በሁሉም ዘርፍ የተጀመረውን አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማፋጠን አምራች ኢንዱስትሪዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል። መንግስት አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማነታቸውን እንዲጨምሩ፣ እንዲስፋፉ፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረው፣ ድጋፍና ክትትል የሚያደርገውም ለእዚህ ነው።
በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ። አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ተኪ ምርቶችንና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከቻይና ባለሃብቶች ጋር ያቋቋመው “ደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት” አንዱ ነው። ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ በመነሳት ትርጉም ያለው ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፤ በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪን በማዳን እንዲሁም ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ይህን መሰረት በማድረግ የድርጅቱን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴና የስኬት ጉዞ እንዲሁም የወደፊት ዕቅዱን በዛሬው የስኬት አምዳችሁ ልናስቃኛችሁ ወደናል።
በ2006 ዓ.ም ተቋቁሞ በ2007 ዓ.ም ወደ ማምረት ስራ የገባው ይህ ድርጅት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይም የውጭ ምንዛሬን በማዳን ረገድ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። በ2008 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ምርቶቹን ለሽያጭ ማቅረብ የጀመረው ደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት፣ በዋናነት የሚያመርተው ጣውላ መሆኑን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ባዩ ደጀኔ ይናገራሉ፡፡
ስራ አስኪያጁ እንደሚያስረዱት፤ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው “ደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት” በአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ 51 በመቶ እንዲሁም በቻይና የግል ባለሃብቶች 49 በመቶ ድርሻ የተመሰረተ ነው። በጥቅሉ ድርጅቱ በ80 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የልማት ድርጅት ነው።
በክልሉ በርካታ የባህር ዛፍ ቁም ደን መኖሩን የጠቀሱት አቶ ባዩ፤ ቀደም ሲል ይህ የቁም ደን ለቤት መስሪያነትና ለማገዶነት ብቻ ያገለግል እንደነበር ያስታውሳሉ፤ ደኑ በአማራ ክልል ደን ኢንተርፕራይዝ ስር መተዳደር ከጀመረ በኋላ ለፋብሪካው ግብዓትነት እንዲውል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የክልሉ መንግሥት ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ከፍላጎት ጋር አጣምረው ከያዙ አገራት ጋር በመሆን ፋብሪካውን ለመቋቋም ሲወጥን በቀዳሚነት ያገኘው ቻይናውያን ባለሃብቶችን ነው። በዚህ ምክንያትም ከክልሉ ጋር ለመስራት ፍላጎት ካሳዩ ባለሃብቶች ጋር በመሆን ወደ ሥራ መግባት ችሏል፡፡
ድርጅቱ በዋናነት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ጣውላ እያመረተ ይገኛል። በአካባቢው የሚገኘውን የቁም ደን ወይም ባህር ዛፍ በግብዓት የሚጠቀመው የደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ ለኮንስትራክሽን እና ለፈርኒቸር አገልግሎት የሚውሉ ጥራት ያላቸውን የጣውላ ምርቶች ያመርታል፡፡
የድርጅቱን ምርቶች ለማምረት ከባህር ዛፍ በተጨማሪ ኬሚካል አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት አቶ ባዩ፤ ኬሚካሉ የሚመጣው ከውጭ አገር እንደሆነ ነው የተናገሩት። ጣውላውን ለማምረት በመጀመሪያ ዜኒር የተባለው ምርት ከባህር ዛፍ ይመረታል። ኬሚካሎቹን ደግሞ ከቻይና፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከግብጽና ከሳውዳረቢያ በማስመጣት ለኮንስትክሽን እና ለፈርኒቸር ምርት በዋነኛነት ግብዓት የሆነውን የጣውላ ምርት በማምረት ለገበያ ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ ወደ ማምረት ስራ ከገባበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም 262 ሺ 624 ነጥብ 93 ቁም ደን ወይም ባህር ዛፍ ገዝቶ ወደ ፋብሪካው አስገብቷል። በዚህም 104 ሺ 209 ኪዩብ ዜኒር ወይም ስስ ጣውላ ማምረት ችሏል። ይህንኑ ዜኒር ወይም ስስ ጣውላ በመጠቀም ደግሞ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ለኮንስትራክሽንና ለፈርኒቸር ግብዓት መሆን የሚችሉ ንብርብር ጣውላዎችን አምርቷል። ይህንኑ ጣውላ ለገበያ በማዋልም 864 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ሽያጭ በማከናወን 193 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት ችሏል።
በ80 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመው ይህ ድርጅት፣ ገቢ በማመንጨት ውጤታማ እየሆነ መጥቷል፤ በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱን ያቋቋሙት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ቻይናውያን ባለሃብቶች የትርፍ ክፍፍል በማድረግ ድርሻቸውን መውሰድ እንደቻሉ አቶ ባዩ ተናግረዋል። ካፒታሉም አሁን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፤ በየዓመቱም የሚገኘውን የትርፍ ትርፍም የክልሉ መንግሥትና ቻይናውያኑ እየተከፋፈሉ እንደሆነ መረዳት ተችሏል፡፡
ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እያሳካ መሆኑን የተናገሩት አቶ ባዩ፤ በቀዳሚነት ለአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር 361 የሚደርሱ ዜጎችን በሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ አድርጓል። በሁለተኛ ደረጃ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ እንዲሸጋገር በማድረግ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በመሆኑም የዕውቀት ሽግግር ማድረግ ተችሏል። የድርጅቱ ሌላኛው ዓላማ የውጭ ምንዛሪን ማዳን በመሆኑ እስካሁን ባለው ሂደት ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪን ማዳን መቻሉንም አቶ ባዩ አስረድተዋል፡፡
ለኮንስትራክሽን እና ለፈርኒቸር አገልግሎት በስፋት የሚውለው ክላውድ ወይም የተነባበረ ጣውላ ከውጭ ይመጣ እንደነበር ያነሱት አቶ ባዩ፤ የደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ በአገር ውስጥ መቋቋሙ ይህን ምርት በሀገር ውስጥ በማምረት በኩል አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል። መሰል ድርጅቶችም ምርቱን ማምረት በመጀመራቸው ከውጭ ይገባ የነበረውን በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ ማዳን በመቻሉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ማበርከት እየተቻለ መሆኑን ነው ያብራሩት። በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ በመቀጠል ከውጭ የሚገባውን የጣውላ ምርት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የመተካት ዕቅድ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡
በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ በተለይም ለምርቱ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በመቀነስ ረገድ የድርሻውን እየተወጣ ያለው የደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ፣ ታማኝ ግብር ከፋይ እንደሆነም ነው የጠቀሱት። በዚህም ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ተሸላሚ መሆን መቻሉን አቶ ባዩ ተናግረዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድም የጣውላ ምርት በሚመረትበት ወቅት በርካታ ተረፈ ምርቶች የሚገኙበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንኑ ተረፈ ምርት በአነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ወጣቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል ይላሉ። 2000 የሚጠጉ አቅመ ደካማ እናቶች ተረፈ ምርቱን በነጻ እንዲጠቀሙ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ አቶ ባዩ አጫውተውናል።
የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ አንዱ ተልዕኮ ደንን ማልማት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ባዩ፤ ኢንተርፕራይዙ የተለያዩ ችግኝ ጣቢያዎችና የማልሚያ ቦታዎች እንዳሉት እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ጭምር በችግኝ ልማት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በደን ልማት ሰፊ ተሳትፎ ያለው የአማራ ደን ኢንተርፕራዝ በክልሉ መንግሥትና በቻይናውያን ባለሃብቶች ለተቋቋመው ድርጅት ደንበኛ በመሆን ቁም ደኑን የአካባቢውን ዋጋ መሰረት በማድረግ ያቀርባል። ፋብሪካው ከሚያገኘው ትርፍ ደግሞ የትርፍ ትርፍ ተከፋይ በመሆን ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የደን ልማቱን አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ እንደሆነ የገለጹት አቶ ባዩ፤ ለዚህም ክልሉ በርካታ ሥራዎችን እንደሚሰራም ይገልጻሉ። ድርጅቱ የሚጠቀመው ባህር ዛፍን ብቻ እንደመሆኑ ለባህር ዛፍ ደን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል ይላሉ። ለአብነትም ባህር ዛፉ ሲቆረጥ በባለሙያ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ነው። ባህር ዛፍ ሲቆረጥ ሌላ ቅርንጫፍ በማውጣት የማበብ ዕድሉ ሰፊ በመሆኑም የደን መመናመን አያስከትልም ሲሉ ያብራራሉ።
በዓመት ከሁለት መቶ ሺ ጣውላ በላይ እያመረተ የሚገኘው ድርጅቱ፣ በቀጣይም በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ በመሆን ጥራቱን የጠበቀ ጣውላ በማምረት ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ዕቅድ አለው። ይህም በአገሪቷ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማቃለል በኩል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ያስችለዋል።
ምርቱን በስፋት ለማምረት ባህር ዛፍ ዋናው ግብዓት መሆኑን ጠቅሰው፣ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ኬሚካሎች እንዳሉም ነው የሚናገሩት። እነዚህን ኬሚካሎች በስፋት በማምጣት እንዲሁም መለዋወጫ ማሽኖችን በማስገባት ምርቱን በስፋት በማምረት ከአገር ውስጥ ባለፈ ማስፋት እንደሚቻል አቶ ባዩ ይጠቁማሉ፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ ስድስት ነጥብ ሶስት ሄክታር ስፋት ባለው መሬት ላይ ያረፈው የደብረ ብርሃን ውድ ፕሮሰሲንግ ድርጅት በርካታ ማሽኖችን በውስጡ አቅፎ ይዟል። ከማሽኖቹ መካከልም ልጥና ቅርፊቱን ከሚለይ ከግንድ መላጫ ጀምሮ እስከ ፕላይድ መቁረጫ ድረስ ያሉ በጥቅሉ ከ30 የሚልቁ የተለያዩ ማሽኖች አሉ።
ድርጅቱ ምርቶቹን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚያደርግና ሰፊ ገበያ ያለው ግን በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን አቶ ባዩ ጠቁመዋል። የተለያዩ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ሥራ የሚያካሂዱ ተቋራጮች ማለትም በሪልስቴት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ምርቱን በስፋት እንደሚገዙም ነው የተናገሩት። ለአብነትም ሀያት ሪልስቴት በዘንድሮ ዓመት ብቻ 47ሺ ጣውላዎችን ከድርጅቱ መግዛቱን አቶ ባዩ ጠቅሰዋል። ከኮንስትራክሽን ዘርፉ በተጨማሪ ፈርኒቸር አምራቾች ምርቱን በስፋት እንደሚጠቀሙ አስታውቀው፣ ገበያውን በመላው አገሪቱ ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል ድርጅቱ በትጋት እየሰራ ይገኛል ይላሉ፡፡
ድርጅቱ ለልዩ ልዩ የግንባታ ሥራዎች እንዲሁም ለፈርኒቸር ምርቶች ሰፊ አገልግሎት የሚሰጠውን ንብርብር ጣውላ በስፋት አምርቶ ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ የምርቶቹን አይነት የማስፋት ዕቅድ እንዳለውም አቶ ባዩ ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ በተረፈ ምርት እና በሌሎች ግብዓቶች የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ይቻላል። ለዚህም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
ምርቱ ጥራት ያለው በመሆኑ የገበያ ችግር ያለበት ያሉት አቶ ባዩ፤ በጥራት ማምረት በመቻሉ ገበያውን ሰብሮ መግባት እንደቻለና ተፈላጊነቱ ሰፊ እንደሆነ ነው ያብራሩት። በቀጣይም ምርቱን በስፋትና በጥራት በማምረት ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ በመገኘት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ትልቁ አላማችን ነው የሚሉት አቶ ባዩ፤ የጣውላ ምርቱ በአገር ውስጥ መመረት በመቻሉ በዓመት ከሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን ነው የተናገሩት። ባለፈው ስድስት ወራትም ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬን ማዳን ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለውን ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባው የጣውላና ሌሎችም የግንባታ ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ባዩ፤ ድርጅቱም ለዚሁ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም