የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን በአህጉሪቱ ከተቋቋሙ አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ ቀዳሚ ነው። በዚህም ሳቢያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ከዛሬው አፍሪካ ህብረት) ሁሉ ቀዳሚው ድርጅት በመሆን በታሪክ ተመዝግቧል።
ድርጅቱን ከመሰረቱት አባል አገራት ውስጥም በፋይናንስና በፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበረችው ግብጽና የእርሷ አጋር እንደነበረች የምትታመነው ሱዳን የፕሬዚደንትነቱን ቦታ እየተፈራረቁ ይይዙት ነበር። ይህም ማለት እ.ኤ.አ ከ1957-58 ግብጻዊው አብድል አዚዝ ሳሌም፣ ከ1958-68 ሌላኛው ግብጻዊ ጀነራል አብዱልአዚዝ ሙስጠፋ፣ ከ1968-72 ሱዳናዊው ዶክተር አብድል ሀኪም ሙሀመድ አንድም ሁለትም እየሆኑ ሲመሩ ቆይተዋል። ካፍ ባለፈው የካቲት 01/2015 66ኛ አመቱን ማክበሩን ተከትሎ በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ልናስታውሳቸው የወደድነው ታላቁን የስፖርት ሰውና የኢትዮጵያ ስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ ግን ቀደም ሲል ካፍን በፕሬዘዳንትነት ካገለገሉ ሰዎች ቀጥሎ የአፍሪካን እግር ኳስ መምራት የቻሉና በስራቸውም ህያው ስም ያተረፉ ሆነው በታሪክ ይወሳሉ።
ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ከምስረታው ጀምሮ በመስራች አባልነትና በምክትል ፕሬዚደንትነት እኤአ እስከ 1972 ካገለገሉ በኋላ በ1972 በሊቀመንበርነት ተመረጡ። ይድነቃቸው ተሰማ ከእርሳቸው በፊት ሁሉ ልቀው ለአራት ተከታታይ የአገልግሎት አመታት ማለትም ከ1972 ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈችበት እስከ 1987 በሊቀመንበርነት አገልግለዋል።
በነዚህ ዘመናትም እግር ኳስ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተዋወቅና መስመር እንዲይዝ ከማገዛቸው ባለፈ የታላቁ ሰው አህጉራዊ ተፅዕኖም ጎልቶ መታየት ችሏል። ካፍ በ1949 ዓ.ም ካርቱም ላይ በሱዳን፣ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ አባልነት ሲመሰረት የተቋሙን መተዳደሪያ ደንብ በመቅረፅ ረገድ የይድነቃቸው አስተዋፅኦ ጉልህ ነበር። የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆን ሲያገለግሉም በዚሁ ዓመት የተጀመረውን የአህጉሪቱን ታላቅ ውድድር የአፍሪካ ዋንጫ እውን በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል።
ይድነቃቸው በአስተዳደሩ ረገድ በካፍ ውስጥ የነበራቸው ተፅዕኖ ከሚገለፅባቸው ነጥቦች አንዱ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት በመቃወም ሀገሪቷ በአህጉራዊው ውድድር ላይ እንዳትሳተፍ እና ከካፍ እንድትገለል ጫና ማሳደራቸው ነው። የታላቁ ሰው የፀና አቋምም ካፍ ሀሳባቸውን ተቀብሎ በ1951 ሀገሪቷን በማገድ በአስከፊው ሥርዓት ላይ ውሳኔ ያስተላለፈ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ተቋም ሆኗል። በወቅቱ አፓርታይድ በፊፋም ሆነ በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ተቀባይነት ነበረው። እነዚህ ትልቅ የስፖርት ተቋማትም የካፍን ውሳኔ “ፖለቲካንና ስፖርትን የሚቀላቅል” በሚል አጣጥለውት ነበር። ያም ሆኖ 1957 ላይ በጃፓን ቶክዮ በተደረገው የፊፋ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ጋና በህብረት አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ከአባልነት እንድትታገድ ያቀረቡት ጥያቄ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተቀባይነት አግኝቶ ደቡብ አፍሪካ ከፊፋ ውጭ እንድትሆን ተደረገ። በተመሳሳይ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ርሆዴሲያ (የአሁኗ ዚምባቡዌ) ከፊፋ እንድትወገድ ይድነቃቸው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በ1962 በሜክሲኮ የተደረገው የፊፋ ጉባዔ ላይም ከተፈሪ በንቲ ጋር በጋራ የህግ መዝገብ በማዘጋጀት እና መዝገቡ ለአባል ሀገራት እንዲቀርብ በማድረግ ርሆዴሲያ ከፊፋ እንድታገድ አድርገዋል።
በ1950ዎቹ መጨረሻ 30 አባል ሀገራት የነበሩት ካፍ በዓለም ዋንጫው ግን ግማሽ ኮታ ብቻ ነበረው። የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ እና የእስያ ዋንጫ አሸናፊ እርስበርስ ተጫውተው ከሁለቱ ያሸነፈው ቡድን ብቻ ዓለም ዋንጫውን ይቀላቀል ነበር። የማጣሪያ ሂደቱ ርዝመት፣ ከፍተኛ ወጪ እና የማለፍ የተመናመነ ተስፋ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በማጣሪያው እንዳይሳተፉ አደረጋቸው። የፊፋ አመራሮችም ይህንን ተጠቅመው የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን ድምፅ ብዛት ለመቀነስ ተንቀሳቀሱ ፤ “በሁለት ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ወይም የኦሊምፒክ ማጣሪያዎች ላይ ያልተሳተፈ ፌዴሬሽን በፊፋ ስብሰባዎች ላይ የመምረጥ መብት የለውም” የሚል ሃሳብ ያለው ህግም ማርቀቅ ጀመሩ።
በዚህ ወቅት ነበር ይድነቃቸው ተሰማ እና የአፍሪካ እግር ኳስ መሪዎች በጋናው ፕሬዘዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ድጋፍ ራሳቸውን ከ1959ኙ የእንግሊዝ ዓለም ዋንጫ ያገለሉት፤ በቀጣይ የዓለም ዋንጫዎችም ለአፍሪካ አንድ ሙሉ ኮታ ካልተሰጣት በቀር እንደማይሳተፉ ገለፁ። ፊፋ በመጀመሪያ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች ይህንን በማድረጋቸው እያንዳንዳቸው 5000 ፍራንክ ቅጣት እንዲከፍሉ ትእዛዝ ቢያስተላልፍም በመጨረሻ በጉዳዩ በመስማማት ለአፍሪካ አንድ የዓለም ዋንጫ ኮታ መደበ። በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በመቀላቀል የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አገር የሆነችው ሞሮኮም በ1963ቱ የዓለም ዋንጫ በመሳተፍ የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ለመሆን በቃች።
በ1965ቱ የያዉንዴ ጠቅላላ ጉባዔ ይድነቃቸው የሱዳኑን ዶ/ር አብዱልሃሊም መሃመድ 15 ለ 12 በሆነ የድምፅ ብልጫ በማሸነፍ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ሆነው ተመረጡ። በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት ይድነቃቸውም ከአማርኛ በተጨማሪ እንግሊዝኛ ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛን በጥሩ ሁኔታ መናገር መቻላቸው ተፅዕኗቸው በአህጉራዊ ደረጃ ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ይቻላል። በካፍ ፕሬዝዳንትነት በሰሩባቸው 15 ዓመታት የፈጠሯቸው ለውጦች በብዙዎች አስተሳሰብ እስካሁን ካየናቸው የአፍሪካ እግር ኳስ መሪዎች ሁሉ የበለጠ ስኬታማ አድርጓቸዋል። በይድነቃቸው የካፍ አመራር ስር በርካታ ፈር ቀዳጅ ስራዎች ተከናውነዋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ውድድር (የአሁኑ የኮንፌዴሬሽኖች ዋንጫ) በይድነቃቸው ጠንሳሽነት የተጀመሩ ውድድሮች ናቸው። የካፍ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ በ1974ቱ የሊቢያ የአፍሪካ ዋንጫ የቴሌቪዥን እና ስርጭት መብት ታይቶ በማይታወቅ ትርፍ ለመሸጥ ተችሏል። ይድነቃቸው የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም ያለውን ስፍራ ለማሳደግም በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል። ለዚህ አላማቸው ቁልፍ መሳሪያ አድርገው የተጠቀሙት ደግሞ በአፍሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ኮንፌዴሬሽኖች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነበር። በብራዚል የነፃነት ድል ማክበሪያ ውድድር ላይ ከአፍሪካ ሀገራት የተወጣጣ ቡድን እንዲሳተፍ ማድረጋቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2015