ስለ ሀገር የተጠበቡ ጠቢባን ሀገርና ሰውነትን በአንድ መርፌና ክር ይሰፉታል። እውነት ነው ሀገርና ሰውነት ከዚህ የተሻለ እውነት የላቸውም። ሰውነት ከሀገር ጋር ሀገር ከሰውነት ጋር የተቆራኙ የአንድ ማንነት ሁለት መልኮች ናቸው። ሰው ከሌለበት ሀገር ትርጉም የለውም። ፍቅር ከሌለበት ሀገር ሙቀት የለውም። ሰላም ከሌለበት ሀገር ጣዕም የለውም። ሀገርን ሀገር ያደረጉት ሰው እና ከሰውነት ቀጥለው የሚመጡ የአብሮነት መንፈሶች ናቸው።
ከዚህ ጽንሰ ሀሳብ በመነሳት አብሮነታችን ለኢትዮጵያ ያለውን ዋጋ መቃኘት እንችላለን። ልክ እንደ ዓድዋ የአንድነታችን ዋጋ የሚገለጽበት ብዙ ሀገራዊ ኩነቶች አሉ። ልክ እንደ ህዳሴ ግድባቸውን ብዙኃነታችን የሚያስፈልግበት ምዕራፍ አለ። እንደ ሀገር ተስፋ ሰንቀን እየኖርን ነው..የመልማትም ሆነ የማደግ ተስፋዎቻችን ፍሬ የሚያፈሩት በአንድነት ስንቆም ነው። ለዘመናት ከተዋረድንበት የድህነት ነቀርሳ ለመሻር በእኔ ውስጥ እናንተ፣ በእናንተ ውስጥ እኔ መብቀል አለብን።
በተናጠል የቆመች ሀገር የለችም። ተያይዘንና ተደጋግፈን ነው ከትላንት ዛሬን ያየንው። በእኔ ውስጥ እናንተ በእናንተ ውስጥ እኔ በቅዬ ነው ኢትዮጵያዊ የተባልነው። ይሄን እውነት ለመረዳት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ ማየቱ በቂ ነው። ኢትዮጵያ የቆመችው በብዙ እጆች ተደግፋ ነው። ኢትዮጵያ ያማረችው በብዙ መልኮች ተውባ ነው። ይሄ ውበት፣ ይሄ ድምቀት ደግሞ በጋራ የመቆም ውጤታችን ነው።
በችግሯ ሰዓት ሆ ብለን የምንነሳው የኢትዮጵያ ጉዳት የእኛም ጉዳት ስለሆነ ነው። እንደ ሕዝብ ተነካክተንና ተጠጋግተን ተሳስረንም እየኖርን የብቻ ሠርግና መርዶ የለንም። ደስታና ኃዘናችን የጋራችን ነው። በጋራ እየኖርን እኔ ላይ ካልደረሰ የምንለው ነገር የለም። ጉዳያችን ሰላም ከሆነ ሰላም ለማምጣት የአንድነት ሀሳብ ያስፈልገናል። ጉዳያችን ዲሞክራሲ ከሆነ ከመንግሥት ጋር ተቆራኝተን ዲሞክራሲን ሕያው ማድረግ ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያ ለአንድ ወገን የምንተዋት አይደለችም። መንግሥት ብቻውን ምንም አያደርጋትም። አንድ ሰው..አንድ ቡድን ..አንድ ፓርቲ አይችላትም። በጋራ ካልሆነ፣ በአብሮነት ካልሆነ ጥያቄዎቻችንን መመለስ አንችልም። በመነጋገር ካልሆነ፣ በመተሳሰብ ካልሆነ ሕልሞቻችንን መውለድ አንችልም። አሁን ላይ በሰላም እጦት እየተሰቃየች ያለችው ለብቻ የተውናት ኢትዮጵያ ናት።
እንደ አብሮነታችን ሁሉ ሰላማችንን የምንመልሰው በአብሮነት ነው። በመልካሙ ጊዜ አብረን ቆመን በችግር ጊዜ የምንለያይ ከሆነ ሀገርና ሰውነት ያልኳችሁ የአብሮነት ቅኔ ልክ አይመጣም። ሀገር በእኛ ውስጥ፣ እኛም በሀገር ውስጥ ነው ልክ የምንሆነው። ኢትዮጵያ የሚል..ከብሔርና ከእኔነት የራቀ የጋራ ስም አለን። በዚህ ስም ስንጠራ ለዘመናት ኖረናል። ይሄን ስም ከፊት አድርገን ብዙ መሰናክሎችን ተራምደናል። አሁንም ሰላማችን እንዲመለስ ከአፋችን ላይ የጠፋውን ይሄን ስም መመለስ አለብን። ውበታችን የሚደበዝዘው ስንራራቅ ነው። አንድነታችን የሚላላው ኢትዮጵያዊነትን ትተን አማራ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ..ትግሬ ነኝ ስንል ነው።
ይብዛም ይነስም ዓለም ላይ የተነሱ ግጭቶች መነሻቸው እኔነት ነው። መነሻቸው ከሀገር በላቁ የብሔር ስሞች የመጣ ነው። እኛም ሀገር በአብዛኛው ያጋጠሙን የሰላም እጦቶች ምክንያታቸው ይኸው ነው። የሚያምርብን ዓድዋን የፈጠረ የአንድነት ስማችን ነው። የሚያምርብን ዓባይን የገደበ የኢትዮጵያዊነት መልካችን ነው። ዓድዋ የማን ታሪክ ነው?..የህዳሴ ግድብ የማን አሻራ ነው? መቼም የአማራና የኦሮሞ ወይም የትግራይ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ።
ዓድዋም ሆነ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊነት የፈጠሩት..የጋራ እጆቻችን ናቸው። ኅብረትና አንድነት የፈጠሩት የኢትዮጵያዊነት መልክ ነው። ከዚህ ውጪ ስም የለውም። ሰላምም..ልማትም እንዲህ ነው..የእኔ የአንተ እየተባባልን የምንፈጥረው ሰላም፣ የምናመጣ ለውጥና ብልጽግና የለም። የእኔ የአንተ እየተባባልን የምንፈጥራት የጋራ ኢትዮጵያ የለችም። በእኔ በአንተ መባባል ውስጥ ልዩነት እንጂ አንድነት የለም። ”የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ” እንደሚባለው በተፎካከርን ቁጥር ኢትዮጵያን እያራቆትናት፤ በተፎካከርን ቁጥር ድህነትን እየተለማመድንው ነው እንሄዳለን ።
ለነገሩ ድህነትን ከተለማመድነው ቆየን..ከመለማመድም አልፈን ድህነት ሲነሳ አብሮ ስማችን የሚነሳባቸው ብዙ አጋጣሚዎችን አስተናግደናል። ይሄ አስጸያፊ ማንነት ከሀገር በፊት ባስቀደምናቸው ድሪቶ ጉዳዮቻችን የተፈጠረ ነው ። ይሄ ነውር በፉክክር ሳንዘጋው ያሳሰርነው የኢትዮጵያ ጉዳይ የወለደው ነው። ከድህነትም ሆነ ከኋላ ቀርነት ለመውጣት አንድ አቋራጭ መንገድ ብቻ አለን እርሱም ኢትዮጵያን ማስቀደም ነው።
ከሀገር ትልቅ ነገር የለንም። ከሀገር የበለጠ ውብ ነገር አልተሰጠንም። ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል፣ ለሁላችንም አንድ ዓይነት መልክ ያላት ነች። ፖለቲካችን ውስጥ የሚፈጠረው የሀሳብ ልዩነት ኢትዮጵያን የሚያደምቅ እንጂ የሚያደበዝዝ መሆን የለበትም። ማኅበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ የሚፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶች በኃላፊነት ስሜት ለኢትዮጵያ ከመቆርቆር የመነጩ መሆን ይገባቸዋል።
እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን ያደመቀ የፖለቲካ ሥርዓት አላየንም። እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያን የጠቀመ የፖለቲከኞች ውሕደት አላየንም። ሁሉም ሥርዓት፣ ሁሉም ውሕደት ኢትዮጵያ እንዳለችበት የሚናገር ነው። ፍጻሜው ግን የሆነ ቡድንን፣ የሆነ ብሔርን፣ የሆነ ፓርቲን የሚጠቅም ሆኖ የሚጠናቀቅ ነው። ይሄ አካሄድ ፖለቲካችንን ነውጥ ፈጣሪ፣ ማኅበረሰባችንን ደግሞ ሰላም ፈላጊ አድርጎ እዛና እዚህ አስቀምጧቸዋል። ይሄ አካሄድ ኢትዮጵያዊነትን ሽሮ የብሔር አስተሳሰብን ፈጥሯል።
መቼም የትም ኢትዮጵያ ያለችበት ፖለቲካና ሀሳብ ነው የሚያስፈልገን። ሕዝብ የቀደመበት፣ ትውልድ የታሰበበት ሥርዓትና ውሕደት ነው የሚጠቅመን። ሰላሞቻችን የሚመጡት፣ ተስፋዎቻችን የሚሰምሩት በዚህ መንገድ ላይ ስንራመድ ብቻ ነው። በድምቀቷ ውስጥ እንዳለን ሁሉ በኢትዮጵያ መደበዘዝ ውስጥ ሁላችንም እንጸልማለን። ከጽልመት የሚያወጡን ደግሞ ከብሔር የራቁ የአንድነት ታሪኮች ናቸው። ልክ እንደ ዓድዋና፣ እንደ አምባላጌ፣ እንደ ካራማራና እንደ ኦጋዴን አይነት የጋራ ታሪኮች።
አንድ ነን..በየትኛውም አጉሊ መነጽር እዩት ከአንድነት ውጪ ሌላ ትርጉም የለንም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአንድ ገመድ የታሰረ ብዙ ፍልጥ ነው። ያ ሁሉ ብዙ ዓይነት ፍልጥ በአንድ ልጥ ነው የታሠረው። ፍልጡ እኛ ነን..ፍልጡ ብዙኃነታችን ነው። ፍልጡ መልክ፣ ቋንቋ፣ ብሔራችን ነው። ፍልጡ ወግ ባሕል ሥርዓታችን ነው። ፍልጡ ታሪክ ትውፊታችን ነው። ይሄ ሁሉ ድብልቅልቅ ማንነት ደግሞ ኢትዮጵያዊ በሚባል በአንድ ልጥ ታስሯል።
ይሄ ነው ማንነታችን..ከዚህ ውጪ እኔና እናንተ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትርጉም የለውም። ከሀገር ብሔርን ስናስበልጥ፣ ከአንድነት መለያየትን ስናስቀድም የታሰርንበትን የኢትዮጵያዊነት ልጥ እያላላን ነው። ስንፎካከር፣ በራስ ወዳድነት ስንቆም የታሰርንበትን የኢትዮጵያነት ልጥ እየገዘገዝን ነው። የታሰርንበት ገመድ ተፈታ ማለት ኢትዮጵያዊነት ተበተነ ማለት ነው። እንዳንበተን ተፋቅሮ መኖርን እንልመድ። ልጣችን እንዳይላላ በሰላምና በእርቅ መኖርን ባሕል እናድርግ።
እኔ እናንተን ነኝ..እናንተም እኔን ናችሁ። የሆነ ነገራችሁ እኔጋ አለ..የኔም የሆነ ነገሬ እናንተ ጋ አለ። ተወራርሰን..ተዋሕደን የቆምን ሕዝቦች ነን። ይሄ ማንነት ሰላምን የፈጠረ፣ አንድነትን የጸነሰ ማንነት ነው። ይሄ ማንነት ለዓለም ኩራት የሆነች፣ ለአፍሪካ መድኅን የሆነችን ኢትዮጵያ የፈጠረ ነው። እናም በእኛ ውስጥ..እናም በእኔና በእናንተ ውስጥ የሚያምርብን ሰላምና አንድነት ብቻ ነው።
ሰላም እንደ እኔና እንደ እናንተ የሚያምርበት የለም። ፍቅር እንደ ኢትዮጵያዊነት የሚደምቅበት የለም። አንድነት እንደ ሀበሻ የሚዋብበት የለም። መለያየት በጣም ያስጠላል.. እኛ ላይ ደግሞ እጅግ በጣም ያስጠላል። ምክንያቱም ተዋደን የቆምን፣ ተፋቅረን ከዛ እዚህ የመጣን ሕዝቦች ስለሆንን።
ሀገር ከእኔና ከእናንተ ውጪ ትርጉም የላትም። የሀገር ሕልውና በእኛ ፍቅር ውስጥ ነው ያለው። የእኛ ሕልውና ደግሞ በሀገር ሉዓላዊነት ውስጥ የሚገለጥ ነው። እኛና ኢትዮጵያ ላንለያይ የተጨባበጥን፣ ላንለያይ የተዋሓድን ነን ። ይሄ ውሕደታችን ትላንት ላይ ባለታሪክ እንዳደረገን ዛሬም ያስፈልገናል። ይሄ መጨባበጣችን ትላንት ላይ ሰላም ፈጣሪዎች እንዳደረገን ዛሬም ሰላም ላጣንው ለእኛ ያስፈልገናል።
ሀገር የእንጀራ ሌማት ናት..ሰንበሌጥና ስንደዶ፣ አለላና አክርማ ያሳመሯት። ብዙ ዓይነት መልኮች፣ ብዙ ዓይነት ውበቶች ያቆነጇት። ሀገር የወርቅ ሙዳይ ናት..ደማቅ ቀለሞች የቀለሟት። እኛም የሀገራችን ውበቶች ነን። ኢትዮጵያ የቆነጀችው በእኔና በእናንተ በሌላውም ሰው ባሕልና ወግ፣ ልማድና ሥርዓት ነው።
የእኛ ባሕልና ወግ፣ ልማድና እምነት የኢትዮጵያ ውበቶች ናቸው። እንደ እንጀራ ሌማት በውበትና በደምግባት ያቆነጀናት እኛ ነን። ብዙኃነታችን ሀገራችንን ደግፎ ያቆመ የመሠረት ድንጋይ ነው። በብዙኃነታችን ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ልዩነት ሀገራችንን የሚነቀንቅ ነው። የአንዳችን አለመኖር ኢትዮጵያን ያደበዝዛታል። የአንዳችን መጉደል ኢትዮጵያዊነትን ያጠይሙታል።
እነሆ ታላቅ እውነት..ሀገር ማለት እኔ፣ እናንተና ሌላውም ሰው ነው። እነሆ ታላቅ ጥያቄ..ሀገር ማለት እኔ አንተና ሌላው ሰው ከሆነ እኔ በአንተ ውስጥ፣ አንተ በኔ ውስጥ መኖር እንዴት አቃተን? ሀገር ማለት እኔ አንተና ሌላው ሰው ከሆነ በተወራረስናቸው ባሕልና ወግ፣ ልማድና ሥርዓት ፍቅርን መስበክ እንዴት ተሳነን? በእኔ ውስጥ አንተ በአንተ ውስጥ እኔ ከጎደልን እኮ ሙሉዎች አይደለንም።
እኔ ባለ ሀገር የሆንኩት በአንተ መኖር፣ በአንተ ወንድምነት ነው። እናንተም፣ ባለሀገር የሆናችሁት በእኔ መኖር፣ በእኔ ወንድምነት ነው። እኔና አንተ ከሌለን ኢትዮጵያ አትኖርም። በአጉል እምነት ኢትዮጵያዊነት ከብሔር እንዳያንስ ለስሜታችን ልጓም እናብጅለት። በአጉል እምነት ራስ ወዳድነታችን ከወንድማማችነታችን እንዳይገዝፍ ልከኛ እንሁን።
በተጓዝንው ስር የሰደደ የእኔነት ልክፍት ሰላማችንን ተነጥቀናል። እንደ ሀገር ጠውልገናል። እንደ ሕዝብ ብዙ ነገር አጥተናል። ትውልዱ የሚያርፍበትን የአዲስ ዘመን ስፍራ ነፍገነዋል። ተጠያቂዎች ነን። ሀሳብ ያስፈልገናል..የአንድነት ሀሳብ፣ የእርቅና የሰላም ሀሳቦች ያስፈልጉናል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም