በዩኒሴፍ ለ14 ዓመታት አገልግለዋል። በተለይም አፍጋኒስታን በጦርነት ውስጥ ሆነው የፕሮጀክት ማናጀርና የሴኪዩሪቲ ኃላፊነታቸውን ለሰባት ዓመት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ፤ ሕይወታቸውን ጭምር አስይዘው ሠርተዋል። ሰብዓዊ መብት እንዲረጋገጥ ብዙ ለፍተዋልም። በካናዳ ፐብሊክ ሄልዝ ኤጀንሲ ውስጥ ማናጀር ሆነው ለ16 ዓመታት ጡረታ እስኪወጡ ድረስ አገልግለዋል። በእነዚህና ሌሎችም ትጋታቸው ሽልማትን አግኝተዋል–አቶ ሰማነህ ታምራት።
በአንዳንዶች “ሰማነህ ጀመረ” ተብለው የሚጠሩት እኝህ ሰው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ታከተኝ ብለው አያውቁም። ሀገር በእውቀት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ እንድትታገዝ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ለአብነት በሁለት ድርጅቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች በመሳተፍ ብዙ ተግባራትን ፈጽመዋል። በዚህም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የእውቅና ስጦታን ተቀብለዋል።
የእንቦጭ አረም ጣናን ባስቸገረበት ወቅት ካናዳውያንን በማስተባበር 260 ሺህ የካናዳ ዶላር በመሰብሰብና ማሽን በማስገዛት እገዛ አድርገዋል። አሁን ገና ከጅምሩ አምስት ሺህ ሄክታር የሸፈነውን እንቦጭ በዚሁ ማሽን ወደ ስምንት መቶ ማውረድ ተችሏል። በጊዜ ሂደትም እንዲጠፋ እንደሚያደርገውም አምነዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማሽኑ ዛሬም መሥራቱ ነው።
አቶ ሰማነህ ሌላም የሚጠቀሱበት ሥራ አላቸው። ይህም አዲስ የሥራ ልምድን ማስጀመራቸው አንዱ ሲሆን፤ ወረታ ላይ የሩዝ ምርት እንዲጀመር ካስቻሉ ኢትዮጵያውያን መካከል መሆናቸው ደግሞ ሌላኛው ነው። ይህንን ያደረጉት ደግሞ ከቻይና ተምረው ወደ አገራቸው ሲመለሱ የቀሰሙትን ልምድ ወደ ተግባር በመቀየር ነው። ለጊዜው ብዙ መሰናክሎች ገጥመዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ሆኖም ገበሬውን በማሳመን ለዛሬ የሩዝ አምራችነቱ መሠረት ጥለዋል። በተመሳሳይ ከሰላም አንጻር በካናዳ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሞጋች ከሚባሉት ዲያስፖራዎች ውስጥ አንዱ እንደሆኑም ይነሳል። “ከግላቸው ባለፈስ፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ምን ምን ተግባራትን አከናውነዋል?” እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ዘለግ ያለ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያ ስለእርስዎ ጥቂት እንበል?
አቶ ሰማነህ፡- እሺ፤ ደስ ይለኛል። በውጪ ብዙ ቦታ ተዘዋውሬ አገልግያለሁ። በካናዳ ብቻ በመንግሥት ሥራ ላይ ከ16 ዓመት በላይ ቆይቻለሁ። ይሁንና ከሁሉም ያስደሰተኝ ሀገሬ ላይ ሆኜ የሠራሁት ነው። ገና ከቻይና ተመርቄ እንደመጣሁ ያደረኩት ማለቴ ነው። ይህም ምሩቅነቴ በግብርናው ዘርፍ ስለሆነ “ሀገር ባላት ሀብት መጠቀም አለባት” በሚል ተነሳሽነት ለውጥ ለማምጣት የገባሁበት ነው። ከጓደኛዬ ጋር በመሆን የሩዝ ምርትን ለመጀመር ብዙ ርቀት ተጉዘናል። በዚህም መልካም ነገሮችን ማየት ችያለሁ። ምክንያቱም ሀገሬ ላይ መልካም ተክል እንደ ተከልኩ ተሰምቶኛል።
ተግባሩን የጀመርነው ከደርግ መንግሥት በተሰጠን ተልዕኮ ሲሆን፣ ሥራው የተጀመረውም ወረታ ላይ ነው።ቦታው ረግረጋማ ስለሆነ ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለውን የሩዝ አይነት መርጠን ወደ ተግባር ገብተናል። ስኬታማም ሆነንበታል። እንደ ሀገር ተመራማሪዎች ሞክረውት ወደ ተግባር ይገባል ቢባልም የሀገራችን ተመራማሪዎች ሊቀበሉን አልቻሉም። እኛም ይተዉት ብለን፣ በድፍረት ከአርሶ አደሩ ጋር በመነጋገር ሥራውን ገባንበት። ለማሳመን ግን ፈታኝ እንደነበር አልረሳውም። ሆኖም ተቀብለውን በሄክታር 40 ኩንታል እንዲያገኙ አስችለናቸዋል።
መንግስት በባሕርዳር ከተማ የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርጎ ከቀጠረኝ በኋላም ቢሆን ይህንን ሥራ እዛ አካባቢ ሰፈራ ለሚያደርጉት ሰዎች እድሉን አመቻችተንላቸዋል። የሳሊኒ ፕሮጀክት ደግሞ በእጅጉ አግዞናል። በመስኖና በፓንፕ እየተጠቀሙ ሩዝን በአንድ ሺህ ሄክታር ላይ እንዲያመርቱ ሆነዋል። በዓመቱ ጥቅሙን ስለተረዱት ወደ 4ሺህ ሄክታር ከፍ አድርገውታል። አሁን የሩዝ ምርቱ በማይታመን ሁኔታ ጨምሯል። ይህ በመሆኑም እንደ አንድ ስኬታማ ባለሙያ የደስታ እንባ አንብቻለሁ። ለሀገሬ ይህንን በማድረጌም እረክቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራው በተለያየ ዘርፍ አበርክቶ ሲያደርግ ነበር። በተለይም ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ፤ ለዚህም መንግሥት እውቅና ሰጥቷል። በእናንተ በኩል የነበረው ምን ይመስል ነበር?
አቶ ሰማነህ፡- እኔ የመጣሁት ከካናዳ ዋና ከተማ፣ ከኦተዋ ነው። በካናዳ ውስጥ በርከት ያሉ አደረጃጀቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል የእኛ አንዱ ነው። እኔ በኃላፊነት የምሠራባቸው ሁለት አደረጃጀቶች አሉ። ‹‹የኢትዮጵያ ካናዳውያን ኔትወርክ ለማኅበራዊ ድጋፍ›› እና ‹‹ጥምረት ለኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ›› የመጀመሪያው ላይ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የማገለግል ሲሆን፤ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን በተለያየ መልኩ ያገዝንበት ነው። 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በማሰባሰብ ለተጎዱ አካባቢዎችና ወገኖች በቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል።
በተለይም መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁሶችን በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በተጨማሪም አጣዬ አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ቤት ሠርተው ካስረከቡት አደረጃጀቶች (አካላት) መካከል አንዱ ነው።
ሁለተኛው ጸሐፊ የሆንኩበት ሲሆን፤ ዋና ሥራው ራስን በራስ ለመቻል በሚደረገው ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ ነው። ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ላይ እንዲደርስ ማገዝ ሲሆን፤ 400ሺህ የካናዳ ዶላር በመላክ ድጋፍ አድርገናል። 100ሺህ ዶላር ያህል በማውጣትም ቦንድ እንዲገዛ አድርገናል። አሁንም ቢሆን ይህንን ድርጊታችንን የምንቀጥል ይሆናል።
ሀገርን የማዳን ጉዳይ የአንድ ቀን ሥራ ብቻ አይደለም። ብዙ መልፋትና መተባበርን ይጠይቃል። በተለይም ተደራራቢ ችግሮች ሲያጋጥም ሀገርን ዳግም ወደ ነበረችበት ለመመለስ መተጋገዝን የግድ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ዲያስፖራው ትልቅ ኃላፊነት አለበት። በተለይም በመልሶ ግንባታው ዙሪያ ብዙ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል። ምክንያቱም ብዙ የፈረሱ ተቋማት አሉ። በሥነልቦና የተጎዱ ዜጎችም እንዲሁ። የጤና እክል የገጠማቸውም ቀላል አይደሉም። ስለሆነም ዲያስፖራው ይህንን ለመጠገን ብዙ አቅም ያለው በመሆኑ ከመቼውም በላይ መትጋት አለበት። በእኛ አደረጃጀት በኩልም ያለው እሳቤ ይህ ነው። በመሆኑም በእውቀት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ያላሰለሰ ድጋፍ ያደርጋል። አሁን እውቅና በአገኘንበት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በምትፈልገን ሁሉ “አለንልሽ!!!” እንደምንላት አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለዲያስፖራው የተሰጠውን እውቅና እንዴት አዩት? ምንስ አንድምታ አለው ይላሉ?
አቶ ሰማነህ፡- ብዙ መልዕክት አለው። በተለይ መንግሥት ይህንን ያህል ትኩረት ሰጥቶና ተዘጋጅቶ እውቅናን መስጠቱ ለዲያስፖራው ብዙ ትርጉም የሰጠው ነው። አንዱ ዲያስፖራው የበለጠ ተነሳሽነት እንዲኖረው ያደርገዋል። “እሸለማለሁ” ብሎ ባይሠራም “ያበረከትከው ይህ ተደርጎበታል” ሲባል አበርክቶውን ስለሚመለከተው ጨምሮ ለሀገሩ እንዲያደርግ ያግዘዋል። “ገንዘቤ አልባከነም” የሚል ስሜት እንዲሰማውም ያደርገዋል።
በተመሳሳይ፣ለዚህ አይነቱ የመንግሥት እውቅና የተመረጡት ብዙ የዲያስፖራ አደረጃጀቶች መሆናቸው፣ ማለትም በአደረጃጀት መልኩ መሆኑ፣ አንዱ በአንዱ ሥራ መንፈሳዊ ቅናት እንዲያድርበት ያደርጋል። ከዚያም ሌሎችም ዘርፎች ላይ ሀገሩን ለመደገፍ ይሠራል። በተጨማሪም በዓለም ሀገራት ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በጋራ ለአንድ ዓላማ እንዲቆሙም አድርጓቸዋል። ከምንም በላይ በቀጣይ ተሳስረው እንዲሠሩ መግባባት ላይ የደረሱበት ነው። ምክንያቱም በሥራቸው ተዋውቀዋል። ስለሀገራቸው ቀድሞውንም አንድ አይነት አቋም ቢኖራቸውም ያንን አጠናክረው ፈተና የሆነባትን ነገር ለመፍታት እጅ ለእጅ ተያይዘውበታል። ሰላምን ከማረጋገጥ፣ ልማትን ከማፋጠንና የተጎዱ ወገኖችን ከመደገፍ አንጻርም በቻሉት ሁሉ ድጋፍ ያደርጉ ዘንድ ያስችላቸዋል።
እውቅናው ከአውሮፓ እስከ አፍሪካና እስያ የዘለቀ ስለነበርም በትብብር መሥራት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የታየበትም ነው። በቀጣይ እኛ ጋር ምን አለ? ሌሎችስ ጋር የሚለውን በመለየት ሀገርን ለመደገፍ በር ይከፍታል። መተሳሰርን የፈጠረ በመሆኑም አኩራፊ ዲያስፖራ እንዳይኖር ያደርጋል። ዲያስፖራው ለሀገሩ የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሆነ አሳይቷልና። አሁንም የተሰጠው ተስፋ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው።
ከእውቅና አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ሌላው ያየሁት ነገር ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ለሀገሩ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ እንደሚችል ነው። የአባቶቹ ልጅ እንደሆነ በደንብ አይቼበታለሁ። ለዚህም አንድ ምሳሌ ማንሳት እችላለሁ ፤በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያሉትን ‹‹ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ሊወጡ ይችላሉ። ኢትዮጵያን ግን ከአዕምሯቸውና ከአስተሳሰባቸው ማውጣት አይችሉም። ማውጣትም አይቻልም።›› እናም ይህ እውቅና ይህንኑ አረጋግጧል። ዲያስፖራዎች በልባቸው አገራቸውን አዝለው የሚዞሩ ዜጎች እንደሆኑም አሳይቷል።
አዲስ ዘመን፡- ዲያስፖራዎች ለአገራቸው ያላቸውን አጋርነትና ውግንና እንዴት እያሳዩ እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉ?
አቶ ሰማነህ፡- በብዙ መንገድ እያሳዩ ነው። ሰልፍ በመውጣት፣ ሀሳባቸውን ለፓርላማ ጭምር በማስረዳት፤ ለውጪው ዓለም የኢትዮጵያን እውነታ በመግለጥ፤ የተሳሳተውን አጀንዳ ተከራክሮና አሳምኖ በማስቀየር ከዚያ ባሻገር በእውቀት፣ በገንዘብና በሌሎች ውግንናቸውን አሳይተዋል። ለአብነት እንደ ካናዳ ዲያስፖራው ብዙ ነገር ሠርቷል። ኢትዮጵያን ለማጠልሸት በሚዘረጉ አጀንዳዎች ዙሪያ ፓርላማ ጭምር ገብቶ ሀሳብ የማስቀየር ሥራ ተሠርቷል። ለዚህም በቅርቡ የሆነውን ብቻ ልጥቀስ። የካናዳ መንግሥት ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ላይ ጄኖሳይድ ፈጽሟል።›› በሚል ውሳኔ ለማስተላለፍ ተሰብስቦ ነበር። የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ተመርጠንም ፓርላማ ገብተን እውነታውን አስረድተናል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነት ገጥሞ ነበር። በጦርነት ደግሞ ሕይወት ማለፉ ግድ ነው። በትግራይ ብቻ ሳይሆን በአፋርና አማራ ላይም ይህ ሆኗል። እናም ትግራይ ብቻ ተመርጣ ልትታይ አይገባም በማለት ተሟግተናል፤ ማሳመንም ችለናል። በዚህም በሳምንቱ የካናዳ መንግሥት ሀሳቡ ወሬ እንደሆነ አረጋግጦ ውሳኔውን ቀልብሷል። ከዚያ በተጨማሪም ለካናዳውያንና ለውጪ ዜጎች “ኢትዮጵያ ማናት፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል?” እና መሰል ወቅታዊ ነገሮችን መሰረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እናከናውናለን። በተለይ የሚዲያ የውሸት ወሬን በመመከት በኩል በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል።
በሙያ የሚሟገቱና የሚያሳምኑ ሰዎችን ወደ ዓለምአቀፉ ሚዲያ ቀርበው ስለኢትዮጵያ ያለውን እውነታ እንዲያደርሱ እናደርጋለን። አለፍ ሲልም መጽሔትና ጋዜጦች ላይ በመጻፍ፤ የተለያዩ ብሮሸሮችን በማዘጋጀትና ካናዳውያን እንዲያነቧቸው በማድረግ የሐሰት ወሬዎችን እንዲቃወሙ አድርገናል። ዓለም አቀፉ ጫናን ጭምር ስንመክት ነበር።
የሰላም ስምምነቱ እንዲሳካም እንዲሁ ብዙ ለፍተናል። በተለይም የካናዳ መንግሥትና ሕዝብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እንዲሰለፍ በማንቃትና ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በመሥራት፣ በሥነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑም በማስተማር፤ ስምምነቱ ከተከናወነ በኋላም ቢሆን አልተኛንም። ስለተግባራዊነቱ፣ ምን ፋይዳ እንዳለው በማሳየትም ጭምር ድጋፍ በሚያስፈልገው ሁሉ ለመተጋገዝ የሚያስችል ሥራ እያከናወንን እንገኛለን።
የህዳሴ ግድብን በተመለከተም በዓረብ ሚዲያዎች ሳይቀር በመቅረብ በባለሙያዎች ትንታኔ ስንሰጥ ነበር። የኢትዮጵያን ትክክለኛነት አስረድተናል። በተጨማሪ ከካናዳ ከተሞች ጋር የኢትዮጵያ ከተሞች ትስስር እንዲኖራቸው እየሠራን ነው። ጅማሯችንንም በደብረማርቆስ ለማድረግ ወስነናል። በዚህ ደግሞ ብዙ ካናዳውያን ደስተኛ ናቸው። ስለዚህም ዲያስፖራው በሠራው ሥራ ካናዳውያን በኢትዮጵያ ልጆች እንዲኮሩ ሆነዋል። በኢትዮጵያ መንግሥት ላይም አመኔታን ማሳደር ችለዋል። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቀበል አግዞናል። አሁንም በዚህ ሁኔታ እንቀጥላለን። ምክንያቱም ሥራችን ኢትዮጵያን የማዳን ጉዳይ እንጂ ፖለቲካ አይደለም።
ኢትዮጵያን የማሻገር ጉዳይ መቼም ቢሆን የፖለቲካ ውግንና ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። ቤተሰብም ሆነ ራስን ማኖር የሚቻለው ሀገር ስትኖር ብቻ ነው። ስለሆነም ዲያስፖራው ያንን ስለሚረዳ ፖለቲከኛ ባይሆንም በፖለቲካው ጭምር ገብቶ ትክክል ያልሆነውን ነገር ይቃወማል። ልማትን ለማረጋገጥ ድህነትን ለማጥፋት ይተጋል። ሀገሩ የነገ መኖሪያው እንድትሆን ይሠራል። ለዚያም ሲል የማይከፍለው ዋጋ የለም።
አዲስ ዘመን፡- የሰላም ሥራ የሁል ጊዜ ተግባር እንደሆነ ይታመናል። እንደ ዲያስፖራ ሰላም እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንጻር ምን ምን ሥራዎች መሠራት አለባቸው ብለው ያስባሉ፤ እንደ ሀገርስ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
አቶ ሰማነህ፡– ሰላም በአንድ አካል ሥራ የሚረጋገጥ አይደለም። ከሁሉም በኩል ቀና አስተሳሰብን ይጠይቃል። ከዚያ ባሻገር ሕዝብ ላይ አመኔታ መጣልን ይፈልጋል። ምክንያቱም በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም መልኩ ጠብን አይፈልግም። ሥራውን የሚያደናቅፍበት አካልንም አይታገሰውም። እናም እንደ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ ሕዝብ የሚለውን መስማት፣ እስከዛሬ የነበረበትን መተጋገዝ ማጎልበት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሳይሆን ለሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ግዴታ ነው። እናም ሕዝብን ተጠቅሞ ችግሮችን ለማለፍ መሞከር የመንግሥት ዋነኛ ሥራ መሆን አለበት እላለሁ።
ሕዝብ የተከፋፈለና ጸብ ፈላጊ ቢሆን ኖሮ አሁን ባለችበት ሁኔታ አገር አትቀጥልም ነበር። ምክንያቱም የዘር ፖለቲካው ሰፍቷል። ሰፈር ውስጥ የገባ ሰው ተበራክቷል። ሆኖም እንደ ማኅበረሰብ ከዚህ ይልቅ ሰላምን የመረጠ በመሆኑ የከፋ ችግር ሳይገጥመን ቀርቷል። ስለዚህ ሕዝብ የመረጠውን ሰላም ለማረጋገጥ ጥቂት ተማርን ብለው ያልተማሩ ግለሰቦችን፣ ጽንፈኛ ቡድኖችን ሀይ ማለት ያስፈልጋል። መስመራቸውን እንዲያስተካክሉ ማድረግም ይገባል። የውጪ ጣልቃ ገብነቱንም በተለያዩ ስልቶች መመከት ተገቢ ነው። አንዱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነገሮችን መፍታት ሲሆን፤ ሁለተኛው ዲያስፖራው ለአገሩ አምባሳደር ሆኖ እንዲሠራ ማበረታታት ነው።
ዲያስፖራው ጎትጓች መፈለግ የለበትም። ሌት ተቀን መረጃዎችን በማነፍነፍ ሞጋች መሆን ይገባዋል። በተለይም ዜጋ የሆኑበት አገር ላይ ተሰሚነት አላቸውና እድላቸውን መጠቀምና ለአገራቸው ዘብ መሆን አለባቸው። ከዚያ ባሻገር ላሉበት የማኅበረሰብ ክፍል ስለአገራቸው ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ ማስረዳትና መልካም እይታ እንዲኖራቸው ማድረግም ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ኃይል የሚገኘው ሕዝብን ጭምር መያዝ ሲቻል ነው። መሰማትም የሚመጣው እውነተኛ መረጃዎችን ስንይዝ ብቻ ነው።
ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ብሎ የሚሠራ ሁሉ እድሎችን አፈላልጎ የሀገሪቱን ሚዲያ በመጠቀም ስለ ኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ማስረዳት ይገባዋል። የዚያን ጊዜ ተቀባዩና ስለ ኢትዮጵያ ሰላም የሚጮኸው ብዙ ይሆናል። ተቃዋሚዎች ዋጋ ያጣሉ። መጫን የሚፈልጉ ሁሉ ቅስማቸው ይሰበራል።
ለአብነት ካናዳ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ጣልቃ ትገባለች። ምክንያቱም የአደጉት ሀገራት አጋር ነች። ስለዚህም ውሳኔ ጭምር ልታስተላልፍ ትችላለች። ይህንን ውሳኔ ማስቀየርና ማስቀየስ ኃላፊነት ያለብን እኛ ብቻ ነን። ታክስ ከፋይ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራው። ስለዚህ ይህንን እያደረግንም ነው። በየሀገሩም ይህ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስትሠሩ የሚያጋጥማችሁ ችግር አለ፤ ካለስ ምንድን ነው?
አቶ ሰማነህ፡- በዋናነት ፈተና የሆነብን የዜጎቻችን የአስተሳሰብ ክፍተት ነው። ሥራዎች ሁሉ ሲከናወኑ ፖለቲካውን ለመደገፍና ሥልጣን ለመፈለግ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህ አይደለም። ኢትዮጵያ ለእኛ መኖር ብዙ ዋጋ ከፍላለች። አስተምራን የምንፈልገውን ቦታ ሰጥታናለች። ለእርሷ ደግሞ ብዙ ያልከፈልነው እዳ አለብን። ስለዚህም የተከፈለልንን ለመክፈል እንጂ ሌላ ዓላማ ኖሮን አንሠራም። የአሁኑ ተግባራችን እዳ የመመለስ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ሰዎችም ማሰብ ያለባቸው ይህንኑና በዚሁ መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ሰላምን ለማረጋገጥ ምን አስቻይ ነገር አለ ይላሉ?
አቶ ሰማነህ፡- ብዙ ነገር ያለ ይመስለኛል። አንዱና ዋነኛው የሕዝቡ ማንነትና ለሀገሩ ያለው ፍቅር ነው። ሰላምን ከምንም በላይ አጥብቆ ይፈልጋል። መጠቀምና ወደ ልማት መቀየር ነው። እናም ሰላምን በሚያሰፍኑ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው። ሰላምን ያረጋግጣሉ ተብለው የሚታመንባቸው ተቋማት ከመቼውም በላይ ሊሠሩ ያስፈልጋል። ለአብነት ከጸጥታ አካሉ ባሻገር የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም መስፈኑ መታገል አለባቸው።
በሙያዬ አግሪካልቸራል ኢኮኖሚስት ነኝ። እናም ከኢኮኖሚው አንጻር ስመጣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ተናገር ብባል፣ ጥናት ባላደርግም፣ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በቻይና ማኦ ከሞተ በኋላ የነበረው የኢኮኖሚው ሞቅታ በዚህ መልኩ የቀጠለ ነው። እኛም ይህንን ያህል ጦርነት አካሂደን ኢኮኖሚያችን እንደጨመረ የሚያስረዱ ነገሮች አሉ። በ2023 የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረትም ኢትዮጵያ ከኬንያ የሚበልጥ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘገብ አስቀምጧል። ይህንንም “13 በመቶ” ሲል ነው የገለፀው። እናም ሰላሙ ተጠብቆለት ሕዝቡ መሥራት ቢችል ምን ያህል ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል እረዳለሁ። እናም አስቻዩ ነገር ሕዝቡና የመሥራት አቅሙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ዋነኛ ፈተና ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ሰማነህ፡– ትልቁ የኢትዮጵያ ፈተና ድህነት ነው። ለዚህ ደግሞ መሠረታዊ ችግሩ ወጣቱን በሥራ ማሰማራት አለመቻሉ ነው። አምራች ኃይሉ ቁጭ ብሎ የሰው እጅ ይጠብቃል። ከአጣ ደግሞ ተቃዋሚ ይሆናል። ስለዚህም የሥራ እድል ሊፈጥር የሚችል ቴክኖሎጂን ማምጣት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በጊዜ ማጠናቀቅና ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በደብረማርቆስ የተከፈተው የዘይት ፋብሪካ ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠር ቢችልም፤ በአቅራቢያው ግባት የሚያቀርቡ ገበሬዎች ቢኖሩም ሥራው በመቆሙ ምክንያት ዜጋው የሚሠራበት እንዲያጣ ሆኗል። ስለዚህ እንደነዚህ አይነት ተግዳሮቶችን መንግሥት በመነጋገር መፍታት ይኖርበታል።
በመምራትና የተሻለ ነገርን በመፍጠር ልዩ የሆኑ ተቋማት አሉን። አየር መንገድና ቴሌ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት በዚያ ልክ ሠርተው እንዲለውጡ ማድረግ ከምንም በላይ ያስፈልጋል። መንግሥት ይህንንና መሰል የመፍትሔ ሀሳቦችን አምጥቶ መሥራት ከቻለ ድህነት ታሪክ መሆኑ አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- የኅብረተሰቡን ንቃተ ሕሊና እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ሰማነህ፡- እኔ ብቻ ሳልሆን ልጄ ጭምር የተመለሰችው ተገርማ ነው ። በተለይ ወጣቱ ያለውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጅግ አድንቃለች። ለልማት ማዋል ላይ ግን ብዙ ይቀራል የሚል እምነት አለን። ይህንን ደግሞ በአሠራር መፍታትና ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ወጣቱ የሥራ እድሉ የሰፋ ስላልሆነ እንደ ውጪው ሁሉ ማንኛውንም ሥራ ሠርቶ ኑሮውን ለማሸነፍ ይሞክራል። ወጣቱ ነቃ ማለት ደግሞ ሕዝቡ ተለወጠ ማለት ነው። ሥራ ሳይፈታ የተገኘውን ሁሉ ሲያደርግም አገሩን ያነቃል። ስለሆነም መንግሥት ይህንን አስቦ መሥራት ይገባዋል። ከዚያ ባሻገር ሕዝቡ ያማረረውን የታክስ
አከፋፈል ሥርዓት ማስተካከል ግድ ነው። ምክንያቱም የበለጠ መክፈል የሚችለው የበለጠ ሠርቶ ተገቢውን ክፍያ ሲጠየቅ ነው። ለዚህም ካናዳ የተሻለ ተሞክሮ አላትና ድጋፍ ማድረግ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- የተማረው ኃይል ከፖለቲካው አስተሳሰብ አንጻር የሚጠበቅበትን አድርጓል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሰማነህ፡– ሁል ጊዜ የሚያሳስበኝ ጉዳይ ቢኖር ይህ ነው። ኢትዮጵያን መጥቀምና ከፍ ማድረግ ሲኖርበት ባልተገባ የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ የገባው ምሑር ቀላል አይደለም። ኢትዮጵያን ችግር ውስጥ የከተታትም ይህ አስተሳሰቡ ነው። ማሠራት ሲችል ኅብረተሰቡን መስመር ያስታል። ስለዚህም ይህ ኃይል የሚጠበቅበትን ሳይሆን የማይጠበቅበትን እየሠራ ነው የሚል አመለካከት አለኝ። ሕዝቡ የነበረውን አብሮነት ይዞ እንዲቀጠል እንኳን አላደረገውም። በቀይ ሽብር ከ66ቱ አብዮት ጀምሮ ሲፈትነን የቆየ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አሁን ደግሞ ነገሩን ቀይሮ በዘር ማዕቀፍ ውስጥ ሕዝቡን አስገብቶታል። ተሰሚነቱን ተጠቅሞ ሰፈርተኛ እንዲሆንም እያደረገው ይገኛል። ለዚህም ማሳያው እነርሱ ያልደረሱባቸው ቦታዎች ላይ ቢኬድ አሁንም ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ ነው። የዘር ቆጠራ የሚባለውን አያውቀውም። ሁሌ ለሥራው ደፋ ቀና ሲል ነው የሚታየው። እናም እንደ ሀገር የምሑራኑ ሚና ታይቷል ለማለት እቸገራለሁ። ለአብነት ከሀገር ውጪም ይህ አስተሳሰብ ሲንጸባረቅ ተመልክቻለሁ።
ሰሜን አሜሪካ ውስጥ “ፒፕል ቱ ፒፕል” የሚባልና 257 ምሑራንን ያቀፈ ስብስብ አለን። ከፍተኛ ውይይት የምናደርግበት ነው። በተለይም ስለ ሀገራችን ጉዳይ። 245ቱ በተለያየ መስክ ዶክተሮች ናቸው። እናም ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶች የሚያነሱት ሀሳብ እጅግ ያሳፍራል። በቅርቡ በነበረን የቪዲዮ ውይይት ላይ አንዱ ተነስቶ “ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን ያለበት እንግሊዝኛ ነው” ሲል ተደምጧል። ብዙዎችንም ያናደደም ነበር። ለዚህ አቋሙ ምክንያት አማርኛ ነው። እርሱን ጠላ ቢባል እንኳን ሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች እንዳሉ ግን አልታሰበውም። እናም ይህ ነገር መገራት እንዳለበት ይሰማኛል።
የተማረው በአስተሳሰብ ጭምር የተሻለ ካልሆነ ብዙ ነገሮችን ያጠፋል። ይህ ማለት ግን ለሀገር ለውጥ እውቀታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን የሚሰጡ የሉም ማለት አይደለም። በሙያቸው ብቻ የሚከራከሩና ሀሳቦችን የሚያስቀይሩ ብዙ ናቸው። ነገር ግን ምን ያህል ሰው ይከተላቸዋል፤ ይጠቀምባቸዋልስ ከተባለ መልሱ “ጥቂት” የሚል ነው የሚሆነው። ስለዚህ ጽንፍ የያዘ አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን ተሐድሶ እንዲወስድ ማድረግ ያስፈልጋል። ከእውቀት ውጪ እንዳይከራከር ማድረጉ ላይም መሥራት ይኖርብናል። ምክንያቱም ያወቀ ሰው ሕዝብን ድህነት ውስጥ የሚከት ሥራን አይሠራም። ለሕዝብ ዋጋ ያለውን ሰላም አያናውጥም። እናም በጉዳዩ ላይ መንግሥትና ምሑራኑ ተቀራርበው መሥራት አለባቸው።
ባለፉት ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳደረጉት ውይይቶች ዓይነት ያስፈልጋሉ። ሁለቱም መደማመጥ ይኖርባቸዋል። ጠያቂና መላሽ አይነት አካሂድ ሳይሆን በመንግሥት በኩል መመለስ ያለባቸው ነገሮች በየደረጃው መፈታትና ምሑራንም የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ውይይቶች ለቴሌቪዥን ፍጆታ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ወርደው ለሕዝብ ጥቅም በሚውሉበት መንገድ መቃኘት አለባቸውም።
አዲስ ዘመን፡- የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን ሥራ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሰማነህ፡- ሀገር ከምክክርና ውይይት ውጪ የሚታደጋት ምንም ነገር አይኖርም። ምክንያቱም በመቀራረብና በመወያየት ችግሮች በሙሉ መፍትሔ ያገኛሉ። ምክንያታዊ ሀሳቦች ከምንጩ ይፈልቃሉ። ወደ አንድ አስተሳሰብ መምጣትም ይቻላል። አንድ መሆን ባለመቻላችን የትናንቱን፣ የአባቶቻችንን ብርቅዬ ገድሎች መፈጸም አልቻልንም። እናም ይህ ኮሚሽን ይህንን የሚፈጥር ሥራ ይሠራል ብዬ አስባለሁ። በተለይም ከሰፈርተኝነት አስተሳሰብ ያላቅቃል ብዬ አምናለሁ።
በኮሚሽኑ በኩል በሚደረግ ምክክር አንድነት ይጠነክራል፤ አዳዲስ ሀሳቦች ይመነጫሉ፤ ዝምድና ይዳብራል፤ አለመረዳቶች በእውቀት ይቀየራሉ። ቁስሎችና ቅሬታዎች ገሀድ ስለሚወጡ ይታከማሉ። ይህ ማለት ደግሞ ጫና ፈጣሪዎች ጥጋቸውን ይይዛሉ። አጣልተው ገንዘብ የሚሰበስቡም ቦታቸውን ይቀይራሉ። ምክንያቱም አስተሳሰቦች ሁሉ ልማትና እድገት ላይ ይሆናሉ። ሀገርም ያሰበችው የብልጽግና ደረጃ ላይ ትደርሳለች። በሰላም የሚፈቱ ነገሮች ስለሚበራከቱ መገፋፋትና ግጭቶች ይቆማሉ። እድገት መሪ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
አቶ ሰማነህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም