የሰላም መገኛዋ መንገድ ሰላማዊ ተግባቦት ብቻ ነው። ከሰላማዊ ተግባቦት ውጪ ሰላም ሊያመጣ የሚችል ሃይል በምድር ላይ የለም። ሰላማዊ ተግባቦት አገርና ሕዝብን አስቀድሞ ፖለቲካዊ መሻትን ያስከተለ ነው። ሰላማዊ ተግባቦት ሁሉም ሰው የተለየ እና ልዩ ልዩ ሃሳብና ፍላጎት እንዳለው በመረዳት ያን ብዙ አይነት ሃሳብ ወደ ጠቃሚ አንድ ሃሳብ መቀየር ነው።
ሰላማዊ ተግባቦት የራስን ፍላጎት ወደ ጎን ብሎ የብዙሃኑን ፍላጎት ማስቀደም ነው። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ሰላም ሊመጣ አይችልም። የሰላም መገኛዎችን ዘግቶ ሰላም ለማምጣት መሞከር መገለጫችን ሆኖ ለዘመናት ዘልቀናል። ሰላም ሊሰጡንና ሊያግባቡን የሚችሉ ብዙ የጋራ ትውፊቶቻችንን ችላ ብለን በሚለያዩን ጥቂት ነገሮች ላይ ጊዜ ስናጠፋ ከርመናል።
ይሄ ሁሉ አካሄድ የምንፈልጋትን አገር አልፈጠረልንም። አሁን አቅጣጫችንን መቀየር አለብን .. ባልሄድንባቸው መንገዶች መሄድ፣ ባልተመለከትነው አቅጣጫ መመልከት ይኖርብናል። ብዙዎች የሰላምን መገኛ መንገድ ሳያውቁ ሰላም ለማምጣት ብዙ ለፍተዋል። ሰላም አንድ ቦታ ነው ያለው እርሱን በመነጋገር ውስጥ ነው። መነጋገር ስንል መግባባት ያለበትን መነጋገር ነው።
ዓለም ሁሌም በመነጋገር ውስጥ ናት ፤ሁሉም መነጋገሮች ግን ሰላም ሲያመጡላት አይታይም። ይሄ የሆነው ደግሞ በራስ ወዳድነትና የአንድ ወገንን የበላይነት በማሳየት ነው። የአንድ ወገን የበላይነት በሚንጸባረቅነት ሁኔታ ላይ ሰላም የለም። ሰላም የእኩል ሃሳብ፣ የእኩል ተግባር ነጸብራቅ ነው።
አገራችን ለምን ሰላም ራቃት ብለን ስንጠይቅ ይሄን እውነት ነው የምናገኘው። እኛ አገር ሁሉም ነገር በእኩልነት ላይ ሲንጸባረቅ አይታይም። ፖለቲካችንን ብናየው የእኔነትና የራስ ወዳድነት እድፍ ያቆሸሸው ነው። የአንድ ቡድን የበላይነት የሚንጸባረቅበት ነው። ይሄ ግለኝነት ደግሞ መጨረሻው ጦርነት ነው። እንደ አገር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እኩል ሃሳብና እኩል ተግባር ያሻናል።
ከኖርንበት የጦርነት ልማድ ወጥተን መነጋገርን መሰረት ያደረገ አዲስ አብዮት ያስፈልገናል። ከነበርንበት የቂመኝነት አካሂድ ወጥተን እርቅን ያስቀደመ አዲስ አስተሳሰብ መላበስ ያስፈልገናል። አገራችን አሁን የሰላም አብዮት ነው የሚያስፈልጋት። የአንድነት፣ የመቻቻል አብዮት ነው የሚያስፈልጋት። ይሄን አዲስና ለዘመኑ የሚመጥን አካሄድ ነው መለማመድ ያለብን።
ለመነጋገር ከተሰናዳን ከጦርነት የሚሻሉ ብዙ ነገሮች አሉን። አገራችን በብዙ ነገር ላይ ኋላ ቀር ናት። ጦርነትና አለመግባባት ሲጨመርበት ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል። በየትኛውም መስፈርት እንየው ለአገራችን ጦርነት ሳይሆን ሰላም ነው የሚያስፈልጋት። ለሕዝባችን መለያየት ሳይሆን አንድነት ነው የሚያስፈልገው።
የተጀመረው ሰላም እንዲቀጥል፣ ቀጥሎም አስተማማኝ እንዲሆን ከትናንቱ የተለየ አዲስ ማንነት ያስፈልገናል። በዚህ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ፖለቲካ፣ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ካልሆነ አዲስና ሰላማዊ አገር መፍጠር አይቻለንም።
እውነተኛ ሰላም ተነጋግሮ በመግባባት ውስጥ ነው የሚገኘው። ሰው ተነጋግሮ መግባባት ካልቻለ አገር ሊለውጥ የሚችል እውቀትም ሞራልም እንደሌለው ነው የማምነው። ጥበብ ማለት.. እውቀት ማለት በብዙሃነት ውስጥ አንድ አገርና አንድ ሕዝብ መፍጠር ነው። ምርጥ ፖለቲከኛ ምርጥ ተናጋሪ ሳይሆን ምርጥ አሳቢ ነው።
ምርጥ ሃሳቦቻችን ናቸው ምርጥ ሀገር የሚፈጥሩልን። ምርጥ ሃሳቦቻችን ናቸው በብዙ ተቃርኖ፣ በብዙ የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ለአገር የሚበጅ እውነት የሚሰጡን። ምርጥ ሃሳቦቻችን ናቸው ከኋላቀርነትና ከዝግምና የሚያወጡን። ተነጋግሮ መግባባት ያልቻልነው ለአገር የሚበጅ፣ አገርን ያስቀደመ፣ ከእኔነት የወጣ ምርጥ ሃሳብ ስለሌለን ነው።
ምርጥ ሃሳብ ሁልጊዜም ማረፊያው አገርና ሕዝብ ነው። በቀሪ ጊዜአችን በምርጥ ሃሳብ ምርጥ አገር መፍጠር አለብን። በምርጥ ሃሳብ ምርጥ አገር ካልፈጠርን በብላሽ ሃሳብ ብላሽ ሀገር ፈጥረን ተበላሽተን ነው የምንቀረው። ይሄ ደግሞ ለማናችንም አይበጅም.. በእርቅና በተግባቦት ወደ ሰላም መሄዱ ነው። ለሁላችንም እኩል ዋጋ ያለው።
አገራችን ሃሳብ አላጣችም.. እንደ ሕዝብ ቁጥሯ፣ እንደ ወጣቷ ብዛት ለአገር የሚሆን ብዙ ሃሳብ አለን። ችግር የሆነብን የሃሳብ ልዩነቶቻችንን ወደአንድነት ማምጣቱ ላይ ነው። ችግር የሆነብን ልዩ ልዩ ሃሳቦቻችንን እንዴት በሰላማዊ መንገድ ለሰላማዊ ነገር መጠቀም እንዳለብን አለማወቃችን ነው።
በአግባቡ መጠቀም ከቻልን የተለያዩ ሃሳቦች በአንድ አገር ላይ ልማትም፣ ብልጽግናም ናቸው። በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ደግሞ ነውጥና ጦርነትን ነው የሚያስከትሉብን። አሁን የሚጠቅመን የሃሳብ ብዙሃነታችንን በሰላማዊ መንገድ ለልማት መጠቀም ነው። ያለፉ የጦርነት ታሪኮቻችን የሃሳብ ብዙሃነትን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ካለማወቅ የመጣ ነው።
አንድ ሰው አንድ ሃሳብ ሲኖረው፣ አንድ ፖለቲከኛ ከሌላው ፖለቲከኛ አዲስ ሃሳብ ሲኖረው በራሳቸው መንገድ ሁሉም ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ማወቅ አለብን። የትኛውም የሃሳብ ልዩነት ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት ጠቃሚ ነው።
የሃሳብ ልዩነቶቻችን ኢትዮጵያን እንዲጠቅሙ እንጂ እንዲጎዱ መፍቀድ የለብንም። የፖለቲካ ልዩነታችን አገር እንዲቀይሩ ሕዝብ እንዲያሻግሩ እንጂ ለጦርነትና ለጉስቁልና እንዲዳርጉን መፍቀድ የለብንም። ይሄ ብላሽ አካሄድ ነው የሃሳብ ልዩነትን በአግባቡ እንዳንጠቀም እክል እየፈጠረብን ያለው።
አገርና ሕዝብን ያስቀደመ ፖለቲካና ፖለቲከኛ በሃሳብ ልዩነት አገር ይሰራል እንጂ ጦርነት አይፈጥርም። ከእኛ በፊት ኢትዮጵያ መቅደም አለባት። ከእኛ በፊት ሕዝብ መቅደም አለበት። ከሥልጣናችን በፊት፣ ከግል ጉዳያችን በፊት ትውልድ ይቅደም። ከአገር በፊት የግል ጉዳያችንን ማስቀደማችን ነው ዛሬ ላይ ለጦርነት እየዳረገን ያለው። ኢትዮጵያን እስካላስቀደምን ድረስ የምንፈልገውን ሰላም ማምጣት አንችልም። ኢትዮጵያን እስካላስቀደምን ድረስ አሁንም ቢሆን ተነጋግሮ ሰላም ማምጣት ይቸግረናል።
ሀገር በአንድ አይነት ሃሳብ አትገነባም። ለሀገር ግንባታ አሁን ላይ እዚም እዛም የምንሰማም ልዩ ልዩ ሃሳብ ያስፈልገናል። ልዩ ልዩ ሃሳቦቻችን ብልሃትን፣ ስኬትን፣ ተስፋን፣ እውቀትን፣ ልምድን ያነገቡ ናቸው። በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ዘርግተን እንወያይባቸው እንጂ የአንተ ሃሳብ ከእኔ ሃሳብ አይገጥምምና ስንል ወደመለያየት መግባት አይኖርብንም።
ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት። የተለያዩ መልኮች፣ የተለያዩ ባህሎች፣ የተለያዩ ወግና ሥርዓቶች ያቆነጇች ናት። ይቺ አገር እንዴት ሆኖ በአንድ አይነት ሃሳብ ብቻ ትቀጥላለች? ኢትዮጵያ ብዙ ናት.. ብዙ ሃሳብ፣ ብዙ እይታ ያስፈልጋታል። የሃሳብ ልዩነቶቻችን ወደጦርነት እንዳይወስዱን ተነጋግሮ መግባባትን መልመድ አለብን።
ተቻችሎ በጋራ መቆምን ባህል ማድረግ አለብን። የመጣው ሰላም በሁላችንም ልብ ላይ ተስፋን ለኩሷል። ሳቅ አድርጎልናል። እንደሳቅን እንድንቀጥል ሰላማችን እክል ሳይገጥመው መዝለቅ አለበት። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ሰላም በሚያመጡ ነገሮች ላይ ብቻ እናተኩር።
ጦርነት በቃን.. ይሄ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ድምጽ ነው። በወንድማማች መካከል ፍቅር እንጂ መለያየት ዋጋ የለውም። ሲገሉንና ስንገልባቸው የነበሩ ሾተሎቻችን ወደ ሰገባቸው ይመለሱ። ሲያደሙንና ሲያጎሳቁሉን የነበሩ ጎራዴዎቻችን ወደ አፎታቸው ይመለሱ።
ፍቅር ነው የሚያስፈልገን.. ወንድማማችነት ነው የቀረን። ብዙ ነገሮችን ሞክረናል.. አሁን የሚቀረን ሰላምና እርቅ ነው። አሁን የሚቀረን ተነጋግሮ መግባባት፣ ተግባብቶ ሰላማዊ አገር መፍጠር ነው። ጦርነት የፈጠሩ ሃሳቦቻችንን ሰላም እንዲፈጥሩ እድል እንስጣቸው። መለያየትን የፈጠሩ ሃሳቦቻችንን አንድነትና ወንድማማችነትን እንዲያጸኑ እናስገድዳቸው።
ኢትዮጵያ ቀፏችን ናት.. ማር እንድትይዝ አርቀን የሰቀልናት ቀፏችን። ማር አበባ በሌለበት.. ምንድነው? ማር ንብ በሌለበት ምንድ ነው? አገራችን ማር እንድትይዝ ማር ሊሰጧት የሚችሉ ነገሮች ያስፈልጓታል። ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው። አበባ በሌለበት ማር እንደሌለ ሁሉ ሰላም በሌለበትም አገር ምንም ናት።
አገራችን ማር እንድትይዝ፣ ህዝባችን ከማሩ እንዲበላ ማር የሚሰራ ሰላም ያስፈልገናል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ድካማችን ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው። አንድን ነገር ስንፈልግ ያ ነገር የሚያስፈልገውን ግብዓት አሟልተን ነው መሆን ያለበት። አሁን ላይ አገራችን ከሰላም ውጪ ምንም አያስፈልጋትም።
የአገራችን ሰላም ደግሞ ከሰማይ የሚወርድ ሳይሆን በእኛ በልጆቿ የሚፈጠር ነው። በመግባባት፣ በውይይት የሚመጣ ነው። ፖለቲካውን በማስተካከል፣ የሃሳብ ልዩነቶችን ወደተግባቦት በመቀየር የሚመጣ ነው።
ዓለም እንደ ሰላም የክብር አክሊል የላትም። ሁሌም ጸጋዎች፣ ሁሉም ክብሮች ከሰላም ቀጥለው የሚመጡ ናቸው። ብዙ ነገር እያለን ምንም እንደሌለው የሆነው ከሁሉም ትልቁ ሰላም ስለጎደለን ነው። በሰላም ካልሆነ በምንም አንሞላም፣ በምንም አንትረፈረፍም። በሰላም መንገድ ከተጓዝን ብቻ ነው የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት የምንችለው። በምክክር መኖር ስንችል ብቻ ነው ለኢትዮጵያ የምንበጀው።
እንደ አገር በሰላማዊ ሃሳብ የቆመች ሰላማዊ አገር ታስፈልገናለች። ድልድይ እንሁን.. ማንም ወጥቶ የሚገባበት ድልድይ። በሰላም ሃሳብ የተገነባ ድልድይ። ከዚህ ወደ እዛ መሻገሪያ ድልድይ ያስፈልገናል። የጥል ግድግዳዎችን አፍርሰን፣ የመለያየት ግንቦችን ደርምሰን አዲስ ምስራቅ ማየት አለብን።
አዲስ ጸሀይ፣ አዲስ ጀምበር መሞቅ አለብን። ወደ ጦርነት የሚወስዱ መንገዶችን እየዘጋን የእርቅና የምክክር መንገዶችን መክፈት አለብን። የመለያየት መንገዶችን እየዘጋን የአንድነትና የወንድማማች መንገዶችን መስራት አለብን። ተስፈኛዋ ኢትዮጵያ በዚህ እውነት ውስጥ ብቻ ነው የምትፈጠረው።
አገር ሰው ከሌለባት ምንም ናት። ሰው አገር ከሌለው ምንም ነው። አገርና ሰው፣ ሰውና አገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። ሰው በአገር .. አገር በሰው ነው የሚከበሩት። አገር በሰላም ካልሆነ በምንም አትቆምም። ሰው በሰላም ካልሆነ በምንም አያምርም። ሰላም ስናጣ፣ አንድነት ሲርቀን የአገራችንን መሰረት እየነቀነቅን ነው።
ተነጋግሮ መግባባት ሲያቅተን፣ ተቻችሎ መኖር ሲከዳን የአገራችንን መሰረት እየገፋን ነው። በእኛ ሰላም ማጣት ከእኛ ውጪ የሚጎዳ ማንም የለም። ሰላም ባጣንባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም አይነት መከራ አይተናል። አሁን ስለሰላም የምንጮህበት ጊዜ ነው.. አሁን የመጣው ሰላም እንዲቀጥል የምንታገልበት ጊዜ ነው።
ኢትዮጵያን እንስራ። ብዙ ሆና ያነሰችውን፣ እልፍ ሆና የጎደለችውን ሀገራችንን እንታደግ። ሰው ሳታጣ ሰው ያጣችውን፣ ሃሳብ ሳታጣ ሃሳብ ያጣችውን አገራችንን እንማግር። ታሪክ ሞልቷት ታሪክ ያጣችውን አገራችንን እናድስ። በሰላሙ ዋዜማ ጥላቻ የሞላቸው አሮጌ አቆማዳዎቻችን በአዲስ እንተካ ።
የፖለቲካ እድፍ ያቆሸሻቸው ትርክቶች በምክንያታዊ ሃሳቦች መሞላት አለባቸው። ከእንግዲህ ጭንቅላቶቻችን የመፍትሄ ሃሳብ እንጂ የጦርነት ሃሳብ ማማጣቸው ይበቃል። ከእንግዲህ ልቦቻችን የይቅርታና የፍቅር ቦታ እንጂ የመለያየት ቦታ መሆናቸው ያበቃል። ከእንግዲህ ጀርባዎቻችን በጥላቻ መጉበጥ የለባቸውም።
ከእንግዲህ ፖለቲከኞቻችን የእርቅ ሃሳብ እንጂ በመለያየት ሃሳብ ጊዜ ማጥፋት የለባቸውም። ከእንግዲህ በሚያግባቡንና በሚያስተቃቅፉን የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እንምከር። ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ እንሳተፍ። በሰላማዊ ተግባቦት ዝቅ ያለችውን አገራችንን ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። በአገራዊ ምክክር አዲስና ነባር ችግሮቻችንን እየቀረፍን ሰንኮፏን የጣለች ኢትዮጵያን እንውለድ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም