ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ሳምንቱ ያለፈው በትምህርት ነበር እንዳላችሁ እርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርት ነው። እናንተ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ እንደሆናችሁ አምናለው። ጎበዝ ተማሪ ትምህርቱን በአግባቡ ያጠናል፣ የቤት ሥራውን ይሠራል እና የቤተሰብ ምክር ይሰማል። እናንተም እነዚህን ተግባራት ስለምታከናውኑ ጎበዝ ናችሁ ማለት ነው።
ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ባለብዙ ተሰጥዖውን ቴዎድሮስ ጌትነትን ነው። ቴዎድሮስ የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ሲሆን በአፄ ናዖድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። የትወናና የዳንስ ችሎታ ያለው ልጅ ሲሆን በትወና ችሎታው የትወና ውድድር እየተሳተፈ ያለና ወደ ሦስተኛ ዙር ለማለፍ የቻለ ልጅ ነው።
ልጆች ቴዎድሮስ ትወና የጀመረው ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር ትምህርት ቤት ውስጥ በሚሰጥ ሥልጠና የትወና ችሎታውን አዳብሮ ትምህርት ቤቱን በመወከል የጠቢቡ ሰለሞንን ገፀ-ባሕሪ በመጫወት ተወዳድሮ ለመሸለም ችሏል፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። ታዲያ ቴዎድሮስ በዚህ ብቻ አላበቃም እስከ ወረዳ ድረስ ውድድሮችን አድርጓል፤ የትወና ችሎታውን የበለጠ ለማዳበር ወ.ወ.ክ.ማ በመግባት ሙያዊ የትወና ጥበብን በመማር ባለው ችሎታ ላይ እውቀትን ጨምሯል። አሁንም በተለያዩ ውድድሮች ላይ ከመወዳደር አልቦዘነም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ሌላ የትወና ውድድር በማካሄድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ውድድሮችን በብቃት በመወጣት ወደ ሦስተኛ ዙር በማለፍ ለቀጣይ ዙር ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል።
ቴዎድሮስ የእግር ኳስ አድናቂ ነው፤ የዓለም የእግር ኳስ ከዋክብት የሆኑት የክርስቲያኑ ሮናልዶ እና የሜሲ አድናቂ ነው። ልጆች ቴዎድሮስ ክርስቲያኑ ሮናልዶ እና ሜሲን የሚያደንቀው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ሁለቱም የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዛሬ የደረሱበት የስኬት ማማ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በርካታ ፈተናዎችን አልፈዋል። ነገር ግን እነዚያ ፈተናዎች መድረስ ከሚፈልጉበት ቦታ ከመድረስ አላገዳቸውም ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል ካሰቡት ቦታ ደርሰዋል። ታዲያ የቴዎድሮስንም ቀልብ የሳበው ይህ በነገሮች ተስፋ ሳይቆርጡ ካሰቡበት የመድረሳቸው ፅናት ነው።
ልጆች ቴዎድሮስ በትምህርቱ ድርድር የማያውቅ ጎበዝ ተማሪ ነው፤ ምንም እንኳን ትወናን ከልቡ የሚወድ ቢሆን ሁሉንም ልምምድም ሆነ ሥልጠና ጊዜ ሰጥቶ የሚከታተለው ከትምህርት ሰዓት ውጪ ነው። ያለበቂ ምክንያት ከትምህርት ቤት አይቀርም። ቴዎድሮስ ልጆች የሚፈልጉትን ነገር ከልጅነታቸው ጀምሮ ማዳበር አለባቸው ብሎ ያምናል። ልጆችዬ ቴዎድሮስ ሲያድግ ሳይንቲስት መሆን ይፈልጋል። ሳይንቲስት መሆን የሚፈልገው ለምን መሰላችሁ፤ በራሱ ተመራምሮ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የራሷ የሆነ አዲስ ቴክኖሎጂ እንዲኖራት እና ከተለያዩ ሀገራት የምታስገባቸውን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በራሷ እንድታመርት በማድረግ ከራሷ አልፋ ለአለም ገበያ የምታቀርብ እንድትሆን ለማድረግ የሚያስብ ትልቅ ልብ ያለው ልጅ ነው።
ቤተሰቦቼ ተለያየ መንገድ ይደግፉኛል የሚለው ቴዎድሮስ ቤተሰቦቹ ትምህርቱን በአግባቡ እንዲከታተል እንደሚከታተሉት፤ ፊልምና ጌም ላይ ብዙ እንዳላተኩር እንደሚመክሩት ይናገራል። ቤተሰቦቹ በዚህ ብቻ አያበቁም ሕልማቸው እሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት መሆኑን ዘወትር ይነግሩታል፤ ይህ ደግሞ እሱ እንዲበረታ ያደርገዋል። ባለብዙው ተሰጥዖው ቴዎድሮስ ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር እንጂ አላስፈላጊ ጫና ሊያደርጉባቸው አይገባም፤ ልጆች የሚሄዱበትን ትክክለኛ መንገድ ማሳየት ግን አለባቸው ይለናል። ልጆች መሆን የሚፈልጉትን ነገር እንዲያሳኩ መደገፍ እና ከጎናቸው በመሆን ሊያበረቷቸው ይገባል በማለት ለወላጆች መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ቴዎድሮስ ስለቴክኖሎጂ ሲናገር፤ ልጆች ቴክኖሎጂን ለበጎ ነገር መጠቀም ይኖርባቸዋል። የተለያዩ ለእድሜያቸው የማይመጥኑና ምንም እውቀት የማይጨምሩላቸውን ምስሎች በማየት ጊዜያቸውን ማባከን የለባቸውም። የሚጫወቷቸው የቪዲዮ ጌሞችም ቢሆኑ የማሰብ እና የማገናዘብ አቅምን የሚፈትኑና የአዕምሮ ብስለትን የሚያዳብሩ መሆን አለባቸው። ቴክኖሎጂው እንዳጠቃቀማችን ሊያለማንም ሊያጠፋንም ይችላል፤ ስለዚህ መርጠን መመልከት ያለብን እኛ ነን ይላል።
ቤተሰቦችም ቢሆኑ ከልጆቻቸው ላይ ዓይናቸውን መንቀል እንደሌለባቸው እና አሁን ላይ ቤተሰቦች በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥረው ስለሚውሉ ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር የሚሰጡት ትኩረት እያነሰ መምጣቱን የሚናገረው ቴዎድሮስ፤ ቤተሰቦች ልጆቻቸው የሚውሉበትን ቦታ ማወቅ፣ አብረዋቸው የሚውሉትን ሰዎች ማወቅ፣ በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ የሚያዩትንም ሆነ የሚያወርዷቸውን መተግበሪያዎች መቆጣጠር ይኖርባቸዋል በማለት ያብራራል። “ልክ የሰው ልጅ ኦክስጂን ሲያጣ እንደሚሞተው ሁሉ እኛ ሕፃናትም የወላጆቻችን ትኩረትና ክትትል ከሌለን በማይሆን አቅጣጫ ተጉዘን የመጥፋት እድላችን ከፍተኛ ነው” በማለት የቤተሰብ ክትትል ለልጆች ወሳኝ መሆኑን ይገልፃል።
ልጆች የሚፈልጉት ነገር ለማግኘት በሚያስችላቸው ትክክለኛ መንገድ መሄድ አለባቸው፣ ቤተሰቦቻቸው የሚመክሯቸውን ነገሮች መስማትና ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ያላቸውን ጊዜ ከፋፍለው መጠቀምና ለተገቢ ነገር መዋል አለባቸው። እኔ ውጤታማ የሆንኩት እነዚህን ነገሮች በማድረጌ ነውና ልጆች ከኔ ይህንን ቢማሩ እላለሁ የሚለው ቴዎድሮስ በትወናው ቀጥሎ ወደፊት ከኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ አልፎ በቦሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ምርጥ ተዋንያን መካከል አንዱ መሆን ይፈልጋል።
ልጆችዬ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ምን እንደሚመኝላት ታውቃላችሁ? ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን፣ ችግሮቿን በራሷ የምትፈታ፣ የራሷን ቴክኖሎጂዎች የምትጠቀም ዘመናዊና የሰለጠነች ሀገር እንድትሆን ይመኝላታል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም የሀገሪቱ ማኅበረሰብ መተባበር እና በፍቅር አብሮ መኖር እንዳለበት ያምናል። በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም