በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት አሉታዊ ተጽዕኖ ካሳረፈባቸው ዘርፎች መካከል ዲፕሎማሲ አንዱ ነው:: ጦርነቱ ሀገሪቱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻክር አድርጓል:: በተለይም ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት ጋር የነበራት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረውና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል:: ግንኙነት ከመሻከሩ ባሻገር ምዕራባዊያኑ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩባት እንደቆዩ የአደባባይ ሚስጢር ነው::
በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ከገባችበት የዲፕሎማሲ ቀውስ በመውጣት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም እንዲሻሻል እድል ፈጥሯል:: በተለይም ጦርነቱ በሰላም ድርድር እንዲቋጭ እና ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ በመንግስት ላይ ጫና ሲያደርጉ ከነበሩ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት ጋር ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሻሻል ማሳ የት ጀምሯል::
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በተለይም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት ያደረጉት ጉብኝቶች የሀገሪቱ የተቀዛቀዘው ዲፕሎማሲ እንዲነቃቃ ከፍተኛ ሚና ተጨውቷል:: በስምምነቱ ማግስት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጋር ባደረጉት ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው የሰሯቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች በሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙኘት ላይ አጥልቶ የነበረውን ጥላ የገፈፈ ከመሆኑም ባሻገር የአሜሪካንን ፈለግ ከሚከተሉ የአውሮፓ ሀገራት ጋርም የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያንሰራራ በር የከፈተ ነበር ማለት ይቻላል::
ባለፈው ሳምንት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን፣ ማልታና ፈረንሳይ ያደረጉት ይፋዊ ስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በሎጂስቲክስ እና በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል:: በዚህ ጉብኝት ለኢትዮጵያ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የተገኘበት ከመሆኑም ከሀገራቱ ጋር የቆየው ዘመን ተሻጋሪ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲያንሰራራ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ነው::
በጣሊያን ባደረጉት ጉብኝት የ180 ሚሊዮን ዩሮ የረጅም ጊዜ ቀላል ብድርና ቀጥተኛ ድጋፍ የተገኘበት ሲሆን፤ የጣሊያን መንግስት በቀጣይም ለኢትዮጵያ ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ማረጋገጫ የሰጠበት መሆኑ ተነግሯል:: ድጋፉ ጉዳት የደረሰበትን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት እና የኢኮኖሚ ሪፎርሙን አጠናክራ እንድትቀጥል አቅም የሚፈጥር ይሆናል::
በፈረንሳይ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ስለመሆኑ እና በዚህ ረገድም ውጤት የተገኘበት ስለመሆኑ የብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ለሚዲያዎች ተናግረዋል:: መንግስት ተግባራዊ እያደረገ ካለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም አንዱ ዋነኛው ሃሳብ ኢትዮጵያ ያለባትን እዳ የማሸጋሸግ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እዳ ሽግሽግን የጋራ ማዕቀፍን የሚመሩት ፈረንሳዮች ናቸው:: ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያለባትን እዳ ለማሸጋሸግ ፈረንሳይን የማግባባት ስራ መስራታቸውንና በዚህም ውጤት መገኘቱ ተጠቁሟል::
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ካሉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉ የተጠቆመ ሲሆን፤ በሎጂስቲክስ፣ በሚዲያ፣ በኢነርጂ፣ በሀይል አቅርቦት ዘርፍ እንዲሁም በባቡር ዘርፍ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን፤ እነዚህን እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ ውይይት ስለመደረጉ ተገልጧል:: በፈረንሳይ መንግስት ሚኒስትሮችና በኢትዮጵያ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መካከል ሰፊ ውይይት ስለመደረጉ ተነግሯል::
ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት የሚገኘው የልማት እና ሰብዓዊ እርዳታ ረገድ መሻሻል ከመታየቱም ባሻገር፤ በምዕራቡ ዓለም ከሚዘወሩት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አጋሮች የሚገኘው የሰብአዊ እና የልማት ዕርዳታ በኩል አዎንታዊ ውጤቶች እየታዩ ነው።
የሰላም ስምምነቱ በተፈረመ ማግስት በሰብዓዊ እና የልማት እርዳታ ላይ አዎንታዊ ውጤቶች ከመመዝገባቸው ባሻገር፤ የተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው የሰላም ስምምነቱ ያስገኘው ሌላኛው ትሩፋት ነው:: በሰላም ስምምነቱ ማግስት የቻይና፣ የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉብኝት ማድረጋቸው ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ አንዱ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማሳደግ በከፍተኛ ዲፕሎማቶች አማካኝነት የገቡት ቃል ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ረገድ ያደረገቻቸው እልህ አስጨራሽ ጥረት ፍሬ የምትቋደስበት ደረጃ ላይ እንዳለች ያሳያል። በተለይም አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የዲፕሎማሲ ክንውን ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን አስቀድመው መጎብኘታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የማይናወጥና ጠንካራ ግንኙነት ያሳያል ሲሉ የጉብኝቱን ፋይዳ አብራርተዋል::
ኢትዮጵያ በሀያላን አገሮች መካከል ያለው ፉክክር ሰለባ እንዳትሆን የምትታወቅበትን የገለልተኝነት አቋሟን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምሶሶ አድርጋ በመያዝ ከምዕራቡም ሆነ ከምስራቁ ንፍቀ ክበብ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ይገባል:: ከሁሉም ሀያላን ሀገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ አጋርነትን ለማስቀጠል የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል አለባት:: የገለልተኝነት አቋሟ ከሀያላን ሀገራት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይደርስባት ከማገዙም ባሻገር ኢትዮጵያ በሀያላን ሀገራት መካከል ያለውን ፉክክር ወደ መልካም እድል መቀየር እንድትችል እድል ይፈጥርላታል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም