ሰሞኑን ለጆሮ በቅተውና የውይይት አጀንዳ በመሆን አገር- ምድሩን ሞልተውት ከነበሩት ዜናዎች መካለከል አንዱ የ“3%” ጉዳይ ነው። ማለትም፣ “ከ980 ሺህ የ12 ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኝ ተማሪዎች ውስጥ 50% እና ከዚያ በላይ ያመጡ ተማሪዎች 28 ሺህ ወይም “3% ናቸው” የሚለው ነው።
ዜናው በዝርዝር እንዳስቀመጠው፣ “በማህበራዊ ሳይንስ ከታረመው ከ600 ውስጥ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት 524 ሲሆን፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ 666 ነው፡፡ ይህንን ውጤት ተመርኩዘን ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ ከ500 በላይ ያመጡት ተማሪዎች 10 ብቻ እንደሆኑ ማየት ተችሏል፡፡ በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ ከ600 በላይ ያመጡ ተማሪዎች 263 ናቸው።”
ውጤቱ እንኳን ባለቤቱን ሌላውንም ክው ያደርጋል። የየአገራቱ ትምህርት ሚኒስትሮችም “በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው በእኛም ላይ እንዳይደርስ” በሚል ርቆ አሳቢነት ተግባር ላይ እንዲጠመዱም ያደርጋል።
ጉዳዩን አስመልክተው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ (የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር) ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ከሆነ፤ የፈተና ውጤቱ በየደረጃው ሁሉም የተፈተነበት ነው:: በተለይም መምህራንና ትምህርት ቤቶች በደንብ የማስተማራቸው አቅም የተፈተሸበት ነው::
ምክንያቱም በአስተማሩትና በአሳወቁት ልክ ተማሪዎቻቸው ውጤት አስመዝግበዋል:: ለምሳሌ፡ – በአጠቃላይ መደበኛ ተፈታኞች ትምህርት ቤቶች 2ሺህ 959 ሲሆኑ፤ ጥሩ ያስተማሩ ሰባት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፈዋል::
ከ50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት የተመዘገበባቸው ትምህርት ቤቶች ደግሞ 1ሺህ 798 (60.76 በመቶ) ማምጣት ችለዋል:: የማስተማርና እውቀት የማስጨበጥ ችግር ያለባቸው 1ሺህ 161 (39.24 በመቶ)፣ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ማሳለፍ አልቻሉም::
“የት ይደርሳል የተባለ ወይፈን ልኳንዳ ቤት ተገኘ” እንዲል ስነ-ቃላችን፣ የት ይደርሳሉ ያልናቸው ልጆቻችን የማይረባ ፖሊሲ ሰለባ ሆኑና እንዲህ ሆኑ። ይሁኑ እንጂ፣ ልጆቹ ገና ብዙ ዕድል ያላቸው ለግላጋ ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር የለባቸውም። ሁሉንም ነገር አሻሽለው የፈለጉበት ደረጃ የመድረስ ዕድል አላቸውና።
እርግጥ ነው፣ ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ “ሀገር አቀፍ ፈተናውን ከወሰዱት 896ሺህ 520 ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 3 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ ናቸው:: ማለትም ከተመዘገቡት 985ሺህ 354 ተማሪዎች መካከል 908ሺህ 256 ፈተና ላይ የተቀመጡ ሲሆኑ፤ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች በመቀጣታቸው የተነሳ 896ሺህ 520 ተማሪዎች ፈተናውን እንዲወስዱ ሆነዋል::
ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 29ሺህ 909 ብቻ ናቸው ማለፍ የቻሉት::” በማለት የገለፁት ውጤት መንስኤው ማንም ሳይሆን የቀድሞው የትምህርት ፖሊሲ መሆኑን የሁላችንም ህሊና አሳምሮ ስለሚያውቀው አርቃቂዎቹን ሳንታዘባቸው ማለፍ ይከብደናል።
አፅዳቂዎቹን “ተሳስታችሁ ነበር። አልሰማ አላችሁ እንጂ መሳሳታችሁም ተነግሯችሁ ነበር። ‘አዲሱ የትምህርት ፖሊሲ የምትሉት ነገር ትውልድ ገዳይ ነው’ ተብላችሁም ነበር። በአጠቃላይ ከአርቃቂ አፅዳቂዎቹ በስተቀር ዜጋው በሙሉ ‘እባካችሁ …’ ብሏችሁ ነበር።
ያገር ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ . . . ያልተባለበት ምንም ዓይነት ጊዜ አልነበረም።” ሳንላቸው ብናልፍ ህሊናችን ይወቅሰናልና የወደፊቶቹ አርቃቂዎችም ሆኑ አፅዳቂዎች ከዚህ ሊማሩ እንደሚገባ አስምረንበት ማለፍ ግድ ይሆንብናል።
ይህ በወቅቱ አስተያየት ሰጪዎች “ትውልድ ገዳይ . . .” የተባለለት፤ እንዲሁም፣ በዘመነ ገነት ዘውዴ ከጣራ በላይ ሲፎከርለት የነበረ (ለእሳቸውም “ዮዲት ጉዲት” የሚል ስያሜን (በኤሊቱ አብዝቶ ይቀንቀን እንጂ ሕዝባዊ ተቃውሞ የወለደው ነው) ያጎናፀፈ የትምህርት ፖሊሲን ውድቀት፣ “ትሩፋቶቹ”ንና አስተማሪነቱን በዚህች ቅንጣቢ ገፅ ብዙ ማለት አይቻል ሆኖ እንጂ በትምህርት ፖሊሲያችን ላይ ቢነገሩ፤ ቢፃፉ … የማያልቁ በርካታ ጉዳዮች አሉ።
ዋናው ነገር መማሩ ነውና፣ የአሁኑ “3% ብቻ . . .” መቼም፣ መቼም . . . እንዳይደገም ወገባችንን ታጥቀን ልንሠራ ይገባል። ክስተቱንም እንደ “መልካም አጋጣሚ” ልንወስደው ይገባል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ “ልጆቹ አይደሉም የወደቁት። የወደቅነው እኛ ነን። እንደ አገር፣ እንደ መንግሥት . . . የወደቅነው እኛ ነን። ይህ የፈተና ውጤት አስተማሪ ነው:: ምክንያቱም ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም መምህራንና መንግሥት ያለባቸውን ክፍተቶች ለይተው ለቀጣይ እንዲሠሩ” ያደርጋቸዋል በማለት የተናገሩትም መልዕክቱ ይኼው እንጂ ሌላ አይደለም።
እኛም ይህንኑ እንጋራለን፤ ከደረሰው ኪሳራም ሁሉም ትምህርት ይወስዳል፤ ስህተቶችንም ያርማል ብለን እንጠብቃለን።
ይህንን ፈተና ከእስከ ዛሬዎቹ ለየት የሚያደርገው አንድ አቢይ ጉዳይ ቢኖር ተፈታኝ ተማሪዎቹ ከ50 በላይ በሚሆኑ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው ከፈተናው ከ – እስከ ድረስ እዚያው ቆይተው በጥብቅ ክትትል፣ ቁጥጥርና የፈተና ዲሲፕሊን ስር ሆነው የወሰዱት መሆኑ ነው።
ሂደቱም በአብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ ፈተናው ከአለፉት በተሻለ ሁኔታ ተፈታኞችን ማስተናገድ የተቻለበት፤ አንዳንድ ወላጆችን ያስደነገጠ ቢሆንም፣ አብዛኞቹን ደግሞ ጥሩ ተሠራ፤ እንዲያውም ለትምህርት ጥራቱ ሁነኛ መፍትሔ የሆነ፤ ኩረጃን እስከነ አካቴው ሊያስቀር የሚችል . . . አዲስ አሠራር ተብሎ የተመሰገነ ነው።
ሌሎች ተቋማትም “አይቻልም”ን ትተው፣ ልክ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉ፣ ያላቸውን ሪሶርስ በሙሉ ተጠቅመው ታላቅ ሞቢላይዜሽን በማድረግ ተአምር ይሠራሉ ብለን እንጠብቃለን። (ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ሞቢላይዜሽን ሲያደርግ ያቀናጃቸውን ተቋማት ልብ ማለት የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ከመከላከያ ጀምሮ፣ አየር መንገድን አካትቶ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ትምህርት ቢሮዎችን፣ ወላጆችን ….. እኔ ሌሎች በርካቶችን እንዳሳተፈ ልብ በማለት ተሞክሮውን መውሰድ ያስፈልጋል።)
እንደ ማጠቃለያ፣ ሥራ ይሠራል። ስህተት ደግሞ መቼም ቢሆን ይኖራል። ትንሽ ከበድና ቸገር የሚለው ግን በትውልድ ላይ ሲሆን ነው። ያ ደግሞ ሆኗልና መጪውን ለማሳመር መጣር ያስፈልጋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም