በታኅሣሥ ወር በ1961 ዓ.ም በታተሙት ጋዜጦች የሚያሳዝኑ ፣ትንግርትንና ጥያቄን የሚያጭሩ እንዲሁም በእኛ አገር የተከሰተ ነው የሚያስብሉ ዘገባዎች ለንባብ በቅተዋል። እኛም በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን እነዚህን ዘገባዎች ለትውስታ ያህል መርጠናል። በተጨማሪም ከልማት ጋር የተያያዙ ዘገባዎችን አካተናል። አማኑኤል ሆስፒታል ለታማሚዎች የሲኒማ አዳራሽ በሕዝብ ትብብር እያሠራ እንደሆነ የሚገልፅ አንድ ዘገባም ዛሬ የሲኒማ አዳራሹ ታሽጎ ነው ወይስ የሚታይ ሲኒማ ጠፍቶ ነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርጋል።
ግመል ሰው በላ
መቀሌ ፤(ኢ-ዜ-አ) በእንደርታ ወረዳ ውስጥ ዓዲ አሙቆ በተባለው ቀበሌ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች በግመል ተነክሰው ሆስፒታል የገቡ መሆናቸውን የትግሬ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ገለጠ።በግመል የተነከሱትም ሰዎች ዕቁባ ሐድጎ የተባለ የ፲፫ ዓመት ወጣትና አቶ ነጋሽ ግርማ የተባሉ ሰው ናቸው።
ግመሉ ይህን አደጋ ሊደርስ የቻለው ፤ በመጀመሪያ ዕቁባ ሐድጎን ራሱ ላይ ነክሶ ብዙ አንገላታው። በዚህም ጊዜ አቶ ነጋሽ ግርማ ወደ ግመሉ ተጠግተው የዕቁባይን ሕይወት ለማዳን ሲሞክሩ ፤ርሳቸውንም ከራሳቸውና ከእግራቸው ላይ በመንከስ ከፍ ያለ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
ቁስለኞቹ አሁን መቀሌ ከተማ በሚገኘው ከልዑል ራስ ስዩም መንገሻ መታሰቢያ ሆስፒታል ገብተው በሕክምና ላይ ይገኛሉ።
በሰዎቹ ላይ አደጋ ያደረሰው ግመል ግን አቶ ሐረጎት ግርማ በተባሉ ሰው አማካይነት በረሽ ጠብመንጃ የተገደለ መሆኑን የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል በተጨማሪ አስታወቀ። የእንደርታ ወረዳ የሚገኘው በትግሬ ጠቅላይ ግዛት በእንደርታ አውራጃ ግዛት ነው።
(ታኅሣሥ 2 ቀን 1961 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ቦምብ ፈንድቶ ሰው ገደለ
በጨቦና ጉራጌ አውራጃ በበቾ ወረዳ በኢሉ ምክትል ወረዳ ግዛት አንድ ቦምብ ፈንድቶ ሰው ሲገድል ሁለት ሰዎች አቆሰለ።
አደጋው የደረሰው ኅዳር ፳፯ ቀን ፷፩ ዓ.ም ዳባ በዳዳ ፤ሁንዴ መስቀሌ የተባሉ ሰዎች እመት ደሴ ጉሜ ቤት ውስጥ አንድ የእጅ ቦምብ ሲፈታቱ ነው። ቦምቡ በፈነዳበት ጊዜ ዳባ በዳዳ የተባለው ወዲያውኑ ሲሞት ፤ሁንዴ መስቀሌና እመት ደሴ ጉሜ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ሲሉ ሻለቃ ከፍያለ ወርቁ የጨቦና ጉራጌ አውራጃ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ማስታወቃቸውን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ የማስታወቂያ ክፍል ገለጠ።
(ታኅሣሥ 2 ቀን 1961 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ብታምኑም ባታምኑም
አንድ የ62 ዓመት አዛውንት ቀንድ አበቀሉ
ጐንደር ፤(ኢ-ዜ-አ) አንድ የ፷፪ ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሰው ራሳቸው ላይ ቀንድ በቀለ።
በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት በጀምናምራ ወረዳ በሳህላ ምክትል ግዛት ነዋሪ የሆኑት አቶ ወልዴ መራ ቀንድ ራሳቸው ላይ የበቀለው ከ፫ ዓመታት በፊት መሆኑን ባለቤቱ መናገራቸውን የደረስጌ ክሊኒክ አላፊ አቶ አያሌው መኰንን ገለጡ።
አቶ ወልዴ መራ ይኸው ከ፫ ዓመት በፊት የበቀለው ቀንድ በየጊዜው እያደገ ወደ ቤት ሲገቡና ሲወጡ ብዙ የሚያስቸግራቸው መሆኑን ለክሊኒኩ አላፊ በሰጡት ቃል አስታውቀዋል።
ከዚህም በቀር እኝሁ ቀንድ የበቀለባቸው አዛውንት ለአንዳንድ ሥራ ወደ ጫካ በሚሔዱበት ጊዜ ግራና ቀኝ እየያዘ የሚያስቸግራቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጠዋል።
አቶ ወልዴ መራ ከራሳቸው ላይ የበቀለው ቀንድ አራት ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ፤ይኸው ቀንዱ የበቀለበት ሥፍራ ግን በየትናው ወገን እንደሆነ አይገልጥም።
አቶ ወልዴ መራ የሚተዳደሩት በእርሻ ሥራ ሲሆን ፤ትዳርም ያላቸው ሰው ናቸው። ይኸው በአቶ ወልዴ ላይ የደረሰው አስደናቂ ታሪክ በክፍሉ ባላባት በአቶ ቸኮል ንጉሤ ተባባሪነት የተገኘ መሆኑን ወኪላችን ከጐንደር ገልጧል።
(ታኅሣሥ 5 ቀን 1961 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ለአማኑኤል ሆስፒታል
ሲኒማ ቤት ርዳታ ይሰበሰባል
የአማኑኤል ሆስፒታል የማኅበራዊ ጉዳይ አገልግሎት ሠራተኞች ፤በቅርቡ ተሠርቶ የነበረው የአእምሮ ሕሙማን የመንፈስ ማደሻ የመደሰቻ (ሲኒማ) አዳራሽ በአገልግሎት ላይ እንዲውል የሥራ ማሟያ ርዳታ በገንዘብ መልክ በሌላም ከልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎች ድርጅት ርዳታ እያገኙ ናቸው።
የሲኒማው አዳራሽ ለመሥራት የበቃው፤ የሆስፒታሉ የማኅበራዊ ጉዳይ አገልጋዮችና አንድ የሰላም ጓድ ባልደረባ ከበጎ አድራጊዎች በሰበሰቡት ገንዘብና የአሜሪካ ተራድኦ ባዋጣው ርዳታ ሲሆን ፤ የአዳራሽ ወለል ጣሪያውና የፕሮጀክተሩ ማስቀመጫው ተሟልቶ ስለአላለቀ ፤የማኅበራዊ ጉዳይ አገልግሎት አስተባባሪዎች ርዳታ ከየትም ቢሆን ማግኘት ግድ ሆኖባቸዋል።
አቶ ደበበ በየነ ፤በአማኑኤል ሆስፒታል የማኅበራዊ ጉዳይ አገልግሎት ሠራተኞች እንደገለጡት ጥቂት በጎ አድራጊ ኩባንያዎችና ድርጅቶች የመሣሪያና የገንዘብ አገልግሎት ሲያደርጉልን ከሌሎችም እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
እስካሁን ለሆስፒታሉ የለገሡት ኩባንያዎችና ስጦታዎች ፤የኢትዮጵያ ሲሚንቶ ኮርፖሬሽን ፩ ሺ ብር፤ የኤካፍኮ ኩባንያ ፪፻፷ ብር የሆነ የጣሪያ ፋየዚቲሲዲ፤ ኩባንያ በግምት ፬፮፻፹ የሆነ ፤ ፺፮ ኩብ ሜትር ሸክላ ለወለል ምንጣፍ የሚሆን የሜጋ ቀለም ኩባንያ በ፩፻፳ብር የሚገመት ፲፭ ጋሎን ቀለም ናቸው ።
(ታኅሣሥ 4 ቀን 1961 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም