አሁን እንደው ከአይን ውስጥ ንብ ብቻ ሳይሆን ንቦች ወጡ አሊያም ተገኙ ቢባል ማን እውነት ብሎ ይቀበላል? ኧረ እንደውም ‹‹ላብ ቀሳሚ›› ናቸው ቢባሉስ? ጆሮ አይሰማው የለ ያስብላል፡፡ እውነታው ግን ይሄ ነው፡፡
በንብ ተነድፎ የሚያውቅ ሰው ‹‹የእንቶኔን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም›› እንደሚባለው አይነት ነው፡፡የተነደፈበት ቦታ ቶሎ አይሽርም፡፡ የንብ ሾክ መርዛማ ነው ስለሚባልም የንብ ቀፎ አካባቢን የሚደፍር የለም፡፡ከቀፎ ውጪ የንቦች መገኛ አበባ እንጂ ላብ ሆኖ መገኘቱ ደግሞ ግርምትን ማጫሩ አልቀረም፡፡
ከወደ ታይዋን የተሰማው ወሬ ለሀኪሞችም እንግዳ ሆኖ ለህዝብ ጆሮ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ሀኪሞች ከአንዲት ሴት አይን ውስጥ በህክምና አራት ንቦች የማውጣታቸው ጉዳይ በታይዋን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። በህክምና ሥራቸው እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥማቸው የመጀመሪያ መሆኑንና ሰምተውም እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ስሟ እንዲገለጥ ያልተፈለገ የ28 አመት ወጣት በሀገሯ ባህልና ወግ መሰረት አመታዊ ልምዷን ለማድረስ በዘመዶችዋ የመቃብር ሥፍራ ላይ ተገኝታ ከመቃብሩ ዙሪያ አረም በማረም ላይ እያለች ነበር በተነሳ ሀይለኛ ንፋስ ንቦቹ በግራ አይኗ ውሰጥ ሊገቡ የቻሉት፡ ፡ በወቅቱም አይኗ ውስጥ አንዳች ነገር ሲገባ ቆሻሻ ይሆናል ብላ ነበር የገመተችው። አይኗ እያበጠና አንዳች ነገር የተከመረባት አይነት ስሜት ሲሰማት ነው ወደ ህክምና የሄደችው፡፡
በህክምና የረዷት ሀኪም ሆንግ ቺ ቲንግ ከታማሚዋ አይን ውስጥ አራት ሚሊ ሜትር ርዝመት ያላቸው ‹‹ሃሊሲቲዴት›› ተብለው የሚጠሩት ወይም ማንኛውንም እርጥበት ስለሚወዱ በተለምዶ ላብ ቀሳሚ የሚል ስያሜ ያላቸው ንቦችን በቀዶ ህክምና ሲያወጡ በጣም ደንግጠው እንደነበር መረጃው ያመለክታል።
ተጎጂዋ በአሁኑ ጊዜ ከሀኪም ቤት ወጥታ በቤቷ ሆና በማገገም ላይ ትገኛለች። ስዊት ቢን (ላብ ቀሳሚ) የሚባሉት የንብ ዝርያዎች በማንኛውም እርጥበት የሚሳቡ ሲሆን፣ ላብና እንባን ለመቅሰም ሲሉ ወደ ሰዎች ይመጣሉ። ያለባቸውን ከፍተኛ የሆነ የፕሮቲን ፍላጎት ለማሟላትም እንባ ቀለባቸው እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ከአበባ ውጪ ሌላ ነገር ላይ ንብ ይገኛል፤ ብሎ ለማያስበው የኔ ቢጤ እንግዳ ነው የሚሆንበት፡፡
ባዩት ነገር መደንገጣቸውንና ተዓምር እንደሆነባቸውም ለቢቢሲ የዜና ምንጭ የተናገሩት ሀኪም እንደገለጹት ተጎጂዋ አይኗን ሙሉ በሙሉ አልጨፈነችም ነበር። በነበረው ክፍተት በአጉሊ መነፅር የነፍሳት እግር የሚመስል ጥቁር ነገር በአይኗ ውስጥ ተመለከቱ፡፡ አንዱን በህክምና መሳሪያ ጎትተው አወጡ፡፡ሌላውንም ተራ በተራ በመጎተት አራት ንቦች ከአይኗ ውስጥ ለማውጣት ችለዋል፡፡
ንቦቹ አይኗ ውስጥ እንደገቡ አይኗን አለማሸትዋም ንቦቹ መርዛቸውን እንዳይረጩ አድርጓል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ጉዳቱ ህይወት እስከማሳጣት ይደርስ ነበር፡ ፡ ንቦቹ ሰው አይተናኮሉም፡፡ ነገር ግን ላብ ይመጣሉ ወይም ይጠጣሉ። ‹‹ስዊት ቢን›› የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ በህክምና ከተጎጂዋ አይን ውስጥ የወጡት አራቱ ንቦች በሕይወት እንዳሉና ለምርምር ወደ ቤተ ሙከራ መላካቸውን ዘገባው አመልክቷል። ንቦች አበባ ጠፋ ቢባሉላብ አለን ይሉ ይሆን?
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
ሙሐመድ ሁሴን