አማርኛችን ተበርዟል:: እረ እንዲያውም ተመርዟል:: በምን አላችሁኝ ? በባዕድ ቃላት ነዋ ! ተጋነነ እንዴ ? ሰውየው እንዳሉት… ብታምኑም ባታምኑም አማርኛችን ተዋርዷል ፤ በቁሙ ሞቷል ብዬ አላስደነገጥኳችሁ:: ታዲያ ምኑ ነው የተጋነነው ?
ራሱ ቴክኖሎጂን ጨምሮ አብረውት የመጡ ቃላት ሰ…ተ…ተ…ተ…ት (ቴዲ አፍሮ) ብለው አማርኛን ይቀላቀላሉ:: ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቶቻችን በቁጥር ቢጨምሩም ለአቅመ ምትክ ቃል ማዘጋጀት አልደረሱም:: ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በተለይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መስፋፋት ልብ ብላችኋል? አንዳንዶቹ እንደ ሸማቾች ሱቅ በየወረዳው ቅርንጫፍ አላቸው:: እኔ የምለው በቪዲዮ ኮንፍረንስ (ምትክ ቃል የለውም) ነው እንዴ የሚያስተምሩት ?
ህዝባችን መፍትሔ የሚጠበቅባቸውን ቁጭ ብሎ አይጠብቅም:: የራሱን መላ ይመታል:: ለአንደበቱ አዲስ የሆኑ ባዕድ ቃላትን ለአጠራር እንዲመቹ አድርጎ ከግብራቸው በማዋደድ ያበጃቸዋል:: «ቆጠሚኒየም» በዚህ መንገድ ኮንዶሚኒየም ለሚለው ባዕድ ቃል የተበጀ መጠሪያ ነው:: በእርግጥ አሁን አሁን ቆጠሚንየምን “የጋራ መኖሪያ ቤቶች” ብሎ መጥራት እየተዘወተረ ነው:: እኔ ግን ቆጠሚንየምን ስለወደድኳት የሙጢኝ አልኳት::
ቆጠሚንየም ዝም ብሎ መጠሪያ ሳይሆን ረቂቂ ስም ነው:: ምክንያቱም በዓመታት ጠብ የሚልን ርቆ የተሰቀለ መና ወካይ ነው:: የተመዘገቡ ብቻ ሳይሆኑ ወደፊት ተመዝግበን እናገኘዋለን ብለው የሚያልሙ ህልመኞች የቀን ከሌሊት ቅዠት ነው:: ሚሊየኖች ከጉሮሯቸው ነጥቀው የሚሞሉት ሆድ ነው:: አንዳንዴም ከቆመበት ቦታ ድንገት የሚሰወር መንፈስ ነው::
ለዚህ ነው አንድ ሰው ቆጠሚኒየም ሲደርሰው ሎተሪ እንደደረሰው ተቆጥሮ ወዳጅ ዘመድ እየደወለ “እንኳን ደስ አለህ” የሚለው:: ከሎተሪ ጋር መነጻጸሩ እንኳን ተገቢ አይመስለኝም:: ሎተሪ የደረሰው ደስታ አሳብዶት በገንዘቡ ሲታከም ባለቆጠሚንየምን ቅድመ ክፍያ አጥወልውሎ እዳ ውስጥ ይነክረዋል::
ሞልቶለት ቆጠሚንየም ውስጥ መኖር የጀመረ ሰው ከቀደመ ህይወቱ የቀዳውን ልማድ ለመድፋት ይገደዳል:: አዲስ የአኗኗር ዘይቤ መልመድ ይኖርበታላ ! ተያይዘው በተሰሩ መፈናፈኛ ደጅ በሌላቸው መንደሮች ውስጥ በጋራ ኖረን፣ ሁሉ ነገር የጋራ በሆነበት ቆጠሚንየም ግለኞች መሆናችን ይገርመኛል::
በእኔ ምልከታ አስር ዘጠና ፣ ሃያ ሰማኒያ እና አርባ ስልሳ በግንባታ ወጪ ብቻ ሳይሆን በኗሪዎቻቸው የእርስ በርስ ግንኙነትም የሰማይና የምድር ያህል ይራራቃሉ:: እንግዲህ የመክፍል አቅም ሲፈረጥም ማህበራዊ ግንኙነት ይከሳል ማለት ነው::
አስር ዘጠና ላይ አንዱ ቤት በተከፈተ ሙዚቃ ሌላኛው ቤት ሲጨፈር ፣ በአርባ ስልሳ ቆጠሚንየም አንድ ቤት ውስጥ ሙዚቃ ስለመከፈቱ ከቤቱ ኗሪዎች ውጪ ማንም አያውቅም:: የቆጠሚንየሞቹ ጥራት በመክፈል አቅማችን ልክ ስለተወሰነ አንዱ ተከብሮ አሳንሰር ተገጥሞለት ሲረከብ ሌላኛው ቸል ተብሎ የአሳንሰር መውረጃውን በቆርቆሮ ከልሎ ኑሮውን ይቀጥላል::
አብዛኞቹ የጋራ መገልገያ ማብሰያዎችና አዳራሾች በቀጥታ ቁልፋቸውን ተረክቦ የሚገባ ባለዕድል ስለሌላቸው ተጠናቅቀው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ለእድሳት ይዳረጋሉ:: ሲታደሱ የስራ ዕድል ስለሚፈጠር ችግሩ አሳሳቢ ተደርጎ የሚታይ አይመስለኝም::
ይህ ነው የሚባል ህግ ባለመኖሩ አንድ ቆጠሚንየም ህንጻ ላይ የሚገኙ ሰላሳ ቤቶች ሰላሳ አይነት ቀለም ተቀብተው አይንን ያጭበረብራሉ:: በዛ ላይ በብረትና ብሎኬት ተጨማሪ ግንባታ እየተደረገ በአንድ አካባቢ ላይ የተሰሩ ተመሳሳይ ቆጠሚኒየሞች ንድፋቸው የተለያየ እስኪመስል ተዥጎርጉረዋል::
ከቤት ፈላጊው አንጻር ግንባታው በኤሊ ፍጥነት መከናወኑ ሳያንስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ ቆጠሚኒየሞች እስከ ሁለተኛ ወለል ድረስ የንግድ ሱቆች ሆነዋል:: ስቱዲዮ (ምትክ ቃል የለውም) ለተመዘገቡ ሱቅ ሊሰጥ ይሆን ?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011
በየትናየት ፈሩ