አዲስ አበባ፡- ለቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና ለሌሎች ከፍተኛ ነባር አመራሮች የሽኝት ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
በአዳማ ከተማ በተካሄደው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተገኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በሽኝቱ ለተገኙ አመራሮች ምስጋና በማቅረብ፤ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞን ህዝብ ፖለቲካ ማነቃቃትና መቀየር የቻሉ፣ በተለይም የዛሬ ሁለት እና ሦሰት ዓመት የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር ራሳቸውን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ የነበሩ፤ ዛሬ ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ ለከፍተኛ የፌዴራል ኃላፊነት ታጭተዋል ብለዋል።
ዶክተር ዐብይ አቶ ለማ አዲስ በታጩበት የሀገር መከላከያ ሚኒስትርነት ስፍራም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ችግር በአጭር ጊዜ በመፍታት እንዲሁም በአፍሪካ አዲስ ታሪክ እንደሚያስመዘግቡ ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዶክተር ወርቅነህና ሌሎች አመራሮችም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልፀው፤ በቀጣይም የሚጠበቅባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚወጡ አምናለሁ ብለዋል።
አዲሱ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሽኝት መርሀ ግብሩ ላይ «የክልሉ መሪዎች ከክልል አመራርነት አልፈው አገርን በመምራትና በራሳቸው ቦታ ሌላውን በመተካት ለአገሪቷ ሠላም ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑም ወቅት ሁሉም በየደረጃው የሥልጣን ሽግግር በማድረግ፤ ለክልሉና ለአገር ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡ እኔም ዛሬ በዚሁ መሠረት ተተኪ ሆኜ የተሰጠኝን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነኝ›› ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ‹‹ይህ ዘመን የለውጥ ዘመን ነው፤ የብልጽግናን ጉዞ እውን የምናደርግበት ምዕራፍ ነው፤ የለውጡ ጉዞ ስኬታማ ሥራዎች እየተከናወኑበት ነው፤ ችግሮች እንዳይከሰቱ መከላከል ይገባል፤ የአገራችን ብሂል ‘ከዝቅታ ከፍታ ይገኛል’ እንዲል በያዝነው ኃላፊነት ሳንኩራራ የህዝብን ችግር የመፍታት ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን፤ ይህንን ካደረግን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማድረስ እንችላለን›› ብለዋ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ታሪካዊ ጉዞ አብሮነትን ማንገስ ታሪካዊ ኃላፊነት በመሆኑ አመራርና ህዝቡን በጋራ ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ በዚህ ሂደት ውስጥ የቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ለአገራዊው የለውጥ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም ተራማጅ ወጣት መሆናቸውን፤ ህዝብን ማስተዳደርም ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን በመገንዘብ ለበለጠ ውጤትና ስኬት ድሀውን ህዝብ ለመታደግና ጠንካራ አገርን መገንባት እንዲችሉ መልካም የሥራ ዘመንን ተመኝተውላቸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል በበ ኩላቸው፤ ‹‹አገራችን በሽግግር ላይ ነች፡፡ የዛሬ ቀንም የሽግግር ጊዜ ነው፡፡ ሽግግሩ ፈታኝ ነው፡፡ ብዙ ችግሮች ገጥመውናል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ፈተና ላይ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ተባብረን ለውጥ እናመጣለን፡ ፡
በችግር ጊዜ ተሸንፈን ሳይሆን ተረዳድተን ስኬት እናመጣለን፡፡ በሽግግር ሂደቱ ውስጥ አቶ ለማ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በቀጣይም አዲሱ ተሿሚ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተለይ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ ከበፊቱ የላቀ ትብብር ማድረግ አለባቸው፤ አብረን ለመሥራትም ዝግጁ ነኝ›› በማለት ችግሮችን አብሮ ለመቅረፍ በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
በሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለአቶ ለማ መገርሳ፣ ለዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ለዶክተር አለሙ ስሜና ለወይዘሮ ጠይባ ሀሰን የወርቅ ሜዳሊያና የየራሳቸውን በእጅ የተሠራ ፎቶ ተሸልመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011