ዛሬ ራዕዩን “ተፈላጊና የላቁ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውለው የዜጎች ሁለንተናዊ ህይወት በፍጹም ተለውጦ ማየት”ን ወዳደረገው፤ ነፍስን በሚያለመልም አፀድ በተዋበው፤ ሙሉ ፀጥታ ባረበበበትና መቀመጫውን ከመገናኛ ወደ ሃያት ሲያቀኑ መሀል ላይ ወደ ቀኝ ገባ ባለው ባደረገውና ከግማሽ ምእተ አመት በላይ በጥናትና መርምር የህይወት ኡደት ውስጥ ወደ ዘለቀው አገራዊ ተቋም አቅንተናል።
ይህ ግዙፍና አንጋፋ ተቋም በውስጡ በአገር ደረጃ የምርምር ስርዓቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ፤ ሙሉ የተመራማሪነት ማዕረግ የተሰጣቸው፤ የመሪ ተመራማሪነት ደረጃን የጨበጡ፤ ለአገራችን ግብርና ሳይንስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ፤ የአገሪቷን የግብርና ዘርፍ በተለያዩ ችግር ፈቺ የግብርና ምርምር ቴክኖሎጂዎችና እውቀትን በማመንጨትና በማቅረብ ለአገራዊ ግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፤ብእር ያልዳሰሳቸው፣ ሚዲያው ያልደረሰባቸው (ባጭሩ፣ ምንም ያልተዘመረላቸው) ተመራማሪዎች ይገኙበታል፡፡
የዚህ ተቋም የምርምር ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ታደሰ ዳባ ሲሆኑ በትህትና በታጀበና ጥኡም አንደበታቸው ስለ ተቋሙ፤ በተለይም ስለ ግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃላይ ሁኔታና ይዞታ እንደሚከተለው አውግተናል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ መድረክ መቼ ተቋቋመ እና አላማው ምንድን ነው?
ዶ/ር ታደሰ፡- የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ከሌሎቹ አኳያ ሲታይ አዲስና ከግብርና ሳይንሶች ሁሉ ረቀቅ ያለ ሳይንስ እንደ መሆኑ መጠን፣ እሱን ለማጥራት፣ ግልፅ ለማድረግና ለህብረተሰቡ ለማስረዳት፤ ከዛም ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ፤ የአካባቢያዊ ችግሮችን ስጋት ለመቀነስ ወዘተ ሲባል የተቋቋመ ነው፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ኬንያ ላይ በ2006 ነው የተቋቋመው። ተግባሩም በአህጉር ደረጃ በግብርና ዙሪያ ማስተባበር ነው። ያኔ፣ ይህ ፎረም ሲቋቋም የአፍሪካ አገራት ስምንት ነበርን። አሁን አስር ደርሰናል።
ተቋሙ በአገራችን እንደ አንድ ወሳኝ የምክክር መድረክ ታስቦ፣ በ2006 የተቋቋመው አፍሪካ አቀፍ ፎረም አባል ሆኖ የተቋቋመው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 ነው። ሲቋቋምም ዋና አላማው እርስ በርሳቸው የማይተዋወቁ በርካታ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የተቋቋሙ፤ እርስ በእርሳቸው ባለመናበባቸው ምክንያት በተፈለገው መጠን ውጤታማ ሊሆኑ ያልቻሉትን፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና አለም አቀፍ ተቋማትን (ግብረ ሰናዮቹን ጨምሮ) እና ሌሎችንም በማሰባሰብ ተናበው፣ ተመጋግበው . . . እንዲሰሩ፤ በጋራ ጥረት የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የግብርናውን ዘርፍ የበለጠ በማዘመን በኩል ተገቢውን ድርሻ እንዲወጡ . . . በማሰብ ነው።
ግንኙነታቸው በጣም የላላ የነበሩትን፤ የሙያተኞች ትስስር (ፕሮፌሽናል ኔትዎርክ) መፍጠርና ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት . . . እየተገናኙ ለጋራ ጥቅም የሚመክሩበት መድረክ መፍጠርም ሌላው ታሳቢ ተደርጎ የነበረ ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ ከአገርም አልፎ አህጉርንም ተሻግሮ አለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ የተቋሙን መቋቋም አስፈላጊነት ተገቢ ያደርገዋል።
ይህ ብቻም አይደለም፣ አንድ ምርት ልውጠ ህያው ምርምር ተካሂዶበት አዋጭነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር በሳይንሳዊ ምርምር የማረጋገጡ ስራ የዚሁ ተቋም ኃላፊነት ነው።
ኬንያ ውስጥ ከላይ በቁጥር በጠቀስናቸው የአፍሪካ አገራት ከተቋቋመው (Open Forum on Agricultural Bio-technology (OFAB)) ፎረም በመነሳት የኢትዮጵያም “OFAB-Ethiopia” በሚል ስያሜ ተመሰረተ። በአዲስ ሳይንስ አራማጅ፣ አስተዋዋቂነቱ (“Agricultural Bio-technology”ን ማለት ነው) እውቅናን አገኘ።
ሌላው የተቋቋመበት አላማ ምርቶች በትክክል ተደራሽ እንዲሆኑና በሚገባ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሲሆን፣ በዚህ በኩልም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
በአሁኑ ሰአት በመንግሥትና የግል ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ተቋሙ (የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂን ስለ መጠቀም፣ በተለይ ለሰብልና ለእንስሳት ምርምር ውጤታማነት ያለውን አስተዋጽኦ፣ ዘረመላቸው የተለወጡ የሰብል ተቋም ኃላፊነት ነው።
ኬንያ ውስጥ ከላይ በቁጥር በጠቀስናቸው የአፍሪካ አገራት ከተቋቋመው (Open Forum on Agricultural Bio-technology (OFAB)) ፎረም በመነሳት የኢትዮጵያም “OFAB-Ethiopia” በሚል ስያሜ ተመሰረተ። በአዲስ ሳይንስ አራማጅ፣ አስተዋዋቂነቱ (“Agricultural Bio-technology”ን ማለት ነው) እውቅናን አገኘ።
ሌላው የተቋቋመበት አላማ ምርቶች በትክክል ተደራሽ እንዲሆኑና በሚገባ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ሲሆን፣ በዚህ በኩልም በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
በአሁኑ ሰአት በመንግሥትና የግል ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካባቢዎች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ተቋሙ (የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) የግብርና ባዮ-ቴክኖሎጂን ስለ መጠቀም፣ በተለይ ለሰብልና ለእንስሳት ምርምር ውጤታማነት ያለውን አስተዋጽኦ፣ ዘረመላቸው የተለወጡ የሰብል ዝርያዎች በኢትየጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉበትን ሁኔታና እያበረከቱ ያሉትን ድርሻ … የመሳሰሉትን ተገቢ መሆን/አለመሆንን የመለየት ስራን ያካተተ ነው።
በዚህ አጋጣሚ የልውጠ ህያው ስራ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ብቻ ተብሎ የሚሰራ አይደለም። ጤናን ከመጠበቅ አንፃር፣ አካባቢን ከመንከባከብ፤ በሽታን፣ የአየር ጠባይን ከመቋቋም ወዘተርፈ አኳያ ሁሉ ነው ታስቦ፣ ታቅዶና ታልሞ የሚሰራ ነው። ይህ ማለት ደግሞ፣ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት ሰብሉን የመቀየር ስራ አይደለም። ሰብሉ የጎደለውን ማሟላት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እና ይህ፣ በጋራ የመምከሩ፤ የመግባባቱ ወይም ውጤት ላይ የመድረሱ ጉዳይ ተሳክቶላችኋል?
ዶ/ር ታደሰ፡- አዎ፣ እየተሳካልን ነው። በርካታ ተበታትነው ይሰሩ የነበሩ ዘርፎችን በማሰባሰብና ተናብበው እንዲሰሩ በማድረግ ጥሩ ጥሩ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን። ባለ ድርሻ አካላትንም እያሳተፍን ስለ ሆነ ጥሩ እየሄደ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማችሁ (ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት) በአብዛኛው በተመራማሪዎች የተሞላ ነው። ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋርም አብራችሁ ትሰራላችሁ። በተለይም አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ልምድን ያካበቱ ኢትዮጵያዊያን ይበዛሉ። ከዚህ አኳያ የምርምር ስራችሁ ለኢትዮጵያ አርሶ አደርም ሆነ ለሌላው (እንደ አገር) ምን አስገኘ?
ዶ/ር ታደሰ፡– እውነት ነው። ይህ የምርምር ተቋም፣ ወይም የግብርና ምርምር ስራ በአገራችን ከ60 አመት በላይ እድሜ አለው። በእነዚህ አመታት ሁሉ የምርምር ስራን ሲያከናውን ነው የቆየው። በርካታ ውጤቶችንም አምጥቷል።
እንደ አገር ከፍተኛ የምርምር ስራዎች የሚሰሩበት ተቋም እንደ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አለ ለማለት ያስቸግራል። በግብርና ምርምር ተቋሟት ነው በርካታ የምርምር ስራዎች የሚካሄዱት።
ለምሳሌ በጤና፣ ኒውትሪሽን (ስነምግብ) እና የመሳሰሉት ላይ የሰራናቸው በርካታ ስራዎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህና የመሳሰሉት ሁሉ በተጠቃሚው ዘንድ በአይን የማይታዩ ናቸው። ተመራማሪዎቻቸውንም እንደዚሁ ብዙም ልብ የሚላቸው የለም። ነገር ግን ከጀርባ ያሉት ትልልቅ ስራዎች ትልቁንና ውስብስቡን ስራ እየሰሩ ለህዝብ ያደርሳሉ። ልክ እንደ እነዚህ ሁሉ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል። እየተሰሩም ይገኛሉ።
በጥቅሉ እንጥቀሰው ብንል እንኳን፣ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሻሽሉ የሚችሉ በአገር ደረጃ ከ1ሺህ 140 በላይ የምርምር ስራዎች ተለቅቀዋል። ቤተ ሙከራ ገብቶ መመልከት እንደሚቻለውም፣ እስከ ዛሬ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ብዛት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ወደ ተግባር ተቀይረው ውጤት ያስገኙ ናቸው። ምናልባት ይሄ ካለን የአገራችን የቆዳ ስፋትና መሰል ጉዳዮች አኳያ በቂ ነው/አይደለም የሚለው ካልሆነ በስተቀር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዘረ መል ልውጥ አካል ወቅታዊ አለም አቀፍ ይዞታው ምን ይመስላል?
ዶ/ር ታደሰ፡- በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው እውነታ እንደሚያሳው ባዮቴክኖሎጂ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣና ምርትና ምርታማነትን እያሻሻለ ይገኛል። ለምሳሌ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኡራጓይ፣ ጃፓን . . . ወዘተ የመሳሰሉ አገራት በዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ሆነዋል። የቴክኖሎጂው ባለቤት የምትባለው አሜሪካም እንደዛው። ሌሎችም አሉ። አፍሪካም በዚሁ መንገድ እየሄደች ትገኛለች።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ውስጥስ? ያስገኘው ውጤት ካለ ማለት ነው።
ዶ/ር ታደሰ፡- እርግጥ ነው፤ ይህ ቴክኖሎጂ እድሜው 35 አመት አካባቢ ይሁን እንጂ ወደ አፍሪካ የገባው በቅርቡ ነው። በተለይም ወደ እኛ አገር የገባው በጣም በቅርቡ ነው። በመሆኑም አስቀድመው ቴክኖሎጂውን ከተቀበሉትና ወደ ተግባር ከገቡት አገራት እኩል ለውጥ አምጥተናል፤ ወይም፣ ውጤት አስመዝግበናል ማለት አይደለም። ያም ሆኖ ከማለማመድና መፈተሽ ጀምሮ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል።
በዘረመል ምሕድስና (ልውጠ ህያው) ትኩረት ተሰጥቶ የማይሰራባቸው ምርት ሰጪ ጉዳዮች አሉ ማለት ባይቻልም፣ ልውጠ ህያው ምርምር ተካሂዶበት ወደ ምርት ከገባው ጥጥ ምርት ጀምሮ በበቆሎ፣ እንሰት፣ ድንች . . . ዝርያዎች ላይ የልውጠ ህያው ምርምር ሲካሄድ ቆይቷል። የምርምር ስራ የሚቆምና እዚህ ጋ በቃ የሚባል ባለመሆኑ ስራው ያለ ማቋረጥ እየተካሄደም ነው።
ሌላው በአገር ውስጥ ለተገኙ ውጤቶችና ስኬቶች ተገቢ ማሳያ የሚሆነው ጥጥ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃው “ቦልዎርም” የተሰኘ ህዋስ ጥጡን እንዳያጠቃ ማድረግ መቻሉ ሲሆን በሌሎች ምርቶችም በተመሳሳይ የተሰሩ ስራዎች አሉ።
በእስከ ዛሬው አሰራር የቅድመ ምርምርና ጥናት እንዲካሄድ ፈቃድ የተሰጣቸውና ወደ ተግባር የተገባባቸው እንዳሉ ሁሉ ወደ ፊትም በዚሁ አሰራር መሰረት በዘረመል ምሕንድስና (ልውጠ ህያው) ላይ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል። የግብርናውን ዘርፍ የማዘመኑ ጉዳይም በዛው ልክ ይካሄዳል ማለት ነው። የ“ክፍት ምክክር መድረክ ፕሮጀክት” (OFAB-Ethiopia) ሂደቱም ሌላው ማሳያ ነው።
በአገር ውስጥ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ለመሆኑ ማሳያው ሳይንሱ እንደ አንድ ራሱን የቻለ ጥናት መስክ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መሰጠቱ፤ በአንዳንድ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ጥናቶች ብቻ ይነካካ የነበረው ዛሬ በስፋት እየተጠና መሆኑ፤ የተለያዩ ተቋማት፣ ለምሳሌ ዩኒቨርሲቲዎችና አካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰሩ፤ በግብርናው መስክ የተሰማሩ እና ሌሎችም ድሮ ለየብቻቸው ይንቀሳቀሱ የነበረው ቀርቶ አሁን በጋራ መስራታቸውና መናበብ መቻላቸው ነው። ይህ ደግሞ በዚሁ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤትና ተጠቃሚነትን እያስገኘ ይገኛልና ፕሮጀክቱ በአገር ውስጥም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። እየተካሄደ ነው ማለት ብቻም ሳይሆን ተቋማዊ ይዘት ባለው መልኩ እየተሰራ ይገኛል።
እንሰትን በተመለከተ ያለውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ሰፊ ሥራ ተሰርቶ (ለምሳሌ በኡጋንዳ) ጥሩ ውጤት እንደ ተገኘው ሁሉ፣ በእንሰት ላይ በተለይ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የኮባ ቅጠልን በማጠውለግ የሚያደርቀውን በሽታ የሚቋቋም የልውጠ ህያው የእንሰት ዝርያ ለማውጣት እየተሰራ ይገኛል። ሌሎችም በርካታ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ፣ ሳይንሱ ወደ አገራችን በቅርቡ የገባ ከመሆኑ አኳያ፣ የሚያበረታቱ ስራዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ዘረመል ልውጥ አካል ((”ልውጠ ህያው” በሚል የሚገልፁትም አሉ) (GMOs)) ሲባል ምን ማለት እንደ ሆነ አውዳዊ በሆነ መልኩ ቢገልፁልን?
ዶ/ር ታደሰ፡– በመጀመሪያ ”ልውጠ ህያው” የሚለው ራሱ ወደ አማርኛ ሲመለስ ችግር አለበትና ወደ ፊት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ሙሉ ለሙሉ ጽንሰ ሀሳቡን በሚገልጽ ደረጃ አይደለም የተተረጎመው። ለዚህ ችግር ዋናው ምክንያቱ ደግሞ ፅንሰ-ሀሳቡ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣም ሰፊና በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ በመሆኑ ነው።
በአሁኑ ሰአት ይህ ”ልውጠ ህያው” የሚባለው በብዙ አገራት የመወያያ ርእሰ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል። ምክንያቱ ደግሞ ይህ የዛሬ 35 አመት አካባቢ ገበያ ላይ በዋለው ጄኔቲክ ኢንጂነሪንግ የሚሰራ፣ በጣም ረቂቅና ከባድ የሆነው “ጄኔቲክ ሞዲፊኬሽን” (ልውጠ ህያው) አዝርእት ወይም እፅዋት ባህሪያቸውን እንዲለውጡ ታስቦ የሚሰራ ስራ (የጥናትና ምርምር መስክ) ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደምንሰማውም፣ እንደምናነበውም ከሆነ “ፀረ ዘረመል ምሕንድስና አቀንቃኞች” የሚባሉ፣ ከእናንተ የተለየ (ተቃራኒ የሆነ) አቋም ያላቸው ወገኖች አሉ። ማን ነው ትክክል፣ እናንተ ወይስ እነሱ?
ዶ/ር ታደሰ፡– ተቃውሞ በሁለት ጉዳዮች ሊመጣ ይችላል። አንዱ ከስጋትና ፍርሀት፣ ቴክኖሎጂውን ከመጠራጠር … የሚመጣውና ጤነኛው ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ከጀርባው ትልልቅ ኩባንያዎች ያሉበት ተቃዋሚነት ነው።
እንዳልከው፣ አዎ፤ እነዚህ አቀንቃኞች አሉ። ይኑሩ እንጂ ሁሉም ከጥቅም በስተቀር ምክንያት የለሾች ሲሆኑ፤ ከፍተኛ ገንዘብ ተከፋዮችም ናቸው። በተለይም በልውጠ ህያዋን መስክ የሚታየው ፅንፈኝነት ከግል ጥቅም የሚመነጭ መነሻ ነው ያለው። ከእነዚህ ወገኖች ጀርባ እነሱ “ኦርጋኒክ” (በመሰረቱ “ኦርጋኒክ” የሚባል ነገር የለም) የሚሉት ምርት አምራች፣ አከፋፋይ … የሆኑ ቱጃር ኩባንያዎች አሉ። እነዚህ ወገኖች የእነሱ ምርት እንዲሸጡላቸው ይሄንን ያጣጥላሉ። ለዚህ ደግሞ እነዚህን፣ በምንም አይነት ሳይንሳዊ መሰረትና መረጃ ላይ ያልቆሙ፣ ሊቆሙም የማይችሉ “በሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ መከራከርን የማይደፍሩ፤ እውነታውን እያወቁ እንዳላወቀ የሚክዱ ወገኖችን ያሰማራሉ። በቃ፣ እውነታው ይሄው ነው።
እኛ የምንፈልገው ሰዎች ይሄንን አጥርተው እንዲያውቁ ነው። ይህንን፣ በገንዘብ የሚሾር ፖለቲካል ኢኮኖሚ አቀንቃኝነትን በውል ለይቶ መታገል ይገባል። ይህንን በምሳሌ ማየት ይቻላል። ፀረ-ተባይና ፀረ-አረም መድሀኒቶች የሚመረቱት አውሮፓ ነው። ገበያቸው ያለው ደግሞ አፍሪካ ነው። በመሆኑም አፍሪካ ያንን መድሀኒት ማምረት ቻለች ማለት የእነሱ ገበያ ተዘጋ ማለት ነውና ያ እንዳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የሀሰት ትርክት የመንዛትና በምንም አይነት መሰረት ላይ ያልቆመን ፕሮፓጋንዳ የመርጨት ሁኔታ ይኖራል። ይህንን ነው እኛ በውል ልገነዘበው የሚገባን ማለት ነው። ባጭሩ፣ በባዮቴክኖሎጂ (ልውጠ ህያው) አማካኝነት ለውጤት የሚበቁ ምርቶች ምንም አይነት ችግሮች የሉባቸውም።
አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር አንድ አዝርእት ከ40 እስከ 48ሺህ ቅንጣት ዘረመል (ዲኤንኤ) ያለው መሆኑና በዚህ ምህንድስና አማካኝነት የሚሰራው ስራ ከእነዚህ ውስጥ አንዷን ለይቶ የማጎልበት ስራ እንጂ ሙሉ ለሙሉ የመለወጥ ስራ የማይሰራ መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኦርጋኒክ ስለሆነና አልሆነው ትንሽ ቢነግሩን?
ዶ/ር ታደሰ፡- በመሰረቱ ይሄ “ኦርጋኒክ” የሚሉት ነገር ውሸት ነው። “ኦርጋኒክ ነው” እያሉ የሚነግሩንም ሆነ በየሱፐር ማርኬቱ የሚሸጡልን የውሸት ነው። “ኦርጋኒክ” ማለት ምንም አይነት ፀረ-አረምም ሆነ ፀረ-ተባይ ወይም ማዳበሪያ፣ ማለትም ማንኛውንም ሳይንሳዊ ድጋፍም ሆነ ተጨማሪ ማበልፀጊያ ያልነካውና ሙሉ ለሙሉ በተፈጥሮ ብቻ የዳበረ ማለት ነው። ያ ደግሞ እጅግ ሲበዛ ውሱን ነው። ያለው ምርት ቢያንስ ፀረ-አረም፣ ፀረ-ተባይ፣ ማዳበሪያ ወዘተ የነካው ነው። ይህ ደግሞ ”ልውጠ ህያው” አይደለም፤ ኦርካኒክም አይደለም። በዚህ መታለል የለብንም። “ኦርጋኒክ ነው” የሚሉን የውሸት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ነባሩን፣ ተፈጥሯዊውን ከማቆየትና እንዳይጠፋ ከማድረግ አኳያ እየተሰራ ያለ ስራ ካለ? ይህ የብዙዎች ስጋት እንደ መሆኑ መጠን በተጨባጭ ቢያስረዱን።
ዶ/ር ታደሰ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። የብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ስራው ይሄ ነው። ማቆየት፣ መለየት፣ ሲያስፈልግ ለስራ ማቅረብ። ይህ ማለት ግን የሱ ስራ ብቻ ነው ማለት አይደለም። እኛም የምንሰራው አለ።
ከሁሉም በፊት ግን የሚጠፋ ነገር አለመኖሩን መረዳት ያስፈልጋል። የመቀየር ነገር ከሆን አዝርእት ራሳቸውን ከተለያዩ ለውጦች ጋር (ለምሳሌ፣ የአየር ለውጥ) ለማዋሃድ፣ አብሮ ለመሄድ፣ ለመቋቋም … ሲሉ ራሳቸውን በሂደት ይቀይራሉ። ባለበት የሚቆይ ነገር የለም። ልክ እንደ ቫይረስ ሁሉ ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም ሲሉ እየተለወጡ ሊሄዱ ይችላሉ። ለምሳሌ እኛ በበቆሎ ምርት ከአፍሪካ አንደኛ ነን። ይህን ስናመርት አንድም የበቆሎ ዘር ከውጭ አምጥተን ዘርተን አናውቅም። ሎሚ ላልከው እስከ ዛሬ ሎሚን ያሻሻለ አገር በአለም የለም። የተሻሻለ የማንጎ ዝርያም እንዲሁ ነው፤ በአንድም አገር በባዮቴክኖሎጂ የተሻሻለ የማንጎ ዝርያ የለም። በመሆኑም ስጋቱ ተገቢ ሲሆን፣ ችግሩ ግን የለም። አይፈጠርም። ማለትም፣ በባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ ትግበራ ምክንያት ነባሩ አይጠፋም።
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ባዮቴክኖሎጂን መጠቀም ግዴታ ነው?
ዶ/ር ታደሰ፡- አዎ፣ ግዴታ የሚሆንባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ የአፈር መኮምጠጥን በምን ትከላከለዋለህ? እሱ ብቻም አይደለም፣ በበቆሎ ምርት አንደኛ ነን እንላለን። በቆሎን የሚያጠቃውን ተምች በሽታ መከላከል ካልተቻለ አንደኝነቱ ከየት ይመጣል? ምርቱስ ቢሆን? ተምችን መከላከል የሚቻለው ደግሞ የባዮቴክኖሎጂ ሳይንስን ስራ ላይ በማዋል ነው። የጥጥንም ጉዳዩ ከዚሁ ጋር አንስቶ በተጓዳኝ ማየት ይቻላል። ባጠቃላይ፣ ከላይ እንዳልነው፣ ልውጠ ህያውን ስራ ላይ የምናውለው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ብቻ አይደለም። ለእነዚህ፣ እዚህ ለጠቀስናቸውና ለሌሎች በርካታ ጉዳዮች መፍትሄ ለመሻት ሲባልም ጭምር ነው። በዚህ ላይ በደንብ አድርጎ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ባለ ድርሻ አካላት አሏችሁ?
ዶ/ር ታደሰ፡– አዎ (ሳቅ)፣ ምግብ የሚመገብ በሙሉ ባለ ድርሻ አካላችን ነው። ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (አሁን ስድስት ሲሆኑ እየጨመረ የሚሄድ ነው) ጋር አብረን እየሰራን ነው። አርሶ አደሩ ባለድርሻ አካላት ባለ ድርሻዎቻችን ናቸው። መሰል የጥናትና ምርምር ተቋማትና ሚዲያውም እንደዛው።
በተለይ ለህዝቡ፣ በተለይም እታች ላለው አርሶ አደር ተደራሽ ከመሆን አኳያ ትልቁ ባለ ድርሻ አካሎቻችን የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ሲሆኑ፤ በቅርብ አብረን እየሰራን ሲሆን ወደፊትም ግብርናው ላይ በማተኮር የበለጠ እንሰራለን ብለን እናስባለን። በተለይ መረጃዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመተንተን፣ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግና እውነታውን ከማስረዳት፣ የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን ከማክሸፍ አንፃር የመገናኛ ብዙሀን ድርሻ የማይተካ ነውና እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ያግዙናል ብለን እናስባለን። በአሉ አሉ … ብቻ ሳይሆን መረጃን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማብራራት በህብረተሰቡ ዘንድ ተገቢው ግንዛቤ ይኖር ዘንድ በመስራት ከጎናችን ይሆናሉ ብለን ነው ከእነሱ ጋር አብረን እየሰራን ያለነው። በተለይ እዚህ አገር በትላልቅና ታዋቂ በሚባሉት ምሁራኑ ዘንድ ሳይቀር ብዥታ ስለሚታይ ያንን ብዥታ ከማስወገድ አንፃር ትልቅ አቅም ያላቸው የመገናኛ ብዙሀን በመሆናቸው በሚገባ ያግዙናል የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- ዘርፉ የመንግስት ፖሊሲ አለው። ይታወቃል?
ዶ/ር ታደሰ፡- አለው። መታወቁን በተመለከተ አሰራጭተናል። መገናኛ ብዙሀን እጅም እንዲገባ አድርገናል። የበለጠ እንዲታወቅ ከማድረግ አኳያም እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንምጣ። አዳዲስ ምሩቃንን ትቀበላላችሁ? ማለትም ‘እንድንማር ግፊት ተደርጎብን ከተመረቅን በኋላ ግን የሚቀጥረን አጣን’ የሚል የምሩቃን ቅሬታ ስላለ ነው። ምናልባት ይሄ እርሶን የማይመለከት ከሆነ ልናልፈው እንችላለን።
ዶ/ር ታደሰ፡- ጉዳዩ የሂዩማን ሪሶርስ ጉዳይ ስለ ሆነ ዞሮ ዞሮ ይመለከተናል። እዚህ ላይ ጉዳዩ እንደ አገር ነው መታየት ያለበት። በእኛ አገር ትልቁ ቀጣሪ መንግስት ነው። ባደጉት አገራት ደግሞ የግሉ ዘርፍ ነው። በመሆኑም፣ እዚህ ያለው የሰው ሀይልን የማሟላት ጉዳይ፣ እንደማንኛውም መስሪያ ቤት ሁሉ፣ በቀጥታ ከመንግስት በጀትና እቅድ ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም፣ በጀት ሲኖር የሰው ሀይል ቅጥር ይካሄዳል። በጀት ከሌለ ቅጥሩ አይካሄድም። ለዚህ ነው፣ እኛም በየሁለት አመቱ እናካሂድ የነበረውን ቅጥር ለጊዜው ያቆምነው። በጀቱ ሲኖር እንቀጥላለን ማለት ነው። ያ ነው እንጂ ሙያውና ሙያተኞቹ በጣም አስፈላጊዎቻችን ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ቀረ የሚሉት ካለ?
ዶ/ር ታደሰ፡- ይህ ቴክኖሎጂ ለአገራችን አዲስ ቴክኖሎጂ ነው። ለእኛ አዲስ ይሁን እንጂ ሌሎች አገራት ወደ ተግባር ቀይረውት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። በመሆኑም ህብረተሰባችን፣ ይሄ የሚነዛውን፣ ምንም አይነት ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን የሀሰት ትርክት ወደዛ ትቶ የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን አለበት። ዘርፉን የምናበለፅገው ኢትዮጵያዊያን ነን። እዚህ ያለነውና ዘርፉን የምንመራውም ሆንን፤ ሳይንቲስቶቻችንና ምሁራኖቻችን ፍፁም ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ወገናቸውን የማገልገል ከፍተኛ ፍላጎትና ግዴታም ያለባቸው … ናቸው። ማንም የተለየ አላማና ፍላጎት የለውም። ሁሉም ወገን አለው። ሁሉም በአገራዊ ኃላፊነት ነው የሚሰራው። ህዝብንም ሆነ አካባቢን ሊጎዳ የሚችል አንድም የግብርና ቴክኖሎጂ ወደ አገር ውስጥ አይገባም። በሳይንስ ያልተረጋገጠ አንድም ነገር ስራ ላይ አይውልም። ወደ ህብረተሰቡ እንዲሄዱ የሚደረጉት ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነውና ህብረተሰቡ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርቶችን ያለ ምንም መጠራጠር ሊጠቀም ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለ ሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
ዶ/ር ታደሰ፡- ለግብርና ባዮቴክኖሎጂው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታችሁ እዚህ ድረስ መጥታችሁ ሃሳቤን እንድገልፅ እድል ስለሰጣችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም