በኮትዲቯር 2023 አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ማጣሪያ ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ሶስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን በፈረንጆቹ መጋቢት 20 ያከናውናሉ። ዋልያዎቹ ከአርባ ቀናት በኋላ ጊኒን ከሜዳቸው ውጪ ገጥመው የመልሱን ጨዋታ በሰባት ቀናት ልዩነት በሜዳቸው እንደሚያከናውኑ ካፍ ያወጣው መርሃግብር ይጠቁማል። ይሁን እንጂ ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንደሚያከናውኑ ከቀናት በፊት ተረጋግጧል።
ዋልያዎቹ ባለፈው ግንቦት በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ በማላዊ 2 ለ1 መሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በሁለተኛው የማጣሪያ ጨዋታ ግብጽን በሜዳቸው ማስተናገድ ስላልቻሉ እዚያው ማላዊ ላይ በገለልተኛ ሜዳ ገጥመው ፈርኦኖቹን 2 ለ0 ማሸነፍ ችለዋል። በዚህም በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ በማግኘት በግብ ልዩነት ቀዳሚ ደረጃን የያዙ ሲሆን በመጪው መጋቢት ወር ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ እና በሜዳቸው ለማድረግ መርሐ-ግብር ተይዟል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ዋልያዎቹ ጨዋታውን በደጋፊያቸው ፊት እንደማያደርጉ ተረጋግጧል።
ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር የሚያደርጉትን አራተኛ የማጣሪያ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በፈረንጆቹ ሰኔ 12 ከማላዊ ጋር የሚጠብቃቸውን አምስተኛ የማጣሪያ ጨዋታም በሜዳቸው የማከናወናቸው ጉዳይ ብዙ ተስፋ ያለው አይደለም። ከማላዊው ጨዋታ በኋላ ከግብጽ ጋር የሚያደርጉት የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታም ከሜዳቸው ውጪ እንደመሆኑ ቀሪዎቹን ሁለት ማጣሪያዎች ዋልያዎቹ በሜዳቸው ማድረግ ሲገባቸው ለመሰደድ ይገደዳሉ ማለት ነው።
ካፍ በቀጣዩ መጋቢት በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሀገራት የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ስታዲየምን ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ መስፈርቱን የሚያሟላ መጫወቻ ሜዳ ማስመዝገብ አልቻለችም። በወጣው ዝርዝር የደርሶ መልስ ጨዋታ መርሃግብር መሰረት የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ጊኒም እንደ ኢትዮጵያ ፍቃድ ያለው ስታዲየም ባለማስመዝገቧ በሜዳዋ የምታደርገውን ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ የምታደርግ ይሆናል። ይህንን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የምታደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ዋልያዎቹ ቀሪዎቹን ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች በሜዳቸው እንዲያደርጉ በመንግሥት በኩል ስቴድየሞች የካፍን መስፈርት እንዲያሟሉ ጥረት እንደሚደረግ ከተገለጸ ቆይቷል። በተለይም ዋልያዎቹን ከስደት ለመታደግ ተስፋ የተጣለበትን አንጋፋውን የአዲስ አበባ ስቴድየም እድሳት በማፋጠን የካፍን መስፈርት እንዲያሟላ ጥረት መደረግ ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም እድሳቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ አለመገኘቱ ካለው የጊዜ እጥረት አኳያ ዋልያዎቹ በቀጣዮቹ ማጣሪያዎች መሰደዳቸው እንደማይቀር ማሳያ ሆኗል።
ዋልያዎቹ ከጊኒና ማላዊ ጋር የሚያደርጉትን የማጣሪያ ጨዋታ ያስተናግዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአዲስ አበባ ስታዲየም አንደኛው ምእራፍ የእድሳት ስራ መጠናቀቁ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል። ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሁለተኛውን ምዕራፍ የዕድሳት ሥራ ለማከናወን 150 ሚሊዮን ብር መመደቡን የገለጸውም ከሳምንት በፊት ነበር።
ስታዲየሙን ካፍ በሚፈቅደው መስፈርት መሰረት አድሶ ወደ ስራ ለማስገባት በሰኔ 2013 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ ሥራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ዕድሳት የአንድ አመት ጊዜ ቀጠሮ ተይዞለት በ39 ሚሊዮን ብር ወጪ በተለያየ ምክንያት በታቀደው ጊዜ ሳይጠናቀቅ ቀርቷል። በቅርቡ ግን የመጀመሪያው ምእራፍ እድሳት ተጠናቆ አሁን ላይ የመጫወቻ ሜዳ ሳር ተከላው መጠናቀቁ ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚሰሩ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች እድሳትን ጨምሮ የስታዲሙ ግንባታ አሁን ላይ 97 በመቶ ስራው ተጠናቋል።
የሁለተኛውን ምዕራፍ ዕድሳት ለማከናወን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ጨረታ መውጣቱን በመግለጽ ጨረታው እንደተጠናቀቀ ከአሸናፊው ድርጀት ጋር ውል በመዋዋል ስራው በፍጥነት እንደሚጀመር አስታውቋል። ይህ ጥረት ግን እንደተገለጸው ቀሪውን ሶስት በመቶ እድሳት ለማጠናቀቅ ዋልያዎቹ ሁለቱን የማጣሪያ ጨዋታዎች ለማከናወን ከቀራቸው ጊዜ አንጻር ይሳካል ተብሎ አይጠበቅም። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሁለተኛው ምእራፍ እድሳት መቼ እንደሚጠናቀቅ ያስቀመጠው ጊዜ የለም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015