አፍላ ወጣትነት ከ10 እስከ 19 ዓመት የእድሜ ክልል ሲሆን፤ ይህ ጊዜ ፈጣን እድገት የሚታይበት ከመሆኑ ባሻገር በህፃንነት ዘመን የተከሰተን የምግብ ሥርዓት አለመመጣጠን ለማስተካከል የሚቻልበት ነው። ከመጀመሪያው አንድሺህ ቀናት ቀጥሎ ሁለተኛው አመቺና ወሳኝ ጊዜ እንደሆነም ይታመንበታል። ይህ ወቅት አፍላ ወጣቶች በተለይ የልጃገረዶችን የአመጋገብ ሁኔታ ማስተካከል ፣ የትምህርት ተሳትፏቸውን ማረጋገጥ ፣ የጤና እንክብካቤ ተጠቃሚነትን መጨመር ፣ ያለእድሜ ጋብቻና ወሊድን በመከላከል ሙሉ አቅም ያላቸውን አገር ተረካቢ ወጣቶችና ቀጣይ ትውልድ ለማፍራትም የሚረዳ ነው።
በሌላ በኩልም ይህ እድሜ ብዙ አይነት ተጽዕኖዎች የሚፈጠሩበት ብሎም ፍላጎቶች የሚንጸባረቁበት ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በአግባቡና በሥርዓቱ መመራት ካልተቻለ ብዙ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያስከትል ነው። በተለይም የሥነ ተዋልዶ ጤና እውቀታቸውን እያዳበሩ እንዲሄዱ የሚያስችሉ መንገዶች ካልተመቻቹላቸው ኤች አይ ቪ ኤድስን ጨምሮ ያለእድሜያቸው በርካታ ሥነ ተዋልዷዊ ችግሮችን እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ።
አቶ እዮብ ጌታቸው በጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶች ጤና ቴክኒካል አማካሪ ሲሆኑ፤ አፍላ ወጣትነት ብዙ እድሎችም ችግሮችም ያሉበት ነው ይላሉ። በጤና ስትራቴጂያችን ላይ ወጣቶች በማለት ጠቅለል ተደርጎ የተቀመጠው የእድሜ ክልል 10 እስከ 24 ዓመት ሲሆን፤ የተለያየ ክፍል ያለው ነው። አፍላ ወጣት የሚባሉት ከ10 እስከ 19 ዓመት ያሉ ናቸው። ይህ እድሜ ደግሞ ከልጅነት ወደ አዋቂነት የሚሄዱበት በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል። በዚህም ልጆቹ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ለውጦች በስፋት የሚስተዋልባቸው ስለሆነ አዋቂዎች የተለየ ድጋፍና ትኩረት ሊሰጧቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።
አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ወጣትነትን ከጤናማነት እና ከጉልበታምነት ጋር ያያይዘዋል። ነገር ግን በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ይህንን አያሳይም። በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ህመሞች ይጠቃሉ። ከዚያም ሲያልፍ ደግሞ ለሞትና ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ ይጋለጣሉ። የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርትም እንደሚነግረን በዓለም ላይ በየቀኑ ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ልንከላከላቸው በምንችላቸው ምክንያቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ። ይህ ለመሆኑ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። እንደ አገርም መወሰድ ያለበት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ወጣቶች በዚህ እድሜያቸው ላይ አካላዊና ማህበራዊ ለውጦችን የሚያሳዩበት እንደመሆኑ መጠን በቂ መረጃን ማግኘት ይኖርባቸዋል። በቂ መረጃ ማግኘት ባልቻሉ መጠን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ እንዲሁም በባህልና በአቻ ግፊቶች ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች የመጋለጥ ሁኔታቸው ከፍ ያለ ይሆናል። ለምሳሌ፡- አንዱ የአፍላ ወጣትነት እርግዝና ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዓለምአቀፋዊ ይዘት አለው። የዓለም ጤና ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ እኤአ በ2019 ባወጣው መረጃ እንዳመላከተው በየዓመቱ 21 ሚሊዮን የሚሆኑ እድሜያቸው ከ 10 እስከ 19 ዓመት የሆናቸው አፍላ ወጣቶች እርግዝና ይፈጠርባቸዋል።
ከዚህ ቁጥር ውስጥ ደግሞ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በሳሃራ አፍሪካ ያሉ አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ነው። ይባስ ብሎም በየዓመቱ ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከሚፈጠርባቸው እርግዝና ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ የማቋረጥ ተግባር ውስጥ ይገባሉ። ይህ ደግሞ ለበርካታ አካላዊ፣ ጤናዊና ማህበራዊ ጉዳቶች እንዲዳረጉ መንገድ ይከፍታል እንደ አቶ እዮብ ማብራሪያ።
የኢትዮጵያ ሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እኤአ በ2016 ባደረገው የዳሰሳ ጥናት እንዳስቀመጠው፤ በአገራችን ያለው ሁኔታ 13 በመቶ የሚሆኑ ትዳር የመሰረቱ አፍላ ወጣቶች አርግዘው እንደሚወልዱ ያሳየናል። ይህም አፍላ ወጣትነት የምንለው አሁን ባለበት ደረጃ 13 በመቶ ነው። ይህን ደግሞ በክልል ደረጃ ስንከፋፍለው በርካታ ልዩነቶች ይኖራሉ። ለምሳሌ፡- አፋር ክልል ከፍ ያለ ቁጥር ሲይዝ አዲስ አበባ ሦስት በመቶውን ይሸፍናል። እዚህ ላይ በአፋር ክልል ሁኔታው በዚህን ያህል ለመጨመሩ ዋናው ምክንያቱ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ናቸው። በዚህ ክልል ላይ አንዲት ታዳጊ ሴት ትዳር እንድትመሰርት የሚፈለገው በለጋነት እድሜዋ ነው። በዚህ እድሜዋ ተድራ ደግሞ በዓመቱ ልጅ እንድትወልድ ይጠበቃል። ከዚህ የተነሳ በ 14 እና 15 ዓመቷ ትዳር ከመሰረተች በ17 ዓመቷ ልጅ ትወልዳለች ማለት ነው። ይህ ደግሞ ባህልና ሃይማኖቱ ተዳምሮ የግንዛቤው ክፍተት ሲጨመርበት የሚከሰት ችግር ነው።
በከተሞች አካባቢ ደግሞ በተለይም በዚህ ጊዜ የሱስ ተጠቃሚ ወጣቶች ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ በመሆኑ ወጣቶች ላይ በርካታ ሥነ ተዋልዷዊ ችግሮች እንዲከሰት አድርጎታል። በተለይም ሱስ አስያዥ የሆኑ ነገሮች እንደ ጫት፣ ሲጋራና አልኮል እንዲሁም ሌሎች የአዕምሮን የማሰብ፣ የማገናዘብ አቅም የሚያዳክሙ ነገሮችን መውሰዳቸው ልቅ የሆነ ወሲባዊ ግንኙነት እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ ላልተፈለገ እርግዝና ያጋልጣል። ወጣቶቹ ከገቡበት ችግር ለመውጣት በማሰብም ደህንነቱ ወዳልተጠበቀ የጽንስ ማቋረጥ እርምጃ ይገባሉ ሲሉም አቶ እዮብ ይናገራሉ።
አፍላ ወጣትነት እርግዝና ከጤናው ዘርፍ ባሻገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የህክምና ችግሮችን ያስከትላል። ማህበራዊ ችግሮቹን ስንመለከት አንዱ 15 እና 16 ዓመት እድሜ ክልል ላይ ያለች ወጣት ከእሷ የሚጠበቀው ዛሬ ላይ በደንብ ተምራ ነገዋን ማሳመር ቢሆንም ወዳልተፈለገ እርግዝና ስትገባ እሱን ተከትሎ የትምህርት ማቋረጥ ይከሰትባታልⵆ እሷና መሰሎቿ በዚህ ሁኔታ ትምህርታቸውን እያቋረጡ በሄዱ መጠን ደግሞ በትምህርት ሴክተሩ ላይ መጠነ ማቋረጥን ያሰፋል። ትምህርት አቋረጡ ማለት ደግሞ ስራ አጥነት ይበራከታል። ለራሷም ለልጇም መሆን የማትችል በምትሆንበት ጊዜ ደግሞ እንደ አገር ድህነት ይሰፋልⵆ ይህም በአገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገለጽ አይሆንም። ወደ ጤናው ዘርፍ ስንመጣ አፍላ ወጣቶች በልጅነታቸው በመጸነሳቸው ለደም ግፊት፣ ለደም ማነስ፣ ያለጊዜ ምጥ መምጣት፣ ለተራዘመ ምጥ እንዲሁም ለፊስቱላ የመጋለጥ እድላቸው ይጨምራል።
በሌላ በኩልም ከግብረ ስጋ ግንኙነት ጋር ተያይዞም ለሚመጡ የመራቢያ አካላት ኢንፌክሽኖች የመጋለጥ እድላቸውን ከፍ ያደርጋሉ። የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሩም ሰፋ ስለሚል ችግርን ለማምለጥና ኢኮኖሚያቸውን ለማገዝ ሲሉ የወሲብ ንግድ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ለመኖር ሲሉም ሌሎች ወንጀል ነክ ተግባራትን ለመፈጸምም ይሞክራሉ።
እንደ አቶ እዮብ ማብራሪያ፤ እነዚህ ወጣቶች በተለይም ለሞት የሚያጋልጣቸው አንዱና ዋናው ችግር ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ የማቋረጥ ሂደት ነው። ጉዳዩ በጣም ስለሚያስጨንቃቸው በአቻ ግፊት በመገፋፋት ያልተገቡ ነገሮችን ያደርጋሉም። ለአብነት ወደ ማህጸን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን መክተት፣ አደገኛ የሆኑ መድሃኒቶችን መዋጥና መጠጣት በዋናነት ይጠቀሳሉ። በዚህም ከአካላዊ ጉዳት እስከ ሞት የሚያደርስ ችግር እንዲደርስባቸው ይሆናሉ።
የአፍላ ወጣትነት እርግዝና በምትወልደው ሴት ላይ ብቻ ሳይሆን በሚወለዱት ህጻናት ላይም የሚኖረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አንደኛው ህጻናቱ ሲወለዱ በጣም ዝቅተኛ የውልደት ክብደት ይዘው መውጣት ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ተደጋግሞ ለሚከሰት ኢንፌክሽን የመጋለጥ፣ በሕይወት አለመወለድ በሕይወት ቢወለዱ እንኳን የአምስት ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ መሞት ያጋጥማቸዋል።
በየአራትና አምስት ዓመቱ ብናስበው ዛሬ አፍላ ወጣት ይባሉ ነበር። በመሆኑም ተከታታይነት ያለው የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትና በእድሜያቸው የተመጠነ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል። ይህንን ደግሞ ከትምህርት ሴክተሩ ጋር በመቀናጀት የምንሰራቸው ሥራዎች ሲሆኑ፤ ለምሳሌ፡- የትምህርት ቤት የጤና ፕሮግራም የሚባል አለ ይህንን ጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር አቅዶና ተቀናጅቶ በመተግበር በስፋት እየሰራ ነው ይላሉ አቶ እዮብ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትን መረጃ በካሪኩለም ውስጥ አካቶ ለተማሪዎች መስጠት የሚለው ሲሆን፤ ትምህርቱን እንዲያገኙ እየተመቻቸ ነው። ይህ ብቻ በቂ ነው ብሎ ለማለት ግን ይከብዳል። በመሆኑ በክበባት፣ በፕሮጀክቶች በእድሜያቸው የተመጠነ ደረጃውን የጠበቀ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትና መረጃ መስጠት ያስፈልጋልና በአሁኑ ወቅት ይህ እየተሰራ ነው። ሆኖም አሁንም ተደራሽነቱ ላይ ብዙ ችግሮች አሉ። ከፍላጎቱ አንጻርም እየተሰራ ያለው ስራ በቂ አይደለም ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የግብዓትና የገንዘብ ውስንነት ነው። ይህም ቢሆን ግን ጤና ሚኒስቴር አጋሮቹን በማስተባበር ሰፋፊ ሥራዎችን ለማከናወን እየሞከረ እንደሆነ ያነሳሉ አቶ ኢዮብ።
ጤና ሚኒስቴር ከአጋሮቹ ጋር ከሚሰራው ስራ በተጓዳኝ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ድረስ በጉዳዩ ላይ በያገባኛል ስሜት ሰፊ ኃላፊነት ወስዶ መስራት ይጠይቃል። አፍላ ወጣቶች በቤታችን፣ በጎረቤታችን፣ በትምህርት ቤት በመንገድ በሁሉ ቦታዎች ላይ አሉ። በመሆኑም እዚያ ጋር የምናየውን ነገርና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደ ግለሰብ ተከታትሎ በጎ ያልሆነውን ማስቆም ፤ መልካሙን መውሰድ ያስፈልጋል። የአቻ ግፊትን ምክንያት አድርጎ ወጣቶች በማይመጥኗቸው ቦታዎች ላይ ሲገኙ ፣ አልኮል ሲጠጡ ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮችን ሲጠቀሙ በአግባብ እርምጃ መውሰድ ይገባል። ከአቅም በላይ ከሆነ ለሕግ አካል በማሳወቅ ወጣቶቹን ከችግር መታደግ ይኖርብናልም ይላሉ።
ለምሳሌ፡- አፍላ ወጣቶች አልኮል እንዲጠጡ በፍጹም አይበረታታም። ነገር ግን ግሮሰሪዎች ላይ አንድ አፍላ ወጣት አልኮል ገዝቶ ሲሄድ ያየ ግለሰብ ጉዳዩን በቸልታ ማለፍ የለበትም ለሚመለከተው አካል መጠቆምና ማሳወቅ ይገባል። በመሆኑም ህብረተሰቡ እንደ ግለሰብም፣ እንደ ቤተሰብም ወጣቶቹ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ስለሁኔታው ማሳወቅ፣ ማስተማር አለበት።
አቶ እዮብ እንደሚሉት፤ አፍላ ወጣቶች ከዚህ ሁሉ ነገሮች አልፈው ችግር ውስጥ ከገቡ በጊዜ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው የሚረዱበት መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ለምሳሌ፡- በጤና ሚኒስቴር የነጻ የስልክ መስመር 952 በመደወል ተገቢውን መረጃ ማግኘትና መደገፍ ይቻላል። ከግለሰብ ወጣ ስንል ደግሞ ተቋማት፣ ማህበራት በሙሉ የሚሰሩትን ስራ ወጣት ተኮር መሆን ይኖርበታል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ሥልጠናዎችን ማድረግ ላይ አጠናክሮ መስራት ተገቢ ነው። እንደ ጤና ሚኒስቴርም የህክምና ተቋማት ለወጣቶች የተመቻቸ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ ተቋማቱን ወጣቶቹን የሚስቡ በማድረግ፣ ግብዓትን በማሟላት፣ ለብቻቸው የምክር አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ በመፍጠርና ሌሎችንም ስራዎች በስፋት እየተሰራ ይገኛል።
በጠቅላላው የወጣቶችን ጤና ማሻሻል የጤና ሴክተሩ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሴክተሮችም ነውና ጤና ሚኒስቴር በቅንጅት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው። በተለይም ከትምህርት ሴክተሩ፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሌሎቹ ጋር ጥሩ የሥራ አጋርነት ተፈጥሯል ይላሉ አቶ እዮብ። በሌላ በኩልም እንደ አገር በየዓመቱ በመስከረም ወር ትልቅ የወጣቶች ጤና ፎረም ይዘጋጃል። በተለይም የአፍላ ወጣትነትን እርግዝና ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን የመወያየትና የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ ስራዎች ይሰራሉ።
ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዲሁም ጤና ተቋማቱን ለእነሱ ምቹ ማድረግ ብቻውን በቂ ስላልሆነ ጤና ሚኒስቴር በዋናነት የአገቡ ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግና “የብልህ ጅምር ” በሚል በሁሉም ክልሎች የመመካከሪያ ዘዴን በመቀየስ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ በመተግብር እየከወነ ይገኛል። በተለይም በገጠር አካባቢ ያሉ ትዳር የመሰረቱ አፍላ ወጣቶች ወደ ልጅ መውለድ ከመሄዳቸው በፊት ሊያደርጉት የሚገባውን ዝግጅት ፤ ሳይዘጋጁ በመውለዳቸው በእናቲቱም ሆነ በልጁ ላይ የሚያስከትለውን ችግር በሚገባቸውና ከሕይወታቸው ጋር በተገተናኘ መንገድ ለማስረዳት እየተሰራ ነው። ይህ ደግሞ ኑሯቸውን አውቀው በምን መልኩ ልዘጋጅ፣ ልጅ ከመውለዴ በፊት ምን ያህል ጊዜ ልውሰድ የሚለውን እንዲወስኑ አስችሏል። ይህ ስራም የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን በመከላከል በኩል ትልቅ ሚና መጫወቱን አንስተዋል አቶ እዮብ።
አቶ እዮብ ጌታቸው በጤና ሚኒስቴር የአፍላ ወጣቶች ጤና ቴክኒካል አማካሪ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም