ልጁ ገና የሶስት ዓመት ህጻን ሆና በተደጋጋሚ እየታመመች ስታስቸግረው ወደ ህክምና ተቋም ይዟት ይሄዳል፤ ህጻኗ የደም ካንሰር እንዳለባትና ወደ አዲስ አበባ ከተማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዳ ካልታከመች ችግሩ እንደሚከፋ ይነገረዋል። እሱም ያለውን ንብረት ሸጦ ጥሪቱን ይዞ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያቀናል፡፡ ሆኖም ከወሎ አዲስ አበባ ከተማ ከመጣ እንደ ቀልድ ሶስት ዓመታት ሆነውታል።
ስሙን መግለጽ ያልፈለገው አባት ምንም እንኳን አዲስ አበባ ሲገባ ለአንድ ቀን እንኳን ተጠልሎ የሚያርፍበት ዘመድ አልነበረውም፡፡ ቢሆንም ልጁን አሳክሞ ለማዳን ሲል ያለችውን ቋጥሮ ከመምጣት አልቦዘነም። እንደተባለው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደርሶ ልጁን አስመረመረ፤ ህጻኗ ልጁም የደም ካንሰር ታማሚ መሆኗንና ሰፋ ያለ የህክምና ክትትል እንደሚያስፈልጋት ተነገረው።
የሰማው ነገር ለእሱም ሆነ ለያዛት ህጻን ልጁ ከባድ ቢሆንም አሳክሞ የማዳን ህልሙ ግን ከውስጡ አልጠፋም፤ እስከ ጥቂት ጊዜ ድረስም ያለችውን ለአልጋና ለምግብ እየከፈለ ልጁን በቀጠሯዋ ቀን ሀኪም ቤት እያመላለስ ታገለ፤ ነገር ግን የህክምናው አስቸጋሪነት፤ ከልጅቷ ሁኔታ፤ እሱም በኪሱ ያለው ገንዝብ እያለቀ መሄዱ ሃሳብ ላይ ጣለው። ጭንቀቱን ይዞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሲንከራተት ለእሱም ሆነ ለልጁ ታላቅ ነገርን ሊያደርጉ ያሰቡ ቅን ኢትዮጵያውያንን አገኘ።
በዚህም ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት (ታፕኮ) እኛ እናግዝሃለን መጠለያም ምግብም አንዳንድ የህክምና ወጪህንም እንሸፍናለን ልጅህም ትድናለች የሚል ተስፋን ሲሰጡት ማመን ተቸግሮ እንደነበር ይናገራል።
አባትና ልጅም በድርጅቱ ማደሪያ ምግብ እንዲሁም ወደ ሆስፒታል ለመመላለስ የሚያስችል ትራንስፖርትና አንዳንድ የህክምና ወጪዎቻቸው ተሸፍነው ልጁ ህክምናውን መከታተል እሱም ከሀሳብ መዳን ቻለ።
የሕፃኗ አባት አሁን የሚያስጨንቀው ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ትቷቸው የመጡት ቤተሰቦቹ ሁኔታ ነው። በቅርብ ሆኖ የአባትነት ሚናውን አለመወጣቱ ያሳዝነዋል። መለስ ሲል ደግሞ ታማሚዋ ልጁ አሁን ላይ ያለችበት የማገገም ሁኔታ ያስደስተዋል። ይህ ሁሉ ነገር አልፎ ደግሞ ልጁን በጤና ይዞ አገሩ በመግባት ከቤተሰቦቹ እንደሚቀላቀል ሲያስብ ተስፋው ያብባል።
“አዲስ ተስፋ ባይኖር ልጄን እንኳን ላሳክማት ላስበውም እንኳን እቸገር ነበር፤ አንድ ቀን ማደሩም ከባድ ይሆንብኛል። መኝታ፣ ምግብ፣ መድሃኒትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉልን ነው፤ በእውነት እንዲህ ያሉ ደጋጎች ሊመሰገኑ ይገባል” ይላል።
ወጣት ወርቅዬ መልካሙ በኩላሊት ካንሰር የታመመች ትንሽ እህቷን ለማሳከም ከራያ ቆቦ ነው የመጣችው። ወርቅዬ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ እህቴን አድናለሁ ብላ ከአገሯ ከወጣችም ወራቶች ተቆጥረዋል። ወርቅዬም አዲስ አበባ የምታርፍበትና የምታውቀው አንድም ሰው ባይኖርም እህቴን ማዳን አለብኝ ብላ ቤተሰቦቿ የሰጧትን ይዛ ነበር የመጣችው።
እሷም በተመሳሳይ በጥቁር አንበሳ ጠቋሚነት ወደተስፋ አዲስ ድርጅት በመምጣት ለእሷም ለእህቷም ማረፊያ ምግብ አግኝታ፤ በቀጠሮዋ ቀን እህቷን ይዛ ሄዳ አሳክማ እየመጣች ነው። “ ይህ ትልቅ እድል ነው፤ የምትለው ወርቅዬ እንደዚህ አይነት ድርጅት ባይኖር ኖሮ ህክምናውን ለመከታተል አቅማችን አይችልም ነበር። እህቴም እስከ አሁን ትጎዳብኝ ነበር” በማለት ሁኔታውን ትናገራለች።
ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት (ታፕኮ) ተርፋማ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን ህጋዊ ህልውና ያለውና ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው። ድርጅቱ የተመሰረተው በወላጆችና አላማውን በሚደግፉ ግለሰቦች ነው፡፡ የካንሰር ታማሚ ሕጻናት በሆስፒታል ቆይታቸው በቂ ህክምናና እንክብካቤ የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠር በቀጣይነት ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ጥረት የሚያደርግ ድርጅት ነው።
የማህበራዊ ዘርፍ ሰራተኛ የሆኑት ፋንቱ ሃዋዝ ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት በወላጆች የተመሰረተና የህጻናት ካንሰር ላይ የሚሰራ እንደመሆኑ እስከ አሁንም በርካታ ህመሙ ያለባቸውን ህጻናት በተለያዩ መንገዶች እያገዘና እየደገፈ መገኘቱን ያወሳሉ።
ድርጅቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጅማ፣ በጎንደር እንዲሁም በመቀሌ ቅርንጫፎችን በመክፈት ህመሙ ያለባቸው ህጻናት በወቅቱ ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ለወላጆቻቸው የምክርና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች ላይ መስጠቱንም ያነሳሉ።
እንደ ፋንቱ ማብራርያ ድርጅቱ ከጥቁር አንበሳና ከጳውሎስ ሆስፒታሎች ጋር በጥምረት የሚሰራ ሲሆን ህመሙ ያለባቸውንና መረዳት የሚያስፈልጋቸውን ህጻናትም ከእነዚህ ሆስፒታሎች የሚላኩ ናቸው። በመረጣው በኩልም በሆስፒታሎቹ ውስጥ የሚሰሩ የድርጅቱ ሰራተኞች መኖራቸውን የሚናገሩት ፋንቱ በዳታና በስነ ልቦና አማካሪነት እየሰሩ ህጻናቱም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እየለዩ ወደ ድርጅቱ እንደሚልኩም ይናገራሉ።
በተለይም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ታማሚ ህጻናቱ እየተመላለሱ ህክምናቸውን በሚያገኙበት ማዕከል ላይ የምግብ አገልግሎትና የስነ ልቦና ማማከር ስራ እንደሚሰራ ገልጸው፤ እነዚህ ባለሙያዎች ደግሞ የልጆቹንና የወላጆቻቸውን ሁኔታ በማየት እንዲሁም ከህክምና ባለሙያዎቹ ጋር በመነጋገር እገዛ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ ማስረጃ በማስያዝ ወደ ድርጅቱ ይልኳቸዋል። በድርጅቱ በኩልም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያገኙ ይሆናል።
“እኛ በአብዛኛው የክልል ታማሚዎች ላይ ነው ትኩረት አድርገን የምንሰራው። ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየኖሩ የአቅም ውስንነት ያለባቸውንና የካንሰር ታማሚ ህጻን ያላቸውን ሰዎች እናግዛለን። እዚህ ላይ ትኩረታችንን ክልሎች ላይ የማድረጋችን ዋናው ምክንያት እነዚህ ሰዎች ካሉበት አገር መጥተው አንዴ ህክምና አግኝተው ወደ አገራቸው ሊሄዱ አልያም ደግሞ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ሊሰጧቸው ይችላሉ፤ በዚህን ጊዜ ብዙዎቹ አቅም ስለማይኖራቸው አገራቸውም ላይ ቤተሰብ መበተን ስላለባቸው አንዴ ከሄዱ ዳግም አይመጡም። ይህ ደግሞ ህክምናው እንዲቋረጥ ያደርጋል። እኛም ይህንን የመከላከል ስራን ነው የምንሰራው” ይላሉ።
በመሆኑም ከሆስፒታል በህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም በእኛ ሰራተኞች የተላኩልንን ህመምተኛ ህጻንና ወላጆቻቸውን በመቀበል ፎርም አስሞልተን የመጠለያ፣ የምግብ፣ ንጽህና እንዲጠብቁ የማድረግ አብዛኞቹ ደግሞ ከቤታቸው ሲወጡ ቶሎ እንመለሳለን የሚል ሀሳብ ስለሚይዙ ቅያሪ ልብስ አይኖራቸውምና እሱን የመሸፈን ፣ በቀጠሯቸው ቀንም ታክሲ በመኮናተር ህክምናቸው ጋር ደርሰው የሚመጡበትን ሁኔታ የማመቻቸት ስራ እንሰራለን ይላሉ።
ህጻናቱም ሆኑ ወላጆቻቸው ቀጠሮ ከሌላቸው ሆስፒታል አይሄዱም በመሆኑ በድርጅቱ ውስጥ ሲቀመጡ ይበልጥ የተረጂነት ስሜት እንዳያዳብሩ ህጻናቱ ትምህርት አቋርጠው ከሆነ እሱን እንዲያስታውሱ የሚያደርግ ትምህርት፤ ያለጀመሩትም ቢሆኑ ከፊደሎች ጋር እንዲተዋወቁ ማድረግ ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህመማቸውን እንዳያስታውሱ የልጅነት ጊዜ እንዲኖራቸው ተጫወትኩ ጓደኛ ኖረኝ የሚለውን ነገር እንዲያዳብሩ በመጫወቻ ክፍላቸው የተለያዩ ጨዋታዎች እንዲጫወቱ ፣ ስዕሎችን እንዲስሉ እርስ በእርሳቸው ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ ።
ወላጆቻቸውም ቢሆኑ በሚችሉት መጠን የእጅ ስራዎችን እየሰሩ ራሳቸውን እንዲደግፉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም ያክላሉ።
ድርጅቱ ወላጆችን በቀን ሶሰት ጊዜ ህጻናቱ ደግሞ በቀን አምስት ጊዜ ይመግባል። በተለይም ህጻናቱ ፕሮቲን ቅባት ያላቸውና ሌሎች ሰውነት ገንቢና በሽታ ተከላካይ ምግቦችን እንዲያገኙ ያደረጋል።
ድርጅቱ በአፍንጮ በር በኩል ባለው የጥቁር አንበሳ ቅርንጫፍ ማዕከል ላይ የካንሰር ህክምናውን ለሚከታተሉ ህጻናት ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት እንቁላል፣ ዳቦና ወተት በማቅረብ የድርጅቱን ህጻናት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ህክምን ሊከታተሉ ለመጡና የፈለጉ ህጻናት በሙሉ ቁርስ ያበላል። በተጨማሪም የምሳ ሰዓትም ላይ በተመሳሳይ ምሳ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ይናገራሉ።
በሌላ በኩልም አብዛኛው የካንሰር ታማሚ ህጻናት የሚታከሙበትን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን እያገዝን ነው በምንችለው አቅም የልጆች ህክምን ክፍሎችና መኝታ ክፍሎች መታደስ ሲፈልጉ እናድሳለን፣ ባሉበት ሁኔታ ስዕል የመሳል ቀለም የመቀባት በጠቅላላው ሳቢ የማድረግ ስራ ይሰራል፤ አቅም ሲፈቅድና ለጋሽ አካላት ሲገኙ ደግሞ የጎደሉ የህክምን መሳሪያዎች እንዲሟሉ የማድረግ ስራም ይሰራል።
ድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ህጻናትና የህክምና ቀጠሯቸው እንዳያልፍ ከፍ ያለ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ገልጸው ምንም እንኳን የራሱ የሆነ መኪና ባይኖረውም በቀጠሯቸው ቀን ታክሲ በመኮናተር አድርሶ የመመለስ ስርም እንደሚሰራ ይናገራሉ።
በሌላ በኩልም ህጻናት ይዘው እዚህ የተቀመጡ ወላጆች አገራቸው ላይ ሌሎች ልጆች፣ ቤተሰብ፣ ስራም አላቸው እናም ሁሉንም እኩል ማስኬድ እንዲችሉ በተለይም ልጆቹ የወር ቀጠሮ በሚሰጣቸው ጊዜ አገራቸው ደርሰው እንዲመጡ ድርጅቱ የትራንስፖርት ወጪያቸውን ይሸፍናል። እዚህ ላይ ግን ሰዎች ለእኔ ነው ብለው እንዲያስቡና ጥገኝነትንም አብዝተው እንዳይለማመዱ መመለሻ የትራንስፖርት ወጪያቸውን የሚችሉት ራሳቸው ናቸው።
“ …… ሁሉም እንዲያወቅ የምፈልገው ድርጅቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥና አምስት ኪሎ ጥቁር አንበሳ ካንሰር ማዕከል ላይ የስነ ልቦና አማካሪዎችን ቀጥሮ በድርጅቱ ለሚታገዙት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ካንሰር ታማሚ ልጅ ላላቸው ቦታ የመምራት ፣ መድሃኒት የማገዝ ፣ እንዳይጨነቁ ምክር የመስጠት ድጋፎችን ያደርጋል” ይላሉ።
ድርጅቱ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላይ አንዲት እናት ጓደኞቿን ይዛ ቡና ጠጡ እያለች ወላጆችንን በማወያየት የመሰረተችው ነው። ከዛ በኋላ ግን አሜሪካን አገር በኢትዮጵያዊ ልጅ ምክንያት የተመሰረተ ዘ- አዝላን የሚባል ፕሮጀክትን የመሰረቱት አሜሪካውያን ነርሶች ዶክተሮች ፕሮፌሰሮች ተሰባስበው ገንዘብ በመሰብሰብ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ይህንንም ድርጅት በጣም እያገዙ ይገኛሉ። በተጨማሪም አሜሪካን ካንሰር ሶሳይቲ ይረዳናል። በአገር ውስጥ ያሉ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ካምፓኒዎች ብዙ ድጋፎችን ያደርጉልናል ብለውናል።
‹‹ለምሳሌ አሁን ላይ ትልቁን ችግራችን የሆነውን የመድሃኒት ወጪ የሚያግዘን የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ነው›› ይላሉ፡፡ እንዳከሉት በጀት መድቦ የሚፈልጉትን መድሃኒት በሙሉ እያገዛላቸው ይገኛል ፤ ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪ ላለፉት ረጅም አመታት የላብራቶሪ ስራዎችን በነጻ ሰርቶላቸዋልም ፤ ውዳሴ ዳያግኖስቲክስ ማዕከል በግማሽ አልያም አንዳንዴ በነጻ ምርመራዎችን በመሥራት ያግዛቸዋል።
ፋንቱ እንደሚሉት እነዚህ ድርጅቶች በህክምናው በኩል መሟላት ያለባቸውን ያግዙ እንጂ ጠዋት ጠዋት በጥቁር አንበሳና አምስት ኪሎ ማዕከል የሚቀርበውን ቁርስ ሙልሙል ዳቦ በማቅረብ ለረጅም ዓመት አብሯቸው እየሰራ ነው፤ ሞዬ ቡና ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ልደት ምርቃትና ሌሎች ዝግጅቶችን በድርጅቱ ውስጥ በማክበር ያግዛል፤ በተነሳሽነት ምሳ እራት የሚያበሉ በርካታ ደጋጎች አሉ፤ ጤፍ፣ ወተት፣ ዘይት፣ ስጋ፣ እንቁላልና ሌሎችንም እያመጡ የሚሰጡ አሉ፤ ይህ በጣም የሚያስደስትና ሊበረታታ የሚገባው ነው። እንደዚህ ዓይነት ድጋፎች ባይኖሩ ደግሞ ድርጅቱም ባለው አቅም መቀጠል ይከብደዋል ባይ ናቸው።
ድርጅቱ እስከ 50 ህጻናት ከነወላጆቻቸው የሚያስተናግድ አቅም ያለው ሲሆን ቁጥሩ እንደ ሁኔታው ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል፤ ምክንያቱም በረጅም ቀጠሮ አገራቸው የሚሄዱ ሊኖሩ ይችላሉ ሆስፒታል ይተኛሉ ዛሬ ላይ 40 ገደማ ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር ይገኛሉ። ድርጅቱ ከጀመረ ጀምሮ አገልግሎቱን አግኝተው የዳኑ ልጆች ግን ከ 2ሺ ይበልጣሉ።
የህጻናት ካንሰር ከአዋቂዎች ጋር ስናወዳድረው በተሻለ ሁኔታ የመዳን እድሉ ከፍ ያለ ነው፤ ብዙ የተደረጉ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይህንን ነው። ነገር ግን በህብረተሰቡ ውስጥ ይድናል የሚለው ግንዛቤ ገና ስለሆነ ወደ ህክምና ቦታ የሚሄዱት ዘግይተው ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የካንሰር ደረጃውን ከፍ ስለሚያደርገው ለማከምም ሆነ ለመዳን ብዙ ህክምናና ወጪን ይጠይቃል። በመሆኑም ግንዛቤ ላይ መስራቱ ገና ይቀረዋል የሚል ግምት አላቸው።
“….. አሁን ላይ ለህጻናት ካንሰር ህመም የተሰጠው ትኩረት ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነጻጻር መሻሻሎች ያሉት ነው። ዘ -አዝላን ፕሮጀክት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰራው ስራ ለምሳሌ ጳውሎስና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች እያንዳንዳቸው ሁለትና ሶስት የህክምን ባለሙያዎች ኖሯቸዋል፤ ጅማ አንድ፣ ጎንደር አንድ፣ መቀሌ አንድ የካንሰር ስፔሻሊስቶች አሉ። ይህ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው። አሁን ደግሞ እየተማሩ ያሉና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደስራው የሚቀላቀሉ በርካቶች አሉ” በማለት ይገልጻሉ።
በሌላ በኩልም ባለሙያዎችን ከማሰልጠን አልፎ ጤና ሚኒስተር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ራሱን የቻለ የስራ ዘርፍ በማድረግ ከእኛ ድርጅት ጋርም ጥሩ የስራ ግንኙነትን በመፍጠር አብሮ እየሰራ መሆኑ እኛንም የሚያበረታታና ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
“50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሀምሳ ሰው ጌጡ” እንደሚባለው ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድሁድ ካንሰር ድርጅት የማህበራዊና ስነልቦናዊ ድጋፎችን ለህጻናቱና ለወላጆቻቸው ያደርጋል። እኛስ ለእነዚህ ህጻናትና ወላጆች አለንላችሁ ብንላቸው መልካም ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም