የክረምት ወቅትን ጠብቆ የሚከናወነውን የኢትዮጵያን ግብርና ስራ የሚያውቅ በዚህ ዘመን በበጋ ወቅት አረንጓዴ የለበሰን ማሳ ለዚያም የስንዴ ማሳን አይቶ ላይጠግብ ይችላል።እኔም በአንድ የስራ አጋጣሚ በቅርቡ በወፍ በረር የቃኘሁት የመስኖ ልማት አካባቢ ይህን ስሜት አሳድሮብኛል።አካባቢው ከፊሉ ማሳ በአትክልትና ፍራፍሬ፤ ከፊሉ ደግሞ በበጋ መስኖ ስንዴ ሰብል ተሸፍኗል።ሁሉም አይንን ይስባሉ። በተለይ በዚህ አቧራ፣ ሀሩር፣ ጸሀይና ሙቀት በተንሰራፉበት የበጋ ወቅት ማሳ በዚህ መልኩ አረንጓዴ ለብሶ ማየት የበጋ ስንዴ መስኖ ልማቱን ፋይዳ በሚገባ ያመልክታል።ከተሰራ በጋውን ሙሉ እህል ማምረት እንደሚቻል በመጠቆምም ትልቅ ተስፋን ያጭራል።
የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በዚህ የበጋ ወቅት መመልከት የተለመደ ነው።በቆሎ በመስኖ ወደ ማልማት ከተገባም እንዲሁ ቆይቷል።የስንዴው ግን የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፤ አግራሞትን በእጅጉ ያጭራል።ልማቱ ለአልሚው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት፣ ለሸማቹ ደግሞ በተሻለ ዋጋ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር ያስችላል። በአካባቢው ማንኛውም የግብርና ሥራ የሚከናወን ቢሆንም፤ በምርታማነት ግን በአትክልትና ፍራፍሬ፤ ከሰብል ልማት ደግሞ በስንዴና በበቆሎ በስፋት እንደሚታወቅ የአካባቢው አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
አካባቢው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ነው።የአካባቢው አርሶ አደሮች አሁን እያከናወኑት ባለው ልማት ደስተኞች ናቸው፤ በቀጣይም የበለጠ ለማልማት ዝግጁ ናቸው። ቀድሞ የሚሰሩበትን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አጠናክረውታል።በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ አርሶ አደር ጀማል በዳሶ ከስንዴና በቆሎ በተጨማሪ አትክልት ያለማሉ።ቀደም ሲል በነበራቸው የግብርና ሥራ ተሞክሮ በክረምት በመኸር ወቅት ስንዴና በቆሎ በበጋው ደግሞ በመስኖ እንደ ቃሪያና ጎመን ያሉትን ያለሙ ነበር።ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ክረምት ከበጋ ሰብልም ሆነ አትክልት በስፋት ማልማት ውስጥ ገብተዋል፡፡
በሁለተኛው ዓመት የበጋ መስኖ ልማት ስራቸው የሥራ ባህል ተምረውበታል፤ ምርታማነታቸውም ጨምሯል።ውሃ በአካባቢያቸው እያለ አቅጣጫውን የሚመራቸው ወይንም ግንዛቤ የሚሰጣቸው ባለመኖሩ ረጅሙን ወቅት ጠብቆ በማልማት ላይ ተወስነው ለመቆየት ተገደው የነበሩት አርሶ አደሩ፣ ምርታማ ሆነው ኑሮአቸውን መለወጥ ሲችሉ ባለመሥራታቸው ይቆጫሉ። አሁንም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተፈጠረው እድል በሚገባ ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ።አምና በበጋ መስኖ ስንዴ አልምተው 15 ኩንታል አግኝተዋል።ይህ ለእሳቸው አዲስ ክስተት ነው።የበጋ መስኖ ልማት ብዙ ፋይዳ እንዳለው ነው አርሶ አደሩ የሚናገሩት።ሰብሉ በቂ ውሃ እንደሚያገኝ፣ የግብአት ፍጆታውም አነስተኛ መሆኑን፣ አረምም በዚህ ወቅት እንደሚቀንስ ነው ያብራሩት፡፡
አካባቢው ላይ የዝናብ እጥረት በመኖሩ በመኸሩ ሰብሉ በቂ ዝናብ ስለማያገኝ ምርታማነቱም አነስተኛ ነው የሚሉት አርሶ አደር ጀማል፣ የበጋ መሥኖ ልማት መጀመሩ እርሳቸውን ጨምሮ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ጥሩ እድል መፈጠሩን ነው የተናገሩት።ጠንክሮ ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመረዳት መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ለመሥኖ ልማት የሚጠቀመው በአቅራቢያው ከሚገኝ ዝዋይ ሐይቅ እንደሆነ የጠቆሙት አርሶ አደር ጀማል ጠቅሰው፣ የተለያየ የስንዴ ዝርያን ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይገልጻሉ።ከእነዚህም መካከል እርሳቸው ‹ቀቀባ›የተባለውን ዝርያ መጠቀማቸውን ይናገራሉ።ይህን ዝርያ ፈጥኖ ስለሚደርስ መርጠውታል።በተያዘው የበጋ ወቅት የዘሩት ስንዴ ለመሰብሰብ እየደረሰ እንደሆነም ገልጸውልኛል፡፡
አርሶ አደር ጀማል ክረምት ከበጋ ማምረት ከጀመሩ ገና ሁለተኛ ዓመታቸው ቢሆንም፣ በኑሮአቸው ላይ ለውጥ አስገኝቶላቸዋል።ይህንንም ‹‹መኪና አልገዛሁም እንጂ ኑሮዬ እየተለወጠ ነው››ሲሉ በጨዋታ መልኩ ነግረውኛል።አርሶ አደሩ የተሻለ መኖሪያቤት መገንባታቸውን፣ ልጆች እያስተማሩ መሆናቸውን፣ በአመጋገብ ሥርአታቸው የመጣው ለውጥ በመግለጽ ህይወታቸው መሻሻሉን ያብራራሉ። አርሶ አደር ጀማል ከቁጭት ለመውጣት እየሰሩ ናቸው።ለእዚህም ክረምት ከበጋ ጠንክረው መስራት ፈልገዋል፤ በመስኖ ልማት የሚያስፈልጋቸውን የውሃ መሳቢያ ሞተር (ፓምፕ) ማግኘት አለማቻላቸው ግን እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ አሁን እየተጠቀሙበት ያለው የውሃ መሳቢያ ሞተር ውሃ የመሳብ አቅሙ አነስተኛ በመሆኑ ከሐይቁ ማሳቸው ድረስ ውሃ ለመሳብ ተቸግረዋል።እየተጠቀሙበት ያለው ሞተር በመንግሥት እገዛ የተገኘ ቢሆንም፣ መንግስት አሁንም የተሻለ ውሃ የመሳብ አቅም ያለው ሞተር በማቅረብ እገዛ እንዲያደርግላቸው ፈልገዋል።ይህም የበለጠ አምራች እንዲሚያደርጋቸው ነው ያመለከቱት።የውሃ መሳቢያ ሞተሩን በራሳቸው ለማሟላት የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፣ የበለጠ መሥራት እየፈለጉ ግን በውስን ለማልማት ተገደዋል።በዘር አቅርቦት በኩልም ከመንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ እንደሆነ ተናግረው፣ መንግስት በመስኖ የሚያለማን እያበረታታ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹አሁን ኑሮ ተወዷል።የሚገዛው ነገር ሁሉ ከአቅም በላይ እየሆነ ነው።እርሻን ማስፋፋትና ተጓዳኝ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል›› የሚሉት አርሶ አደር ጀማል፣ አርቀው በማሰብ መሥራት ያለባቸውንም ከወዲሁ እያቀዱ ነው።ለዚህ ደግሞ ብድር የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻችላቸው የመጀመሪያው ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ ናቸው፡፡ መንግሥት ብድር በማመቻቸት እንዲያበረታታቸው ጠይቀዋል።የመንግሥትን ድጋፍ ብቻ ከመጠበቅ ራስን ለመቻል የሚደረግ ጥረት መኖር የለበትም ወይ? በማለት አርሶ አደር ጀማል ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ‹‹ገበሬ ከዚህ ቀደም ብድርም ሆነ ድጋፍ ጠይቆ አያውቅም።ከተማ ላይ ህንፃ የሚሰራ ነው እየጠየቀ ያለው።መንግሥትም ብድር ሲያመቻች የኖረው ለከተማው ነው።ገበሬው ግን እንዲህ አይነት እድል አልነበረውም።አሁን ላይ ገበሬው ብድር እንዲያገኝ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ አይደለም›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አርሶ አደሩ አካባቢው ላይ ለእርሻ የሚውል ትራክተር፣ ማጨጃና መውቂያ ማሽን (ኮባይነር) አቅርቦት እንዳለ ጠቅሰው፣ ውስንነት እንዳለም ተናግረዋል።ከዝዋይ እሳቸው ያሉበት መንደር ድረስ ማሽነሪዎቹን በማስመጣት በአገልግሎቱ ለመጠቀም ዋጋው ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ በዚህ ምክንያት ብቻ አገልግሎቱን እንደማይጠቀሙ ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት፤ የሜካናይዜሽን አገልግሎቱ የሚሰጠው እንደ ምርቱ መጠን ነው።ምርቱ ከፍተኛ ከሆነ በኩንታል፣ ምርቱ አነስተኛ ከሆነ ደግሞ በቀርጥ ነው የሚደራደሩት።ሁለቱም ከገበሬው አቅም በላይ ናቸው።በዚህ የተነሳ አብዛኛው አርሶ አደር አገልግሎቱን አይጠቀምም።
በዚህ ረገድ ወረዳው አርሶ አደሩ በዋጋ እንዳይጎዳ ለማድረግ ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር መክሮ ዋጋ እንዲተመን ጥረት እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩም ጠብቆ እንዲጠቀም ምክር እንደሚሰጥ ገልጸዋል።ይሁን እንጂ በግንዛቤ እጥረት፣ አገልግሎቱን በሚያቀርቡት ግፊትና በደላሎች ተቻኩሎ የመጠቀም ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ፤ ከወረዳው ጋር ያለመናበብ ችግር መኖሩንም ይጠቁማሉ፡፡ በሶሰት ሄክታር ማሳቸው ላይ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴና ገብስ በስፋት እያለሙ እንደሆነ የነገሩኝ ሌላው አርሶ አደር ጌታቸው ዋሾ ናቸው።በ2014 እስከ 2015 ድረስ የመኸር ምርት ዘመን ስለነበራቸው እንቅስቃሴና ስላገኙት ምርት እንዳጫወቱኝ፤ በምርት ዘመኑ አካባቢው ላይ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት በመከሰቱ ምክንያት የጠበቁትን ያህል ምርት አላገኙም።የዝናብ እጥረቱ በተለይ በቆሎ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፤ በእሸትነቱ ከመጠቀም ያለፈ ምርት ማግኘት አልቻሉም።የዝናብ እጥረቱ ባያጋጥምና በወቅቱም አስፈላጊው ግብአት ቀርቦ በደንብ ሰርተው ቢሆን ከሄክታር እስከ 60 ኩንታል ይገኛል የሚል እቅድ ነበራቸው።
አርሶ አደሩ በስንዴና በገብስ ግን የተሻለ ምርት አግኝተዋል።በተለይ ስንዴ በሄክታር እስከ 30 ኩንታል አግኝተዋል።አካባቢው ለጤፍ አመቺ ባይሆንም፣ ለቀለብ የሚሆን ምርት አግኝተውበታል፡፡ አርሶ አደር ጌታቸው፤ እንደ ሌሎች የአካባቢያቸው አርሶአደሮች በበጋ መሥኖ ልማት ውስጥ እንዳልገቡ ይናገራሉ።ዋና ምክንያታቸው የውሃ መሣቢያ ሞተር (ፓምፕ) አለማግኘት ነው።ማሣቸው ውሃ ከሚገኝበት አካባቢ ርቀት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውሃ መሣቢያ ሞተር ማግኘት ግድ ነው ይላሉ።አንዳንድ አርሶ አደሮች የውሃ መሳቢያ ሞተር እንዳገኙት ለምን ማግኘት እንዳልቻሉና በውሰትም ቢሆን ለመጠቀም ለምን እንዳልሞከሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ በሁለቱም አማራጭ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የገለጹት።
‹‹አርሶ አደሩ በስፋት በልማቱ ውስጥ እንዲሳተፍ መንግሥት የማነቃቃት ሥራ በመሥራቱ ገበሬው ከወቅታዊ ሥራ ወጥቶ ዓመቱን ሙሉ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ይገኛል።ነገር ግን ለመስኖ ልማቱ ግብርናው ሥራ የሚያግዝ አቅርቦት ከሌለ የተፈለገው ውጤት ላይ መድረስ አይቻልም።ለበጋ መሥኖ ልማቱ የውሃ መሣቢያ ሞተር ወሳኝ ቢሆንም፣ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ አይደለም›› ሲሉ አርሶ አደር ጌታቸው ያመለክታሉ።የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን ወረዳው እያቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአቅርቦት በኩል የፍትሐዊነት ችግር እንዳለም ይጠቁማሉ። በዚህ ላይ የሞተሮቹ ውሃ የመሳብ አቅም አነስተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት።እሳቸው በውሃ መሳቢያ ሞተሮች በአቅርቦት በኩል መንግሥት እገዛ ማድረጉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።አቅርቦቱ ብድር ቢመቻች በግላቸው ገዝተው ለመጠቀም ዝግጁ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽን በመጠቀም ረገድም ብዙ ሥራ እንደሚቀር በመጥቀስ የአርሶ አደር ጀማልን ሀሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።የሜካናይዜሽን አገልግሎት በዋጋ ውድ መሆንም አርሶ አደሩ የባህላዊውን ዘዴ ወደ መጠቀም እያዘነበለ እንዲሄድ እንደሚያደርገውም ነው የጠቆሙት።አገልግሎቱ ቢሰፋ በውድድር ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ስለውሃ መሣቢያ ሞተር ያነሱትን እንዲሁም በወረዳው በኩል አርሶ አደሩ የሚፈልገውን በመደገፍና ክትትል በማድረግ በአጠቃላይ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው በአዳሚቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ግብርና ጽሕፈትቤት የእንስሳት ሀብትና የዘር ማሻሻያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገመቹ ጃምቦ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ የአርሶ አደሮቹ ጥያቄ ተገቢነት አለው፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተስፋፋ ከመጣ ወዲህ እና አምርቶ የመለወጥ ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የውሃ መሣቢያ ሞተር ፍላጎትም እየጨመረ መጥቷል።በተለይ በዚህ ዓመት በግለሰብ፣ በማህበር ተደራጅተው በመስኖ ልማት የተሰማሩ ወጣቶችና ሴት አርሶ አደሮች በስፋት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው።በዚህ ምክንያት ሲሰራበት የቆየው የውሃ መሣቢያ ሞተር አቅርቦት መንገድ የጥያቄ አቅራቢዎችን ፍላጎት ለማሟላት አላስቻለም፡፡ይህን ሰፊ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ገመቹ፣ ወረዳው ቀደም ሲል ያቀረበው የውሃ መሣቢያ ሞተር ጥያቄ በ18ሺ ሄክታር መሬት ላይ ለሚከናወን ልማት እንደሆነ አመልክተዋል።የውሃ መሣቢያ ሞተሮች ከፍተኛ በሆነበት አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው፣ አነስተኛ ፍላጎት በነበረበት አካባቢ እንደአስፈላጊነቱ ለማቅረብ ጥረት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በአካባቢው ላይ አሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን ያህል የውሃ መሣቢያ ሞተር ቀርቦ እንደማያውቅ አቶ ገመቹ ጠቅሰው፣ የነበረው ተሞክሮ በኮታ ማቅረብ እንደነበር ገልጸዋል።መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በአቅርቦቱ ላይ ትኩረት መስጠቱን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያመልክትም ተናግረዋል፡፡በወረዳው የመኸር ወቅት ስለነበረው የምርት ሁኔታ አቶ ገመቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አካባቢው ላይ የዝናብ እጥረት ተከስቶ እንደነበር እሳቸውም ጠቅሰዋል።ምርቱ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በተወሰነ ደረጃም መገኘቱን ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ አርሶ አደሩ በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ እየሆነ ያለው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ነው።በዚህ እንዲበረታታ እየተደረገ ነው።ከሐይቅ ከሚገኘው ውሃ በተጨማሪ የከርሰ ምድር ውሃም ጥቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ ታስቦበታል።ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር አቅም ስለሚጠይቅ የሌሎች ድጋፍና ትብብር ይጠበቃል፡፡የግብርና ሜካናይዜሽንም በአካባቢው በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ከአቅራቢዎች ጋር በመወያየት ዋጋ በመወሰን አስፈላጊውን እገዛ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም