እርግጥ ነው ሳቅ ጨዋታ የለመዱ ቦታና ጊዜያት ጭር ሲሉ ማንም አይወድም። መኖሪያ ቤትም ሆነ አካባቢ እንደዛው ነው። ይሁን እንጂ፣ እያወራን ያለነው ከአገርና ሕዝብ አጠቃላይ ደህንነት አኳያ በመሆኑ ከዚህ ጋር የሚጋጭ አይደለም።
ከሁሉም በላይ “ጭር ሲል አልወድም” የሚለው መሰረተ ሃሳብ፣ እድሜ ለድምፃዊት እናና ዱባለ፣ በዜማ ይታወቃል። ድምፃዊቷ “ጭር ሲል አልወድም” ያለችው በመግቢያችን ላይ ካነሳነው ማህባራዊ አውድ አኳያ ነው።
ልዩነታችን እኛ ጉዳዩን እዚህ ያነሳንበት አቢይ ምክንያት ከ“አገርና ሕዝብ ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት . . .” አንፃር መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ሰፊ ልዩነት ነውና ሁለቱንም በየአውዳቸው ማየቱ ፋይዳው ብዙ ስለሆነ ለዛሬ ይህንን የያዝነውን ይዘን እንዝለቅ።
ዛሬ ላይ ሆነን ድሮን ስናስታውሰው በርካታ ልዩነቶች ያሏቸው ሲሆን፣ ከልዩነቶቻቸውም አንዱ ለጋራ ሰላምና ፀጥታ፤ ደህንነትና ለጋራ ማንነት ቅድሚያና ትኩረት መሰጠቱ ነው። ከሁሉም፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገርና ሕዝብ ላይ ምንም አይነት ድርድር አለመኖሩ ነው። በቃ፤ ይኸው ነው።
ድሮ፣ (“ድሮ” ስንል በዚሁ ጸሐፊ እድሜ ማለት መሆኑን ልብ ይሏል)፣ በማንም ሰፈርና አካባቢ፤ በየትኛውም ቦታና ስፍራ … ጭር እንዳይል አይፈለግም። ድሮ፣ በየትኛውም ሁኔታና አኳኋን ውስጥ ሰላም እንጂ ሁከትና ረብሻ ቦታ የላቸውም። አንዱ ለአንዱ ከማሰብ ውጭ፣ እንዲህ እንደ ዛሬው፣ አይን ያወጣ ባላንጣነትና ጠላትነት የለም።
ሁሉም ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃና ከመኝታው ሲነሳ “አገራችንን ሰላም አድርግልን” ብሎ ከመፀለይና ፈጣሪውን አመስግኖ ከመማፀን ውጭ ሌላ ነገር የለም። ይህ ደግሞ በሴራውም ሆነ እሬቻው፤ ጨምበላላውም ሆነ ሌላው ያውና ያው ነው። ዛሬስ? ዛሬ “ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ ሆኗል” መባል ከተጀመረ ሰንብቷል። ልክ ሰላም እንደ ራቀን፣ ፍቅር እንደራበን … ሁሉ የምንወደው በማንወደው ከተተካ ቆይቷል።
ዛሬ፣ በችግር ላይ ችግር እንጂ በፍቅር ላይ ፍቅር … ተረት የሆነ ሁሉ ይመስላል። ዛሬ፣ ነገሩ ሁሉ “የበላችው ያገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንደ ተባለው ነገሮች ሁሉ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄዱ እንጂ በተቃራኒው ሲጓዙ አይታዩም። ያኛው ትኩሳት “በረደ” ሲባል ይሄኛው ያገረሽበታል።
እዛጋ እየነደደ ያለው እሳት “ጠፋ” ሲባል እዚህ ጋ ያለው ይለኮስና ይንቦለቦላል፣ ይንቀለቀል ዘንድ ይቆሰቆሳል። እዛ ማዶ ያለው ውሃ “ጠራ” ሲባል እዚህ ያለው ይደፈርሳል። በመሆኑም፣ እምንጠጣው እያጣን ተቸግረናል። ብርሀን በጭለማ እየተተካብን እነሆ ከቀናት ወደ ቀናት፣ ከወራት ወደ ወራት፣ ከአመታት ወደ አመታት … “እየተሸጋገርን” እንገኛለን።
መሸጋገራችን ባልከፋ፣ ችግሩ ሁሌም “መሸጋገሪያ …” እየተባለ (ገጣሚው “መለየት አቃተኝ ዳንሱን ከዳንሰኛ” እንዳለው አይነት) የሚሻገረውን ከማይሻገረው፤ የማይሸጋገረውን ከሚሸጋገረው መለየት ማቃቱ እንጂ።
ድሮ፣ “የሰው ጠላት አውሬ ነው” ይባል ነበር ነው የሚባለው። ዘመናትን በድርጊት ቅደም ተከተል የገመገሙ ሊቃውንት አባቶቻችን ዛሬ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆነና “የሰው ጠላት ሰው ነው” ወደ’ሚል አሳዛኝ ተረክ ተቀይሯል ነው የሚሉት።
እዚህ ላይ በምሁራን ዘንድ አብዝቶ የሚጠቀሰውን የእንግሊዙን ፈላስፋ፣ በርትራንድ ራስልን መጥቀስ ይቻላል። በርትራንድ አንዲት እናት በወቅቱ በነበረው ብልሹ አሰራርና አመራር ተበሳተጭው ወደ ጫካ ሲሄዱ ያገኛቸዋል። “ምነው፣ ወዴት ነው?” ሲልም ይጠይቃቸዋል።
ሁሉንም ይነግሩታል። አቅጣጫቸውም ወደ ጫካው መሆኑንም ራስል ይረዳል። “እዛ እኮ አውሬ አለ” ሲልም ይነግራቸዋል። “እዚህ ካለው [ዘ’ለነዋል] እዛ ያለው አውሬ ይሻላል።” ብለውት መንገዳቸውን ቀጠሉ።
እርግጥ ነው፣ እኛ እዛ ደረጃ ደርሰናል/ አልደረስንም ሌላ ነገር ነው። ምናልባትም ያከራክር ይሆናል። ባያከራክር እንኳን ያወያይ ይሆናል። ጉዳያችን እሱ አይደለምና ወደ“ጭር ሲል አልወድም” ርእሰ ጉዳያችን እንሂድ።
አንዳንድ ቆሽታቸው እርርርርር… ድብን…. ያለ ሰዎች ሲናገሩ እንደሚሰማው የዚህ ሁሉ ክፋትና ተከታዮቹ መንስኤ “ጭር ሲል” የማይወዱ ሰዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፤ የንፁሀንን ሕይወት አሲዘው የፖለቲካ ቁማር የሚቆምሩቱ እየበዙ መምጣታቸው ነው።
“አንዳንድ” (እቺ “አንዳንድ” በየት በኩል ዞራ መጣች ደግሞ) “የድሮ ናፋቂዎች” እንደሚሉት፣ ድሮ የቅድሚያ ቅድሚያ ሲሰጥ የነበረው ለአብሮነት፣ አብሮ ስለመኖር ነበር። ዛሬ ይህ ተራውን ለ“እኔ”ነት አስረክቦ እብስ ብሏል። የ’ሱ እብስ ማለት ደግሞ የዘመኑን እዳ ከመረው እንጂ ገብስ አላደረገውም።
እነዚሁ “አንዳንድ … የድሮ ናፋቂዎች” እንደሚሉት “83”ን ተገን አድርጎ ብቅ ያለው “እኔ”ነት፣ ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለች … እንዲሉ፣ “ድሆ ድሆ …”፤ በፍጥነት ኢትዮጵያን አጥለቅልቆ ኢትዮጵያዊነትን አደብዝዟል።
ከሁሉም የከፋው መግባቢያ ይሆን ዘንድ ታስቦበት ለሰው ልጅ ብቻ በፈጣሪ የተሰጠው ቋንቋ ሳይቀር እያታኮሰ መገኘቱ፣ አካባቢያዊነት እያጋደለና እያገዳደለ ለ“ጭር ሲል አልወድም” አፍቃሪና አቀንቃኞች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ “ጭር ሲል አልወድም …” ከወዴት ይገኛል?
ባጠቃላይ፣ ይህ ጽሑፍ ለጥያቄያዊ ርእሳችን፣ ”ጭር ሲል የማንወድ ከሆነ፣ የምንወደው ምንድን ነው?” በማለት ለሰየምነው ርእሰ ጉዳያችን ምላሽ ሰጥቶ ይሁን ወይም/እና አይሁን አናውቅም። ምላሽ ሰጠም አልሰጠም ጉዳዩ እሱ ባለ መሆኑ ብዙም አያሳስብም።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለጉዳዩ መልስ የሚሆነው “እያንዳንዳችን ጭር ሲል እንወዳለን፣ ወይስ ሳይል?” ለሚለው “ራስ መዛኝ ጥያቄ” የምንሰጠው መልስ ነውና እሱው ላይ አተኩረን አንዳች አገራዊና ሕዝባዊ ፋይዳ ያለው ውሳኔ ላይ ከደረስን በቂ ነው።
ቸር እንሰንብት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም