የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዛሬ በሚካሄደው የዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ለመመልከት ከሚጓጓላቸው አትሌቶች መካከል ቀዳሚዋ ናት፡፡ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃቷን ተጠቅማ ሌሎችን በማስከተል የአሸናፊነት መስመሩን በኩራት ስትረግጥ የሚያሳየው ልብ አንጠልጣይ ድራማ ዛሬ በፈታኙ ውድድር ይጠበቃል። የዓለምን ህዝብ በስኬቷ ያስደነቀችው ኢትዮጵያዊት አትሌት፤ ሶስት የዓለም ክብረ ወሰኖችን በመሰባበር ተደጋጋሚ የክብር ካባዎችን ደርባለች። ዛሬም በተደጋጋሚ በስኬት ስሟ በተጠራበት የሃገር አቋራጭ ውድድር አዲስ ታሪክ በማስመዝገብ የስፖርቱን ወዳጆች አጀብ ልታሰኝ ተዘጋጅታለች፡፡ በዚህ ወቅት በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሴት አትሌቶች መካከል ቀዳሚ የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ፡፡
ይህቺ ዓይን አፋር ኮከብ ያለመችውን ሳታሳካ እንቅልፍ የማይወስዳት እልኸኛ አትሌት በዚህ ውድድር ከሚጠበቁ ደማቅ ተወርዋሪ ኮከቦች መካከል ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ የዕለቱ የዓለም ህዝብ ዓይንና ጆሮ ትኩረቱን ከወደ አውስትራሊያ ባትረስት የማድረጉ ምክንያት አንድም ለምትፈጽመው ተዓምር ምስክር ለመሆን ነው። ምክንያቱ ደግሞ እአአ ከ2015 መነሻውን ባደረገው የለተሰንበት ዓለም አቀፍ የውድድር ታሪክ በ5ሺ፣ 10ሺ እና ግማሽ ማራቶን የዓለምን ክብረወሰን በመሰባበር ጭምር የታጀበ በመሆኑ ነው፡፡
ስኬታማ የአትሌቲክስ ህይወቷ መነሻ የሆነው 5ሺ ሜትር ርቀት ቢሆንም፤ የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ውድድርን ማሸነፏን ተከትሎ ጉያንግ ቻይና ላይ በተካሄደው ቻምፒዮና በወጣት ምድብ ሃገሯን ለመወከል በቃች፡፡ በመጀመሪያው የብሄራዊ ቡድን ተሳትፎዋም በግሏም ሆነ በቡድን ለሃገሯ የወርቅ ሜዳሊያን በማስገኘት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ እአአ በ2017 የዩጋንዳዋ ካምፓላ አዘጋጅ በነበረችበት ቻምፒዮናም በድጋሚ በወጣት ቡድን የግልና የቡድን የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። በወቅቱም በርቀቱ የነበራትን ሰዓት ከአንድ ደቂቃ በላይ አሻሽላ መግባቷም አትሌቷን በስፖርቱ አዲሷ ኮከብ እየደመቀች ስለመሆኑ አመላካችና ተስፋ ሰጪም ነበረ፡፡
ለተሰንበት ከሁለት ዓመት (2019) በኋላ ደግሞ በዚህ የውድድር መድረክ በአዋቂ ዘርፍ ነበር ሃገሯን መወከል የቻለችው፡፡ በዴንማርክ አህሩስ በተደረገው በዚህ ቻምፒዮና ላይ ጠንካራ ፉክክር ብታደርግም በጥቂት ሰከንዶች በኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቤሪ እና በሃገሯ ልጅ ደራ ዲዳ ተቀድማ በሶስተኝነት ነበር ያጠናቀቀችው። በግሏ የነሃስ ሜዳሊያን ብታጠልቅም በቡድን ግን የወርቅ ሜዳሊያውን ለሃገሯ ማስገኘትም ችላለች፡፡ አትሌቷ ከአራት ዓመታት በፊት የሆነውን የያኔውን ሁኔታ ስታስታውስም ‹‹በዚያ ውድድር የተሳተፍኩት ወርቅ ለማግኘት ነበር፤ ነገር ግን በወቅቱ ይሰማኝ በነበረው ስሜት በሙሉ አቅም አልነበረም የሮጥኩት፡፡ ከደራ ጋር በመሆን ኬንያዊቷን አትሌት ለመርታት ያላደረግነው ጥረት አልነበረም፤ ነገር ግን ቀድማን ገባች፡፡ በዚህም ቁጭት ይሰማኛል›› ትላለች፡፡
በዚህ ውድድር ላይም ይህኑ የቁጭት ስሜት በመፋቅ ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷንም ትገልጻለች፡፡ እአአ ከ2019 ወዲህ በስፖርቱ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች አስደናቂ ከመሆናቸውም ባለፈ ክብረወሰኖችንም ያሻሻለችበት በመሆኑ ወቅታዊ አቋሟ መልካም የሚባል ነው፡፡ በቅርቡም ከመም ውድድር አልፋ በጎዳና (ማራቶን እና ግማሽ ማራቶን) ሩጫዎች ላይ በመሳተፍም ብቃቷ የትድረስ እንደሆነ ማስመስከር ችላለች፡፡
ዓመለ ሸጋዋ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ዘንድሮ በዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና መድረክ ለአራተኛ ጊዜ ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡ ለዚህ ውድድርም እንደ ብሄራዊ ቡድን ሲከናወን የነበረው ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ ማለፉን አትሌቷ አስታውሳለች፡፡ ስልጠናው ቡድኑን ውጤታማ ሊያደርግ በሚችልበት መልኩ አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላና በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጭምርም ሲሰጥ የነበረ ነው፡፡ በመሆኑም የተለመደውን ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጠችውም ‹‹ሀገሬ በአትሌቲክስ የለመደችውን የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ ለማስገኘት ሁሌም ዝግጁ ነኝ፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት በትግራይ ክልል የነበረው ሁኔታ ወደ ሰላም የተመለሰ በመሆኑ በተረጋጋ መንፈስ በሙሉ አቅም የሃገሬን ሰንደቅ ከፍ ለማድረግ እሮጣለሁ›› በማለት ነው፡፡
ከቆይታ በኋላ በሚጀምረው ቻምፒዮና ላይ አትሌቷ እንዳቀደችውም የወርቅ ሜዳሊያውን የምታስመዘግብ ከሆነም፤ ከአንጋፋዎቹ አትሌቶች ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ጥሩነሽ ዲባባ በእኩል ሶስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን የማጥለቅ ታሪክ የምትጋራ ይሆናል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015