
ኢትዮጵያ የወጣት ምድር ናት። በዚህ ላይ የበለፀገ የግብርና ጸጋ ያደላት፣ፈጣን የከተሞች መስፋፋት እና እድገት የሚታይባት እንዲሁም የዲጂታል መሠረተ ልማቷ በፍጥነት እየለማ ስለሆነ ለጀማሪ ፈጠራዎች ወይም ስታርትአፖች አልያም ለቢዝነስ ሥራ ጀማሪዎች ምቹ ወይም ለም አፈር ናት። ከአፍ የወደቀ የፈጠራ ሃሳብ ሳይቀር የምታበቅል ሀገር ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከኡበር አፍ የወደቀ የሜትር ታክሲዎችን እዚህ ላይ ልብ ይሏል። በዚህ መጣጥፍ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚንሰላሰሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ግን ደግሞ ማህበራዊ ተፅዕኗቸው የጎላ በሴክተር ላይ የተመሠረቱ ለጀማሪዎች ሃሳቦችን አቀብላለሁ።
- አግሪቴክ (ግብርና + ቴክኖሎጂ)፦ ለገበሬዎች እንደ ኤስኤምኤስ/አይቪአር ያሉ የሞባይል ፕላት ፎርሞች ወይም መድረኮችን በመጠቀም የምክር አገልግሎት መስጠት። ያው SMS አጭር የጹሑፍ መልእክትን በመጠቀም ሲሆን IVR ወይም በይነተገናኝ የድምፅ ምላሽ ማለት ነው። ደዋዮች ከኮምፒዩተር ሲስተም ጋር በድምጽ ወይም በቁልፍ ፓድ ግብዓቶች እንዲያገኙ የሚያስችላቸው አውቶሜትድ የስልኮ ሲስተም ቴክኖሎጂ ሲሆን በመረጡት ምርጫ መሠረት አማራጮችን በማቅረብ እና ጥሪዎችን ማስተላለፍ ያስችላል። በመሠረቱ ይህ ፕላትፎርም ለእያንዳንዱ መስተጋብር የቀጥታ ወኪል ሳይጠይቁ ንግዶችንና እና ጥሪዎችን ያሳልጣል።
እንዲሁም ገበሬዎችን በቀጥታ ከሸማቾች ጋር የሚያገናኙ ዲጂታል የመገበያያ ፕላት ፎርሞችን በመፍጠር አምራቹንም ሆነ ሸማቹን ከቀማኛ ደላላ መታደግና ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። ይህ ቴክኖሎጂ እያለ ነው ደላላ ከማሳ እስከ አዲስ አበባ ተሰግስጎ አምራቹንም ሸማቹንም የሚገፈው። ሌላው በፀሐይ የሚሠራ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘመናዊ የመስኖ ዘዴዎችን ለገበሬው በማስተዋወቅ ራስንም ሀገርንም መጥቀም ይቻላል። የአፈር ምርመራ አገልግሎትን በተንቀሳቃሽ የአፈር ላብራቶሪ መስጠት፤ ሊበላሹ ለሚችሉ የግብርና ምርቶች የቀዝቃዛ ሰንሰለት ሎጂስቲክስ መስጠት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
- ዲጂታል አገልግሎቶች እና መድረኮች፦ የሞባይል ገንዘብን ከኢ-ኮሜርስ መድረኮች ጋር በማዋሀድ አገልግሎት የሚሰጥ ሥራ መጀመር ይቻላል። ሌላው የጊግ ኢኮኖሚ ወይም ከቋሚ ሥራዎች በተቃራኒ የአጭር ጊዜ ኮንትራቶችን ወይም የፍሪላንስ ሥራዎችን ለማስፋፋት የሚያግዙ መድረኮችን የሚያመቻቹ መተግበሪያዎችን ወደ ሥራ በማስገባት ቢዝነስ መጀመር ይቻላል።
- ፊንቴክ እና አካታች የፋይናንስ መድረክ፦ የቁጠባና የብድር አገልግሎት የሚሰጡ እንደ “ዕቁብ” ያሉ አካታች መድረኮችን በመፍጠር ወደ ሥራ ማስገባት፤ ከትውልደ ኢትዮጵያውያንና ከኢትዮጵያውን ወደ ሀገር ቤት የሚላኩ ገንዘቦችን ወይም ሬሚታንሶችን በአነስተኛ ክፍያ የሚያስተላልፉ፤ሀገር በቀል የርዳታና የገንዘብ ማሰባሰቢያ እንደ ጎ ፈንድሚ አይነት ፕላት ፎርሞችን ይዞ ወደ ሥራ መግባት ይቻላል። ለጀማሪዎች የሚሆኑ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሃሳቦች ቢኖርም በዚህ ላብቃና ይሄን ዘርፍ በእጅጉ ወደሚያበረታታው ይበል ወደሚያሰኘው ረቂቅ አዋጅ ልለፍ። አዎ እንደ “የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ” መስራቿና ባለቤቷ ሳምራዊት ፍቅሩ ላሉ እልፍ አእላፍ አዲስ የቢዝነስ ጀማሪዎች ተስፋ ወዳሰነቀው ዘመነኛ የዘርፉ መደላድል እንለፍ።
አዲስ ሥራ ጀማሪዎች በመንግሥት በጀት መሥራት የሚችሉበት ድንጋጌን የያዘ ዘመኑንና ትውልዱን የዋጀ ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለፓርላማ ቀርቧል። እንደ የአማርኛው የሪፖርተር ዘገባ፤ በመጀመሪያ የዕድገት ደረጃዎች ላይ ያሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስያሜ የሚሰጣቸውን ስታርትአፖችን (የቢዝነስ ሥራ ጀማሪዎች)፣ ወደ ሥራ ማስገቢያነት የሚውል ፕሮግራም ለማስጀመር የሚያስፈልግ ገንዘብ በመንግሥት በጀት መሸፈን የሚያስችል ድንጋጌን የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ለውይይት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 2320/2017 ሆኖ ለዝርዝር ዕይታ ለሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ የተመራው ‹‹የስታርትአፖች›› ረቂቅ አዋጅ፣ በተለይ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ረቂቅ አዋጁ በመጀመሪያ የዕድገት ደረጃዎች ላይ ያሉ ስያሜ የተሰጣቸውን ስታርታፖች ወደ ሥራ ማስገቢያ ከልማትና ከንግድ ሥራ ሒደት ጋር የሚያያዙ ወጪዎችን ለመሸፈን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቀርብ ገንዘብ (ግራንት) ያቋቋመ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚተዳደር እንደሚሆንም ይጠቅሳል።
ረቂቅ አዋጁ ስታርታፕ (የቢዝነስ ሥራ ጀማሪዎች) ሲል ዕውቅና የሚሰጣቸው ምንም የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ታሪክ ሳይኖረው ወይም የተወሰነ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ታሪክ ብቻ ኖሮት ኢኖቬሽንን ተግባራዊ የሚያደርግ፣ ቴክኖሎጂ ወይም በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ተመንዳጊና የገበያ መዋቅር የሚለውጥ ምርትን፣ አገልግሎትን ወይም ሒደትን በማስተዋወቅ፣ በመፍጠር፣ በማበልፀግ፣ ትራንስፕላንት በማድረግ፣ ወይም በምልስ ምሕንድስና አማካይነት ኢኮኖሚያዊ እሴትን በመፍጠር ላይ የተሰማራ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ድርጅት ወይም ጥምረትን ነው።
ስያሜ ለተሰጣቸው ስታርትአፖች ከሚሰጡ ማትጊያዎች መካከል አንዱ ሆኖ የቀረበው ‹‹የስታርትአፕ ግራንት ፕሮግራም›› ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገው በጀትም በመንግሥት እንደሚሸፈን፣ ገንዘቡም ከልማት አጋሮች የሚገኝ ድጋፍና የገንዘብ ሚኒስቴር የግራንቱ አካል እንዲሆን ከሚያፀድቀው ማንኛውም ሌሎች ምንጮች ሊገኝ እንደሚችልም ተገልጿል።
በተያያዘም የገንዘብ ሚኒስቴር የግራንቱን አመራር፣ አስተዳደርና አሠራር የሚመለከት መመርያ እንደሚያወጣም ተጠቅሷል። የሚሰጠው ግራንት ዓላማዎችም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በሚያወጣው መመርያ መሠረት በመጀመርያ የዕድገት ደረጃዎች ላይ ያሉ ስያሜ ለተሰጣቸው፣ ስታርትአፕ ስያሜ ለተሰጠበት ምርት ወይም አገልግሎት የምርምር ሥራ ወደ ሥራ ማስገቢያ፣ ከልማትና ከንግድ ሥራ ሒደት ጋር የሚያያዙ ወጪዎችን ለመሸፈን ጥቅም ላይ መዋል እንደሚገባውም ተደንግጓል።
ገንዘቡን የሚያገኘው ስታርትአፕ ስያሜ ከተሰጠው የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የግል ወጪዎች፣ በግራንቱ ማመልከቻ ላይ ያልተጠቀሱ የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ የግል ወይም የድርጅት ዕዳዎችን መልሶ ለመክፈል፣ ስያሜው ከተሰጠበት ዓላማ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ስያሜ ከተሰጠው ስታርትአፕ ምሥረታ፣ ትግበራ፣ ልማትና የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ጋር የማይገናኝ የሪል ስቴት ወይም የሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግዥዎች ላይ ማዋል የተከለከለ መሆኑም ተገልጿል።
ከእነዚህ በተጨማሪም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ወደፊት በሚያወጣው መመርያ ሊካተቱ የሚችሉ ሌሎች ክልከላዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ረቂቁ ይጠቁማል። ስያሜ ለተሰጠው ስታርትአፕ የሚሰጠው ዝቅተኛና ከፍተኛ የግራንት ገንዘብ መጠን በረቂቅ አዋጁ የተቀመጡትን ለታለሙለት ዓላማዎችና የገንዘብ ሚኒስቴር የግራንቱን አስተዳደር በሚመለከት የሚያወጣውን መመርያ ከግምት በማስገባት፣ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደሚወሰን ተገልጿል።
ግራንት የተቀበለ ስያሜ ያለው ስታርትአፕ ለአንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ለሌላ ግራንት ማመልከቻ ማቅረብ እንደማይችል የተደነገገ ሲሆን፣ ስያሜ ያለው ስታርትአፕ ውስጥ 25 በመቶ ወይም ከዚያ የሚበልጥ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸውና በሌላ ስያሜ ያለው ስታርትአፕ በኩል ግራንት ያገኙ ግለሰብ መሥራቾች ወይም የጋራ መሥራቾች ለአንድ ዓመት ለሚቆይ ጊዜ ለሌላ ግራንት ማመልከቻ ማቅረብ እንደማይችሉም ተጠቅሷል። ይሁንና እነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ግራንት የተሰጠው ስታርትአፕ ሒሳብ በሕግ ከተጣራ እነዚህ ገደቦች ተፈጻሚ እንደማይሆኑም ረቂቁ ያብራራል።
የግራንቱ ተጠቃሚዎችና ግራንቱን የሚያከፋፍሉ ስያሜ ያላቸው ‹የስታርትአፕ ምህዳር ገንቢ› ማለትም ለስታርትአፕ ምሥረታ፣ ልማትና ዘላቂነት በንቃት አስተዋጽኦ ለማድረግ ብቁ ስለመሆናቸው በሚኒስቴሩ የምስክር ወረቀት የሚሰጣቸው አካላት፣ ስለግራንቱ ክፍፍልና አጠቃቀም ለሚኒስቴሩ በየጊዜው ወቅታዊ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸውም ተገልጿል።
ለስታርትአፖች መቅረብ እንዲችል ከተደነገገው የግራንት ፕሮግራም ማትጊያ ስልት በተጨማሪ፣ በረቂቅ አዋጁ ተጨማሪ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችም ቀርበዋል። ከእነዚህም መካከል ስያሜ የተሰጠው ስታርታፕ አግባብነት ባላቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሕጎች ውስጥ የተዘረዘሩ ማበረታቻዎች ተጠቃሚ እንደሚሆን፣ እንዲሁም ስያሜ ያለው ስታርትአፕ የስያሜው ዘመን ከማብቃቱ የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት ከማንኛውም ገቢ ግብር፣ ለባለአክሲዮኖች በሚከፋፈል የትርፍ ድርሻ ላይ ከሚጣል የገቢ ግብርና በከፋዩ ተቀንሶ ከሚቀር ግብር ነፃ እንደሚሆንም የሚገልጹ ድንጋጌዎችም ይገኙበታል።
በተጨማሪም ስያሜ ለተሰጠው ስታርትአፕ የሚሰጥና ምንም ዓይነት ወደ ባለቤትነት ድርሻ ወይም ወደ ዕዳ የመለወጥ ዕድል የሌለው ማንኛውም የግራንት ማበረታቻ፣ ስጦታ፣ ልገሳ ወይም ተመሳሳይ የመዋጮ ዓይነት ለገቢ ግብር አዋጁ ዓላማ ገቢ እንዳልሆነ ተቆጥሮ ከግብር ነፃ የሚደረግ መሆኑም ተጠቅሷል። ስያሜ በተሰጠው ስታርታፕ ሠራተኛ ሆነው የተቀጠሩ የውጪ ዜጎች የስታርታፕ ስያሜው ጊዜ ከማብቃቱ በፊት በመቀጠር የሚያገኙት ገቢ ከገቢ ግብር ነፃ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ስታርታፖች በእነዚህ ማትጊያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከግብር ነፃ ለመደረግ የሚቀርቡ ማመልከቻዎች በሚኒስቴሩ ተረጋግጠው ለገንዘብ ሚኒስቴር መላክ እንደሚኖርባቸው ረቂቁ ያስረዳል።ረቂቅ አዋጁ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን የድንጋጌዎቹ አስፈጻሚ ከፍተኛው አካል አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጅ ቁጥር 1205/2012 አንቀጽ ስድስት (6) መሠረት የተቋቋመው የብሔራዊ ዲጂታል ኢኮኖሚ ምክር ቤትም የተለያዩ ሥልጣንና ተግባራት እንደሚኖሩት ያስረዳል።
‹‹ብሔራዊ የስታርትአፕ ስያሜ ኮሚቴ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ከመንግሥት ተቋም፣ ከዩኒቨርሲቲ ወይም ከምርምር ተቋም፣ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከቴክኖሎጂ አማካሪ የተውጣጡ፣ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከ11 የማያንሱ አባላት ያሉትና በሚኒስቴሩ ሰብሳቢነት አስፈላጊው በጀት ተመድቦለት እንደሚቋቋም በረቂቁ ተገልጿል:: መቼም ስለ ስታርትአፕ ቢዝነስ አንስተን በዘርፉ ፋና ወጊዋን ባለራዕይዋን ጀግኒት ሳምራዊት ፍቅሩን አለማውሳት አይቻልም። ያለፈችው ፈተና ለጀማሪዎች ትምህርት ነውና እግረ መንገድ እናነሳዋለን።
“አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ” ሽልማት አሸናፊዋ የራይድ መስራች በርካታ መሰናክሎች አልፋ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ “አብዮት” ያስነሳች፣ ስኬታማ የፈጠራ ባለሙያና የጠንካራ ሴቶች ምሳሌ የሆነች ፈርጥ ናት። በበርካታ ችግር ተተብትቦ የቆየውን አገልግሎትበፈጠራ ቴክኖሎጂ በማገዝ ቀልጣፋ፣ በጥራት የታገዘ፣ ጊዜንና ጉልበትን የቆጠበ እንዲሆን የዚህች ብርቱ ሰው ትጋት ጉልህ ድርሻ ይወስዳል።
ተገልጋዮች በቀላሉ ስልካቸውን ተጠቅመው ከአቅራቢያቸው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የሚደርስባቸውን እንግልት፣ ዘረፋና ትንኮሳ የሚያስቀር፣ ከየአስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎችና የመኪና ባለንብረቶች ሥራ እንዲፈጠርላቸው፣ እንዲሁም አዲስና ዘመናዊ ሥርዓት እንዲዘረጋ በማስቻል የዘርፉ ተጨማሪ ሃይልና ጉልበት ሆናለች። የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን የሆነችው “የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ” መስራችና ሥራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ ናት ይለናል ከዚሁ ጋዜጣ ያገኘሁት ማስረጃ።
ይሁን እንጂ ሥራውን ስትጀምረው በርካታ ፈተና ገጠማት። የመጀመሪያው “የፈጠራ ውጤቷን” ገበያው ላይ ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት “ፋይናንስ” የሚያደርጋት ማግኘት አለመቻሏ ነበር። ይህን እንቅፋት ለማለፍ፣ ብድሮችን ለማግኘትና የሚያግዛት አካል ለመፈለግ በርካታ ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዞራለች። ግን ሁሉም ስጋታቸውን ብቻ በመግለፅ ፍቃደኛ መሆን አልቻሉም። ከብዙ ልፋትና ሥራዋን ለኢንቨስተሮች የማስተዋወቅ ትጋት በኋላ ግን የሚደግፋት አካል አገኘች።
ሆኖም የሳምራዊት አዲስ የትራንስፖርት “አብዮት” የሚፈጥር የሞባይል መተግበሪያ ሌላ ፈተና ከመንግሥት አካላት ገጠመው። ዋናው ምክንያት ደግሞ “እንደዚህ አይነት ሥርዓት ማስተናገድ የሚችል የሕግ ማሕቀፍ፣ መመሪያ የለንም። ሥራውን ማቆም ይኖርብሻል” የሚል ተደጋጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ሙከራዎች ተደረጉባት። ችግሩ እያለ መፍትሄ የሚሰጥ “የሥራ ፈጠራ ውጤት” በጥቂት ባለስልጣናት አለማወቅ ተደጋጋሚ መታሸግና የሥራ ክልከላ ተደረገበት። ይሁን እንጂ በፍርድ ቤት እግድ እየሠራች ለሶስት ዓመት ተከራክራ በመጨረሻ መፍትሄ አገኘ። ሥራዋን ስኬታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትልቅ እገዛ አደረጉላት።
“ራይድ የተነሳው ከችግር ነው። የማህበረሰቡን የትራንስፖርት ፈተናና ተያይዞ የሚመጡ ስጋቶችን ለመቅረፍ ነበር የተነሳነው” የምትለው ሳምራዊት ስትጀምረው ብቻዋን በ40 ሺህ ብር ካፒታል የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ስድስት የአክሲዮን አባላትን በባለድርሻነት ይሳተፉበታል። መተግበሪያውን ለመሥራት አራት ወር ወስዶባታል። አሁን ላይ ይህ ግዙፍ የከተማችን በኢንተርኔት፣ በስማርት ስልክና በትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች የሚሠራ፣ 37 ሺህ አሽከርካሪዎችና የመኪና ባለቤቶች የሚሳተፉበት፣ ከ500 በላይ ቋሚ ሠራተኞችና በኮንትራት የሚሠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ያቀፈ “የትራንስፖርት አብዮት” የፈጠረ ድርጅት ሆኗል።
የራይድ መስራችና ሥራ አስፈፃሚ ሳምራዊት አሁን ላይ በክልሎች አገልግሎቱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ትናገራለች። ወጣቱና የስራ ፈጣሪው አዲሱ ትውልድ ምንም አይነት ፈተናዎች ከፊት ለፊቱ ቢጋረጡ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለበትና ህልሙ ወደ ተግባር ለመቀየር መትጋት እንዳለበት ትናገራለች። በተለይ ሴቶች “ከጭምተኝነትና ራሳቸውን ከመቆጠብ” ወጥተው ህልማቸውን እንዲኖሩ እንደምትሻ ትመክራለች። ለዚህ ደግሞ በእርግጥም ከእርሷ የተሻለ ምሳሌ አይገኝም።
ራይድ ከአንድ ኮምፒውተርና ከ40 ሺህ ብር ካፒታል ተነስቶ የሚሊዮን ብሮች ካፒታልና ግዙፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል። ዛሬ የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ የአፍሪካዊ ቢዝነስ ባለ ራዕይ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች። በየዓመቱ የሚዘጋጀው የአፍሪካ ኦፕን ቢዝነስ አዋርድ ሳምራዊት ፍቅሩን ለበርካቶች የሥራ እድል በመፍጠር ምርጥ አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ (BestAfrican Business Visionary) ብሎ የ2021 ተሸላሚ አድርጓታል።
ይህ ብቻ አይደለም ራይድ ከምንም በላይ በኢትዮጵያውያን የሥራ ፈጣሪዎች፣ ተገልጋዮች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት አለው። የቀድሞው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማይክ ፖምፒዮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ ግዙፍ አገልግሎት ሰጪ የመጪው ትውልድ የቴክኖሎጂና የስልጣኔ አርማ መሆኑን መስክረውለታል።
በ40 ሺህ ብር የመሰረተችው “ራይድ” አሁን ላይ ለመንግሥት ብቻ አሽከርካሪዎቹን ጨምሮ እስከ 347 ሚሊዮን ብር በዓመት የገቢ ግብር እየከፈለ ነው። ከምንም በላይ ግን የትራንስፖርት ዘርፉ እንዲዘምን ጉልህ ድርሻ አበርክታለች። በዚህ ትልቅ ስኬታማና ለወጣቱ “አርአያ መሆን የምትችል የሥራ ፈጣሪ ሆናለች። እሷ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ሥራ ትሥራ እንጂ በግሏ ግን በጥንካሬውና በትጋቱ “አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረሥላሴን በጣም ነው የማደንቀውና የማከብረው” ትላለች።
ሀገሩን በስፖርቱ በዓለም መድረክ ላይ ከማስተዋወቁም በላይ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለብዙዎች የሥራ እድል መፍጠሩን አንስታ “የሁላችንም ጀግና ነው። በወቅቱ እስካሁን እድሉ ባይፈጠርልኝም በቅርቡ ላገኘውና ምስጋናዬን ላቀርብለት እወዳለሁ” ብላለች። ይሄን ያለችው ከሶስት ዓመት በፊት ስለሆነ እስከዛሬ አግኝታው አድናቆቷን ገልጻለት ይሆናል።
ሻሎም !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም