ይህ ወቅት መደበኛው የመኸር አዝመራ ስብሰባና በጥር ወር የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እየተጠናቀቁ ያሉበትና በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለበልግ ግብርና ዝግጅት የሚደረግበት ነው። በልግ አብቃይ አካባቢዎች ይህን ወቅት በእጅጉ ይፈልጉታል፤ በቀጣይ የሚጥለውን ዝናብ በመጠቀም የግብርና ሥራቸውን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት ያደርጉበታልና።
የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትም አርሶ አደሩ ይህን ወቅት በሚገባ እንዲጠቀምበት ዝግጅት መረጃዎችን ግብአቶችን ያደርሳሉ። ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃም ይህንኑ ያመለክታል። ኢንስቲትዩቱ የየካቲት ወር በበልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ለበልግ ሥራ እንቅስቃሴ ዝግጅት የሚጀመርበት መሆኑን ማስታወቁም ወቅቱ ለበልግ እርሻ ያለውን ፋይዳ ይጠቁማል።
ወቅቱ የበልግ ወቅቶች በሆኑት ከየካቲት እስከ ግንቦት እንዲሁም በበጋው ጥቅምትና ኅዳር ወራቶች መደበኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ሶማሌ ቦረና ጉጂ የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ቆላማ አካባቢዎች ወሳኝ ጊዜ እንደሆነም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሊጂ ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል። ባለፈው አመት በዚህ ወቅት ይጠበቅ የነበረው ዝናብ ባለመጣሉ አካባቢዎቹ ለከፋ ድርቅ መጋለጣቸው ይታወሳል።
አካባቢዎቹ ዘንድሮም ለተመሳሳይ ችግር እንዳይጋለጡ በተለይም ወቅታዊ የአየር ጠባይ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም በክረምቱ ለሚከናወነው መደበኛ የግብርና ሥራ ወሳኝ የሆነውን የአየር ጠባይ መረጃ በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የተናበበ ሥራ መሥራት ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ባለድርሻ አካላት፣ የአየር ጠባይ ትንበያ መረጃና ትንተና የሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት እጅና ጓንት ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲዩት የአየር ጠባይን በመተንተንና መረጃ በመስጠት ከግብርናው በተጨማሪ ለጤና፣ ለትምህርትና ለሌሎች ተቋማት እንደ አስፈላጊነቱ መረጃ በመስጠት ከአራት አስርት አመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል። ኢንስቲትዩቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ከመሆን፣ ከተአማኒነትና ከወቅታዊ ተደራሽነት ጋር ተያይዞ ይነሱበት የነበሩ አስተያየቶች አይዘነጉም። በቀደመው ጊዜ ግብርናውም ያን ያህል ለአየር ጠባይ መረጃ ትኩረት የሰጠ ነው ለማለት አያስደፍርም። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አሁን የምንገኝበት ዘመን ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዕለት ተዕለት የሚሰጥ የአየር ጠባይ መረጃ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
መንግሥት በግብርናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ እቅዶችን ይዞ እየሠራ ለመሆኑ እየታዩ ካሉ ውጤቶች መገንዘብ ይቻላል። ለዚህም በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በሌማት ቱሩፋት ልማት ሥራዎች ስኬት ለማስመዝገብ እያከናወነ ያለው ተግባር ይጠቀሳል። ክረምት ከበጋ ልማት እንዲከናወን በተቀመጠው አቅጣጫም የቆላ በጋ ስንዴ ልማት ለአብነት በማሳያነት ይነሳል።
የግብርና ሥራው በግብርና ሜካናይዜሽን እንዲታገዝም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የመንግሥትን ልዩ ትኩረት የሚያሳዩ ናቸው። የአየር ጠባይ ትንተናና መረጃውም ይህንን ሁሉ ጥረት በማገዝና ለስኬት እንዲበቃ በማድረግ ድርሻ አለው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደሚሉት፤ ኢንስቲትዩቱ በባለፉት ወቅቶች በሰጠው የአየር ጠባይ የትንተና መረጃ እና በመሬት ላይ ወይንም በተግባር የታየውን እንዲሁም በተለያዩ አስፈጻሚ ተቋማት ላይ ያመጣቸውን አሉታዊ እና አወንታዊ ተጽእኖዎች በመገምገም ለቀጣይ በልግ ወቅት የሚኖረውን የአየር ጠባይ በተመለከተ አስፈላጊውን ቅድመ ማስጠንቀቂያና የምክር አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል።
በዚሁ መሠረትም ያለፈው በጋ በአብዛኛው በሰሜን አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅና ፀሐያማ የአየር ሁኔታ የሚያይልበት፣ በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎችም በተለይ ሱማሌ፣ ቦረና ጉጂ ቆላማ ዞኖች ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው እንደሆነና በነዚህ አካባቢዎች ከተሰጠ ትንበያ ጋር የተጣጣመ ስለመሆኑ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት ጊዜያት የተሰጡት ትንተናዎችና የነበራቸውን ጥንካሬዎች በመያዝ፣ ክፍተቶችንም በማረም ለቀጣዩ ዝግጅት መደረጉን ነው ያስረዱት።
በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው ከሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አካባቢዎቹ በጋውም የክረምት ወቅታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በተለይ በበጋ ወቅት ዝናብ የሚያገኙ የአገሪቱ አካባቢዎች ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ሶማሌ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ክልል ቆላማ አካባቢዎች በተለይ ጥቅምትና ኅዳር ላይ ዝናብ የሚያገኙበት ወቅት እንደሆነ ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ አካባቢዎቹ በተጠቀሰው ወቅት ያገኙት ዝናብ ከመደበኛ በታች እንደሆነ በተሰጠው ትንበያ በግምገማ መለየቱን አመልክተዋል። በተለይም ቦረና፣ ጉጂ፣ የባሌ ቆላማ ዞኖች፣ ደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ሶማሌ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ሰገን ሕዝቦች አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት የተስተዋለባቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሬ ማብራሪያ፤ የሚቲዎሮሎጂ ዝናብ ሰጪ ክስተቶች ግምገማ በሚደረግበት ወቅት በዋናነት በበልግ የኢትዮጵያን የአየር ጠባይ ወይንም የዝናብ ሁኔታን የሚወስነው የላሊና እና የኢሊኖ ሁኔታ እንዲሁም የውቂያኖሶች መሞቅና መቀዝቀዝ ነው። የባለፉት የበልግና የበጋ ወቅቶችም በላሊና ተጽእኖ ሥር የወደቁ ነበሩ። ክስተቱም የበልግና በጋ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ችሏል። ላሊና በበልግና በበጋ ወቅቶች ከተከሰተ የዝናብ ሰጪ ክስተቶችን ያዳክማል። በተቃራኒው ደግሞ ላሊና በክረምት ወቅት ሲከሰት ጥሩ የዝናብ ወቅት ይሆናል።
በባለፈው በላሊና ተጽእኖ የተጎዱ የበልግና የበጋ ዝናብ ተጠቃሚዎች በዚህ የበልግ ወቅት ዝናብ የሚያገኙበት ሁኔታ ከተስፋ ያለፈ አይደለም። አሁን ባለው መረጃ ላሊና ተጽእኖ የሚያሳድርበት ሁኔታ እየቀነሰ በመሆኑ ነው ተስፋ የተደረገው። ወደ መደበኛ ዝናብ የመምጣቱ ሁኔታ እስኪረጋገጥ ድረስ ግን የዝናብ እጥረት እንደማያጋጥም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ይህን መሠረት በማድረግም የበልግ ዝናብ ዘግይቶ እንደሚገባ፣ ላሊና ወደ መደበኛው ከመጣ ደግሞ ወደ መደበኛው የተጠጋ ዝናብ እንደሚኖር ነው የኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ ትንበያ የሚያሳየው። ከአወጣጥ አንጻርም መደበኛውን የዝናብ ሂደት ተከትሎ እንደሚወጣም ትንበያው አካትቷል።
ይህን ተስፋ ሰጪ የሆነ ትንተናና የምክረ ሀሳብ መረጃ ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሮ መጠቀም ከግብርና፣ ከጤና፣ ከትምህርትና ከሌሎችም መረጃውን ከሚጠቀሙ ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል። ኢንስቲትዩቱ በመካከል ላይ ያሉ ለውጦችን ተከታትሎ መረጃ የማድረስ ሚናው እንደተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋርም በተለያዩ የኮሚቴ አወቃቀሮች አማካኝነት የሚጠበቁ ሥራዎችን በመሥራት ለድርቅ አደጋ ተጋላጭነትን የመቀነስ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ ቀደም ሲል ይነሱበት የነበሩ የመረጃ ተደራሽነትና የተአማኒነት ጉዳዮች እንዲሁም ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ አገር በትኩረት እየሠራ ነው። በተለይም በግብርናው ዘርፍ ወቅቱን የጠበቀ የአየር ጠባይ ትንተና መረጃ በማድረስ በመደገፍ በኩል ኢንስቲትዩቱ ያለውን ዝግጁነት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ ዋና ተልዕኮውን ለመወጣት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በመጥቀስ ነው።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም በ2007 ዓ.ም ካጋጠመው የኢሊኖ ክስተት ጀምሮ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተካተቱበት ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ኮሚቴ በማቋቋም በኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን መረጃ መሠረት በማድረግ ትንበያ የሚሰጥበትን ሁኔታ በማመቻቸት ነው ሲሠራ የቆየው። የተቋቋመው ኮሚቴም በሚሰጠው ትንበያ የዝናብ እጥረት መኖሩን ከተገነዘበ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ሰብአዊ ድጋፍ በሚመቻችበት፣ ችግሮችንም ለመቋቋም የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህ በተቀናጀ አሠራርም የእንስሳት መኖ እና ውሃ አቅርቦትና ሌሎችም የተከናወኑት ተያያዥ ጉዳዮች ሥራዎች መሠራታቸውን የሚያሳዩ ናቸው። ይሰጥ የነበረው ትንበያም መሬት ላይ በተጨባጭ ከሚያጋጥም ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንደነበር የኢንስቲትዩቱ የሥራ ግምገማ ያሳያል። የተሠራው ሥራ የጉዳት ተጋላጭነትን ባያስቀርም ለመቀነስ ግን አስችሏል።
ኢትዮጵያ በሁለቱም የአየር ሁኔታና ጠባይ ጽንፎች እንደሚያጋጥማት በምላሻቸው የጠቆሙት አቶ ፈጠነ፣ አንዴ ድርቅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ክረምት ዋና የዝናብ ወቅታቸው በሆኑባቸው አካባቢዎች ላይ የጎርፍ ተጋላጭነት መኖሩንና ለዚህም ዝግጁ ሆኖ መገኘት ይጠበቃል ብለዋል። እስካሁንም ሥራዎች ሲሠሩ የቆዩት በዚህ መንገድ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ አመልክተዋል። የትንበያው ተአማኒነትም ከተሠሩት ሥራዎች ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንጻር የሚገኝበትን ደረጃ አስመልክተው እንደገለጹት፤ ተቋሙ በደረጃ ነው ወደ ኢንስቲትዩት ያደገው። ይህም አንዱ የለውጥ እድገት ማሳያ ነው። በሌላ በኩልም በሰው መረጃን ከመሰብሰብ ጀምሮ በተራዘመ ጊዜ ወደ አውቶማቲክ የአየር መሰብሰቢያ መሳሪያ መሸጋገር የቻለው። ያደጉ አገራት የሚጠቀሙበት የአየር መሰብሰቢያ፣ በተለይም በከተሞች የአየር ብክለት መከታተያ ራዳር በመጠቀም ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። በሜትሮሎጂ አሰባሰብ ዙሪያ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት በመረጃ አሰባሰብ ሌሎች አገሮች የደረሱበት ደረጃ በመድረስ ወቅቱ የሚጠይቀውን በጥራት የመረጃ ተደራሽነት ለማረጋገጥ ኢንስቲትዩቱ ዝግጁ ሆኖ እየሠራ ይገኛል። ከባለድርሻ አካላት ጋርም የተናበበ ሥራ ለመሥራት የሚደረገው ጥረት ቀደም ሲል በተዘጋጀው ብሔራዊ የአየር ጠባይ ማዕቀፍ አገልግሎት በተከናወነው የሰነድ ስምምነት ፊርማ መሠረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በአገሪቱ እየተከናወነ ባለው ልማት ላይ እስያገኘ ካለው ጠቀሜታ አንጻር ሲገመገም በተለይ ግብርናውን ጨምሮ ሁሉም የመረጃው ተጠቃሚ ባለድርሻ አካላት ጋር ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ ሰነድ በማዘጋጀትና ሰነዱም የጋራ እንዲሆን የተከናወነ ተግባር መኖሩንም ነው ያመለከቱት። በግብርናም በኩል የራሱ አግሮ ሚቲዮሮሎጂ በሚባለው ዘርፍ ላይ እስከ ልማት ጣቢያ ሠራተኛ ድረስ መረጃው እንዲደርስ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
አጠቃላይ ከአረንጓዴ አሻራ፣ እንዲሁም የሌማት ቱሩፋትን ጨምሮ እየተከናወነ ላለው የልማት ሥራ አጋዥ የሆነ መረጃ የመስጠት ሥራ እየተሠራ ነው የሚል እምነት በኢንስቲትዩቱ መኖሩን አቶ ፈጠነ አመልክተዋል።
‹‹የአገሪቱን የአየር ጠባይ በመረዳት ለዚያ የሚመጥን ስትራቴጂ በመንደፍ በተለይም በግድቦች ውሃ ይዞ የመጠቀም ጥረት ያስፈልጋል። ዝናብን በመጠበቅ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አይቻልም። በመሆኑም የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል›› ሲሉም አስገነዝበዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በልግ በባህሪው ከፍተኛ የሆነ ሙቀት የሚስተዋልበት ሲሆን፣በክረምትና በበጋ ወቅቶች ከፍተኛ ቅዝቃዜ እንደሚስተዋለው በበልግ ወቅትም ሙቀት ማጋጠሙ የተለመደ ነው። ይህንን መቋቋም የሚያስችል በተለይም ከጤና አንጻር የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲባል ግን አንድ ቀንም ቢሆን የጣለ ዝናብ መደበኛ የሚሆንበት ወይንም በበልግ ወቅት የጣለ ዝናብ ሆኖ ሊመዘገብ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም