ልብን የታደገ መልካም ልብ፤
ታሪኩን ያደመጡ የዓለም ሕዝቦችን በሙሉ በእምባ ያራጨ አንድ እውነተኛ ታሪክ በማስታወስ ልንደርደር:: ይህንን ታሪክ ያሰራጨው MBC4 Channel የተባለው ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነበር:: ሐምሌ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ከምሽቱ አንድ ሰዓት ግድም ትልቅ ዝና ባተረፈችው በኦፕራ ዊንፍሬ ሾው ላይ የተላለፈው ይህ ታሪክ እንደ አዘቦት ቀን ዝግጅቷ ታዳሚዎቿ እየሳቁ የተፍነከነኩበትና ያጨበጭቡበት ታሪክ አልነበረም:: ታዳሚው በሙሉ የተከታተለው ሲቃ እየተናነቀው እንደነበር እድል ገጥሟቸው ያዩት ያስታውሱታል::
“የቺካጎ ቢርስ” (Chicago Bears) ዝነኛ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች የሆነው የቻርለስ ቲልማን ጨቅላ ሕጻን ቲያና ቲልማን በተወለደች በ6 ወር እድሜዋ በከባድ የልብ ሕመም መሰቃየት ትጀምራለች:: ይህንን የልጃቸውን ጭንቀት ያስተዋሉት ዝነኛው የቅርጫት ኳስ ጠቢብ አባቷ እና እናቷ ጃኪ በቤታቸው የሞት ጥላ አጥልቶ ስለነበር ትኩረታቸው ሁሉ በሕጻን ልጃቸው ላይ ነበር::
የልጃቸው ሕመም ቅስማቸውን የሰበረው አባትና እናት እንባቸውን የእለት ቀለባቸው አድርገውና በራቸውን ዘግተው እህህ እያሉ በሚቃትቱበት በዚያ ክፉ ወቅት ወሬ አነፍናፊዎቹ የሚዲያ ሪፖርተሮች ዝነኛው ኮከብ ስፖርተኛ ስለምን ሊሰውር እንደቻለ ፍንጭ ስላጡ “ቲልማን ሆይ! ወዴት ተሰወርክ? ተወዳጁ የቅርጫት ኳስ ስፖርት በቲልማን መጥፋት ምክንያት ጦም ውሎ ጦም አደረ! ቲልማን ሆይ ድምጽህን አሰማ!?” እያሉ በቤቱ አካባቢ ማንዣበብን ልማድ አድርገው ሰነበቱ::
ይህ ጉዳይ እጅግ ያስጨነቀው ቲልማን ከስፖርቱ ሜዳ ለምን ሊርቅ እንደቻለ እየጎተጎቱ ፋታ ከነሱት አስጨናቂ የሚዲያ ባለሙያዎች መገላገሉን ስለፈለገ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚዲያ ፊት ቀርቦ ስለ ታማሚዋ ልጁ ሕዝቡና አድናቂዎቹ እንዲጸልዩለት በመማጸን በቅርብ ጊዜ ወደሚወደው ስፖርት እንደሚመለስ አጭር መግለጫ ሰጠ::
በዚያው ተመሳሳይ ወቅት በሚኒሶታ ስቴት በሚገኝ አንድ የልጆች ሆስፒታል ውስጥ አማንዶ የሚባል የዘጠኝ ወር ሕጻን በልብ ሕመም እየተሰቃየ በጽኑ ሕሙማን ዋርድ ውስጥ በከፍተኛ ሕክምና ላይ ነበር:: ካለ አባት ልጇን ከምታሳድገው እናቱና ከአንድ ሴት ልጇ በስተቀር ተንከባካቢ ያልነበረው ይህ ሕጻን ሕክምናው ሳያሳካለት ቀርቶ ዜና እረፍቱ የተሰማው የቲያና አባት የልጁን ሕመም በሚዲያ በገለጸበት ሰሞን ነበር::
የቲልማን የጸሎት ተማጽኖና የልጁ ሕመም ከጆሯቸው የደረሰው ሐኪሞች በሕጻኑ ሞት ምክንያት ማዘናቸው ባይቀርም ለእናቱ አንድ ጥያቄ አቀረቡላት:: “እባክሽ የሟች ልጅሽን ልብ በልብ ሕመም እየተሰቃየች ላለችው ለቺካጎዋ ሕጻን ለቲያና ቲልማን እንዲሰጥ ፍቀጅልን?” የሟች እናት አላመነታችም:: የሞቷን ቀን ለምትጠባበቀው ለጭቅላዋ ቲያና የልጇ ልብ እንዲሰጥ ተስማምታ ፈረመች::
የሚኒሶታ ሐኪሞችም የአማንዶን ልብ ለቲያና ለማድረስ ዝግጅታቸውን አጠናቀው በግል ቻርተር አውሮፕላን ሊንቀሳቀሱ ሲሉ ወቅቱ ክረምት ስለነበር “መላ ቢሱ” የሚኒሶታ ክፍለ ግዛት በረዶ “ሰማዩን ቀዶ” ቁልቁል መንዥቅዠቅ ጀመረ:: ይህ ጸሐፊ ክፍለ ግዛቱን በሚገባ ስለሚያውቀውና ስለኖረበትም ለበረዶው የሰጠው ገለጻ ተጋነነ የሚሰኝ አይደለም::
በበረዶው ምክንያት የተቋረጠው የአውሮፕላኖች በረራ ትልቅ ችግር ቢፈጥርም ሐኪሞቹ አንዴ ቆርጠዋልና በነፍስ ለምትጠብቃቸው ጨቅላ ሕጻን የሚቻለውን ሁሉ ዘዴ በመሞከርና እጅግ ኃላፊነትን የሚጠይቅ እርምጃ በመውሰድ የተሰረዘው በረራ እንዲቀጥል ተወስኖ የአማንዶ ልብ ለቲያና እንዲደርስ ተደርጓል:: የሟቹ ልብ ወደ ችካጎ ሆስፒታል እንደደረሰም ሐኪሞች በርብርብ
የልብ ነቀላውንና ተከላውን በተሳካ ሁኔታ አከናውነው ለመሞት ስድስት ሰዓት ብቻ የቀራት ቲያና በሕይወት ተርፋ የቤተሰቡ ሀዘን ሊገፈፍ ችሏል::
ይህ ክስተት ከተፈጸመ ሦስት ዓመት በኋላ የሟች ልጇን የአማንዶን ልብ የለገሰቸው እናት፣ ልቡ ለልጃቸው የተበረከተላቸው የቻርለስ ቲልማን ቤተሰቦችና እድለኛዋ ቲያና፣ የኦፕራ ዊንፍሬ በርካታ ታዳሚዎችና በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች በታደሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሁለቱ ቤተሰቦች ተገናኝተው ምን እንደተሰማቸው ስሜታቸውን እንዲገልጹ የፕሮግራሙ መሪ ኦፕራ ትጠይቀቸው ጀመር::
የእምባ ሣግ እየተናነቃቸው መጀመሪያ ተሸቀዳድመው ሃሳባቸውን የገለጹት የቲያና እናትና አባት ነበሩ:: “ልጃችን በሕይወት እንድትኖር የሟች ልጅሽን ልብ በቸርነትና በርህራሄ ስለ ለገስሽን በጣም እናመሰግናለን::…” የአማንዶ እናት የምሥጋና ንግግራቸውን ሳታስጨርስ ጣልቃ በመግባት “ምሥጋናውን በአክብሮት ተቀብያለሁ:: ‹የሟች ልጅሽን› በማለት በገለጻችሁት ሃሳብ ግን አልስማማም::” ወደ ሕጻኗ ቲያና እየጠቆመች “ልጄ እኮ አልሞተም:: በቲያና ልብ ውስጥ ሲተነፍስ እያደመጥኩት ነው::
”እናንተስ ትርታው አይደመጣችሁም? በፍጹም ልጄ እንደሞተ አላስብም:: ምክንያቱም በቲያና ውስጥ ሕያው ሆኖ እንደሚኖር እርግጠኛ ነኝ::” ይህንን ፕሮግራም ስቱዲዮ ውስጥ በአካል ተገኝተው የሚመለከቱት ብቻ ሳይሆኑ በየቤታቸው ተቀምጠው ፕሮግራሙን የሚከታተሉ ታዳሚዎች ስሜታቸውን የገለጹት እየተንሰቀሰቁ በማልቀስ ነበር::
ሁለቱ ቤተሰቦች ተነስተው ሲተቃቀፉማ የነበረውን ስሜት በቃላት ለመግለጽ በእጅጉ ይከብድ ነበር:: “ልጄ አልሞተም! በቲያና ልብ ውስጥ ሲተነፍስና ትር ትር ሲል ይሰማኛል! እናንተስ አይሰማችሁም?” ይህ ዓረፍተ ነገር በጊዜው በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚጠቀስ ኃይለ ቃል ነበር::
ልብ ያለው ልብ ያድርግ፤
የኢትዮጵያ ልብ በጽኑ እየታመመ ይመስላል:: ህመሙ የጸናባት ይህቺ ምስኪን ሀገር ከእለት ወደ እለት መከራ አታጣም:: በሽታው አልጋ ላይ ባይጥላትም እንደ ልብ እንዳትሆንና ሕዝቦቿ በሰላም ተረጋግተው እንዳይኖሩ የተወሳሰበው ህመሟ ፋታ ሊሰጣት ከቶውንም አልቻለም::
ፖለቲካውም ህመሟን አክሞ ልቧን ሊፈውስላት አቅም አጥቷል:: ኢኮኖሚውም ሆነ ማሕበራዊ መስተጋብሩ ልባቸው ፈሶ ልባችንን ካፈሰሱት ውለው አድረዋል:: ነገራችን ሁሉ “ልብ ሲያውቅ ገንፎ ያንቅ” እንዲሉ፤ ሀገር ስትታመም አብረን እህህ የምንለው መፍትሔው ጠፍቶን ሳይሆን የልብ ሀሞታችን ስለፈሰሰ ብቻ ነው::
ለልብ ህመማችን የነበረን አንድ ተስፋ ከምድርም አሻግሮ በዘለዓለሙ የጽድቅ መንገድ ይመራናል እያልን የምንተማመንበት አንድ ቀሪ ሞገሳችን የየግላችን ሃይማኖት ነበር:: የምንተማመንበት እምነታችንም ራሱ ታማሚ ሆኖ በማቃሰት ላይ እንደሆነ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ያንዣበበውን አደጋ እየሰማንም እያየንም ነው::
ተስፋ በማድረግ እንጽናና የነበረው የሕያው ፈጣሪ ቃል በሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ምክር ነበር:: “አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ፤ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ እኖራለሁ:: የድንጋይ ልባችሁን ከእናንተ አስወግዳለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ” (ሕዝቅኤል ምዕ. 36፡26):: የሚለው ዋስትና ትልቁ ማረፊያችን እንደሆነ ስናምን ብንኖርም ዛሬ ዛሬ “ሁሉም ከንቱ የከንቱ ከንቱ” ያለው ጠቢቡ ሰሎሞን ለካስ ቢቸግርው ነው እንድንል ተገደናል::
እለት በእለት እያየን ያለነው “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት” መስጠቱን ሳይሆን “ቅንአትና እብሪት አጥንትን እያነቀዘ” (ምሳሌ 14፡30) ጤና ማጣታችንን ነው:: በሁሉም የማሕበራዊ መስተጋብራችን ውስጥ ገኖ የሚስተዋለውና የሚተገበረው ለሌላው በጎነት ከመኖር ይልቅ መግደልና መጋደል፣ ጠብ መጫርና ማጋጋል፣ ሻምላ መዝዞ በመፋለም ጥሎ ለመውደቅ መጨከንን ነው::
የኢትዮጵያ ልብ ክፉኛ ታሟል:: በዚሁ ጋዜጣ የጥር 27 ቀን 2015 እትም በጥልቀት ለመፈተሽ እንደተሞከረው የልጆቻችን አእምሮ የሚገራበትና የሚሰለጥንበት የትምህርቱ ዘርፍ የልብ ህመሙ ጠንክሮበት ጭራሹኑ ከመቃብር አፋፍ መድረሱን ያረጋገጥነው በልጆቻችን የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት መሆኑን በዝርዝር ዳሰሳ ቅኝት ማድረጋችን አይዘነጋም:: የኑሯችንን ጉዳይ ከጨማመርንበትማ ልባችን አንደኛውን ፈስሶ እንደወጣን እንዳንቀር በእጅጉ ያሰጋናል::
ልብ ሊፈስ ይችላል እንዴ? ተብለን የምንሞገት ከሆነ ለዋቢነት የምንጠራው “ልቤ ፈሷል” እያልን በአዘቦት ቀናት የምንግባባበትን እድሜ ጠገብ ብሂላችንን ነው:: ይህንን ጠነን ያለ መከራከሪያ ውድቅ ለማድረግ የኢትዮጵያ ልብ አልታመመም፤ አልፈሰሰም እያሉ የሚከራከሩ ካሉ የአደባባዩ በር ወለል ተደርጎ ይከፈትላቸውና ባመኑበት እውነታ ሊሞግቱን ከመረጡ እንኪያ ሰላንትያውን ልንገጥም ፈቃደኞች ነን::
የእረፍት አልባዋን ሀገሬን ታሪክና እውነታ ለማነጻጸር የምሞክረው የግብጹን ታላቅ ፈርኦን የሴሶስትሪስን ሕልም በማስታወስ ይሆናል:: ቅዱስ መጽሐፍ ታሪኩን የሚያስነብበን በሚከተለው ውብ ትረካ ነው:: “እነሆ በሕልሜ በዐባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር:: ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲግጡ አየሁ:: ከእነርሱም በኋላ፣ አቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና አጥንታቸውም ያገጠጠ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ::
“እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብጽ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም:: አጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን ሰባት ያማሩ ላሞች ዋጧው:: ከዋጧቸውም በኋላ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር::”
ይህ የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ ለኢትዮጵያ የየዘመናቱ ጉዞ ጥሩ ማነጻጸሪያ መሆን ይችላል:: የሚያማምሩና የሚያስጎመጁ ሀገራዊ ስኬቶች ታዩ ብለን መስክረን ሳንጨርስ እንዴትና ስለምን እንዲያ ሊሆን ቻለ? የምንለው አዲስ አውዳሚ ክስተት ተፈጥሮ ተስፋችንን ውጦ ሀገሪቱን በእርቃኗ ሲያስቀራት ከታሪካችን ደጋግመን ተምረናል::
የደርግ መንግሥት የገጠርን መሬት ለአራሹ ባለ ሀገር እንዲመለስ በአዋጅ ሲያጸና፣ የከተማ ትርፍ ቤትና ቦታ ለደሃው ዜጋ ሲደለድል፣ የሱማሊያ ወረራ ተቀልብሶ ጉሮ ወሸባዬ እየተባለ ሲዘፈን ወዘተ… አብዛኛው ዜጋ “እንብል ሃሌሉያ ታላቅ የመሥራች” እያለ እንደዘመረ ጉደኛው እድሜያችን ለጉድ ጎልቶ ሁሉንም አሳይቶናል:: “የሃሌሉያውን” ፍንደቃ አጨብጭበን ሳንጨርስ ወታደራዊው መንግሥት የጭቃ ጅራፉን አንስቶ እንደምን “አንድ ትውልድ” እምሽክ አድርጎ እንደጎረሰ የሚረሳ አይደለም::
የወታደራዊውን በትረ ሥልጣን ነጥቆ ሀገር ለመምራት የበቃው የወያኔ/ኢህአዴግ አስተዳደር ይህን ያህል ኪሎ ሜትሮች መንገድ ገንብቼ፣ ኮንዶሚኒዬም አስፋፍቼ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን አበራክቼ፣ በዲሞክራሲ ሕዝቡን አረስርሼ ወዘተ… እያለ ሲፎክር “በእምበር ተገዳላይ” ዝላይ ብዙዎች አብረነው በከበሮው ድምቀት እስክስታ ወርደናል::
ውሎ አድሮ ግን ሕዝቡን በጊንጥ እየገረፈ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ራሷን ውጦ እርቃኗን ሲያስቀራት ስናስተውልም ጩኸታችንን ወደ ጸባኦት አዥጎድጉደን ፈጣሪ ስለተለመነን ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና ማድረግ ጀመረች ብለን ተስፋ ጥለን ነበር:: ደስታችን ውሎ ሳያድር ምን “ጉድ” እንደተፈጠረ የምናውቀው ስለሆነ አልደግመውም:: በእነዚህ ሥርዓቶች ኢትዮጵያ የልቧ ህምም ብሶባት ከሞት አፋፍ እንደተመለሰች የትናንትናና የዛሬ ታሪካችን ስለሆነ ለትዝታ ወግ እንኳን አልደረሰም::
ከሲታዎቹ የሕልመኛው ላሞች የወፈሩትን ላሞች እንደዋጡና ውጠውም አንዳች ለውጥ እንዳላመጡ ሁሉ ይኼኛው የእኛ ዘመንም አፉን ከፍቶ የዋጣቸው ብዙ መልካም ጉዳዮቻችን ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም:: ስለዚህም ኢትዮጵያ ልቧ ቆስሏል፤ ክፉኛም ታሟል:: የፈውስ ያለህ እያለች የምትማጸንባቸው ጉዳዮቿም የትዬለሌዎች ናቸው::
ሊሞት ለሚያጣጥረው የተስፋችን ልብ መፈወሻ እንዲሆን ባለ መልካም ልቦች ካልታደጉን በስተቀር ሀገሬ ጤና ስለማግኘቷ እጠራጠራለሁ:: ሀገሬ እየቃተተች ያለችው መልካም “ፖለቲከኞች” እንዲታደጓት ሳይሆን ባለ ልበ ብርሃን “ባለጸጎች” እንዲታደጓት ነው:: “ልብ” ስንል በአማካይ የእጃችንን ጭብጥ የምታህለውንና 320 ግራም ያህል የምትመዝነውን፣ በቀን ውስጥ ወደ 7570 ሊትር ደም በሰውነታችን ውስጥ የምትረጨውንና በአንድ ጎልማሳ ሰው አማካይ ዕድሜ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ጋሎን ደም በደም ሥሮቻችን እንዲዘዋወር ምክንያት የሆነችውን ሚጢጢዬ ሥጋዊ አካላችንን ማለታችን አይደለም::
“የኢትዮጵያ ልብ” በማለት በዘይቤያዊ አገላለጽ የወከልነው ከላይ ካናቱ መሪዎቻችንን፣ ከመሃል ያገለግሉናል ብለን ካርዳችንን ያባከንባቸውን ሹማምንቶቻችንን፣ የሃይማኖት መሪዎቻችንን፣ ምሁራንንና የሀብት ባለጸጎችን፤ ወደ ታች ላቡን ጠብ አድርጎ የሚያገለግለው ሠርቶ አደር፣ ገበሬ፣ የየኪዮስካችን ነፍስ አድን ነጋዴዎች ወዘተ… ማለታችን ነው:: እውነት እውነቱን እንነጋገር ካልን ማን ያልታመመ አለ? ማንስ ህመሙ ጸንቶበት የማያቃስት አለ? ካለ መልካም! ግን ያለ አይመስለንም::
ስለዚህም ኢትዮጵያ ታማለች፤ ያውም ልቧን:: መፍትሔዋ የሚመጣው በጤነኛ ልብ የሚመሩን፣ የሚያገለግሉን፣ በፈረሰው በኩል ቅጥሯን ለመድፈን የሚታትሩ ዜጎች ሲበረክቱ ነው:: የወንጀለኛና የፍትሐ ብሔር ሕግ እየጠቀሱ፣ በሕገ መንግሥት ሰነድ እያስፈራሩ አንገት የሚያስደፉንን ሳይሆን ለእውነት ኖረው ለእውነት የሚሞቱ ጥቂት ባለ መድኃኒቶች ተገኝተው ለብዙኃን የልብ ህመም ፈውስ መሆን ሲችሉ ብቻ ነው:: ሰላም ለሕዝባችን፤ በጎ ፈቃድ ለዜጎቻችን::
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም