የታሪካዊው ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ ስርአተ ቀብር ዛሬ በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ከቀኑ 8 ሰአት ላይ ይፈጸማል። በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት እንዲሁም የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ካሳረፉ ድንቅና ግንባር ቀደም ስፖርተኞች አንዱ የሆኑት ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከትናንት በስቲያ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ታውቋል፡፡
ታህሳስ 7 ቀን 1925 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱት ብስክሌተኛ ገረመው፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት እኤአ 1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ እና ሰንደቅአላማዋን በመያዝ ቀዳሚው አትሌት መሆናቸው ይታወቃል።
አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፏቸው ኢትዮጵያ ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ያስቻሉበት ታሪክ በስፖርቱ ትልቅ ውጤት ሆኖ ይጠቀሳል።
እኤአ በ1960 የሮም ኦሊምፒክም እኚህ ታሪካዊ ብስክሌተኛ ተሳትፈው ከ11 ዙር ውስጥ 9ኙን በአንደኝነት እየመሩ ያሸንፋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በድንገት ከኋላ ተገጭተው በመውደቃቸው አቋርጠው ለመውጣት ተገደው ነበር። ይህም በወቅቱ አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ተገቢ ያልሆነ ግጭት ባያስተናግዱ ማሸነፍ ይችሉ እንደነበር በዓለም ጋዜጦች ተዘግቦላቸዋል።
ገረመው ደንቦባ በቀጣዩ 1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክም በዋና አሰልጣኝነት የኢትዮጵያን የብስክሌት ቡድን መምራት የቻሉ ሲሆን፤ በተወዳዳሪነት ዘመናቸው በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ከ 30 በላይ ዋንጫ እና 32 የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስመዝገብ እንደቻሉ ከህይወት ታሪካቸው መረዳት ተችሏል።
ገረመው ደንቦባ በኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራን ከማሳረፋቸው ባሻገር አቅማቸው ደክሞ እቤት መዋል እስከጀመሩበት ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ መድረኮች እየተገኙ ልምዳቸውን በማካፈል ይታወቃሉ። ከእሳቸው በኋላ በኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ታሪክ ጎልተው መውጣት ለቻሉት እንደ ተሰማ አሞሳ፣ አድማሱ መርጋ፣ አላዛር ክፍሎም፣ጆቫኒ ማሶላ፣ጀማል ሮጎራና ጽጋቡ ገብረማርያም ለመሳሰሉ ብስክሌተኞች አርአያ መሆን ችለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም