2022 የውድድር ዓመትን በስኬታማ ዓለም አቀፍ የውድድር ውጤቶች ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በቅርቡ የተያዘውን 2023 የውድድር ዓመትም በውጤት ለመጀመር ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህንንም በአውስትራሊያ ባትሪስ በሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ለመጀመር የቀናት ዕድሜ ብቻ ቀርተውታል::
የዘንድሮው የ44ኛው የዓለም ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና አዘጋጇ ከተማ ባትረስት እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች:: በመድረኩ በውጤታማነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድንም ወደ ስፍራው ከሚያቀኑት አንዱ ነው::
በወጣትና ምርጥ ብቃት ላይ በሚገኙ አትሌቶች የተገነባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን 28 አትሌቶችን እና 5 ተጠባባቂዎችን አካቶ ከትናንት በስቲያ ምሽት ወደ አውስትራሊያ ያቀና ሲሆን፤ በወጣት ወንድና ሴት፣ በአዋቂ ወንድና ሴት እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ(ዱላ ቅብብል) የሚወዳደርም ይሆናል:: ከጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ውድድር በብቃታቸው ተመርጠው የተሰባሰቡ አትሌቶች ከጥር 3/2015 ዓም አንስቶ ዝግጅታቸውን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ ጃንሜዳ፣ እንጦጦ፣ ሱሉልታ፣ ቃሊቲ፣ ወንጂና የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ሲያከናውኑ ቆይተዋል:: ቡድኑ በሥነምግባርና በስልጠና አቀባበሉ ምስጉን እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ ስኬታማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ስብስብ ያለው ጥንካሬም ለሌሎች ተፎካካሪ ሀገራት ፈተና እንደሚሆን የዓለም አትሌቲክስን ጨምሮ ትኩረታቸውን በአትሌቲክስ ላይ ያደረጉ ድረገጾች ከወዲሁ ቅድመ ግምታቸውን በማስቀመጥ ላይ ይገኛሉ::
ቡድኑ ወደ አውስትራሊያ ከማቅናቱ አስቀድሞ በተካሄደው የሽኝት መርሐ ግብር ላይም ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንዳለፉት ጊዜያት የሃገራቸውን ስም በአሸናፊነት ያስጠሩ ዘንድ የአደራ ሰንደቅ ዓላማ ርክክብ ተከናውኗል:: ይህንን ተከትሎም የሃገር አቋራጮች ውድድር ልዑኩን የሚመሩት የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሳራ ሐሰን፤ ቡድኑ ድልን አልሞ እንደሚጓዝ ገልጸዋል:: የቡድኑ ዝግጅት መልካም ውጤት ሊመዘገብበት እንደሚችል የሚያመለክት መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ሣራ፤ በልምምድ ላይ የታየውን የቡድን ስሜት በማጠናከር አትሌቶቹ ለድል እንዲዘጋጁም አሳስበዋል::
የቀድሞዋ ድንቅ አትሌት የአሁኗ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ በሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና የበርካታ ጊዜ ተሳትፎዋ ሦስት የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያዎችን ለሃገሯ ማስመዝገብ ችላለች:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች ሕይወት ስጋት በነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ከአራት ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ውድድር አስመልክቶም ለቡድኑ የሥራ መመሪያ ሰጥታለች:: በዚህም መሠረት በዝግጅት ወቅት ቡድኑ ያሳየውን መከባበርና መተባበር በውድድሩም በተግባር ማሳየት እንደሚገባው አሳስባለች::
በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር የባህልና ቋንቋ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በበኩላቸው፤ የቡድኑ አባላት ከቀደሙ አትሌቶች ተምረው አሁንም የሃገራቸውን ስም ከፍ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል:: የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር አትሌቶች በሄዱበት ውጤታማ እንዲሆኑ የሃገርን ስም በማስጠራት ባንዲራዋን እንዲያውለበልቡ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በመሆኑም ቡድኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ውጤት አስመዝግቦ እንዲመለስ ተስፋ በመሰነቅ በጉጉት የሸኛቸው ሕዝብ በድል ሲመለሱም በሞቀ ሁኔታ አቀባበል እንደሚደረግላቸውም መልካም ምኞቻቸውን ገልጸዋል::
ከአራት ዓመት በፊት በዴንማርክ አህሩስ በተካሄደው የዓለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 2 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ኬንያ እና ዩጋንዳን በማስከተል ቀዳሚ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው:: ቻምፒዮናው ከተጀመረ አንስቶ በተካሄዱ 35 ተከታታይ ውድድሮች ላይ የተካፈለችው ኢትዮጵያ፣ 105 የወርቅ፣ 108 የብር እና 62 የነሐስ በድምሩ 275 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች:: ይኸውም ጎረቤት ሃገር ኬንያን ተከትላ በውድድሩ ታሪክ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ልትቀመጥ ችላለች:: ከእነዚህ ሜዳሊያዎች መካከል የሃገር አቋራጭ ንጉሱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ 6 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ቀዳሚው ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑን በዚህ ወቅት እየመራች ያለችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እና ሌላኛዋ ምርጥ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ሶስት ሶስት ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ይከተላሉ::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም