11ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አጠቃላይ የቻምፒዮናው አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቀ ሲሆን በወንዶች ደግሞ ሦስተኛ ሆኖ ጨርሷል። ይህም አጠቃላይ ውድድሩን በነጥብ ቀዳሚ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል። በወንዶች ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማእከል በአጠቃላይ በሰበሰበው ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል። ኦሮሚያ ክልል በበኩሉ በሁለቱም ጾታ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን እንደ አጠቃላይ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ጨርሷል።
ቻምፒዮናው ባለፉት ሁለት ቀናት በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች ጠንካራ ፉክክሮችን ያስተናገደ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል በአራት በአራት መቶ ድብልቅ ሪሌይ (የዱላ ቅብብል) ከፉተኛ ፉክክር በማሳየት ጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማእከል አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ኦሮሚያ ክልል ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳለያውን ወስዷል። ሦስተኛና የነሐስ ሜዳለያ ተሸላሚው ደግሞ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መሆን ችሏል።
ሌላው የተመልካችን ትኩረት የሳበውና ተወዳዳሪዎች በእጅጉ የተፎካከሩበት የወንዶች ከፍታ ዝላይ ውድድር ሲሆን፣ ኦኬሎ ኡጁሉ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አሸናፊ ሆኗል። ኡጁሉ አንበሴ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ ሁለት ሜትር ከፍታን የዘለለ ሲሆን፣ ገመዳ አባተ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ
ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በውድድሩ ተመሳሳይ ከፍታ መዝለል የቻለው ኡጁሉ አንበሴ ለአዲስ ዘመን በሰጠው አስተያየት፣ ዝግጅቱ ጥሩ እንደነበረና ውድድሩ ፈታኝ እንደሆነ ተናግሯል። ክለቡ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ጥሩ ቢሆንም የመለማመጃ መሣሪያ እጥረት እንዳለም አልሸሸገም። አትሌት ኡጁሉ ለሉሳካው ውድድር ጠንክሮ እንደሚሠራና ለአገሩም ወርቅ እንደሚያስመዘግብ ጨምሮ ገልጿል። ኦኬሎ ኡጁሉ በበኩሉ «መጀመሪያ ስገባ ፈርቼ ነበር ግን ብዙ የሚያበረታታ ደጋፊ በመኖሩ አንደኛ ልወጣ ችያለሁ» ሲል ገልጿል። አትሌት ኦኬሎ በአካዳሚው ስልጠና በሳምንት ሦስቴ እንደሚያደርግ ገልጾ ስፖርቱ የሚፈልገው ቁሳቁስ እጥረት ቢቀረፍ የተሻለ ውጤት እንደሚመዘገብ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ውድድሩ ትናንት ፍፃሜ ሲያገኝ በሁለቱም ጾታ የተካሄደ የ10ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድር ማለዳ ላይ ተካሂዷል። በዚህም በሴቶች አባቡ አያሌ ከመቻል 52:30:20 በሆነ ሰዓት በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ፣ ብርሃን ሙሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ56:42:05 ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። አልማዝ እሸቱ ደግሞ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በ58:55:89 ሰዓት ሦስተኛ ሆና ጨርሳለች። በወንዶች ምስጋና ዋቁማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 42:37:91 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆኖ ጨርሷል፣ እሱን ተከትሎ መለስ ሙሉ ከአማራ ክልል 42:48:81 በሆነ ሰዓት መግባት ችሏል። የሦስተኝነቱን ቦታ ደግሞ ፍቃዱ ጥላሁን ከአማራ ፖሊስ በ43:06:10 በሆነ ሰዓት ይዟል።
የወንዶች 5 ሺ ሜትር ከፍተኛ የሆነና በአስሩም ዙሮች ሁሉም ተወዳዳሪዎች እልህ አስጨራሽ ፉክክርን ያደረጉበት ነው። ውድድሩን ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ ንብረት ክንዴ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ 14:26:45 በመግባት የወርቅ ሜዳሊያውን ሲወስድ ፣ መንግስቱ አማረ ከአማራ ክልል 14:26:94 ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ይበልጣል ጋሻው ከአማራ ማረሚያ 14:27:95 በመግባት ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።
በወንዶች የጦር ውርወራም ከፍተኛ ፉክክርና የተደረገ ሲሆን ሳሙኤል ደበላ ከኦሮሚያ ክልል 70.78 ሜትር በመወርወር አንደኛ መሆን ችሏል። ታደሰ ሂርቦዬ ከኦሮሚያ ክልል 68.68 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ አኮት ጀምስ ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ሦስተኛ በመሆን ጨርሷል። ቻምፒዮናው በቆየባቸው ስድስት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ርቀቶችና የሜዳ ላይ ተግባራት ውድድሮች ጠንካራ ፉክክሮችን ሲያስመለክት መቆየት ችሏል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ የውድድሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት፣ ከዕድሜ ተገቢነት ክፍተት ውጪ ቻምፒዮናው በጥሩ ሁኔታ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። ጥሩ ተፎካካሪዎችና አዳዲስ አትሌቶችም የታዩበት መሆኑንም አክለዋል። አላማውም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በዕድሜ ተገቢነት የተቀነሱ አትሌቶች ውሳኔውን በጸጋ መቀበላቸው መልካምና ወደፊትም መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።
አጠቃላይ ውድድሩን በሦስተኝነት የጨረሰው የኦሮሚያ ክልል አትሌት የሆነውና የጦር ውርወራን ያሸነፈው ሳሙኤል ደበላ ውድድሩ ቆንጆ መሆኑን ተናግሮ ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ በፌዴሬሽኑ የተወሰደው እርምጃ በደንብ ሊታይ እንደሚገባ አስረድቷል። አትሌት ሳሙኤል የተወሰደው እርምጃ ሁሉንም ያማከለና ለሁሉም የሚያሳምን ሊሆን ይገባል ሲልም ገልጿል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም