ሲኤን ኤን እና ቢቢሲ ሌሎችም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያስተላልፉት ዘገባ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይደመጣሉ:: በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ላይ ኢትዮጵያ የምትቀርብበት ጊዜን እና መንገድ እንዲሁም የአቀራረባቸው ሁኔታን በተመለከተ የዘርፉ ምሁራን የሚሉት አላቸው::
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ደምመላሽ መንግስቱ እንደሚናገሩት፤ በዋናነት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃኑ ቅድሚያ የሚሰጡት ለራሳቸው እና ያሉበት ሀገር መንግስት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሀገራት ነው:: በዋናነት ለራሳቸው ቅድሚያ ይሰጣሉ:: የአሜሪካ ሚዲያ ቅድሚያ ለአሜሪካውያን ይሰጣል:: ከሀገሮቹ ፍላጎት አንፃር የእንግሊዙ ቢቢሲ ከእንግሊዝ ውጭ ላሉት ሀገሮች የሚሰጠው ትኩረት አንድ ዓይነት አይደለም::
ዓለም አቀፍ ተብለው እንደሞዴል የሚታዩ መገናኛ ብዙኃን በጥቅስ ምልክት ውስጥ የሚገቡ ናቸው:: ምክንያቱም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የሚያዩበት ሁኔታ፣ ስነምግባራቸው በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ እና የተዛባ በመሆኑ ነው:: እነቢቢሲ፣ ሲኤን ኤን እና አልጀዚራ የሚባሉት ትላልቅ መገናኛ ብዙኃን በሙሉ ስለተለያዩ ሀገሮች በተለይ ደግሞ ስለአደጉ ሀገሮች እና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ድሃ እና ያላደጉ ሀገሮችን በተመለከተ የሚዘግቡበት መንገድ እና የሀገሪቱን ሁኔታ የሚረዱበት እንዲሁም ለዓለም የሚያስረዱበት ሁኔታ የተሳሳተ እና ደሃ ነው::
ዶክተር ደምመላሽ ፤‹‹መገናኛ ብዙኃኑ የአዘጋገባቸው ሁኔታ ድሃ ነው›› ለማለት ያነሳሳቸው፤ እውነታውን ከማሳየት ይልቅ በራሳቸው መነፅር እንዲሆኑ የሚፈልጉትን ያላደጉ አገሮች ተገዢነትን ሲያንፀባረቁ ይታያል:: እይታቸው የተንሸዋረረ ነው:: እነርሱ የሚፈልጉት ሲከሰት ማለትም ሀገሮች ላይ ቀውስ ሲፈጠር በተደጋጋሚ ይዘግባሉ::
ያደጉ እና ሃያላን ሀገራት ባላደጉት ሀገሮች ላይ የተለያዩ ሴራዎችን ሲሸርቡ፤ የጠሉትን መሪ ለማውረድ ሲሉ ያላደጉ ሀገሮችን መሪዎች ስማቸውን ይጠፋል:: ደካማ ጎን በመፈለግ ያራግባሉ:: ሀገሮቹን ለብጥብጥ እና ለቀውስ ይዳርጓቸዋል፤ በመጨረሻም መንግስታትን የሚለወጡባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራል:: ይህ ሲሆን ዓለም አቀፉ መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ይዘግባል:: ሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ በማለት ኢትዮጵያን በተመለከተም የሚዘግቡበትን መንገድ ያብራራሉ::
ወደ ኢትዮጵያ ጉዳይ ሲመጣ በተመሳሳይ መልኩ አንድ የጥይት ተኩስ ድምፅ ተሰማ ሲባል፤ በተደጋጋሚ እያራገቡ ይዘግባሉ:: ከዛ ውጭ ስኬቶችን፣ ለውጦችን፣ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ እና ልማትን በተመለከተ በምንም መልኩ በዘገባቸው አይሸፈንም:: በሚያስገርም መልኩ ስንዴ ቢመረት ዘርፈ ብዙ ለውጦች ቢታዩም በጣም የተዛባ እና የተንሸዋረረ እይታ ስላላቸው መልካሙን ውጤት አያሳዩም።
ዶክተር ደምመላሽ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ጥቁሮች ከነጮች እኩል መሆናቸውን ከጥንት ጀምሮ ለዓለም ያሳየች ብቸኛዋ ታሪካዊ ሀገር ነች:: ይሄ ለእነርሱ ታሪካዊ የፖለቲካ ጠባሳቸው ነው:: በሌላ በኩል ኢትዮጵያን እንደፈለጉ ለማድረግ ሲሞክሩ እምቢ የሚላቸው ሲመጣ ኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ እንዲካሄድ ያደርጋሉ:: ምክንያቱም የዓድዋ ድል ለእነርሱ ቀላል አይደለም፤ አይረሱትም፤ በተለይ ኢትዮጵያ ላይ የተዛባ ዘገባ የሚያስተላልፉበት ምክንያት በፖለቲካዊ ታሪኩ ሳቢያ መሆኑ መታወቅ አለበት።
በተደጋጋሚ እንደሚታየው ኢትዮጵያን የሚበጠብጥ እና ገፅታዋን የሚያበላሽ ነገር ሲኖር እግር በእግር ተከትለው ይዘግባሉ:: ለተቀረው የዓለም ክፍል ሀገሪቱ የማትረባ፣ የወደቀች እና ቆሻሻ ሀገር ተደርጋ እንድትታይ ማድረግ ትኩረታቸው ነው:: ምክንያቱም መገናኛ ብዙኃኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መጠቀሚያዎች ናቸው:: የዓባይ ግድብን አይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እንደስኬት አያቀርቡም::
መልካም ነገሮች ላይ ይጠፋሉ፤ አደጋ ሲደርስ አደጋውን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ደካማነት አጉልተው ለመውጣት ይሞክራሉ ብለዋል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሳምሶን መኮንን በበኩላቸው፤ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን በጣም ትላልቅ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነቱ ጊዜ ሲዘግቡ የነበረው ሁኔታ በብዙ መልኩ የሚተች መሆኑን ያብራራሉ::
አብዛኛዎቹ ቢ ቢ ስ፣ አልጄዚራ እና ሲ ኤን ኤን እንዲሁም የተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ማለትም ዋሽንግተን ፖስት እና ኒውዮርክ ታይምስ ስለ ኢትዮጵያ ሲዘግቡበት የነበረው መንገድ በጣም ችግር ያለበት እንደነበር እና ከጋዜጠኝነት መርህ አንፃር ሙያዊ ያልሆነ ሥራ ሲሰሩ ነበር ብለዋል:: በምሳሌ ሲያስረዱ፤ ጦርነት ሲዘገብ ሚዛናዊ መሆን እያለባቸው ግለሰቦችን ተጠቅመው የአንድ ወገን ዘገባን አስተላልፈዋል:: ከዚህ ባሻገር ጦርነት እንዲባባስ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ለማሳጣት ሲሞክሩ ነበር ብለዋል:: ለአብነት ተከዜ ወንዝ ላይ የነበረውን ዘገባ ያስተላለፉበትን መንገድ ወቅሰው፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርመራ አድርጎ አጥንቶ ያገኘውን ወደ ጎን በመተው ግለሰቦችን እንደምንጭ እየጠቀሱ ሲዘግቡ እንደነበር አስታውሰዋል::
የወቅቱ ዘገባቸው ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥሮ፤ ባለስልጣናት ከሀገር ሀገር እንዳይዘዋወሩ እና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲጣል ለማድረግ የሰሩትን ሥራ የሚረሳ አይደለም ይላሉ:: ኬንያ እና ኳተር ሆነው እየዘገቡ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ሚዛናዊ ያልሆኑ ሽፋኖችን ሲያስተለልፉ ነበር ብለዋል::
ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሳምሶን ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በኢትዮጵያ የተሻሉ ነገሮች መኖራቸውን በማስታወስ፤ አልፎ አልፎ የሚተላለፉ ዘገባዎች በተመሳሳይ መልኩ ከእውነት የራቁ እና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ነበሩ:: ናይሮቢ ላይ ስምምነቱን በተመለከተ ለፌዴራል መንግስት እና ለሕወሓት ዕድል በመስጠት ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሲዘግቡ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ቢኖሩም፤ የሰላም ስምምነቱ እንዳይሳካ እና አተገባበሩ ላይ ችግር እንዲፈጠር ልክ እንደቀድሞ ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው አሁንም ጦርነት አለ በሚል መንገድ ሲዘግቡ የነበሩ መኖራቸው የሚዘነጋ አይደለም ይላሉ::
ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሳምሶን፤ መካድ የሌለበት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን ሀገራት የፖለቲካ አቋምን የሚመስሉ ናቸው:: የሀገሩ የፖለቲካ እና የፖለቲካል ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ መገናኛ ብዙኃኑ ፈንድ በሚያደርጋቸው እና በሚያስተዳድራቸው አካል የተቀኙ ሊሆኑ እንደሚችሉ መረሳት የለበትም ባይ ናቸው::
ከትልልቅ መገናኛ ብዙኃን ጀርባ ትልልቅ መንግስታት አሉ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሳምሶን፤ መገናኛ ብዙኃኑ በየጊዜው እነርሱን የማገልገል ስራ ሲሰሩ ዘገባቸውም ከሙያው ያፈነገጠ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ያስረዳሉ:: የመንግስታቸውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስፈፀሚዎች መሆናቸውን በማስታወስ፤ ጥሩም ሆነ መጥፎ ሲዘግቡ የመንግስታቸው ነፀብራቅ መሆኑ መታወቅ አለበት ይላሉ::
ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሳምሶን እንደሚያስረዱት፤ የአውሮፓውያን ጣልቃ ገብነት የሚታወቅ ነው:: በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በሩስያ እና ዩክሬን መሃል ጣልቃ ሲገቡ ታይተዋል:: በኢትዮጵያም ረገድ ጥቅማቸውን አስልተው የመካከለኛው ምስራቅ ወይም የምዕራብ ሀገራት መንግስታት ጣልቃ አይገቡም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ሀገር ናት:: የአፍሪካ ቀንድ ላይ መሆኗ እንድትፈለግ የሚስገድድ ነው:: በተጨማሪ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር አላት:: ይህ ስድስት ወይም ሰባት የአፍሪካ ሀገራት አሊያም አስር የአውሮፓ ሀገራትን የሚያክል የህዝብ ቁጥር ያላት መሆኑም በራሱ በልዩ ሁኔታ እንድትታይ ያደርጋታል የሚል ግምት እንዳላቸው ያብራራሉ::
እንደረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ሳምሶን ገለፃ፤ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጊዜ መጥፎ መጥፎ ላይ ብቻ የሚያተኩር ዘገባ የሚያስተላልፉት በምዕራባውያኑ የኢኮኖሚ ፍላጎት ምክንያት ነው::
የፖለቲካ ፍላጎትም ይኖራቸዋል:: በአፍሪካ ጠንካራ መንግስት እንዲፈጠረ አይፈልጉም፤ ይሄ የተለመደ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገሮች ላይም የሚፈፀም መሆኑን ያስረዳሉ:: ጅቡቲ አቀማመጧ (ጅኦ እስትራቴጂክ ሎኬሽኗ) ለፈረንሳይ ትልቅ ጠቀሜታ ስላላት ፈረንሳይ በዛች ሀገር ጠንካራ መንግስት እንዳይኖር ትሠራለች::
ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን አውሮፓውያኑ የአፍሪካ መንግስታት ጠንካራ በሆኑ ቁጥር የአውሮፓውያኑ የኢኮኖሚ ፍላጎት ጥያቄ ውስጥ ስለሚገባ፤ ጠንካራ መንግስት እንዳይፈጠር ትልቁን ሥራ የሚሠሩት በእነዚሁ መገናኛ ብዙኃናቸው መሆኑን ያመለክታሉ:: በውሸት ዜና አምባጋነን እያስባሉ፤ ጦርነት ሲፈጠር የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲኖር ተገንጣይ ሀይሎችን በመደገፍ በመገናኛ ብዙኃናቸው ወታደራዊ ግጭቶች ላይ ቤንዚል የማርከፍከፍ ስራን እንደሚሠሩም ተናግረዋል::
ሀብት ለመበዝበዝ እና የተዳከመች አፍሪካን ለመፍጠር በዓለም አቀፍ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን በተለያየ መንገድ እንደሚሠሩ የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሳምሶን፤ አሁን በመገናኛ ብዙኃኑ አሰራር ምክንያት አፍሪካ ውስጥ እውነተኛ ነገር ቢፈጠር እንኳ ሪፖርት ሲያደርጉ ሰዎች በተቀራኒው እንዲታዩ እያስገደደ መሆኑን አመልክተዋል::
ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ብዙ ልማቶች እና አመርቂ ስራዎች ቢሰሩም፤ ሽፋን አይሰጡም:: በየትኛውም መገናኛ ብዙኃን የሚያስተጋቡት በጦርነት የተሞላች አፍሪካ፤ በረሃብ የተዳከመች አፍሪካ፣ ዕርዳታ የሚያስፈልጋት አፍሪካ እያሉ የሚያቀርቡት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ አፍሪካን ለማጠልሸት ነው ይላሉ::
መገናኛ ብዙኃን ልማትን ለመምጣት የሚጠቅሙ ትልቅ መሳሪያዎች ናቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሳምሶን፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለአፍሪካ ሲሆን የሚጠቀሙበት የተለየ ነው:: ይሄንን የሰላም ስምምነቱ ያመጣቸውን መልካም ነገሮች ምን ያህል ሽፋን እንዳልሰጡት በማየት ማረጋገጥ እንደሚቻል ያስረዳሉ::
መገናኛ ብዙኃኑ የመንግስታቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት ሲኖራቸው፤ ያለውን ግጭት ማስጮህ የሰላም ስምምነት ሲኖር ሰላምን ከማስተጋባት ይልቅ፤ በተቀራኒው የሚዘግቡበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ::
የወደፊቱን አስመልክቶ የሚናገሩት ዶክተር ደምመላሽ በበኩላቸው፤ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ሀገሪቱን ወደፊት ማስጓዝ በሚቻልበት መንገድ ላይ ማሰብ አለባቸው:: በዲፕሎማሲው በተለይም በዲጂታል ዲፕሎማሲው፣ በማቴሪያል ዲፕሎማሲው፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በእርሻም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ትምህርት እና ምርምርን በማዘመን፣ ዜጎችን በማክበር፣ በመከባበር፣ ፖለቲካውን በማዘመን መስራት ቢቻል የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አዘጋገባቸው ሁኔታ አሳሳቢ አይሆንም::
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን በመተው፤ የሀገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ማዘመን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ማድረግ ያስፈልጋል:: የሕትመት ሚዲያው፣ የብሮድካስት ሚዲያውም ሆነ የሶሻል ሚዲያው ዜናዎችን መስራት ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ አንባቢ እና አድማጭ እንዲኖር መስራት አለባቸው ብለዋል።
ለጊዜውም ቢሆን ግን የተዛባውን የዓለም አቀፍ የሚዲያ ዘገባ ለመከላከል ቢያንስ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ዲፕሎማሲውን ለማዘመን መስራት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው የጠቀሱት።
ምሁራኑ እንደገለፁት፤ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡበት መንገድ የተዛባ እና ጥላቻ የተሞላበት ነው:: ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃኑን ከመሰረተው እና ከሚደግፍ መንግስት የመነጨ በመሆኑ ይህን ችግር ለማቃለል መፍትሔው በጊዜያዊነት የዲፕሎማሲ ሥራው ከላይ ትኩረት ማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሁሉም መስክ ውጤታማ ሥራን በማከናወን እና የሀገሪቷን ዕድገት በማረጋገጥ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም