የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር ተመጋጋቢ ሆኖ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ላይ ላቅ ያለ ድርሻ እንዲኖረው የሚያስችል የምጣኔ ሀብት አቅጣጫ ነድፋ ስትንቀሳቀስ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ያለው ድርሻ እንዲሻሻል የሚያስችሉ ውጤቶችን አስመዝግባለች። አገሪቱ ያላትን ግዙፍ አምራች ኃይል፣ ወሳኝ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ምቹ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ለኢንዱስትሪ ዘርፉ እድገት አወንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሌሎች መልካም አጋጣሚዎችና አስቻይ ሁኔታዎች ተጠቅማ ያከናወነቻቸው ተግባራት ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።
ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ ነው። በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት የአቅማቸውን ግማሽ ያህል ብቻ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ጥቅል አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ሲሆን፣ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል።
ሀገር በቀል የምርት ዘዴዎችን ዘመኑ ካፈራቸው የቴክኖሎጂ ስርዓቶች ጋር በማጣመር መተግበር የአምራች ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ከሚያስችሉ አዋጭ የመፍትሄ አማራጮች መካከል ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማዕከል ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት የእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን ለማምረት እንደሚያስችል በተግባር አሳይቷል። ይህ የምርት ዘዴ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በፋይናንስ፣ በውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ከሚገኙት አምራች ዘርፎች መካከል አንዱ ለሆነው የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ታምኖበታል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የማኑፋክቸሪንግና የኬሚካል ዘርፍ የቴክኖሎጂና ምርምር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ደሲሳ ያደታ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትንና የወረቀት ግብዓቶችን የማምረት ዘዴው በስፋት ሲተገበር የኢትዮጵያን የወረቀት ምርት ችግር በዘላቂነት የመፍታት አቅም እንዳለው ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ የሀገሪቱ የወረቀት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በዋጋ ንረትና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት በእጅጉ በመዳከሙ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትንና የወረቀት ግብዓቶችን የማምረት ዘዴው ለዘርፉ ትልቅ ብስራት ነው።
‹‹የወረቀት ምርት ፍላጎትን ለማሟላት እየተሞከረ ያለው ያገለገለ ወረቀትን ለአምስት ወይም ለስድስት ጊዜያት ያህል መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል (ሪሳይክል) በማድረግ ነው። ይህ ዓይነት የምርት ዘዴ ደግሞ የወረቀት ግብዓት የሆነው የፋይበሩ ርዝመትና ጥራት እንዲቀንስና እንዲበጣጠስ ያደርጋል፤ በዚህም ምክንያት የሚመረተው የወረቀት ጥራት እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል። ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትንና የወረቀት ግብዓቶችን የማምረት ዘዴው ግን የተሻለ ጥራት ያለው የወረቀት ምርት ለማግኘት ያስችላል። ይህ የምርት ዘዴ በዋጋ፣ በጊዜ፣ በቴክኖሎጂ እና በአካባቢ ጥበቃ ረገድ አዋጭና ተመራጭ ነው። የምርት ወጪው ከእንጨት ነክ የፐልፕ ምርቶች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው። በቀላል ቴክኖሎጂ የሚሰራ እና ለአካባቢ ብክለት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ለምርት ግብዓትነት የሚጠቀም በመሆኑ ለፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግርና ለአካባቢ ጥበቃ በጎ አስተዋፅኦዎችን ያበረክታል›› ይላሉ።
‹‹ኢትዮጵያ ‹የሰው ዘር መገኛ ናት› ከተባለ በቴክኖሎጂውም ቀዳሚ መሆን ነበረብን›› የሚሉት ዶክተር ደሲሳ፣ ‹‹ሀገሪቱ እምቅ ሀብት እያላት ለምርት እጥረት መዳረግ አልነበረባትም። የወረቀት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው ዝቅተኛ ነው። የዚህ ምክንያቱ የግብዓት እጥረት ነው። ለምርት ግብዓት የሚሆን ሀብትና አቅም ግን አለ። ከዚህ ሀብት ጥቂቱን እንኳ መጠቀም ቢቻል ብዙ ችግር መፍታት ይቻላል›› በማለት ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ሀብቶችን በመጠቀም የምርት እጥረትን ማስወገድ እንደሚገባ ያስረዳሉ። በቀጣይ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን በማምረት ዘዴ የተገኘው ውጤት ጥራቱ እንዲሻሻልና በስፋት ለገበያ እንዲቀርብ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
እንሰት በብዛት ከሚመረትባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። የክልሉ የኢንተርፕራይዝ ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢረጋ ብርሃኑ ከእንሰት ተፈረ ምርት ወረቀትን የማምረት ተግባር እንሰት አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ተጨማሪ ጥቅም የሚያስገኝ እርምጃ እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ እንሰት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን ለፋብሪካዎች የወረቀት ምርት ግብዓት የሚሆን የእንሰት ተረፈ ምርት የሚሰበሰብበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። በቀበሌ ደረጃ ተረፈ ምርቱን ሰብስበው ለወረዳዎችና ከዚያም ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡ አደረጃጀቶችን መፍጠር ያስፈልጋል። ለስራ አጥ ወጣቶች፣ በተለይም ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ ለሌላቸው ሴቶች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የስራ ፈጠራ ስልጠናዎችን በመስጠት በስራው ላይ እንዲሰማሩ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ የእንሰት ተረፈ ምርት ፍላጎት ሲጨምር የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት የእንሰት ተክልን በስፋት በመትከል ስራውን ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባም ያሳስባሉ። ለዚህም የእንሰት በሽታን በመከላከል አቅርቦቱን አስተማማኝ የማድረግ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አቶ ቢረጋ ይናገራሉ።
የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞንም እንሰት ከሚመረትባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ ነው። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታዬ ሙሊሳ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን ለማምረት ያስቻለው የምርት ዘዴ ለአርሶ አደሩ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ያስረዳሉ። እንደርሳቸው ገለፃ፣ ከእንሰት ተረፈ ምርት ተጨማሪ ጥቅም ማግኘት እንደሚቻል ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው ላለው አመራርም ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል።
‹‹ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን የማምረት ተግባር በዞኑ የሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ስራ ለማስያዝ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ተረፈ ምርቱን ሰብስቦ ለፋብሪካዎች የማቅረቡ ስራ አስቸጋሪ አይሆንም። አርሶ አደሩ፣ በተለይም ሴቶች ተደራጅተው፣ ተረፈ ምርቱን ሰብስበው በቀጥታ ለፋብሪካዎች እንዲያቀርቡ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቶችን በማደራጀትና ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ ግብዓቱን እንዲያቀርቡ ማድረግ ይቻላል›› በማለት ከዚህ የምርት ዘዴ ተጠቃሚ ለመሆን ዞኑ ዝግጁ መሆኑን ይገልፃሉ።
የአምራች ኢንዱትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሚልኬሳ ጃገማ በሀገር ውስጥ ያሉት የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች በግብዓት እጥረት ምክንያት በሚፈለገው ልክ እያመረቱ ባለመሆኑ ሀገሪቱ የወረቀት ምርትንና ግብዓቶችን ከውጭ እንደምታስገባ ይናገራሉ።
‹‹የእንሰት ተረፈ ምርት ለወረቀት ምርት ግብዓት እንደሚያገለግል በምርምር ተረጋግጧል። የሙከራ ምርትም እውን ማድረግ ተችሏል። ቴክኖሎጂው የቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል፤ ከውጭ የሚገባውን የወረቀት ምርት በሀገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል። ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ ለማስገባት ተጨማሪ እድል ይፈጥራል። እያንዳንዱ ተቋም ወረቀትና የወረቀት ውጤቶችን ስለሚጠቀም ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው። ይህን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሟላት ምርትን መጨመር ያስፈልጋል። ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን የማምረት ተግባር ደግሞ ምርትን ለመጨመር የሚያግዝ ነው። ስለሆነም በቀጣይ ወጣቶችን በማደራጀት በግብዓት አቅርቦት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል። ተረፈ ምርቱን በብዛት ለማግኘት ለተፈረ ምርቱ ብቻ ሳይሆን ስለእንሰት በሽታዎች፣ ስለምርታማነቱና ተያያዥ ጉዳዮችም ጠቅላላ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ይህ ተግባር ደግሞ የግብርናና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንና እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን የጋራ ቅንጅት ይፈልጋል›› ይላሉ። የምርት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ተልዕኮን ለማሳካት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር፣ ግብዓት አቅራቢዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማገናኘት እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተደራጀው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እና የጥናትና ምርምር ተግባራትን በማከናወን የአምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ለማድረግ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በአጠቃላይ የኢንዱስትሪዎቹን ችግሮች በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ለማሳደግ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሚልኬሳ፣ ኢንስቲትዩቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው የስልጠና፣ የቤተ ሙከራ ፍተሻ፣ የማማከር፣ የአዋጭነት ጥናት፣ የጥናትና ምርምር፣ የቴክኒክ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል ባለፈው ዓመት ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው። የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው። ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል። በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል።
ዶክተር ሚልኬሳ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ከእንሰት ተረፈ ምርት ወረቀትን ማምረትን የመሰሉ ሀገር በቀል የምርት ዘዴዎችን ለማበረታታት ትልቅ አቅም እንደሚሰጥ ይገልፃሉ። በኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽንና ኬሚካል ምርምር ማዕከል አማካኝነት በተደረገ የጥናትና ምርምር ስራ ስኬታማ የሆነው ይህ የምርት ዘዴ፣ በንቅናቄው ከተቀመጡ ዓላማዎች ጋር ተመጋጋቢ የሆኑ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ነው። ሀገር በቀል የምርት ዘዴዎችንና ግብዓቶችን በመጠቀም የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የሥራ እድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትንና ተኪ ምርቶችን የማምረት ተግባራትን ለማሳካት የሚያግዝ ነው።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት የሚመጣጠኑ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የአምራች ዘርፉን ችግሮች መፍታት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም