‹‹ታሞ የተነሳ ፈጣሪን አይረሳ›› አሉ አበው፡፡ አንድን ነገር ትኩረት የምንሰጠው ከደረሰብን በኋላ ነው፡፡ ሰሞኑን ታምሜ ነበር (አሜን ብያለሁ እግዜር ይማርህ ብላችሁኝ ከሆነ) እናላችሁ ያላማከርኩት ሰው፣ ያላነበብኩት ጤና ነክ ጋዜጣና መጽሔት፣ ያልበረበርኩት ድረ ገጽ የለም፤ እንዲያውም ሰሞኑን ጤና ነክ መረጃዎችን ከማንበቤ የተነሳ ህክምና ትምህርት ክፍል ገብቼ ብፈተን ጥሩ ውጤት የማመጣ ይመስለኛል (ይሄን ነገርማ ሳልሞክረው አልቀርም)፡፡
ከዚህ በፊት ጋዜጣና መጽሔት ሳነብ የጤና ዓምድ ላይ ስደርስ አልፌው ነበር የምሄደው፡፡ ይሄ ነገር ግን የኔ ችግር ብቻ አይመስለኝም፤ ብዙዎቻችን የጤና ነክ መረጃዎችን ትኩረት አንሰጣቸውም፡፡ ‹‹ዋናው ነገር ጤና›› እያልን ነው እንግዲህ የጤናን ነገር ትኩረት የነፈግነው፡፡ ነገሩማ ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› የሚባል ወርቅ የሆነ አባባልም ነበረን! በነገራችን ላይ የግል ሕክምና እና መድኃኒት ቤቶች ይችን አባባል ይወዷት ይሆን? አይመስለኝም፤ ምክንያቱም አስቀድሞ ከመጠንቀቅ መድኃኒት መግዛት ነው ለእነርሱ የሚበጃቸው፡፡
ይልቅ ለእነርሱ ይችኛዋ አባባል ጥሩ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ‹‹ህመሙን የሸሸገ መድኃኒት አይገኝለትም›› ይቺን አባባል እንዲህ ይተገብሯታል፡ ፡ ህመምተኛ ሲታመም ሐኪም ቤት ይሄዳል፤ ሕመሙን ተናገረ ማለት ነው፡፡ ሐኪሙም አይቶ ለበሽታው ስም ካወጣለት በኋላ መድኃኒት ይገዛ ዘንድ ዝርዝሩን ጽፎ ይሰጠዋል፡፡ ታማሚ ሆዬ ያንን ይዞ በየመድኃኒት ቤቱ መዞር ነው፡፡ ይቺን አባባልማ ከመድኃኒት ቤታቸው በር ላይ በትልቁ መጻፍ አለባቸው፡፡
ወደራሴው ገጠመኝ ልመለስ
በመጀመሪያ ምን እንዳመመኝ አላወቅኩትም ነበር፡፡ ሐኪም ቤት መሄድ የፈለኩት በሽታው ምን እንደሆነ እንዲነግሩኝና የሚያስፈልገውን ህክምና እንዲያደርጉልኝ ነው፡፡ ደግሞ ጥሎብኝ ሐኪም ቤት መሄድ በጣም ነው የምጠላው (በእርግጥ ማንም ወዶ አይደለም!) ያው እንግዲህ የግድ ሆነና ‹‹ዛሬ መሄድ አለብኝ›› ብዬ ተነሳሁ፡፡ ገና ከቤት ወጥቼ ዋናው መስመር ስደርስ ‹‹እገሌ የጥርስ ክሊኒክ፣ እገሌ የጥርስ ህክምና፣ እገሌ የጥርስ ልዩ ህክምና፣ እገሌ የጥርስ ስፔሻሊስት…›› በቃ በግራም በቀኝም ጥርስ በጥርስ ሆኗል፡፡ ‹‹እዚሁ እየኖርኩ ይሄን ሁሉ የጥርስ ህክምና አላየሁትም ነበር?›› ብዬ ተገረምኩ፡ ፡ ለካ ነገሮችን ልብ የምንላቸው ሲያስፈልጉን ብቻ ነው፤ ያው የጥርስ ህክምና ባያስፈልገኝም ሐኪም ቤት ስፈልግ የሚታየው ሁሉ ጥርስ ብቻ ሆነብኝ፡፡
ከአካባቢው ራቅ ብዬ ብዙ ሄድኩ፡፡ አሁንም መቶ ሜትር ባልሞላ ርቀት ውስጥ የማገኘው የጥርስ ህክምና ነው፡፡ በኋላ ህመሜን ረስቼው ስለጥርስ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ጥርስ የመጀመሪያው የምግብ ሥርዓተ ልመት የሚጀመርበት መሆኑን የ4ኛ ክፍል የአካባቢ ሳይንስ መምህራችን የነገረን ትዝ አለኝ (ግን እስከዛሬ የጥርስ ጥቅም ምን መስሎኝ ነበር?) ጥርስ በቁጥር 32 ነው፡፡
የኋላ ጥርስ፣ የፊት ጥርስ፣ ወተቴ ጥርስ…. እያልኩ እኔም ሃሳቤ ሁሉ ጥርስ ሆነ፡፡ ‹‹በቃ አገራችን ጥርሳም ይበዛባታል ማለት ነው?›› ብዬ ራሴን ስጠይቅ ደግሞ የጥርስ ፈሊጣዊ ትርጉሞች መጡብኝ፡፡ ‹‹ጥርሱን ነክሶ›› ከተባለ ጨክኖ ወይም ደግሞ ቂም ይዞ ማለት ነው:: ‹‹የጥርስ ሥጋ›› ከተባለ ጨቅጫቃ፣ ነዝናዛ፣ ነገረኛ ማለት ነው፡፡ አሁን የጥርስ ህክምና ለምን እንደበዛ ገብቶኛል!
ነገሩ ስላስገረመኝ ለአንድ ጓደኛዬ ነግሬው ነበር፡፡ ሰው ዓይኑን ይታመማል፤ ብዙ የዓይን ህክምና ግን የለም፣ ሴቶች በማህጸንና በጡት ካንሰር በተደጋጋሚ ይታመማሉ፤ የማህጸን ካንሰር፣ የጡት ካንሰር ህክምና ግን በብዛት የለም፡፡ ብዙ ዓይነት በሽታዎች አሉ ግን የሚበዛው የጥርስ ህክምና ነው ያልኩት ጓደኛዬ እንደ ቀልድም እንደቁምነገርም አድርጎ እንደነገረኝ የጥርስ ህክምና የበዛው የጥርስ ታማሚ ከሌላው በላይ ሆኖ አይደለም፡፡ ብዙዎች ለውበት (ለቅንጦት መሆኑ ነው) ይሄዳሉ፡፡
ነገሩ የምር መሆኑን የምናውቀው ራሳቸው የጥርስ ሐኪሞች ራሱ ሲያስተዋውቁ ከጤንነት ይልቅ ውበትን መሰረት አድርገው ነው፡፡ ስለዚህ የሚሄድላቸው ሰው ከታመመው ይልቅ ‹‹ጥርሴ ወጣ ገባ ያለ ሆኖብኝ ነው፤ ከሰው ፊት እንደፈለገኝ ለመሳቅ ብየ ነው›› ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ ሰው የሳቅ ነገር ይህን ያህል ያሳስበዋል ማለት ነው? እርግጥ ነው ሳቅ ለጤና ይመከራል፤ ዳሩ ግን ሕዝቡ ሲያማርር ነው የሚሰማው፣ አገሩን ሲወቅስ ነው የሚሰማው፣ በአገሪቱ ለቅሶ እንጂ ሳቅ እንደሌለ ነው የሚናገረው፤ ኧሃ! ሕዝቤ ለካ ከቤቱ ሲሆን ይስቃል ማለት ነው!
ከጥርስ እንውጣ!
‹‹የጥርስ ክሊኒክ›› የሚል ጽሑፍ ያለመታከት ሳነብ ቆይቼ ለራሴ የሚሆን አገኘሁ፡፡ የወረፋውን ነገር ፈርቼ በሌለ ቤቴ የግል ክሊኒክ ገባሁ፡ ፡ ገና ካርድ ክፍል እያለሁ ለሙሉ የህክምና ወጪ ያሰብኩትን ጠየቀችኝ፡፡ ‹‹ኧሃ! የግል ክሊኒክ ሲሆን ሁሉም አንዴ ነው የሚከፈለው ማለት ነው›› አልኩና ከፍዬ ወረፋ ያዝኩ፤ ተጠራሁ ገባሁ፡፡ ከዶክተሯ ጋር ትንሽ ካወራን በኋላ የሆነ የማላውቀው ረጅም ሳይንሳዊ ስም ጠራችልኝ፡፡
‹‹ኧረ ባክሽ ባክሽ ምንድነው የታመምክ እንኳን ስባል ለመናገር የሚያመች ግልጽና አጠር ያለ አድርጊልኝ›› አልኳት፡፡
‹‹ሰውዬ አትቀልድ! ይሄ እኮ ሳይንሳዊ ስሙ ነው››
‹‹ሆይ ጉድ! እኔ ሳይንሳዊ ስሙ ምን ይሰራልኛል? ስታይኝ ለጥናትና ምርምር የመጣሁ እመስላለሁ?››
‹‹ታዲያ ለበሽታህ የዳቦ ስም ልታስወጣ ነበር የመጣህ?››
‹‹አዎ››
‹‹ታዲያ ለምን የሰፈር ሽማግሎች አያወጡልህም?››
‹‹አይ! ዶክተሮች ለበሽታ ስም ያወጣሉ ሲባል ነው የሰማሁ››
‹‹ሰውዬ ጤነኛ አይደለህም እንዴ?
‹‹እንዴ! ታምሜ መስሎኝ የመጣሁ?››
‹‹ምንህን ነው ያመመህ?››
‹‹ጥርሴን›› አልኳት ለካንስ በብዙ የጥርስ ክሊኒኮች መካከል ሳልፍ ጥርስ የሚለው ነገር በሃሳቤ ውስጥ ተሰንቅሮ ህመሜን አስረስቶኝ ነበር።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011
በዋለልኝ አየለ