አፍሪካውያንን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ እንዲሁም የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ውህደት ለመፍጠር የተመሠረተው ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት›› (Organization of African Unity – OAU)፤ እ.አ.አ በ2002 ዓ.ም በአፍሪካ ኅብረት (African Union – AU) ሲተካ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ወጥተው ነበር፡፡
የኅብረቱ ዓላማዎች ተብለው የተቀመጡት በርካታ ጉዳዮች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ ‹‹ሰላሟና ፀጥታዋ የተጠበቀ፣ በምጣኔ ሀብት ያደገችና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደት ያላት አፍሪካን እውን ማድረግ›› የሚለው ዐቢይ ተግባር ላይ ያርፋሉ፡፡
በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዘመን የነበረችው አፍሪካ በአፍሪካ ኅብረት ዘመን ካለችው አፍሪካ በብዙ መልኩ የተለየችና የተሻለች እንደሆነ አይካድም፡፡ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ፣ እምቅ አቅምና ዘርፈ ብዙ ሀብት ያላት አህጉር ግን ማሳካት የሚጠበቅባት እጅግ ብዙ ነው፡፡
አፍሪካን የማበልፀግና የማዋሃድ ተግባርን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት፣ አፍሪካ ማሳካት የሚጠበቅባትን እንድትፈፅም የበዛ ኃላፊነት አለበት ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ኅብረቱ ይህን ኃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ረገድ ብዙ ድክመቶች አሉበት፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ሲበሰር በዕለቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ባደረጉት ንግግር ‹‹ … ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በሙሉ ታላቅና ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ ሕዝቦቻችን ከእኛ የሚጠብቁትን ተግባር ለመፈፀምና ክፍለዓለማችን በዓለም አቀፍ ጉባዔ የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ እንድትይዝ ለማድረግ ተሰብስበናል፡፡ በዛሬው ቀን መላው ዓለም አተኩሮ ይመለከተናል፡፡ አፍሪካውያን እርስበእርሳቸው በመጣላት የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አካላት አሉ፤ እውነትም አንዳንድ አለ፤ ቢሆንም ይህ መጥፎ አስተያየት ያላቸው ሁሉ የተሳሳተና ሃሳባቸው ሁሉ ከንቱ መሆኑን በሥራችን እናሳያቸው! አፍሪካ ከትናንትናዋ አፍሪካ ወደነገዋ አፍሪካ በመሸጋገር ላይ ትገኛለች፡፡ አፍሪካ ከሞላ ጎደል ነፃ ሆናለች፡፡
«ነፃ ሆነን እንደገና ተወልደናል፡፡ ለእኛ ሲሉ ሕይወታቸውን የሰጡ አፍሪካውያን ስማቸው ሕያው ሆኖ ይኖራል፤ሐውልትም ሊቆምላቸው ይገባል! ሕይወት ያለነፃነት ዋጋ የለውም! ትግሉ ያለቀ መስሎን ሳናመነታ ወደፊት እንግፋበት! ትግላችንን ለማጠንከር ጊዜው አሁን ነው! ለአፍሪካ ነፃነት የረዱትን ልንረሳቸው አይገባም! አንድነት ኃይል እንደሆነ መለያየት ደግሞ ደካማነት እንደሆነ እናውቃለን! በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች ወደጎን ትተን ሁላችንንም ለሚያስተባብረን ለአፍሪካ አንድነት መድከም አለብን! እርስ በእርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መሆን ነው!።
«አፍሪካ የበለጠ እንድትነቃ ማድረግ አለብን! የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ታማኝነት ለጎሳውና ለመንግሥቱ ሳይሆን ለአንድ አፍሪካ ሊሆን ይገባል! በጎሳ መለያየት የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ነው! በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚና በሶሻል እድገት ካልተደገፈ ከፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል …›› ብለው ነበር፡፡
የአፍሪካ ኅብረትን የእስካሁን ተግባራትና ቁመና ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንግግር አንፃር ስንፈትሸው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወራሽ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት የድርጅቱ መስራች አባቶች ያስቀመጡትን አደራ ከግብ ለማድረስ እጅግ በጣም ብዙ ሥራ እንደሚቀረው እንረዳለን፡፡
ምንም እንኳ ኅብረቱ ዓላማዎቹን ለማሳካት ያከናወናቸው አንዳንዶቹ ተግባራት በበጎነት የሚጠቀሱለት ጅምሮቹ ቢሆኑም፣ አፍሪካ ካላት አቅምና ካሉባት ችግሮች አንፃር ግን የሚጠበቅበትን አድርጓል ለማለት አያስደፍርም፡፡
ከድርጅቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ጣልቃ ገብነትን መከላከል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአፍሪካውያን የቀድሞ ቅኝ ገዢዎች (በተለይ እንግሊዝና ፈረንሳይ) እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በአፍሪካውያን ጉዳይ ባለቤትና አድራጊ የመሆናቸው ነገር ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡
‹‹የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ጣልቃ ገብነትን መከላከል ዓላማዬ ነው›› የሚለው የአፍሪካ ኅብረት ግን ይህን ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ወኔ አጥሮታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኅብረቱ አባል አገራትም አፍሪካዊ አቋምና እሳቤ ከመያዝ ይልቅ በየፊናቸው የምሥራቁና የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ ሆነው ይታያሉ፡፡ ኅብረቱም አፍሪካውያን ከውጫዊ የአስተሳሰብ ጥገኝነት ተላቀው አፍሪካዊ እሳቤ መያዝ ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ኅብረቱ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ቢያቅድም የእቀዶቹ ተግባራዊነት ግን ‹‹እቅድ ዶሮ፣ ተግባር ሽሮ›› እንደሚባለው ሆነው ይታያሉ፡፡ ለዚህ አንካሳነት ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል ቁርጠኛነት፣ ብቁ የሰው ኃይል እና የገንዘብ አቅም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከኅብረቱ አባል አገራት መካከል አብዛኞቹ ለኅብረቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በተገቢው ሁኔታ የሚከፍሉ አይደሉም፡፡
በዚህም ምክንያት ኅብረቱ ለመደበኛ ወጪዎች እንኳ ባለፀጋዎቹን የምዕራብና የምሥራቅ አገራትን ደጅ እንዲጠና ይገደዳል፡፡ ‹‹ነፃ ምሳ የለም›› የሚሉት ቱጃሮቹ ደግሞ ጥቂት ገንዘብ ሰጥተው ከአፍሪካ ብዙ ይወስዳሉ፤ ፍላጎታቸውንም ያስፈፅማሉ፡፡ በዚህ መሀል ‹‹የአባል አገራትን ሉዓላዊነት ማስጠበቅና ጣልቃ ገብነትን መከላከል›› የተባለው የኅብረቱ ዓላማም በወረቀት ላይ የሰፈረ ምኞት ሆኖ ይቀራል፡፡
የኅብረቱ ውስጣዊ አሠራር (በተለይ የሰው ሀብት አስተዳደሩ) ‹‹በተለመደው የአፍሪካውያን ፖለቲከኞች እሳቤና አሠራር›› የተቃኘ፣ ችሎታን ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንዲሁም በጥቅምና ትውውቅ ላይ የተመሠረተ፣ እንደሆነ ተደጋጋሚ አቤቱታ ይቀርብበታል፡፡ ይህን አቤቱታም ኅብረቱ በጥናት ማረጋገጡንም ከአራት ዓመታት በፊት ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
ይህ መሰሉ ሕገ ወጥ አሠራር ደግሞ ኅብረቱ ዓላማውን እንዳያሳካ መሰናክል ይሆንበታል፡፡ ችሎታን ከግምት ውስጥ ባላስገባ እንዲሁም በጥቅምና ትውውቅ ላይ በተመሠረተ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚገኝ የሰው ኃይል ደግሞ ጠንካራ አፍሪካን እውን ለማድረግ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች (ብቃትና ቁርጠኛነት) ያሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የኅብረቱ ዓላማ ተብለው በተቀመጡት እቅዶች ላይ የጠራ ግንዛቤና ጠንካራ አፍሪካዊ የማሳካት ፍላጎት ሊኖር ይገባል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ንግግር ውስጥ ‹‹ … አንድነት ኃይል እንደሆነ መለያየት ደግሞ ደካማነት እንደሆነ እናውቃለን! በመካከላችን ሊኖሩ የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች ወደጎን ትተን ሁላችንንም ለሚያስተባብረን ለአፍሪካ አንድነት መድከም አለብን! እርስ በእርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መሆን ነው! … የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ታማኝነት ለጎሳውና ለመንግሥቱ ሳይሆን ለአንድ አፍሪካ ሊሆን ይገባል! በጎሳ መለያየት የአገርን አንድነት የሚያፈርስ ነው! በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኮኖሚና በሶሻል እድገት ካልተደገፈ ከፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል …›› የሚለው ሃሳብ ዛሬም በተግባር እንዳልተተረጎመ የአፍሪካ አሁናዊ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
እውን ዛሬ የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ታማኝነት ለራሱ ነው ወይንስ ለአንድ አፍሪካ? አንድነት ኃይል፤ መለያየት ደግሞ ደካማነት እንደሆነ የተረዳው አፍሪካዊ ምን ያህል ነው? የኅብረቱን ቁመና ለመገምገም ‹‹ኅብረቱ እስካሁን ድረስ ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል ምን ያህል ተግባራዊ እንዲሆኑ አደረገ?›› የሚል መሠረታዊ ጥያቄ ቢጠየቅ መልሱ አጥጋቢ አይሆንም፡፡
በእርግጥ በጎሳ ግጭት፣ በሙስናና በዝርፊያ የሚታመሱ ብዙ አገራት ባሉበት ሁኔታ ኅብረቱ ለሁሉም ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም፡፡ ዓላማቸው ስልጣን መያዝና አገር መዝረፍ ብቻ የሆኑ በርካታ ገዢዎች ባሉባት አህጉር ውስጥ አህጉራዊ የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ ውህደት የሚባሉት ሃሳቦች ቀልድ ተደርገው መቆጠራቸው አይቀርም፡፡
ጠንካራ አፍሪካን ለማየት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያለው አፍሪካዊ ያስፈልጋል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የዓለማችን ሁለተኛው ትልቅ አህጉር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ ተወካይ የለውም የሚለው መራራ እውነት የሚያበሳጨው አፍሪካዊ ስንት ነው?
ስለሆነም ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ያላት ጠንካራ አፍሪካን ለማየት ይህን ዓላማ አስፈፅማለሁ ብሎ የተነሳውን የአፍሪካ ኅብረትን በጥልቀት በመገምገም ለዓላማውና ለዘመኑ የሚመጥን አድርጎ ማደራጀት ለነገ የማይባል ተግባር መሆን አለበት፡፡
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም