አዲስ አበባ፡- በስደት አስከፊነት ላይ ባተኮረው የሀገር አቀፍ የፊልም ውድድር አሸናፊዎች በአውሮፓ ህብረት ሽልማት ተበረከተላቸው።
በስደት ላይ የሚያጋጥሙ እንግልቶችን በማስተማሪያነት ለማቅረብ ታስቦ በአውሮፓ ህብረት የተዘጋጀው አጭር የፊልም ውድድር የአሸናፊዎች ሽልማት ስነስርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ትናንትና ተካሂዷል።
በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ቡድን መሪ አምባሳደር ሮላንድ ኮብያ፤ ውድድሩ የስደት እድሎችና ተግዳሮቶቹን አጉልቶ ከማሳየት ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ወጣቶች የፈጠራ ክህሎት ለማሳደግና የስራ እድል ለማመቻቸት ያግዛል ብለዋል።
በውድድሩ ስድስት የአንድ ደቂቃ አስተማሪ ፊልሞች የተመረጡ ሲሆን፤ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ ተወዳዳሪዎች ሽልማት እንደተበረከተላቸው ገልጸዋል።
የውድድሩ አላማ ስለስደት አስከፊነት ወጣቱ እንዲገነዘብና ስለጉዳዩ በነጻነት እንዲወያይ ለማበረታታት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ህገወጥ የስደት እንቅስቃሴ ለመቀነስ ከአካባቢው ሀገራት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፤ በህገወጥ የስደት አስከፊነት ላይ አስተማሪ መልዕክት ለማስተላለፍ ታስቦ የተዘጋጀው ውድድር ወጣት ኢትዮጵያውያን በአንድ ጠቃሚ ርዕስ ላይ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ እድል ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ የአውሮፓ ህብረት ከ2015 እ.ኤ.አ ጀምሮ ከስደት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ድጋፍ በአውሮፓ ህብረት የአደጋ ጊዜ ትረስት ፈንድ (EUTF) በኩል ተፈጻሚ ሲያደርግ ቆይቷል።
ህብረቱ ለዜጎች መፈናቀልና እና ለስደት መንስኤዎች የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት እንዲሁም የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲፈጠር በሚያግዙ ስራዎች ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ስደት መቀነስ ቢቻል እንጂ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይቻልም ያሉት አምባሳደሩ፤ ችግሮች እንዳይባባሱና ሰብዓዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ የአውሮፓ ህብረት ቀድሞ ከሚያደርገው ድጋፍ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ከታህሳስ ወር 2022 እ.ኤ.አ ጀምሮ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን በማስመልከት ‹‹የስደት እድሎች እና ተግዳሮቶች›› በሚል መሪ ሀሳብ አጭር የፊልም ውድድር በኢትዮጵያ ሲያካሂድ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በውድድሩ እድሜያቸው ከ15 እስከ 35 የሆኑ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸው ታውቋል። የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ቡድን መሪ አምባሳደር ሮላንድ ኮብያ፣ የፋሽን ባለሙያና ስራ ፈጣሪ ማህሌት አፈወርቅና አርቲስት ካስማሰ የውድድሩ አሸናፊዎችን ምርጫ አካሂደዋል።
ወድድሩን ካሸነፉት ስድስት ተወዳዳሪዎች መካከል ተስፋማርያም ዳርጌ አንደኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን፤ በሀገራችን በተገኘው ሰላም አማካኝነት ቤተሰቦቼ ከመቀሌ መጥተው የደስታዬ ተካፋይ በመሆናቸው ድርብ ደስታ ፈጥሮልኛል ብሏል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም