድሩ አሸናፊ መሆን የቻለችው ኢማኔ በበኩሏ የርቀቱን ግማሽ ኪሎ ሜትር 1:30:28 በሆነ ሰዓት መሸፈን ችላለች። ከአጋሮቿ ውጪ ለብቻዋ ስትሮጥ የቆየችው አትሌቷ 40ኛውን ኪሎ ሜትር 2:24:46 በሆነ በሰዓት በማቋረጥ የመጨረሻውን መስመር ለመርገጥ ያደረገችው ጥረት የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር በአንድ ደቂቃ ብቻ የዘገየ ሆኖባታል። ይሁንና 3:00:29 የሆነ የቦታውን የምንጊዜም ምርጥ ሰዓት ልታስመዘግብ ችላለች። ከሩጫው በኋላም አትሌቷ ‹‹ስሜቴን ለመግለጽ ቃላቶች የሉኝም፤ በጥቅሉ እጅግ አስደሳች ነው›› ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
በግማሽ ማራቶንም በርካታ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ በናፖሊ ታዋቂው አትሌት ሙክታር እድሪስ አሸናፊ ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመም ሩጫዎች ይልቅ በጎዳና ላይ ውድድሮች ላይ እየተስተዋለ የሚገኘው የሁለት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮኑ አትሌት ሙክታር ርቀቱን በበላይነት ለመፈጸም የፈጀበት ጊዜ 1:00:27 ነው። በአትላንታ ግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ አትሌት ጸጋዬ ኪዳኑ 1:00:39 በሆነ ሰዓት በመሮጥ አሸንፏል። በዚህ ውድድር የሴቶች ምድብ ላይም ሰላም ፈንቴ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች። በሜክስኮ በተካሄደ ሌላ ውድድር ላይም በወንዶች አትሌት ያሲን ሃጂ እንዲሁም በሴቶች ህይወት ገብረኪዳን አሸናፊዎች ሆነዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም