በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖረው እየተሰራ ነው። ቢሮው በከተማዋ የሚታየውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል። ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ በየደረጃው ችግር መኖሩ ይታወቃል። ይህንን ችግር ለመፍታት በተለያዩ ከተሞች እየተገነቡ ከሚገኙ ስታዲየሞች መካከል አንዱ የአቃቂ ዞናል ስታዲየም ነው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ባለቤትነት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ስታዲየም ሲጀመር የዞናል ደረጃ የተሰጠው እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ዓለም አቀፍ ደረጃን ሊመጥኑ የሚችሉ ማስተካከያዎችን በማድረግ እንደ አገር ያለውን ችግር መቅረፍ እንዲችል ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፤ ተጨማሪ መስራት የሚገባቸውን በማሟላት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ደረጃን እንዲመጥን የዲዛይን ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ስታዲየሙ በአሁኑ ወቅት የጣራ ግንባታው እየተከናወነ ሲሆን፤ 20ሺ የሚሆኑ ጥራታቸውን የጠበቁ ወንበሮች የሚገጠሙለትም ይሆናል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የቢሮው ኃላፊዎች ወንበሮቹን እየሰራ በሚገኘው ሚድሮክ እህት ኩባንያ አዲስ ጋዝና ፕላስቲክ ፋብሪካ በመገኘት ስለ ስራው ምልከታ አድርገዋል። ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶችንም ያሟላ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ሜዳ እንዲሆን ዲዛይኑ በፍጥነት ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ እንዲውልና ችግሩም እንዲፈታ እየተሰራ ነው። ይህ ስታዲየም ከዚህ ቀደም ይጠናቀቃል በሚል ከተያዘለት ጊዜ ሊዘገይ የቻለውም ከኮንትራክተሮችና ሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ነበር፤ በዚህ ወቅት ግን ተስተካክሎ በስራ ላይ እንደሚገኝ ነው ኃላፊው ያስገነዘቡት።
ከተማ አስተዳደሩ እንደ አገርም ሆነ እንደ ከተማ በዜጎች በተደጋጋሚ የሚነሳውን የስፖርት ማዘውተሪያዎች ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም አሳውቋል። ቢሮው ከስፖርት ጋዜጠኞች ጋር በነበረው የውይይት መርሃ ግብር ላይ በተደጋጋሚ ከተነሱ ችግሮች መካከል አንዱ ከማዘውተሪያ ስፍራ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተከትሎም እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች አብራርተዋል። በዚህም በእድሳት ላይ ቆይቶ አሁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ቀሪ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ እየተደረገ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል። አማራጭ ስታዲየም እንደመሆኑ ሜዳው ላይ ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ እየተደረገም ነው።
ችግሩ ከእግር ኳስ ባሻገር በሌሎች ስፖርቶችም የሚስተዋል እንደመሆኑ የራስ ኃይሉ የመዋኛ ገንዳ ጉዳይም ተነስቷል። ለረጅም ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየው የመዋኛ ገንዳ በዚህ ወቅት በስራ ላይ ያለ ቢሆንም ቀሪ ስራዎች እንዲሁም የጥራት መጓደሎች አሉበት። ከዚህም ጋር ተያይዞ ማሽኖቹ የገቡት ከውጪ አገራት እንደመሆኑ ከባለሙያ ጋር የተያያዙ ቴክኒካዊ ችግሮች ገጥመዋል። በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል።
በየአካባቢው በብዛት አስፈላጊ የሆኑ የጥርጊያ ሜዳን እንዲሁም የ1ለ3 ሜዳዎችን በሚመለከትም በተለይ ትም ህርት ቤቶች ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል። ከተማሪ ዎችና በየትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ ፕሮጀክቶች ባለፈ ከትምህርት ሰዓት ውጪ የአካባቢው ህብረተሰብም ተጠቃሚ መሆን በሚችልበት መልኩ ከትምህርት ቢሮ ጋር እየተሰራበት ነው። በየቦታው የሚገነቡ ሜዳዎችን በሚመለከትም በስፋት የሚስተ ዋለው ከአስተዳደር ጋር የተያያዘ ችግር ሲሆን፤ ይህንን ለመቅረፍ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ እስኪጸድቅ እየተጠበቀ ይገኛል። በጥቅሉ በከተማዋ በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ላይ ወደ 900 የሚሆኑ ሜዳዎች መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፤ ለተፈለጉበት ዓላማ እንዲውሉ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አቶ በላይ አስታውቀዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም