የማጣቀሻ ወግ፤
ክብርት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዴ አዳነች አቤቤ በቅርቡ ለአምስት አንጋፋ የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች (ለጌታቸው ካሣ፣ ለይልማ ገብረ አብ፣ ለአሸናፊ ከበደ፣ ለሻምበል በላይነህ እና ለመስፍን ጌታቸው እናት) የመኖሪያ ቤት ስጦታ ማበርከታቸውን ሰምተናል። በከተማችን ከንቲባ ከተባረኩት ባለሙያዎች መካከል አራቱ በሙዚቃው ዘርፍ ያገለገሉ ጎምቱ አንቱዎች መሆናቸው እርግጥ ነው። ከእነዚህ ዕድለኞች መካከል ለዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያነት የሚጠቀሰው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ ይሆናል።
ይህ ድምጻዊ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ በመንገሥ አሻራውን አኑሮ ከበሬታን ማትረፉንና ለሦስት አሠርት ዓመታት ያህልም ዜግነቱን ሳይለውጥ አሜሪካ ሀገር ኖሮ መመለሱን በራሱ አንደበት ሲመሰክር አድምጠናል። ድምጻዊውን ያስታወስንበት ዋናው ምክንያት ግለ ታሪኩን በዝርዝር ለመተረክ በማሰብ ሳይሆን አንድ ዘመን ጠገብ ዜማውን ለመንደርደሪያነት ስለመረጥን ነው።
ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ ከበርካታ ዓመታት በፊት ለሕዝብ ካቀረባቸው ተወዳጅ ሙዚቃዎቹ መካከል “እመኛለሁ” በሚል ርእስ ያንጎራጎረው ዜማ መልእክቱም ሆነ ለዛው ሳይደበዝዝ “እንዳሸተ” ዛሬም ድረስ እየተደመጠ ይገኛል።
“እመኛለሁ ዘወትር በየዕለቱ፣
ላሳካ ኑሮን ከብልሃቱ።”
በሚል አዝማች በመንደርደር ያዜመው ሙዚቃው የእርሱን ዘመንና ያለንበትን ይህንን “ግራ አጋቢ” የጋራ ዘመናችንን በእኩልነት ሊገልጹ በሚችሉ የስንኝ ውቅሮች በሚገባ የተዋቀረ ነው። ጥቂት ስንኞችን ለአብነት እናስታውስ።
“ኑሮና ብልሃቱ እስኪቃናልኝ፣
በሃሳብ ግስጋሴ ወደርም የለኝ።
አልቃና እያለኝ ኑሮና ብልሃቱ፣
መቼውም አልቀረ ምኞት መዘግየቱ።”
እነዚህ አራት ስንኞች የዘመናችን መልክ የተሳለባቸውን በርካታ ሸክሞች ጥቅልል አድርገው የተሸከሙ ስለመሆናቸው ኑሯችን ራሱ ምስክር ነው። ስለዚህም የግጥሙ መልእክት ካለፈው ዘመን ይልቅ ወደዚህኛው ዘመን ያጋደለ ይዘት አለው ብሎ ለመመስከር የሚገድ አይሆንም።
“አሻቅቤ ስሮጥ ከበላይ ቋጥኝ፣
እየተጫነኝ ነው ያልተሳካልኝ።”
የሚሉት ሁለቱ ስንኞችማ ከትናንቱ ዘመናት ይልቅ የዛሬዋን ሀገሬንና ሕዝቤን በተሻለ ሥዕላዊ ገለጻ የሚያመልከቱ ይመስለናል።
“አሰብኩኝ አለምኩኝ፣
እኔም ሁሌም አዲስ ነን ለዛሬ።”
የሚሉት የመደምደሚያ ስንኞቹ አጠቃላዩን የዜማውን መልእክት በሚገባ ሰብስበው ያሰሩ ስለሆነ ዘለግ አድርገን እንተንትን ብንል እጅግም የምንጠቅሳቸው እውነታዎች ይኖራሉ ብለን ስለማንገምት ጌታቸው ካሣን አመስግነንና ከግማሽ ክፍለ ዘመን አገልግሎት በኋላ ምኞቱ ተሳክቶለትና ህልሙ ፍቺ አግኝቶ ከመኖሪያ ቤት ጋር የተያያዘው የችግሩ ቋጥኝ ከላዩ ላይ ስለተንከባለለት እንኳን ደስ ያለህ በማለት ወደ ተያያዥ ትዝብታችን እናቀናለን።
“ትምህርታችን ለፍርድ ይቅረብ!”
መደበኛ አስኳላ ከገባንበት ዕለት ጀምሮ ዛሬም ድረስ የትምህርት ሥርዓታችን “እያላዘነበት” ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለ መሠረታዊ የሰው ልጆች ፍላጎት በምርምርና በጥናት ያረጋገጡ “ሳይንቲስቶች ቀምረውልኛል” የሚለው ከእውነታ ጋር የሚጣረሰው ሃሳብ የማይጨበጥ ህልም ሆኖ መኖሩ በእጅጉ የሚገርም ነው።
ሦስቱ መሠረታዊ ፍላጎቶች የተባሉት “ምግብ፣ ልብስና መጠለያ” ለአጥኚዎቹ በረከት ለእኛ ትምህርቱን ከልብ ተቀብለን ስንፈተንበት ለኖርነው ስለምን በዘመናት መካከል “የመከራ ቀንበር” ሆነውብን እንደኖሩ ለመገመት እጅግ ያዳግታል።
እንኳንስ እኛን መሰል ለወላጅነት ወግ ደርሰን ለጉድ የጎለተን የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ቀርቶ ጡጧቸውን እስኪጥሉ ድረስ “ለተንከባካቢዎች – Daycare” አደራ የምንሰጣቸው ልጆቻችን ሳይቀሩ በኮልታፋ አንደበታቸው ይህንን ዘመን ያሸበተ ጎዶሎ ትምህርት ከሀዘን ጋር ተንትነው ማስረዳት የሚሳናቸው አይደለም።
“ሕጻናት ይህንን መሰሉን ፍርድ ለመስጠት እንደምን እድሜያቸው ይፈቅድላቸዋል?” ብሎ ለሚሟገት አንባቢ “ከሕጻናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ…ጠላትንና ምቀኛን ለማሳፈር” (መዝሙር 8፡2) የሚለው የነብየ እግዚአብሔር የዳዊት ምሥክርነት ለማስረጃነት ይቆምልኛል። በዚህ የቅዱስ መጽሐፍ እውነታ ላይ በመጠራጠር ከውሎ አምሽቷችን ብቻ ማረጋገጫ ለሚሹ “የአቴና ፈላስፋ ወገኖቼ” በየማሕበራዊ ሚዲያው እየቀረቡ “እሳት ከአፋቸው የሚተፉ” ጨቅላዎችን ዋቢ መጥራቱ አይገድም።
እርግጥ ነው፡- በሌሎች ሀገራት “ያለ ምግብ” መኖር አይቻል ይሆናል። በእኛ ሀገር አኗኗር ግን ኑሮና ብልሃቱ አልገጥም በማለት ጦም ውለን ጦም የምናድር ሻምፒዎናዎች ሆነን እንድንኖር የተፈረደብን ምንዱባን መሆናችን ከገባን ሰነባብቷል። ይህንን አዚማችንን ደግሞ በታዳጊ ሕጻናቶቻችን የእለት ተእለት ጨዋታ ሳይቀር እያዘመርን ለመኖር መገደዳችን የእንቆቅልሻችንን ውስብስብነት በሚገባ ያመለክታል።
“…አለሁ በመከራ እንባዬን ሳዘራ።
ለምን ታዘሪያለሽ አገዳ እየበላሽ?
አገዳም የለኝ ምስኪን ደሃ ነኝ።
ምስኪን ደሃ ሆነሽ ምን በልተሽ ታድሪያለሽ?
ባገኝም በልቼ፤ ባጣም ተደፍቼ።
ይድፋኝ ይደፋፋኝ ጦም ማደርሽ ከፋኝ።”
የሚለው ዘመን ጠገብ እንጉርጉሮ ዛሬም ድረስ በታዳጊዎቹ ሴት ልጆቻችን አፍ ለኢትዮጵያ በውክልና እየተዘመረና እየተደመጠ “የእርግማናችንን ክብደት” ለማሳያነት ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ኖሯል።
ወጋችን እጅግ እየተለጠጠ ወዲያ ወዲህ ለመናወዝ መገደዳችን የርሃብና የርሃብተኛ ባህርይ መገለጫ መሆኑን የታችኞቹ የማሕበረሰብ ክፍሎች በሚገባ ይገነዘቡታል። ለዚህ የገጣሚያችንን የጸጋዬ ገ/መድኅንን ግጥም ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል።
“ርሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል›
ይባላል ዱሮም ይባላል፤
ለእኔና [ለእነሳቸው] ብጤማ ትርጉሙ፣
የሁለት ድምጽ ፊደል ነው፣
ራብ የሚሉት ከነስሙ።
እንጂ ለእኛና ለእነሱ ብጤማ፣
የት አውቀነው ጠባዩንማ።
ብቻ ሲነገር ይሰማል፣
ይህንን ሁለት ፊደል ቃል።”
እነሆ በተቃርኖ የተሞላው የዕለት ኑሮ አኗኗችን መልኩ ይህንን ይመስላል። ግና የፌዴራሉ መንግሥታችንና የየከተማችን አስተዳዳሪዎች ጆሮ ሰጥተው ለመስማት ጊዜ የሚኖራቸው ከሆነ አንድ ኮስተር ያለ መልእክት አለን።
በትልቁም ሆነ በመካከለኛው መዋቅር ላይ የተሰየሙ የንግድ ሚኒስቴርና በየደረጃው ያሉ የንግድ ቢሮዎች ሙሉ ለሙሉ ታጥፈው በምትኩ የግብርና ሚኒስቴርና በሥሩ ያሉ ዘርፎች ተለጥጠው የሰማይ ያህል እንዲሰፉልን ቢደረግ የምድራዊ ርሃባችን እርግማን በቀላሉ የሚቀጭ ይመስለናል።
ቢያንስ በየወሩ በነዳጅ ላይ እንደሚቆለለው ተመን በአንድ ኩርማን ብጥሌ ዳቦ ላይ በነጋ በጠባ ግራሙ እየተቀነሰ ዋጋው በማሻቀብ ወደ ላይ እየተወነጨፈ ግራ ላጋባን የዕለት ጉርሳችን “በርሃብ ልናልቅ ነው” እያልን ኡኡ ማለታችን ምናልባትም መፍትሔ ሊሆን ይችል ይመስለናል።
የተጣበቀውን አንጀቱን በእለት ጉርስ መደለል የተሳነው ሕዝብ እንባውን ወደ ጸባኦት እየረጨ እዬዬ ሲል ፍራሻቸው ተሞችቷቸው ተኝተው የሚያድሩ የንግድ ሥርዓቱ አስተዳዳሪዎች “እየኖርንም፤ እያገለገልንም ነው” ብለው የሚናገሩ ከሆነ እንኳንስ በድምጻችን ለወንበር ያበቃናቸው እኛ ዜጎች ቀርተን “ከሰው መርጦ ለሹመት” ለሚለው መርህ ጠንካራ አቋም ያለውና ያከበራቸው አምላክም ራሱ ተቆጥቶ ፍርድ መስጠቱ አይቀርም።
ከሠፈር ጉልት የዕለት ምግብ ለመግዛት ካልተቻለ፣ መደበኛ ገበያም ወጥቶ መገብየት የማይሞከር ከሆነ፣ የዘመናዊዎቹ የምግብ ስቶሮች የሸቀጥ ዋጋ ድንጋጤ ላይ እየጣለ ለደም ብዛትና ለስኳር ህመም መዳረጉ ለማይገባቸው ሹመኞቻችን “የችግራችንን ግዝፈት እያሳየን ስንማጠናቸው” ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያዩ ከሆነ፤ “አርኩም ይሄድና ሶልዲውም ያልቅና፤ ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና” አለች ይባላል፤ በክፉ የጠላት ወረራ ዘመን ጎረቤቷን የታዘበች ምስኪን እህት።
የመኖሪያ ቤት ጉዳይማ “ተከድኖ ይብሰል” ማለቱ ይበጃል። የኮንዶሚኒዬም ዕጣን ተስፋ አድርገው ኖረው ተስፋቸው ሳይሞላ ያለፉትን ቤታቸው ይቁጠረው። ከዛሬ ነገ ዕጣው ይደርሰናል እያሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩትን ግፉዓንም እንዲሁ እግዜር ይካሳቸው። ዋጋቸው ሰማይ ሰማያት ከመድረሱ የተነሳ እንኳንም በግዢ ማግኘት ቀርቶ በምኞትም ተንጠራርቶ ሊደረስባቸው የማይቻለው የሪል እስቴት አፓርትመንቶችን መመኘትማ በባዕድ ሀገር በምቾት ለመኖር ከማለም እኩል የሚታሰብ ነው። “የራሴ ግቢ” የሚሉት ቋንቋማ በታሪክና በተረት ካልሆነ በስተቀር በእውን ሊሳካ የሚችል ምኞት አይደለም። የጌታቸው ካሣ ዜማ እንኳንም ተዜመልን።
በዚህን መሰሉ የመጠለያ መብት ቅዠት ሲባትቱ ከመኖር ይልቅ በክርስቶስ ትንቢታዊ ቃል ላይ ማረፉ ሳይሻል አይቀርም። “ልባችሁ አይታወክ…በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ። እኔም ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጀሁላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ በዚያ ትኖራላችሁ” (ዮሐንስ 14፡1-3)። ግሩም የማጽናኛ ቃል ነው።
የአልባሳትን ጉዳይ በተመለከተ ግን “ተመስገን!” ብሎ ማለፉ ተገቢነት ይኖረዋል። ስለምን ቢሉ “ሳይደግስ አይጣላም” እንዲሉ ልባሽ አልባሳትን (ሳልቫጅ) ገዝቶ እንዳቅም እርቃንን መሸፈን የባህል ያህል ተላምደን እየኖርንበት ነው። ክፋቱ በየአደባባዩ የተሠማሩት ደንብ አስከባሪ ተብዬዎች ሳልቫጅ ነጋዴዎቹን ቁም ስቅል እያሳዩ ሲያሰቃዩአቸው መዋላቸው ነው። የቆመጣቸው ስንዝር ለሸማቾች መትረፉም የማይዘለል እውነት ነው።
በመኪና መሃል ማሳደዳቸውና በቆመጣቸው ቅዝምዝም ዳፋ “ነፍስ በእጃቸው ላይ የጠፋ ዕለት” እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ያሰማራቸው ክፍልም በጋራ የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀርም። እንደ ግሪሳ ወፍ ግር እያሉ በመባተት የዕለት ጉርሳቸውን ለማሸነፍ ለሚታተሩት ሳልቫጅ ነጋዴዎች የዜግነትና የመኖር አርቴፊሻል የመብታቸው ጉዳይ እንኳን ቢቀር “በጽድቅ ሂሳብ” ታስቦላቸው ተረጋግተው የሚነግዱበት ቦታ ቢመቻችላቸው የሚሻል ይመስለናል።
ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ተሻሙ፣ ጎዳናውን አቆሸሹ፣ መንገድ ዘጉ ወዘተ. የሚለውን ጉንጭ አልፋ ምክንያት ለመስጠት የሚፈጥኑት “የሕዝብ ካርድ ባላደራ” ሹመኞች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ሊያቋቁሟቸው ይገባል። የልባሽ ጨርቅ ንግድ በእነርሱ ዐይን ፊት ሞገስ ቢነፈግም ለተጠቃሚው ግን ትልቅ እፎይታ መስጠቱን በሚገባ ሊያስታውሱ ይገባል።
ሦስቱን መሠረታዊ ፍላጎታችንን በተመለከተ ይህንን ያህል ከተወያየን ዘንድ ለቀሪዎቹ ጉዳዮች ደግሞ “ኑሮና ብልሃቱ ለእኔ እስከሚቃና” እንዳለው ድምጻዊ፤ የብሶት እሪታችንና ጸሎታችን ቢቻል በምድራዊ መንግሥታችን፣ ካልሆነም ከሰማያዊው ጸባኦት እስኪመለስልን ድረስ ባለመታከት የሀገራዊ ችግሮቻችን ገመና እየጠቃቀስን መቆዘማችንን አናቋርጥም። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።
የመኖሪያ ቤት ጉዳይማ “ተከድኖ ይብሰል” ማለቱ ይበጃል። የኮንዶሚኒዬም ዕጣን ተስፋ አድርገው ኖረው ተስፋቸው ሳይሞላ ያለፉትን ቤታቸው ይቁጠረው። ከዛሬ ነገ ዕጣው ይደርሰናል እያሉ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩትን ግፉዓንም እንዲሁ እግዜር ይካሳቸው። ዋጋቸው ሰማይ ሰማያት ከመድረሱ የተነሳ እንኳንም በግዢ ማግኘት ቀርቶ በምኞትም ተንጠራርቶ ሊደረስባቸው የማይቻለው የሪል እስቴት አፓርትመንቶችን መመኘትማ በባዕድ ሀገር በምቾት ለመኖር ከማለም እኩል የሚታሰብ ነው። “የራሴ ግቢ” የሚሉት ቋንቋማ በታሪክና በተረት ካልሆነ በስተቀር በእውን ሊሳካ የሚችል ምኞት አይደለም
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም