(ክፍል አንድ)
የዘንድሮው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት እንደ ሀገር ፣ ሕዝብና ተቋማት ገመናችንን አደባባይ በማስጣት አንገታችንን አስደፍቶናል። አሸማቆናል። ከዚህም ባሻገር ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እኛም እንደ ሀገር ፣ ሕዝብና ተቋማት ከተፈታኞች ጋር መውደቃችንን አርድቶናል ። የዘራነውን አሳጭዶናል። በዚህ አሳፋሪ ውጤት የተማሪዎች ፣ የአስተማሪዎች ፣ የወላጆችና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ ቅስም ተሰብሯል ። በሌላ በኩል የመጣንበትን መንገድ ቆም ብለን እንድናብሰለስል አድርጎናል ።
የትምህርት ስርዓቱ ወሳኝ መታጠፊያ ላይ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል ። በእልህና በቁጭት በመነሳሳት ድክመታችንን በማረም የወደቀውን የትምህርት ጥራት በአንድነት ማሻሻል የመጀመሪያው ወሳኝ መታጠፊያ ሲሆን ፤ መጭውን ጊዜ ራስን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ጣት በመቀሳሰር ማሳለፍ እና ሌላ ትውልድ ይዞ እንደገና መውደቅ ሁለተኛው ወሳኝ መታጠፊያ ነው ።
መቼም የአብዛኛዎቻችን ምርጫ የመጀመሪያው ወሳኝ መታጠፊያ ነውና በእልህና በቁጭት በመነሳት ይሄን ሀገራዊ ስብራት አክመን ውጤታማ እናደርገዋለን ብዬ አምናለሁ ። ለመግቢያ ያህል ይሄን ካልሁ መጀመሪያ አመዳችንን ቡን ወዳደረገው የዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ፤ በማስከተል ደግሞ ለዚህ ውጤት የዳረገንን መንገዳችንን መለስ ብዬ እቃኛለሁ ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የ2014 ዓም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤትን በማስመልከት አዲስ አበባ ውስጥ በዚያ ሰሞን በሰጡት መግለጫ ላይ ለፈተናው ከተቀመጡት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከአራት በመቶ በታች ናቸው ። የተመዘገበውን ውጤት “አስደንጋጭ” ያሉት ሚኒስትሩ ፈተናውን ከወሰዱት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ወደ 30 ሺህ የሚጠጉት ብቻ ናቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት ።
በተደጋጋሚ በብሔራዊው ፈተና ይከሰታል ሲባል የቆየውን የፈተና ስርቆት ለማስወገድ በሚል የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ዕቅድ መሠረት ተማሪዎቹ ፈተናውን ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መውሰዳቸው ይታወሳል ።በተጨማሪም ቀደም ሲል ከነበረው የፈተና አሰጣጥ በተለየ የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች በተለያየ ጊዜ በተናጠል ፈተናውን ወስደዋል።
ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ተግባራዊ በተደረገው አዲስ አሠራር መሠረት በፈተና ወቅት ምንም ዓይነት ስርቆት አልተፈጸመም ። ባለፈው ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓም ይፋ የተደረገው ውጤትም በፈተና ወቅት የኮረጁ ተማሪዎችን ሳያካትት በሥርዓቱ መሠረት የተፈኑ ተማሪዎች ውጤት ብቻ ነው ።
ለፈተናው ለመሳተፍ በአጠቃላይ 985,384 ተማሪዎች ተመዝግበው ተፈትነው ውጤት የተያዘላቸው ተማሪዎች ደግሞ 896,520 ናቸው ። ከእነዚህም ውስጥ ለፈተናው ተመዝግበው ያልተፈተኑ 77,098 ተማሪዎች እንዲሁም 20,170 የሚሆኑት ደግሞ በፈተናው ላይ ተገኝተው “በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች እንዳይፈተኑ የተደረጉ እና ፈተናውን ትተው የሄዱ” መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገልጸዋል ። በአማራ ክልል በፈተናው ወቅት የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ 12 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ላለመውሰድ ወስነው ትተው የወጡትንም ያካትታል ።
ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደማይገቡ ሚንስትሩ ገልጸው ፤ ነገር ግን የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በውጤታቸው መሠረት ተጨማሪ ተማሪዎችን በመቀበል ለቀጣይ ዓመት ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችላቸውን ውጤት እንዲያገኙ ይሠራል። በመቶኛ ሲሰላ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ተፈታኞች ከ50 በመቶ ባላይ ውጤት በማስመዝገብ ከማኅበራዊ ሳይንስ አቻዎቻቸው የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል ።
ከ339,642 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች መካከል 6.8 በመቶው እንዲሁም የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተናን ከወሰዱት 556,878 ተማሪዎች መካከል ደግሞ 1.3 በመቶው ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ አግኝተዋል። በዚህም መሠረት ከ50 በመቶ በላይ ነጥብ ያስመዘገቡ 30 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች በቀጥታ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብተው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ይሆናል ።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅምን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት “የተሻለ ውጤት ያመጡት ተመርጠው ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ የሚደረግ ቢሆንም እነዚህ ተማሪዎች በቀጥታ የዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንደማይሆኑ” ተናግረዋል ። ከዚያ ይልቅ ተማሪዎቹ ደካማ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲማሩ ተደርገው፤ የሚሰጣቸውን የመመዘኛ ፈተና የሚያልፉ ከሆነ የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ይጀምራሉ ።
የትምህርት ሚንስትሩ አሁን ለታየው የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል “ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው” ብለዋል ።ለዚህም ከመንግሥት እና ሁሉም የትምህርት ማኅበረሰቡ መሆኑን በመግለጽ፣ ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆን ዘንድ አጠቃላዩን የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ለማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለ ጠቁመዋል።
አበው ፣ ”ተምሮ የማይፅፍ ፣ አክፍሎ ማይገድፍ፤” የሚል ወርቅ ይትበሀል ፤ ፍልስፍና አላቸው ። አዎ ! ተምሮ … ተምሮ … ካልፃፈ ፤ ካላነበበ ፤ ፈተና ካላለፈ ፣ በተጠየቅ ፣ በአመክንዮ ፣ በጥበብ ካልተጓዘ ፤ ካልተመላለሰ ፤ ማሰብ ማሰላሰል ከተሳነው ፤ ምኑን ተማረው ! ? ፊደል መቁጠሩ ፤ መማር መመራመሩ መና ቀረ ፤ ፉርሽ ሆነ ፤ ቀኑን ሙሉ ፆሞ ፣ አክፍሎ ማይገድፍ ፣ ፆም ማይፈታ ከሆነ ደግሞ የከፋ ነው ።
በመንፈሳዊ አውድ ካየነውም ፀሎቱ ፣ ልመናው ፤ አልሰመረም ፤ ወደሚል እሳቤ ይወስዳል ። የተማሪውም ፤ የአክፋዩም ቃል ኪዳን ፣ ውል በምክንያትና በውጤት የታሰረ ነው ። ከተማረ ፈተና በማለፍ / ከተማረ በመፃፍ ፤ ካከፈለ በመግደፍ ። ተማሪውም አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰብም ይሄን ቃል ኪዳን ባለመጠበቁ ከፍ ብሎ የተገለጸውን አሳፋሪ ውጤት አስመዝግቧል ።
ባለፋት 20 አመታት በብዙ መቶ ቢሊዮን ብር የሚገመት የሀገር የሕዝብ ሀብት በማፍሰስ ወደ ሀምሳ የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች ፤ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የ1ኛና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል ። ለመምህራን ስልጠና ፣ ለመፅሐፍ ሕትመት ፣ ለቤተ መፅሐፍትና ሙከራ ግንባታም ቀላል የማይባል የሀገር ሀብት ባክኗል ።
ከዚህ ሁሉ ጊዜ ፣ ድካምና ሀብት ብክነት በኃላ ግን ከ1ኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በየደረጃው ካሉ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ፣ ሰልጣኞች መመዘኛው ፣ መስፈርቱ የሚጠይቀውን ያህል የማይፅፉ ፣ የማያነቡ ፣ የማያገናዝቡ፣ የማያንሰላስሉና የማያመዛዝኑ ናቸው ። የአንዳንድ ጥናቶች ግኝትም ይሄን ከማረጋገጥ አልፎ የሚያስደነግጥ ነው ።
ቢዘገይም የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተነድፎ ፤ ስራዎች እዚህም እዚያም እየተሞካከሩ ይገኛል ። የችግሩን መነሻ ማወቅ የመፍትሔው አካል ነውና አንድ ሁለት ነጥቦችን ላነሳሳ ፤
የተደራሽነት ታረክ ፦ ለሀገራችን ትምህርት ጥራት መውደቅ ግንባር ቀደም ምክንያት ጥራትን ወደ ጎን ገሸሽ አድርጎ ተደራሽነትን ብቻ የሙጥኝ ብሎ በፓለቲካ ቅኝት ሲመራ የኖረው የተንጋደደ የመንግስት የትምህርት ፓሊሲ ነው ። ትምህርትን ተደራሽ ከማድረጉ ጎን ለጎን ጥራት ላይ አለመሰራቱ ዛሬ በየደረጃው ለተከሰተው ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ቀውስ ዋናው ምክንያት ነው።
መንግስት በማህበራዊ ሚዲያዎች የታዘብናቸውን የዛፍ ጥላ ፣ የጎጆና የሰቀላ እንዲሁም በየ”ቀበሌው ተሰሩ ” የተባሉ ት/ቤቶችን እንዲሁም ተማሪዎቻቸውን እየቆጠረ በአኃዝ ሲዘናጋ ጥራቱን ለተደራሽነት መስዋዕት አድርጓል ። የጥራት ጉዳይ ከተደራሽነት ጎን ለጎን ሊሰራ ሲገባው ይሄን ያህል አመታት ችላ መባሉ ቀውሱን አባብሶታል ።
እንደ አንዳንድ የትምህርት ጥናት ጥቆማዎች ፤ የጥራት ጉዳይ ቢያንስ ከአስር አመታት በፊት ትኩረት ሊያገኝ ይገባ ነበር ። ሆኖም ዛሬ ከሁለት አስርት አመታት በኃላ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ትኩረት ያገኘ ይመስላል ። ኩረጃን ባስቀረ አግባብ የተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መግቢያና ሰሞኑን ይፋ የሆነው ውጤት፤ ከፈተና ውጤትነት በላይ የስርዓተ ትምህርቱ የሲቲ ስካን ምርመራ ውጤት አድርጌ ነው የወሰድኩት ። የበሽታውን ደረጃ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናልና ። ይሄን የሚያክም መድኅኒት መቀመም የሁላችንም ኃላፊነት ነው ።
2ኛ . የጥራት ጉዳይ ፦ የቁጥር ፣ ጨዋታ በራሱ የጥራት መለኪያ ፤ የጥራት መገለጫና ግብ ባይሆንም እንደ ጥራት መመዘኛ ተደርጎ ተወስዷል ።የትምህርት ጥራትን በተለይ የሚለካ ፣ የሚመዝን ሳይንሳዊ ስነ ዘዴ መሬት ላይ አልነበረም ። ቢኖርም በአግባቡ ስራ ላይ አልዋለም ነበር ። ወጥነት በጎደለውና በተዝረከረከ ሁኔታ አልፎ አልፎ ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት ቢኖርም አልዘለቀም ።
አንድ ተማሪ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ለመዘዋወር ምን ማሟላት ፤ ምን ያህል ዕውቀት መገብየት እንደሚጠበቅበት የሚለካበት ፣ የሚመዝንበት ስልት አልነበረም ። ቢኖርም ስራ ላይ አልዋለም ። ምንም እንኳ የተማሪዎች የፈተናውጤት ከጥራት መስፈርቶች አንዱ ቢሆንም ፤ ተቋማዊ አስተዳደራዊ እየሆነ በመጣው ኩረጃ የተነሳ መመዘኛነቱ አፈር ድሜ በልቷል ።
ኩረጃው ሲቀር ውጤቱ ምን እንደሆነ ደግሞ ዘንድሮ በአይናችን በብረቱ አየነው ። ምክንያቱም ት/ ቤቶች ይወዳደሩት የነበረው ባሳለፉት ተማሪ ብዛት እንጅ በሚሰጡት የትምህርት ጥራት ደረጃ ስላልሆነ ፤ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መምህራን ፣ የትምህርት አመራሩ ከፍ ሲልም የአስተዳደር አካሉ የተሳተፉበት የተደራጀና ተቋማዊ የሆነ ኩረጃ በተማሪዎች መካከል እንዲካሄድ ፤ ከፍ ሲልም መምህራን የፈተና መልስ ሰርቶ በማደል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ በማሳለፍ ትምህርት ቤታቸውን ተሸለሚ ለማድረግ የሚካሄድ ” ከንቱ ውድድር ! ” ጥራቱን ይባስ ሲገድለው ኖሯል ።
በትምህርቱ ደከም ያለን ተማሪ ክፍል ማስደገም ሀብት እንደማባከን እና እንደመምህራን ድክመት ስለሚቆጠር መምህራን ተማሪዎችን ለማስደገም አይደፍሩም ። ተማሪ እንዲደግም ያደረጉ አንዳንድ” ደፋር… ” መምህራንም እንደ ድክመት ተቆጥሮባቸው ይገመገሙ ነበር ። እንዲሸማቀቁም ተደርጓል ። ከፍ ሲልም በትምህርት አመራሩ ግፊትና አስገዳጅነት የደገሙ ተማሪዎችን እንዲያሳልፉ ይታዘዛሉ ፤ ይህን ትዕዛዝ የማይቀበሉ መምህራን ደግሞ ስራቸውን እንዲለቁ ጫና ይደረግባቸው ነበር ።
3ኛ . የትምህርት ነፃነት አለመኖር ፦ በሀገራችን በየደረጃው ለተፈጠረው የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት በትምህርት ተቋማቱ የቀለም ትምህርት ነፃነት ስላልነበር
(violation of acadamic freedom ) ነው። የትምህርት ስራውን በነፃነት ከመምራት ይልቅ በየደረጃው ፓለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ይስተዋልበት ነበር ። የትምህርት አስተዳደር አመራሩ ፣ ርዕሰ መምህሩ ፣ የፈረቃ መሪው ሳይቀር ፤ በየደረጃው የሚመደበው በብቃቱ ተወዳድሮ ሳይሆን በፓለቲካ ታማኝነቱ ነበር።
መምህራን በት/ቤቱ በነፃነት ሀሳባቸውን እንዲገልፁ፣ እንዲጠይቁ ፣ እንዲሞግቱ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩ ፤ ተማሪዎች ስለትምህርታቸውም ሆነ ስለሀገራቸው በነፃነት እንዲመክሩ አለመፈቀዱ ፤ በትምህርት ስራ ማህበረሰቡ ላይ ተጭኖ የነበረው መዋቅራዊ አፈና መምህሩ ፣ የትምህርት ስራ አመራሩ ፣ ተማሪው የትምህርት ፓሊሲውንም ሆነ ፤ ስርአተ ትምህርቱን በነፃነት ከስር ከስር እንዲተች እንዲታረም ስለማይደረግ ችግሩ እየተሽፋፈነ እና በፈጠራ የአፈፃፀም ሪፓርት እየተኳኳለ ዛሬ ለደረስንበት ቀውስ ዳርጎናል ።
በተለይ ከ1997 ዓም ምርጫ ወዲህ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካዳሚያዊ ነፃነት ሙሉ በሙሉ ተጨፍልቋል ማለት ይቻላል ። በነፃነት የመማር ማስተማር ፣ የምርምር ፣ የመሰብሰብ ፣ የመወያየት ፣ ነፃነት ከሌለበት ዩኒቨርሲቲ እንዴት ብቃት ፣ ጥራት ያለው ምሩቅ ማፍራት ይቻላል ?።
ብቁ መምህራን በሌሉበት ፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ዝግጁነት የሌለው ተማሪን ይዞ ፤ የመማሪያ መፅሐፍት የይዛት ጥራት ባልተሟላበት ፤ የትምህርት መሰረተ ልማት በአግባቡ ባልተሟሉበት ፤ የወላጅ ተሳትፎ ዝቅተኛ በሆነበት ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች መባባስ ፤ ለምሩቃን ምቹ የስራ ዕድል አለመመቻቸት የችግሩ በአንድ አካል ነው።
በዚህም ማህበረሰቡ ስለ ትምህርት የነበረው በጎ አመለካከት መሸርሸሩ ፤ በየደረጃው ለሕብረተሰቡ ምሳሌ ፣ አርኣያ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎች አለመፈጠራቸው ፤ ተምሮ ጥሮ ሳይሆን በአቋራጭ ዘርፎ መበልፀግ እንደ ጀግና የሚቆጠርበት ዘመን መፈጠሩ በአንድም በሌላ በኩል ለሀገራችን የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ሌላኛው ምክንያት ነው ።
ከፍ ብሎ የትምህርት ሚንስትሩ እንዳሳሰቡት በሀገራችን የትምህርት ጥራት ላይ የተከሰተውን አሳሳቢ ቀውስ ለመቀልበስ ስር ነቀልና ከፓለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ፤ መላ ሕዝቡን ያሳተፈ ሀገራዊና ሁሉን አካታች የትምህርት ዘርፍ መዋቅራዊ ክለሳ ሊካሄ ይገባል ።
ሻሎም ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015