እንደ ሀገር ያለው የተማሪዎች ሥነምግባር ጉዳይ አደጋ ውስጥ እንደገባ የምንመለከትበት ብዙ ማሳያ አለ። ለአብነት ሰዎችን ማክበር፣ኃላፊነት መውሰድ፤ ሀገርን መውደድና ለሀገር ብሎ መሥራት፤ ራስን ለመለወጥ መሞከር ላይ ያለንበት ደረጃ እጅግ የወረደ ነው። አንዳንዴ እነዚህ ነገሮች የሉም ሊያስብሉን የሚችሉ ነገሮችም ያጋጥሙናል። ምክንያቱ ታዲያ ምንድነው ከተባለ ባሕልን፣ ወግንና የሥራ ልምድን የሚሸረሽሩ ነገሮች መብዛታቸው ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ ሥነምግባር ላይ በተጨባጭ አለመሥራቱ መሠረቱ የተበላሸ ትውልድ እንዲፈጠር አድርጓል።
መምህርና ተማሪው ተገፋፍቶ እንጂ ተከባብሮ እንደማይጓዝ ሲታይ ሀይ የሚል መጥፋቱ፣ ያልሠራውን ውጤት ካልሰጠኸኝ ብሎ ሲሳደብና ሲማታ ዝም መባሉ፤ወላጁም ቢሆን ለምን ልጄን ትመታለህ በሚል የሚጋጭበት ሁኔታ ዜጋውን መብቱን እንጂ ግዴታውን እንዳያውቅም አበረታቶታል። በሀገር ደረጃ ለእኔ ብቻ የሚል ዜጋን ፈጥሯል። ሀገሩን ትቶ የሌላ ሀገርን የሚናፍቅም ትውልድ እንዲበራከትም አድርጓል።
እና ምን ይሁን ከተባለ ይህንን የሚያስተካክል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ይህም በትምህርቱ ዘርፍ መሥራት ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴርና ይህ የሚመለከታቸው ተቋማት በመቀናጀት የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን እየጣሩ እንደሆነ ከሰሞኑ የሰማነው ነገር ያረጋግጣል። በእርግጥ ከዚህም በፊት ትምህርት ሚኒስቴር ሥነምግባርን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ትምህርቶችን በመቅረጽ ወደ ሥራ አስገብቷል። ሆኖም ትምህርቱ እውቀት ከማስጨበጥ ይልቅ ውጤት (ማርክ) ላይ ያተኮረ በመሆኑ የተማሪዎችን ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። እንደውም ከግዴታ ይልቅ መብትን ብቻ የሚያረጋግጥ ሆኖባቸው ብዙዎች ወደአልተፈለገ መስመር እንዲገቡ መርቷቸዋል። እናም የትምህርቱ ችግር በአግባቡ እንዲፈተሸና በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ ሌሎች ትምህርቶች እንዲቀየሱ አስችሏል።
እነዚህ ትምህርቶች የስነ ዜጋ ትምህርት የሚለው የዜግነት በሚል ተቀይሮ የሚይዘው ይዘትም ተለይቶ እንዲገባ ሆኗል። በተመሳሳይ የግብረገብነት ትምህርትም እንዲሁ በትምህርት ደረጃ ተካቶ እንዲሰጥ ተደርጓል። አሁን ደግሞ የሰብዓዊነት ትምህርት በእነዚህ ትምህርቶች ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ ከሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር መፈራረም ተችሏል። እነዚህ ትምህርቶች መልካም ስነምግባርን ከመፍጠርም በላይ የነበሩ መልካም ወግና ባህሎቻችንን በማስቀጠል በኩል የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው በወቅቱ የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች ሲናገሩ ነበር።
እውቀት ያለሥነምግባር ስኬታማ እንደማይሆን ተረድቶ ስነምግባርን ለማሻሻል የሚሠሩ ተግባራትን ማስፋት ከምንም በላይ እንደሚያስፈልግም መስማማት ላይ ተደርሶበታል። የትናንቱ ይብቃን በማለትም በቀለም ትምህርትነት ብቻ ሳይሆን በሕይወት እንዲኖሩት ለማድረግም እንሠራለን ነው የተባለው። ምክንያቱም ባለፉት ጊዜያት ይሰጥ የነበረውን የሥነዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ከለውጥ ይልቅ ነውጠኛ ተማሪ እንደፈጠረ በሚገባ ታይቷል። ስለሆነም የሥነምግባር ትምህርቱ ለተግባራዊ ለውጥ እንዲሆን የቁጥር ውጤት ከመሆኑ ባለፈ መሠራት እንዳለበትም ታምኖበታል።
ትምህርት ከቀለሙ ሻገር ብሎ የለውጥ መሠረት መሆን እንዳለበት የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፤ ተግባር የለውጥ ምንጭ ነው። በተግባር የተደገፈ ትምህርት በስፋት ባለመሰጠቱ የተነሳ ብዙ ነገሮች እንደሀገር ችግር ሆነው አልፈዋል። ለዚህም ማሳያው የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ነው። በሕይወትም በሥራም የሚለውጥ ነገር በተማሪዎቹ ላይ አልተሠራም። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ሁሉም ሰው ነው። እንደሀገር የወደቅንበትም ስለሆነ ሁሉም ማስተካከልና ለለውጡ መሥራት አለበት። የሥነምግባር ትምህርት ደግሞ ለዚህ ችግራችን የመጀመሪያው መፍትሔ ይሆነናል ይላሉ።
የባሕሪይ ለውጥ ትምህርት ሰዎች መሠረታዊ የሥነ ምግባር እሴቶችን (መርሆዎችን) እንዲረዱ፤እንዲጠብቁና እንዲኖሩበት ያደርጋል። በዚህም በዕቅድ ተመርቶ የጠቅላላ ባሕሪይ ለውጥ ትምህርት ሆኖ በትምህርት ቤቶች የመልካም ሥነምግባር ማጎልበቻ ማዕከል ይሆናል። እንዴት ከተባለ ደግሞ የባሕሪይ ለውጥ ትምህርት በትምህርት ሥርዓተ ውስጥ ተካቶ መሰጠት ሲችል ነው። እናም የሥነ ምግባር ጉዳዮችን በመፈተሽ መልካም ባሕሪይን ማጎልበት ያስፈልጋል። በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት ሂደትም ይህ እየተደረገ እንደሆነም ያነሳሉ።
በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት ሁለቱም ተቋማት ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው የሥራ ድርሻ እንዳለ ያነሱት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፤ የትምህርት ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን አመቺ በሆኑ የትምህርት ዓይነቶች በተለይም በግብረ-ገብና በዜግነት ትምህርቶች በግልፅ እና ትርጉም ባለው ደረጃ መካተታቸውን ለማረጋገጥና በተጓዳኝ የትምህርት ዘርፎች እንዲሰጥ ማድረጉ ላይ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
በተጨማሪም በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት ሥራ ላይ ያሉ ሥርዓተ ትምህርቶችና የሥልጠና መጻሕፍት ይዘት በተሟላ መንገድ የሰብዓዊ መብቶችን ፅንሰ ሃሳብና መርሆችን እውቀት የሚያስጨብጥ መሆኑን ለማረጋገጥ እና በየዓመቱ ኮሚሽኑ የሚያካሂደውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምስለ ፍርድ ቤት (moot court) ውድድር በተመለከተ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ ነው። ለዚህም መብትና ግዴታውን መለየት የሚችል ማኅበረሰብ መፍጠር ይገባል። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በተማሪዎች በኩል ሲሆን፤ ተማሪዎች የሰብዓዊ መብት ትምህርቶችን እውቀት ኑሮ እንዲያደርጉት መሥራት ያስፈልጋል። ስለሆነም በመንግሥት ደረጃ ይህንን ለማድረግ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ያላሰለሰ ተግባር ይከናወናልም ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ።
የሰብዓዊ ትምህርት ተማሪዎች፤ መምህራን፤ ሠራተኞች፤ ወላጆችና መላው ኅብረተሰብ የሚሳተፍበት አዎንታዊ ከባቢን የሚፈጥር ትምህርት ነው። ቅሬታዎችን በፍትሐዊነት ለመፍታት የሚያስችል፤ ከሁከትና ከማንኛውም የፀጥታ ችግር ነጻ የሆነ የመማር ማስተማር ሥራን የሚፈጥር፤ ሰላም የሰፈነበት አካባቢን ብቻ ሳይሆን መንደርን ጭምር ለመፍጠር እድል የሚሰጥ ነው። ከዚያም ባሻገር ተማሪዎች በዚህ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ማለፋቸው ለትልቅ ዓላማ መዘጋጀት እንዲችሉ፤ ሰውንም ሆነ ሀገር ወዳድ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሰው ደራሽነትን እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል ያሉት ደግሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዋናነት ከትምህርቱ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፤ ለሰብዓዊ መብቶች ትምህርት ማስተማሪያ የሚሆኑ፣ ለመምህራንም ሆነ ለተማሪዎች የሚያገለግሉ የተለያዩ ደጋፊ ጽሑፎች የሚገኙበትን የመረጃ ቋት (ዳታ ቤዝ) ያዘጋጃል። ትምህርት ቤቶች በመደበኛውና በተጓዳኝ ሥርዓተ ትምህርቶች ሰብዓዊ መብቶችን በማስረፅ የዕለት ተዕለት የትምህርት ሂደቱ አካል አድርገው የሚሠሩ እንዲሆኑ ለመደገፍ ይሠራል። በየዓመቱ የሚካሂደውን ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምስለ ፍርድ ቤት ውድድር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በስምምነቱ ወቅት ያሉት ሀሳብ ነበር።
የሰብዓዊ ትምህርቱ ዋነኛ ዓላማ የሰብዓዊ መብት እሴቶችና መርሆችን ተገንዝቦ በእለት ተለት ግንኙነቱና በባሕርይው የሚያንፀባርቅ ትውልድ መፍጠር፤ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብን በመከባበር፣ በመቻቻልና በመግባባት አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ ነው። ለሰላምና አብሮ ለመኖርም ሁነኛ መንገድን መክፈት ነው። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ ሥራ አለመሥራት ሀገራችን ያለችበትን የሰብዓዊ መብቶች ፈተና ማባባስ ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በሀገራችን ያለው መጠነ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ ቀውስ የሚታከመው በእነዚህ ሥራዎች እንደሆነ ይገልጻሉ። የሰብዓዊ መብት ፈተናን ለማለፍ ትውልዱን በዚህ ትምህርት ማነጽና በሕይወቱ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚያስፈልግም አበክረው ይናገራሉ።
ትምህርቱ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባና ሥራው መጠነ ሰፊ ተግባርን የሚጠቅም በአጭር ጊዜ ለውጡን ማየት የማይቻልበት ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች የዚህ ዓይነት ፀባይ ያላቸውና የረጅም ጊዜ ራዕይ የሚጠይቁ ናቸው ጅማሮው እውን እንደሚሆንም እምነት አላቸው።
ክብር ያለው፣ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋን ለመፍጠር ሁነኛው መፍትሔ ተማሪዎችን ከታች ጀምሮ በሰብዓዊ ትምህርት ዙሪያ ቀርጾ ማሳደግ ሲቻል እንደሆነ የሚያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብዓዊ ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ዶክተር መቅደስ ታደለ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኃላፊነት ለራስ ባሕርይ ተጠያቂ በመሆን ታማኝነትን ማረጋገጥ አለበት። ይህ ደግሞ በቃልም በተግባርም ይተረጎማል። ስለዚህም በትምህርታቸው ውስጥ ለሌሎች ደህንነት መቆርቆርን፤ ፍትሐዊነትና ያለ አድሎ ማገልገልን እየተማሩት ብቻ ሳይሆን እየኖሩት እንዲሄዱ ይደረጋል። ይህ ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማውና ደፋር ያደርጋቸዋል። ሕሊናቸውን ተከትለው የሚሠሩ ልጆችም እንዲሆኑ ዕድል ይሰጣቸዋል።
በተማሩት ትምህርት ለችግሮች ትክክለኛ መፍትሔ ሰጪ፣ ፅናትን የተላበሱና ተስፈኛ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል። እንደ ሀገርም ቢሆን የራሱን መብት እስክብሮ የሌላውን መብት አክባሪ ዜጋ እንዲበራከት የሚያደርግ ነው። መብትና ግዴታውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዜጋን በስፋት እናገኝበታለን። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቀላሉ ሁሉም ዜጎች ጋር መድረስ ያስፈልጋል። ለዚህ ዋናው መንገድ ትምህርት ነው። ከተማሪዎች እስከ መምህራን ከቤተሰብ እስከ ጎረቤት ድረስ መድረስ ይቻላል። የማኅበረሰቡን አዕምሮ በመቀየር በኩልም ሚናው ከፍ ያለ ነው።
ስምምነቱ የሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን ወደ ማኅበረሰቡ ከማስረፅ አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ተደራሽነትን በመጨመር ረገድም በኢትዮጵያ ዘላቂና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሰብዓዊ መብቶች ባሕልን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። በተለይም ተማሪዎች ስለእኩልነት፣ ሰብዓዊ ክብር፣ ፍትሐዊነት፣ ሰላም፣ መከባበርና ኃላፊነትን መውሰድ እንዲሁም በእውቀት የዳበረ ልምድ ለማግኘት ብዙ አማራጮችን እንዲያዩና እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የሰብዓዊ መብቶች እሴቶች መገለጫ የሆኑ የባሕርይና የአመለካከት ለውጦችን እንዲያመጡም ያደርጋቸዋል ይላሉ ዶክተር መቅደስ።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ሥልጠና መግለጫ እንዳስቀመጠው፤ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ስልጠና በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን የእድሜ ልክ ሂደትም ነው። ስለዚህም ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች መድረስ አለበት።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ይህ የሰብዓዊ ትምህርት የመስጠት ስምምነት በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ ተካቶ የሚሰጥ ነው። በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲጠናከርና እንዲስፋፋም ይደረጋል። የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በተጓዳኝ የትምህርት መንገዶች በተለይም በክበቦች እና በሌሎች የማስተማሪያ ማዕቀፎች ውስጥ በማካተት ለተማሪዎች የሚደርስም ነው። በተጨማሪ ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር መሥራት የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎችን እንደያዘ በስምምነቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፤ ቃል በተግባር ይዋል በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ አበቃን።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም