የኢትዮጵያ አርሶ አደር የእለት ኑሮውንም ሆነ የዓመት ጉርሱን የሚያገኘው ዓመት ጠብቆ ከሚያገኘው ምርት ነው። ለግብርና ልማቱ ከሚያስፈልገው በተጨማሪ ሠርግም ሆነ ማኅበር የሚደግሰው፣ ሕክምናውንም የሚያደርገው፣ ሌሎችንም ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያከናውነው በግብርና ምርቱ ነው። ይህ በመሆኑም ምርቱን አቆይቶ በደህና ዋጋ ለመሸጥ ዕድል አያገኝም።
ጠንካራ አርሶ አደር ካልሆነና ሰፊ የእርሻ መሬት ከሌለው የዓመት ቀለቡን እንኳን ለመሸፈን ይቸገራል። አብዛኛው አርሶ አደርም በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ስለመሆኑ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል። አርሶ አደሩ በዓመት ከሚያከናውነው የግብርና ሥራ ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ሥራ የመሥራት ባሕል ባለማዳበሩ ለሥራ የደረሱ ልጆቹም ቢሆኑ ሥራ ፈጣሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
የምንገኝበት ዘመን ደግሞ በዓመት በማምረት ፍላጎትን ለማሟላት ቀርቶ ቀለብንም ለመቻል አስቸጋሪ የሆነበት ነው። ለዚህም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች አርሶ አደሩ በቀደመው ዘመን ይዞት የመጣውን የሥራ ባሕል መቀየር እንዳለበት፣ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ልማቶች ላይም ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ የሚመክሩትና አቅጣጫ የሚሰጡት።
መንግሥትም በዚህ ረገድ ልማትን ከሚደግፉ አጋሮች ጋር በመሆን አርሶ አደሩን እያበረታታ ይገኛል። በቅርቡ የተተገበረው የሌማት ትሩፋትም ለእዚህ በሁነኛ አብነት ሊጠቀስ ይችላል። አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ከብት በማርባት፣ በወተት ልማት፣በንብ ማነብና በሌሎችም በሚያከናውናቸው ተጓዳኝ ገቢ ማስገኛዎች ተጠቃሚ ለመሆን ያስችለዋል።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሰፊ የሥራ ዘርፍ ያለው ግብርናው በመሆኑ አርሶ አደሩም ሆነ ልጆቹ ከዓመት ዓመት ያልተቋረጠ የግብርና ሥራ በማከናወን ተጓዳኝ በሆነ ልማት የሚሠማሩበት እድል እየተመቻቸ ይገኛል። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ተገኝተን ይህንኑ ጥረት ተመልክተናል።
በወረዳው አነስተኛ መሬት ያላቸው፣ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነና ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩ በማኅበር የተደራጁ ወጣቶች ወረዳው ባመቻቸላቸው የእርሻ መሬት ላይ ስንዴ፣በቆሎ፣ቦሎቄ እያፈራረቁ ያለማሉ፤ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙም ናቸው።
ከዚህ በተጓዳኝ በተሰጣቸው የመሥሪያ ቦታ ላይ ደግሞ ለሐር ልማት የሚውል ጉሎ በመትከል ቅጠሉን ለሐር ትል በማዋል ወደ ሐር በመቀየር፣ ሸጠው ገቢ ያገኛሉ። የጉሎው ፍሬም ለገበያ ውሎ ተጨማሪ ገቢ ይሆናል። ወጣቶቹ በዚህ መንገድ ኑሮአቸውን ለመለወጥ ጥረት ሲያደርጉ ለመመልከት ችለናል።
እንዲህ ያለው የአካባቢው ወጣቶች ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ደግሞ ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በጋራ በትብብር የሚሠራው ዓለምአቀፍ ስነ ነፍሳትና ሳይንስ ሥነምሕዳር ማዕከል(ኢ ሲ ፒኤ) የሥልጠና፣ የቁሳቁስና የክትትል ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል። ይህ የተመቻቸው የገቢ ማስገኛ የልማት መርሐ ግብር ሴት አርሶ አደሮችን የበለጠ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሆነም መገንዘብ ችለናል።
ከማኅበሩ ተጠቃሚዎች መካከል ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ራዲያ ነሻህ እንደገለጹት፤ 36 ወንዶችና 64 ሴቶች ሆነው ነው በ2012ዓም በማኅበር ተደራጅተው ወደ ልማቱ የገቡት።ወረዳቸው በአጠቃላይ ለልማቱ የሰጣቸው ሰባት ሄክታር መሬት ሲሆን፣ከዚህ ውስጥ አራቱን ሄክታር ስንዴ፣በቆሎ፣ቦለቄ፣አትክልትና ፍራፍሬ እያፈራረቁ በማልማት ይጠቀማሉ።በቀሪው መሬት ላይ ደግሞ ለሐር ልማቱ የሚሆን ጉሎ መትከያ፣እንዲሁም የሐር ትል ልማት ለሚያከናውኑበትና የመሸጫ ቤት ሠርተውበታል። ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡበት ወቅት ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ የተስፋፋበት ጊዜ በመሆኑ የተጠናከረ ሥራ አልሠሩም። ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ግን በስፋት በመንቀሳቀሳቸው ለውጤት የሚያበቃ ተስፋ አግኝተውበታል።
‹‹ከልማቱ የሚወድቅ ነገር የለም። ሁሉም ገቢ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ራዲያ እንደገለጹልን፤ ለሐር ትል የሚውለው የጉሎ ቅጠሉን ለትሉ ምግብነት ካዋሉ በኋላ ፍሬውን ለገበያ በማዋል ገቢ ያገኙበታል። ትሉን ወደ ሐር ከቀየሩ በኋላም ፈትለውና አዳውረው ነው ለገበያ የሚያውሉት። ከእርሻ መሬታቸው ያገኙት ምርት ተጨምሮ በአጠቃላይ በያዝነው በጀት ዓመት ከ230ሺ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል። ይህም ጠንክረው በመሥራታቸው ያገኙት ውጤት እንደሆነም ወይዘሮ ራዲያ ተናግረዋል። አምና 90 ሺህ ብር እንዳገኙ ነው ያስታወሱት።
ልማቱ በአጠቃላይ መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ወይዘሮ ራዲያ ይገልጻሉ። እሳቸው እንደተናገሩት፤ በልማቱ የተሻለ ገቢ በማግኘታቸው በመበረታታት ወደፊት በስፋት ለማልማት ለመስኖ ውሃ መሳቢያ ሞተር(ፓምፕ) ገዝተዋል። ከወረዳ በብድር የወሰዱትንም የስንዴ ዘር መመለስ ችለዋል።
ጠንክሮ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግ እንዳዩበትና ያለሥራ ያባከኑትን ጊዜ በቁጭት ይገልጻሉ። በትምህርታቸው 12ኛ ክፍል ደርሰዋል። ትምህርት ለመቀጠልም ሆነ ሥራ ተቀጥረው የመሥራት እድል አላገኙም፤ ትዳር መሥርተው እየኖሩ ናቸው።
ያላቸው የእርሻ መሬት አነስተኛ በመሆኑ የቤተሰብ ፍላጎት ለማሟላት አላስቻላቸውም። አሁን ላይ ግን ከሌሎች ጋር በመሆን በተጓዳኝ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ መሆናቸው ለወደፊት ኑሮአቸው እንደሚሻሻል ተስፋ አድርገዋል። ቤተሰቦቻቸው ከግብርናው ጎን ለጎን እንዲህ ያለ ተጓዳኝ ሥራ ሠርተው ቢሆን፣ የአምራች ደሀ አይሆኑም ነበር ይላሉ። ወቅትን ጠብቀው አንድ የምርት አይነት ላይ በመወሰናቸው እንደተጎዱም ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ ራዲያ፤አሁን እያከናወኑት ያሉት የሐር ልማትና የግብርና ሥራ ብዙ ድካም ይጠይቃል። በተለይም የሐር ልማቱ ለአካባቢው አዲስ በመሆኑ ብዙዎች ፍላጎት አላደረባቸውም። ተስፋም አላደረጉም። በዚህ ምክንያት በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራው ከገቡት አንድ መቶ አባላት መካከል ወደ 30 የሚሆኑት አቋርጠዋል። ከ36 ወንዶች የቀሩት ሦስት ብቻ ናቸው።
ተስፋ ያልቆረጡት የቀሩት ተሞክሮ ለማግኘት አርባ ምንጭ ድረስ ሄደዋል። የግብርና ሥራውን የትዳር አጋሮቻቸው እንዲያግዟቸው በማድረግ ነው ተጠናክረው የቀጠሉት።
ፈትለውና አዳውረው ያዘጋጁትን ሐርም ለገበያ ለማቅረብ በአዲስ አበባ ከተማ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸው የነገሩን ወይዘሮ ራዲያ፤ የምርቱ ሁኔታ ቋሚ እንዳልሆነና በደንብ ምርት የሚገኘው በሙቀት ወቅት እንደሆነ ነው የገለጹት።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ቅዝቃዜ ለትሎቹ ምቹ አይደለም። በዚህም ምርቱ አንዳንዴ ይቀንሳል። አቅም እየፈጠሩ ሲሄዱና እርዳታም ማግኘት ከቻሉ በኤሌክትሪክ ኃይል በመታገዝ በዘመናዊ መሣሪያ ለመጠቀም እቅዱ አላቸው። ፈትለው ያዘጋጁትን ሐርም ወደ ልብስ የመቀየር እቅድ አላቸው። እቅዳቸውም ወደፋብሪካ ደረጃ የማሳደግ ነው። እንዲህ ያለውን ትልቅ ተስፋ ለመጣል አሁን ኢ ሲ ፒኤ በክህሎትና በተለያየ እገዛ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍና ወረዳውም አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ከጎናቸው በመሆኑ እንደሆነም አጫውተውናል።
በዓለምአቀፍ ሥነ ነፍሳትና ሳይንስ ሥነምሕዳር ማዕከል(ኢ ሲ ፒኤ) የኦሮሚያ ክልል ሞይሽ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ተሾመ ኩመላ፤አጠቃላይ የልማቱን እንቅስቃሴና ፤፤ለሐር አልሚዎቹ እየተደረገላቸው ስላለው ድጋፍ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ከመንግሥት ጋር በመሆን እያደረገ ባለው በዚህ ድጋፍ ሥራ በአምስት ዓመት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ለአንድ መቶ ሺ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ 25 በመቶ የሚሆነው የሥራ ዕድል ለመፍጠር የታቀደው በሐር ልማት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም እያለ ነገር ግን ያልተሠራበት የሐር ልማት እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ተሾመ፤ይህን መሠረት በማድረግ ተቋማቸው ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በተከናወነ ጥናት ወደ ልማቱ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል። የሐር ልማት ሞቃታማ አካባቢዎችን የሚፈልግ እንደሆነና ኢ ሲ ፒኤም በሞይሽ ፕሮግራሙ፤አንዱ የመረጠው አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ አዳሚቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ተሾመ ማብራሪያ፤ በወረዳው የልማቱ ሥራ ከተጀመረ ሦስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን፤ከወረዳው ግብርና፣ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጽሕፈት ቤቶችና ከመልካሳ ግብርና ምርምር ጋር ነው የሚከናወነው። ወደ ልማቱ ማስገባት የተቻለውም 42 የወጣቶች ቡድኖችን ነው። እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ ተጠናክረው የቀጠሉት 32 ቡድኖች ናቸው። እነሱም ውጤታማ መሆን ችለዋል።
በቡድኑ ውስጥ የሚገኙት ወጣቶችም ከ18 እስከ 34 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ፣80 በመቶ ሴቶች የሚገኙበት ነው። ኢ ሲ ፒኤ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ሥልጠና በመስጠት፤ የሐር ትሎችን የሚያራቡበት ቤት በመገንባት፣ ትሎቹ የሚራቡባቸውን ግብዓት በማቅረብ፣ሐር የሚፈትሉበትና የሚያዳውሩበትን መሣሪያና የሚያራቧቸውንም ትሎች በማቅረብ እንዲሁም ለትሎቹ የሚሆን የጉሎ ዘር በመስጠት ነው ወደልማቱ ያስገባቸው። በማዕከሉ ባለሙያዎችም ያልተቋረጠ ክትትል ይደረግላቸዋል። በአሁኑ ጊዜም አልሚዎቹ የትሉን እንቁላል ደረጃ ጠብቀው ወደ ሐር እስከሚቀየር ያለውን ሂደት ተከትለው የሚሠሩበትን ክህሎት በማግኘታቸው ራሳቸውን ችለው በመሥራት ውጤት ላይ ደርሰዋል።አንድ ኪሎ የሐር ጥጥ እስከ 400 ብር ዋጋ ያለው እንደሆነ፣ወደ ክር ሲቀይሩ ደግሞ በኪሎ እስከ 1400ብር እንደሚያወጣ እና ይህም ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው አቶ ተሾመ አመልክተዋል።
ዓመቱን ሙሉ የሐር ልማት ላይ ብቻ ይቆያሉ ማለት እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ተሾመ፤ ወረዳው ባመቻቸላቸው የእርሻ መሬት ላይ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነጭ ቦሎቄ እንዲያመርቱም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። ቦሎቄውን ከዘር አቅራቢ ድርጅት በመውሰድ እንደሚያመርቱና አንዴ ያመረቱት ቦሎቄም ውጤታማ እንዳደረጋቸው አመልክተዋል። በመቀጠልም ስንዴ እንዳለሙ ጠቁመዋል።
እስካሁን ያካሄዱት ልማትም ወደ ገንዘብ ሲቀየር ከፍተኛ እንደሆነና አንድ የመንግሥት ተቀጣሪ በወር ከሚያገኘው እንደማይተናነስም ገልጸዋል። ይህም በጅምር ውጤት የሚታይ እንጂ የበለጠ በሠሩ ቁጥር ውጤታማነታቸውም አብሮ ከፍ እንደሚል አስረድተዋል። በተጨማሪም በሥራ ባህል ውስጥ እንዲያልፉ መደረጉ በራሱ ውጤታማ እንደሆነ ነው የገለጹት።
በኢስፒኤ ሞይሽ ፕሮግራም በጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ አራት ቀበሌ ውስጥ ባለሙያ ተቀጥሮላቸው ድጋፍ እያገኙ እንደሆነና የበለጠ ውጤት እንደሚጠበቅም ገልፀዋል። በኦሮሚያ ክልል በሐር ልማት ለአንድ ሺ340 ወጣቶች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም አስታውቀዋል።
የልማቱ ተሳታፊዎች የቁጠባ ባሕልንና ራስን የመቻል ልምድ እንዲያዳብሩም ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ወደ ልማቱ ከመግባታቸው በፊት የሥልጠና ክህሎት ሲሰጣቸው ከሚያገኙት የውሎ አበል ላይ እንዲቆጥቡ በማድረግ ጭምር የቁጠባን አስፈላጊነት ተገንዝበው አሁን ላይ ከልማት ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ እንዲቆጥቡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
በዚህ የልማት ሥራ ውስጥ ስኬቶች እንዳሉ ሁሉ ተግዳሮቶችም ስለማይጠፉ የነበሩትን ክፍተቶችም አቶ ተሾመ ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ የሐር ልማት ለብዙዎች አዲስና አንድ የግብርና አካል አድርጎ አለማየት በመኖሩ ፈጥኖ ተቀባይነት ለማግኘት በጅምሩ ላይ ችግር ሆነ ነበር። በሂደት ሲለመድ ግን እየቀነሰ ይሄዳል።
በተለይ ደግሞ የሐር ትል ቅዝቃዜ የማይችል በመሆኑ ፈታኝ ስለሚሆን ተስፋ መቁረጥ ያጋጥማል። ጥቅሙን እያዩ ከሄዱ በኋላ ግን ትሎቹን ቤታቸው ውስጥ በማድረግ ጭምር ችግሮችን ለመቋቋም ጥረት ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ጊዜ ውስዶ ለመሥራት ትዕግሥት አለመኖርና ቶሎ ትርፋማ ለመሆን የመፈለግ ሁኔታዎችን ያጋጥማሉ።
መልካሳ ምርምር ማዕከል በሐር ልማቱ ላይ እያደረገ ስላለው እገዛም አቶ ተሾመ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ለሐር የሚሆነውን ትል እንቁላልና የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን በማቅረብ፣ ተመራማሪዎችም ሥራውን በመከታተልና ምርምር በማደረግ፣ለሥራው የሚያስፈልጉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ እያገዘ ይገኛል። በተለይም ከሐር የሚሠራ አልባሳት በዓለም ገበያ ተፈላጊና በዋጋም ውድ እንደሆኑ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። በመሆኑም ልማቱ ተጠናክሮ ቢከናወን በልማቱ የሚሳተፉትን ይበልጥ ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለሀገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም